Monday, September 26, 2016

ስለ “ደህንነቱ” መሥሪያ ቤት ከማውቀው በጥቂቱTadesse Biru Kersmo.


በርዕሴ ላይ “ደህንነትን” በጥቅስ ያስገባሁት ለተቋሙ የሚገባ ስያሜ ባለመሆኑ ነው ። ሙሉ ስሙ “የአገርና የሕዝብ ደህነት ጽ/ቤት” የሚባል ይመስለኛል፤ እርግጠኛ አይደለሁም፤ ኦፊሳላዊ ስሙን የማወቅ ፍላጎትም የለኝም። የጽ/ቤቱ ሥራ ከአገርም ከሕዝብም በተቃራኒ የቆመ፤ የህወሓት አገዛዝን ለማስቀጠል ማናቸውንም ዓይነት ክፋቶች የመፈጸም ስልጣንም ፍላጎትም ያለው፤ ሰዎችን በማሰቃየት የሚደሰቱ ሳዲስቶች የተሰባሰቡበት ነው። እኔ የአገዛዙ የስለላ ተቋም ወይም የአገዛዙ ጆሮ ጠቢዎች በሚል ስያሜ ነው ልጠራቸው የምፈልገው።
ስለዚህ መሥሪያ ቤት የተቻለኝን ያህል ማወቅ የሚያዝናናኝ ሥራዬ (hobby) ነው። ስለዚህ አሳፋሪ መሥሪያ ቤት ከማውቀው ጥቂቱን ከማካፈሌ በፊት ከቆዩ ግጥሞቼ አንዱን ልጋብዛችሁ።
የአምባገነኖች “ደህንነት”

“መልከ ጥፉ
በስም ይደግፉ”
ሆነና .... 
አንተን ፀረ-መብት ወአርነት
የነፃነት ተጋድሎ እንቅፋት
ስምህ ነው አሉን “ደህነት”

አንት ጆሮ ጠቢ አሳባቂ
የግል ምስጢርን አውላቂ 
መብት ነጣቂ 
የከንፈር ዚፕ 
የብዕር ክዳን 
መች አጣነው
መቆምህን ለአምባገነን ሥልጣን

ሕዝብ ርቦት “ራበኝ” ‘ዳይል
ጠምቶት “ጠማኝ” ‘ዳይል
መከፋቱ፣
መጎዳቱ፣ 
“እዩልኝ፣ ተመልከቱ 
አይታችሁም ፍረዱኝ” 
እንዳይል ....
በልሳኑ የተወተፍክ ውታፍ
በመንገዱ የተቸከልክ ችካል 
እንቅፋት!!!

የአምባገነኖች “ደህነት” - የብዙሃን ሰቆቃ በር
የሰብዓዊ መብቶች ፀር። 
______________

የካቲት 12 ቀን 2006 ተሻሽሎ እንደተፃፈ
Feb 19, 2014


የህወሓት አገዛዝ የስለላ ተቋም ምን ይመስላል?

ከሰው አመዳደብ ልጀመር። በከፍተኛ አመራር ላይ ከሚገኙት አድራጊና ፈጣሪዎች ከ90 በመቶ በላይ የሆኑት የትግራይ ተወላጆች ናቸው፤ ሁሉም የህወሓት አባላት ናቸው። ለህወሓት የሚከፍሉት መዋጮ ከየወሩ ደመወዛቸው ይቆረጣል። ከእነዚህ ውስጥ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት የህወሓት “ነባር” ታጋዮች የነበሩ ናቸው። እድሜያቸው በርከት ያሉት ከ 60ዎቹ የዘለሉ አዛውንት ሊባሉ የሚችሉ ናቸው። የእነዚህ ሰዎች የስለላ እውቀት “ከባዶ ስድስት” ልምዶቻቸው የዘለለ አይደል። ህወሓት ያስተማራቸው ጭካኔና በሰው ስቃይ መደሰትን ነው። ለእነሱ ስለላ ማለት ሰውን በመደብደብ መረጃ ማግኘት፤ በጨለማ አድፍጦ መምታት፤ ቤትና ቢሮ ሰብሮ ሰነድ መዝረፍ፤ በተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ውስጥ አንጃዎች እንዲፈጠሩ በማድረግ እርስ በርስ ማባላት ነው።
የድድብናቸው ጥልቀት ይገርማል። አንዱ የዚሁ መሥሪያ ቤት ከፍተኛ ባለሥልጣን “ብፈልግ የአሜሪካን ዲሞክራቲክ ፓርቲ ማዳከም እችላለሁ፤ ተለጣፊ መፍጠር ምን ይከብዳል” ብሏል። እነዚህ ሰዎች ለሚሠሯቸው የተንኮልና የሸር ሥራዎች ተቀባይነት ያለው ሽፋን ለመፍጠር እንኳን አይሞክሩም። Plausible deniability የሚባል ነገር የለም። መሥሪያ ቤቶችን ከእዝ ሰንሰለት ውጭ በድፍረት በቀጥታ ያዛሉ። የስለላ መሥሪያ ቤት መሥራታቸው የሁሉም መሥሪያ ቤቶች አለቃ አድርጓቸዋል፤ ይህ የህወሓት አገዛዝ በአፍጢሙ የተደፋ የመንግሥት አደረጃጀት አቢይ መገለጫ ነው። ለምሳሌ፤ አንድ ፓርቲ አዲስ አበባ ሰልፍ ቢጠራ እና የስለላው ቢሮ አዛውንት ሰልፉ መፈቀድ የለበት ብለው ካሰቡ ለአዲስ አበባ መስተዳደር የሰልፎች እውቅና ክፍል ኃላፊ በግል ሞባይሉ ይደውሉና እውቅና እንዳይሰጥ፤ ይህንን ትዕዛዝ የሰጠውን አካል ግን እንዳይናገር ያዛሉ። ይህ የክፍል ኃላፊ በምን የህግ አግባብ ፈቃዱን እንደሚከልክል አይነግሩትም፤ የደህንነት መሥሪያ ቤት ከልክሏል ማለት ደግሞ አይችልም። እንዲህ ዓይነት አጣብቂኝ ውስጥ የገቡ ኃፊዎች በጭንቀት ቢሮ ዘግተው የሚጠፉበት አጋጣሚ ይፈጠራል። ሌላ ቀላል ምሳሌ፤ አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ ለስብሰባ የሆቴል አዳራሽ ተከራይቷል። ስብሰባው ሊጀመር 1 ሰዓት ሲቀር አዳራሽ እንዳታከራይ ተብሎ ይነገረዋል፤ ይህ ውሳኔ “የደህንነቱ” መሥሪያ ቤት ውሳኔ ነው እንዳይል ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል። አሁን ደንበኞችን የማስቀየም ሸክም የሚወድቀው በሆቴሉ ኃላፊ ነው። እንዲህ ዓይነት ተግባር በሰለጠነ የስለላ አሰራር አሳፋሪ ነው፤ በህግም ያስጠይቃል። ተንኮል እንኳን ቢሠራ ህጋዊ አሳማኝ ምክንያት የመፍጠር ሸክም መውደቅ የነበረበት በስላላው መሥሪያ ቤት ነው።
በእድሜ የገፉት ከፍተኛዎቹ ባለሥልጣኖች ይህ ዓይነቱ አሠራር ህገወጥና ጊዜ ያለፈበት መሆኑ አይረዱም። እንዲያም በእኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ፉክክር ውስጥ ገብተዋል። በመካከላቸው ከፍተኛ መናናቅ አለ። በአራቱ ምክትል ዳይሬክተሮች መካከል መካከል መናናቅ አለ እያንዳንዱን ፓርቲ የሚከታተል ቢሮ ከፈተዋል፤ ይህ በህጋሚ መንግድ የተመዘገቡትም ይጨራል። ፒያሳ-ቴዎድሮስ አደባባይ አካባቢ እና እንቁላል ፋብርካ -የስደተኞች እና ከሰደት ተመላሾች ግቢ ዉስጥ ካሉት ቢሮዎቻቸው በተጨማሪ አዲስ አበባ ውስጥ safe house እያሉ የሚያቆላምጧቸው ሰዎችን አፍኖ በመውሰድ ማሰቃያ ቦታዎች አሏቸው። በ safe houses የሚሠራው ማፍያ እንጂ ሌላ ድርጅት ይሠራዋል ተብሎ የሚታሰብ አይደለም። በህግ የሚመራ፣ የሰለጠነ፣ ኃላፊነት የሚሰማው የስለላ ተቋም የሚያስመስሉት አንዳችም ነገር አታገኙም። አዛውንቶቹ በመሥሪያ ቤቱ ሥራ ላይ ከሚያውሉት ጊዜ ይበልጥ ሀብት ለማጋበስ የሚያውሉት ይበልጣል፤ ሁሉም ቱጃሮች ናቸው። የመሥሪያ ቤታቸውን መታወቂያ በቢስነስም ውስጥ ይጠቀሙበታል። መጠጥ ቤትም ውስጥም ይመዙታል። በአጋጣሚም ይሁን በቢስነስ ጉዳይ የተከራከራቸው ሰው ጠላት ነው። ከእነሱ ጋር በማናቸውም ምክንያት መጣላት ከፓለቲካ ልዪነት እኩል ነው።
ከእነዚህ ሰዎች በታች ያሉት ቆሻሻው ሥራ የሚሠሩ “ኦፊሰሮች” የሚል የመሸንገያ ስያሜ የተሰጣቸው በእድሜ ወጣቶች፣ በትምህርትም ሻል ያሉ የሚበዙበት ስብስብ ነው። እዚህ የብሄር ስብጥሩ የተሻለ ነው። ከሕዝብ ብዛት አንፃር ከታየ የትግራይ ድርሻ ከፍ ያለ ቢሆንም እንኳን የኦሮሞና የአማራ ተወላጆች በብዛት አሉበት፤ ከሌሎችም እንደዚሁ። ከእነዚህ ኦፊሰሮች አንዳንዶቹ በስልጠናም በግል ንባብም የዘመናዊ የስለላ ድርጅቶችን አሠራር የማወቅ እድል አግኝተዋል፤ እናም “አሠራራችን እናዘምን፤ ከ CIA, FBI, MI5, MI6, ከሞሳድ … ልምድ እንቅሰም፤ የመንደር ጉልበተኛ ቦዘኔ አንምሰል” እያሉ ይጨቃጨቃሉ፤ የሚሰማቸው ግን የለም።
ኦፊሰሮቹ ሰፈር የሚሰማው ምሬት ነው። ቁጥር አንድ የምሬት ምክንያት ደግሞ ገንዘብ ነው። ኦፊሰሮች ብዙ ሰው የሚገምተውን ያህል አይከፈላቸውም፤ ከሚዘረፈውም ገንዘብ አይደርሳቸውም። በትርፍ ጊዜዓቸው ሌላ ሥራ ለመሥራት ቢፈልጉም አይችሉም። በግል መማርም አይፈቀድላቸውም። የመንግሥት ሠራተኖች ይሁኑ ባሮች ግልጽ አይደለም።
ኦፎሰሮች በሥራቸው ምክንያት ከማኅበረሰቡ የተገለሉ ናቸው። ቅን ህሊናቸው አንዳንዴ በመጠጥ አንዳንዴ ደግሞ በህልማቸው ተሸፍኖ ይመጣና እረፍት ይነሳቸዋል። ሥራው ለቆ ለመውጣት ያስባሉ ግን ይፈራሉ። የአብዛኛዎቹ ኦፊሰሮች ስነልቦናዊ ሕይወት የሚገለፀው በፍርሃት ነው፤ ሁሌ እንደፈሩ ናቸው። የሚተማመኑ ሁለት ጓደኛሞች እዚያ መሥሪያ ቤት ውስጥ ማግኘት አይቻልም። ፍርሀት እጃቸው ውስጥ የገቡ ምስኪኖች ላይ ጨካኞች ያደርጋቸዋል፤ በዚህም ምክንያት ብዙ የጭካኔ ተግባር ይፈጽማሉ። በታሳሪዎች ላይ ሽንታቸውን መሽናት የመሰለ ተግባር የሚፈፅሙት እነዚህ በፍርሃት የሚባንኑት ኦፊሰሮች ናቸው። በተለይ በአሁኑ ሰዓት የኦፊሰሮች ሕይወት እየተመሰቃቀለ ነው። የኑሮ መወደድ እነሱንም አደህቷቸዋል፤ የአለቆቻቸው በሀብት መንበሽበሽ ያውቃሉ፤ ያያሉ። NGO ውስጥ ስለመቀጠር ወይም ትንሽም ብትሆን የራስ ቢዝነስ ስለመጀመር ያልማሉ፤ ከማለም አልፈው የተሳካላቸው አሉ ግን ጥቂቶች ናቸው።
ያለምንም ማጋነን የደህንነቱ መሥሪያ ቤት መረጃ ሰብሳቢዎች ከኢቲቪ/EBC ዜና አጠናቃሪዎች የተሻለ መረጃ አያመጡም። መረጃ ብለው የሚያመጧቸው ነገሮች የተሳሳቱ ወይም የተጋነኑ ናቸው። ሁሉም ኦፊሰሮችም የፓርቲ አባላት ናቸው፤ በየብሔራቸው። አብዛኛዎቹ በየመጡበት ድርጅት ሰላይነታቸው ስለሚታወቅ እዚያም መረጃ ስጡን ይሏቸዋል። አለቃቸው ፓርቲያቸው ይሁን የስለላው መሥሪያ ቤት አይታወቅም። ለሁለት አለቆች ማደር አለባቸው። ከህወሓት የመጡት ኦፊሰሮች ህወሓትን የመጠበቅ ተጨማሪ ሥራ አለባቸው፤ ሥርዓቱን የመጠበቅ የተለየ ኃላፊነት እንዳለባቸው ይነገራቸዋል። የህወሓት ደጋፊ ያልሆነ ሁሉ ጠላት እንደሆነ ነው የሚያውቁት። ከህወሓት በመጡት እና ከኦህዴድ፣ ብአዴን፣ ደህዴድ ... በመጡት መካከል ከፍተኛ አለመተማመን አለ።
ከኦፊሰሮች ውስጥ የህሊናቸውን ወቀሳ እያዳመጡ ያሉ ወገኖች አሉ። መወላወሉን ትተው በቶሎ ቢወስኑ ይሻላቸዋል። የህወሓት አገዛዝ መወደቁ አይቀርም። የሥርዓቱ መበስበስ ከሚታይባቸው ቦታዎች ቁጥር 1 የገዛ ጥላውን መፍራት የጀመረው የስለላው መሥሪያ ቤት ነው። መሥሪያ ቤቱ ራሱ እንደተቋም ፍርሀት ውስጥ ገብቷል። ወደ መሥሪያ ቤቱ ጎራ የሚል እያንዳንዱ ተሽከርካሪ ታርጋው ይመዘገባል። እያንዳንዱ ኦፊሰር በሌላ ኦፊሰር ይሰለላል። ከላይ ያሉት ሽማግሌዎች የጦር ሜዳ ተረታቸውን እያወሩ የተዋጉበት ካሳ ይመስል በሀብት ላይ ሀብት ይከምራሉ። ይህ የወጣት ኦፊሰሮችን ልብ እያሸፈተ ነው።
ለእነዚህ ወጣት ኦፊሰሮች የግል መልዕክት አለኝ።
እኔ ስለላ በተለይም ኢንተለጀንስ የተከበረ ሙያ መሆኑን አውቃለሁ፤ ትምህርትና ስልጠና እንደሚፈልግም እረዳለሁ፤ አውቃለሁ። ኢንተለጀንስ ከፍተኛ የስነምግባርና የህግ ልጓም እንዳለበትም አውቃለሁ። እናንተ የምትሠሩት ግን እሱን አይደለም። እናንተ ባለሙያ የሆናችሁ ይመስላችኋል እንጂ አይደላችሁም። የምትሠሩት ሥራ እጅግ አሳፋሪ ነው። ህግም ስነምግባርም አይገዛችሁም። በግጥሜ ላይ እንደገለጽኩት እናንተ የከንፈር ዚፕ እና የብዕር ክዳን ነው የሆናችሁት፤ ይህ ሙያ አይባልም። በነፃነት መንገድ ላይ የተቸከላችሁ እንቅፋቶች መሆናችሁ መብቃት አለበት። ወገኞቼ፣ የዚህ ሥርዓት መለወጥ ጥቅሙ ለእናንተም ነው። የሙያው ፍቅርና እውቀት ያላችሁ ወገኖች የሙያውን ስነምግባር ጠብቆ ህግን አክብሮ በሚሠራ መንግሥት ሥር አገልግሎታችሁን ትቀጥላላችሁ። የነፃነት እንቅፋቶች ሳይሆን የነፃነት ዘብ ጠባቂዎች መሆን ትችላላችሁ። የፍትህ ፀሮች ሳይሆን የፍትህ ጠበቆች መሆን ትችላላችሁ። ውሳኔ መወሰን ያለባችሁ ግን ዛሬ ነው። ከቻላችሁ ለቃችሁ ውጡ፤ ካልሆነ እውስጡ ሆናችሁ አሳፋሪውን መሥሪያ ቤታችሁን ግደሉት።

No comments:

Post a Comment