ከአለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት (ግሎባል አሊያንስ) ለአትሌት ሙሉጌታ ዘውዴ የቀረበ የድጋፍ ጥሪ
አትሌት ሙሉጌታ ዘውዴ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ሴፕቴምበር 6 እና 7 ቀናት 2014 ዓ/ም በምዕራብ ኖርዌይ ክላርቪክ ሚላን በተካሄደው በአስር ሺህ ሜትር እና በግማሽ ማራቶን ውድድሮች አንደኛ በመሆን ያጠናቀቀ ጀግና አትሌት ነው።
በኖርዌይ ያሉ በርካታ የንግድ ድርጅቶች አትሌት ሙሉጌታ ዘውዴ በውድድሮቹ የድርጅቶቻቸውን አርማ ለብሶ እንዲሮጥ በክፍያ በተደጋጋሚ ሲጠይቁት ፤ “ አሁን ከገንዘብ ይልቅ ለነፃነት የምሮጥበት ጊዜ ነው” በማለት ለነጻነቱ፣ ለወገኑና ለሀገሩ ያለውን ፍቅር በተግባር ያስመሰከረ አትሌት ነው ።
በተደጋጋሚ እንደሚባለው ዛሬ የሚታዬው ህዝባዊ ትግል በአንድ ጀምበር የተከሰተ አይደለም። ትግሉ እዚህ ደረጃ እንዲደርስ በሁሉም ዘርፍ ችቦውን የለኮሱ የነጻነት ታጋዮችና የህዝብ ድምጾች አሉ። በስፖርቱ ዘርፍ ይህን ችቦ ከለኮሱት መካከል ከዓመታት በፊት በኖርዌይ በተካሄዱ ተደጋጋሚ የማራቶን ውድድሮች አሸኛፊ የሆነው ይኸው ጀግና አትሌት ሙሉጌታ ዘውዴ አንዱ ነው።
” የለኮስኩትን የነጻነት ትግል ችቦ ዛሬ እነ ፈይሳ ሌሊሳ በታላቅ መድረክ ላይ በድምቀት ሲያበሩት ሳይ ልዩ የደስታ ስሜት ይወረኛል” የሚለው አትሌት ሙሉጌታ፣ እሱ ስለሚገኝበት ሁኔታ ስንጠይቀው ግን እንባው እየቀደመው መናገር አልቻለም።
በኖርዌይ መንግስት የመኖሪያ ወረቀት ባለማግኘቱ የመጣውን ለመቀበል በመወሰን “ ሀገሬ መልሱኝ” እስከማለት መድረሱን የሚገልጸው ሙሉጌታ፤ ለዚህ የአትሌቱ ጥያቄ የኢትዮጵያ መንግስት “ አትሌቱ አሸባሪ ስለሆነ አልቀበልም” በማለት ለኖርዌይ መንግስት ምላሽ መስጠቱ ታውቋል።
ኦገስት 2011 ዓ/ም በስደት ኖርዌይ የገባው አትሌት ሙሉጌታ ዘውዴ ከኖርዌይ በርገን ከተማ 25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ባለውና “አርና” በተስኘው የስደተኞች መጠላያ ካምፕ” የሚገኝ ሲሆን ፤ በአሁኑ ሰዓት ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ የኢትዮጵያውያንን ወገኖቹን ድጋፍ እንደሚሻ በእንባ እየተማጸነ ይገኛል።
የአትሌት ሙሉጌታ ጉዳይ ለአየር መብቃቱን ተከትሎ በርካታ ሀገር ወዳዶች ስልክ በመደወል ከማጽናናት አልፋችሁ “ በምን በኩል እንደግፍህ?” በማለት ባሳያችሁት ድጋፍ እጅግ መደሰቱን የገለጸው ሙሉጌታ፤ “ በስደት የጭንቀት ህይወትን ስገፋ ብቻዬን የሆንኩ ይመስለኝ ነበር፤ ለካ ወገን አለኝ” በማለት በእንባ ተሞልቶ ደስታውን ገልጿል።
አለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት (Global alliance for the Rights of Ethiopia) ቦርድ አባላት ላለፉት ሁለት ሳምንታት ከአትሌቱና ለአትሌቱ ቅርብ ከሆኑ ወገኖች ጋር ውይይት ሲያደርግ ሰንብቶ በትናንትናው ምሽት ባካሄደው የቦርድ ስብሰባ ለውዱ አትሌታችን ሊደረጉለት የሚገባቸውን ወገናዊ ድጋፎች ከመረመረ በዃላ የሚከተሉትን ለማድረግ ወስኗል
1ኛ: የኖርዌይ መንግስት አትሌርቱ ያቀረበውን የፖለቲካ ጥገኝነት ጥያቄ ይቀበል ዘንድ የሚመለከታቸው አካላትን ለመጠየቅና በሙያቸው በበጎ ፈቃደኝነት ድጋፍ ሊያደርጉለት የሚፈልጉትን የሕግ ባለሙያዎችን እንዳስፈላጊነቱም በክፍያ ሊሰሩ የሚችሉ ሌሎች የሕግ ባለሙያዎችን በመቅጠር አፋጣኝ መፍትሄ ለመፈለግና ህብረተሰቡን ተሳታፊ የሚያደርግ የፊርማ ማሰባሰብ( Petition) ፕሮግራም መዘርጋት
2ኛ: ለአትሌቱ ህብረተሰቡ የገንዘብ ድጋፍ ያደርግለት ዘንድ ለገንዘብ ማሰባሰቢያ አካውንት (GoFundMe) በስሙ መክፈትና አካውንቱ ተከፍቶ ለህብረተሰቡ ሲተዋወቅ ለመነሻ 1 ሺህ ዶላር ከግሎባል አሊያንስ አካውንት ወጪ በማድረግ ርዳታውን ለማስጀመር
3ኛ: የኖርዌይ መንግስት ለስደት ጥያቄው አዎንታዊ ምላሽ የማይሰጠውም ከሆነም ወደ 3ኛ ሃገር የሚዛወርበትን መንገድ ማመቻችት
4ኛ: ህብረተሰቡ በተጠናከረ መልኩ ለአትሌቱ ድጋፍ ያደርግ ዘንድ በሚከፈቱት የግንዛቤ ማስጨበጫ ማህበራዊ የመገናኛ ብዙሃን መድረኮችና ሌሎች የመገናኛ ብዙሃን አውታሮች ላይ የጎላ ተሳትፎ ለማድረግ ወስኗል።
በመኾኑም “አትሌት ሙሉጌታን በምን መልኩ እንደግፈው?” የሚሉ ጥያቄዎች ምላሽ ያገኙ ዘንድ ልትድግፉት ፈቃደኛ የሆናችሁ ሁሉ ከዚህ በታች ያለውን ማስፈንጠሪያ (Link) በመጫን እንደየአቅማችሁ ድጋፋችሁን ልታደርጉለት እንደምትችሉ በአክብሮት እንጠይቃለን።
“ሀገር አለኝ፣ ወገን አለኝ!”
አለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት
መስከረም 2016 ዓ/ም
Global alliance for the Rights of Ethiopia(GARE)
P.O. BOX 1836
Rancho Cordova, CA 95741
No comments:
Post a Comment