ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ሁኔታ አሳሳቢ በመሆኑ፣ በሃገሪቱ ውስጥ ያለውን ቀውስ ለመሻገር ባለአደራ መንግስት እንዲቋቋም ፕ/ር መስፍን ወ/ማሪያም ጥሪ አቀረብ።
በተለያየ መንገድ ከሃገሪቱ የተዘረፈውን ገንዘብ በተመለከተም የሂሳብና የህግ አዋቂዎች የሚሳተፉበት የምርመራ ስራ እንዲካሄድና የውጭ አማካሪዎችም ሂደቱን እንዲያግዙ የመፍትሄ ሃሳብ አቅርበዋል።
ታዋቂው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ኢትዮጵያዊው ምሁር ፕ/ር መስፍን ወ/ማሪያም ይህንን ጥሪ ያደረጉት ዛሬ ሰኞ መስከረም 16 ፥ 2009 ባሰራጩት ባለ11 ገፅ ጹሁፍ ነው።
“የወያኔ አገዛዝና የኢትዮጵያ ወደፊት” በሚል ርዕስ ባሰራጩት መልዕክት የትግራይ ህዝብ በህወሃት ሳቢያ ከፍተኛ መከራ እንደተደቀነበት አስረድተው፣ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በመሰለፍ አደጋውን እንዲሻገረው ጥሪ አቅርበዋል።
“የወያኔን አገዛዝ ማውረድ የጊዜው አንገብጋቢ ጥያቄ ሆኗል፣ ይህ የሚያከራክር አይመስለኝም” ያሉት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም፣ ከ25 አመታት በላይ በጠመንጃ ጉልበትና በሲአይኤ (CIA) ድጋፍ ሰንጎ የገዛን ቡድድን በቃህ ቢባል አይደንቀኝም” በማለት ጽሁፋቸውን ቀጥለዋል።
ስርዓቱ እንዴት ይውረድ የሚለውን ጥያቄ አስከትለው በዚህ ረገድ አሉ ያሏቸውን ያልጠሩ አመለካከቶች በዝርዝር ተመልክተዋል።
“የወያኔ ሎሌዎች በትግራይ ህዝብ ላይ ያደረሱትንም የቃጡበትን ከባድ አደጋ በጥልቀት ስለተገነዘብኩ የምችለውን ያህል ለማስተካከል ቆርጫለሁ ያሉት ፕ/ር መስፍን ወልደማሪያም፣ ትግራይ በሁለት ሆን ተብሎ ወያኔ ጠላት ባደረጋቸው ህዝቦች መሃከል ተጥዶ እንደገና ዳቦ እሳት እስኪቀጣጠልበት እየተጠበቀ ነው” በማለት የችግሩን ስፋትና አሳሳቢነት ዘርዝረው ሃገሪቱ ላለችበት ጥልቅ ችግር መፍትሄ ያሉትን የባለአደራ መንግስት ሃሳብ በዝርዝር አቅርበዋል።
በዚህም ነጻ የተወካዮች ም/ቤት እንዲቋቋም፣ በዚህ ም/ቤት ተቆጣጣሪነትም ለሁለት አመታት የሚቆይ የባለአደራ መንግስት እንዲቋቋም የመነሻ ሃሳብ አቅርበዋል። ከሃገሪቱ የተዘረፈውን ገንዘብ በተመለከተም የህወሃት ባለስልጣናት ንብረት በህግና በሂሳብ አዋቂዎች እንደመረመር፣ በሂደቱም የአለም ባንክና የተባበሩት መንግስታት እንዲሁም የምዕራብ መንግስታት አማካሪዎች እንዲሳተፉበት ጠይቀዋል።
ተጣርቶ የተገኘው ሃብትና ለሃገሪቱ ልማት፣ የአካል ጉዳት ለደረሰባቸውና ለሟች ቤተሰቦች እንዲውል ፕ/ር መስፍን የመፍትሄ ሃሳብ አቅርበዋል።
እነርሱ በለቀቁ ማግስት በሚካሄደው የመጀመሪያው ምርጫ የህወሃት መሪዎች ሆነ ካድሬዎች እንዳይሳተፉ በህግ ገደብ እንዲጣልባቸው ባለ 11 ገጽ ጽሁፋቸው፣ ፕ/ር መስፍን የመፍትሄ ሃሳብ አቅርበዋል።
ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማሪያምና ሌሎች ታዋቂ ኢትዮጵያውያን ምሁራን ለደርግ መንግስት በተመሳሳይ የአደራ መንግስት ጥያቄ ማቅረባቸው ሲቃወም፣ ስርዓቱ አልቀበልም ማለቱን ተከትሎ በወራት ልዩነት ከስልጣኑ መባረሩ አይዘነጋም።
No comments:
Post a Comment