Saturday, September 24, 2016

ለትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ትህዴን) ሁለተኛ ጉባኤ የእንኳን ደስ አላችሁ September 23, 2016


dr-berhanu-Nega
ለደምሂት ሁለተኛ ጉባኤ የእንኳን ደስ አላችሁ አጭር ንግግር

(ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ)
እሁድ መስከረም 8፤ 2009 ዓ፡ም

– ታጋይ መኮንን ተስፋዬ፤ የዴምህት ተመራጭ ሊቀመንበር
– በተለያየ ደረጃ የምትገኙ የድርጅቱ ያመራር አባላት
– ሰፊው የዴምህት ታጋዮች
– ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶች
– ክቡራትና ክቡራን

በመጀመሪያ ለትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ትህዴን) ወይንም ካሁን በኋላ በትግርኛው ስሙ ለምጠራው ዴሞክራሲያዊ ምንቅስቃስ ህዝብ ትግራይ (ዴምህት) ታጋዮች፤ አመራሮችና ደጋፊዎች ድርጅታዊ ጉባኤያችሁን ስኬታማ በሆነ መንገድ በማጠናቀቃችሁ እንኳን ደስ አላችሁ። የእናንተ ስኬትና ደስታ የእኛም ስኬትና ደስታ ነውና ደስታችሁን ስንጋራ ደስ ይለናል። ይህ ጉባኤ ድርጅቱን ከድቶ፤ ምንም የማያውቁ ታጋዮችን አስከትሎና ለአደጋ አጋልጦ ከህወሀት/ኢህአዴግ ጋር የተቀላቀለው የቀድሞው የዴምህት ሊቀመንበር ሞላ አስገዶም (የአዲስ አበባ ወጣቶች ሞላ አስከዶም ነው አሉ የሚሉት) በከዳ በአመቱ፤ የሱ መክዳት በድርጅቱ ውስጥ ይዟቸው የመጣውን ብዙ ራስን የመመዘንና የማወቅ ጥያቄዎች በእርጋታና በሰከነ መንገድ፤ ከበቂ በላይ ግዜ ሰጥቶ መርምሮና መልሶ፤ ከዚህ በፊት ከነበረበትም የበለጠ የጠራ መስመርና የተጠናከረ ድርጅት ይዞ፤ የተነሳበትን የትግል አላማ ከዳር ለማድረስ ቆርጦ፤ የተነሳ ድርጅት ሆኖ በመውጣቱ ደስታችሁ የላቀ መሆኑ ይሰማኛል። ይህ ሂደት በራሱ ትልቅ ድል ነውና እንደገና እንኳን ደስ አላችሁ እላለሁ።
እኔ ዴምህት ስለሚባል ድርጅት በመጀመሪያ የሰማሁት ከምርጫ 97 በኋላ ቃሊቲ እስር ቤት ሆነን በአንድ ወቅት በጊዜው የድርጅቱ ሊቀመንበር የነበረው ታጋይ ፍሰሀ ኃይለ ማርያም ከዴምህት ሬድዮ ጋር ያደረገውን ሰፊ ቃለምልልስ ከሰማሁ በኋላ ነበር። መቼም እስር ቤት ውስጥ በተለይ በ11 ሰዓት አንዴ በር ከተዘጋብን በኋላ ከእስር ቤት ውጭ ስላለው ሁኔታ በዋናነት እንከታተል የነበረው የተለያዩ ተቃዋሚ ድርጅቶች ከተለያየ ቦታ የሚያስተላልፉትን የሬድዮ ፕሮግራም በመስማት ነበር። የፍሰሀ ቃለ መጠይቅ እንደማስታውሰው ከሆነ በ3 ክፍል ተቆራርጦ ነበር የቀረበው። ሶስቱንም በጥሞና ነበር የተከታተልኩት። በጊዜው እኛ በሰላማዊ መንገድ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ለማምጣት ያደረግነው እንቅስቃሴ በወያኔ ጉልበት ከተጨናገፈና እኛም ፍጹም አይን ባወጣ ውሸት “በዘር ማጥፋት ወንጀል” ተከሰን ወህኒ ከወረድን በኋላ “ያለው አማራጭ ምንድን ነው?” ብዬ እራሴን የምጠይቅበት ጊዜ ነበር። ምናልባት እኛም ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት መመስረት የጀመርነው ሰላማዊ ትግል በህወኃት/ኢህአዴግ ግፊት ወደ ትጥቅ አመጽ መሸጋገሩ ላይቀር ነው የሚል ግምት ነበረኝ። ስለዚህም በትጥቅ ትግል ከተሰማሩ ታጋዮች አቅጣጫ የሚሰጡትን መግለጫዎች ዝም ብሎ እንደ ተራ አድማጭ ሳይሆን
“በእርግጥ ይህ አካሄድ ያዋጣል ወይ? ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ይወስደናል ወይ? በመሳሪያ ታግዞ ስልጣን የያዘ ኃይል ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላ ተመልሶ አምባገነናዊ የመሆን እድሉ የሰፋ አይደለም ወይ? (ከህወኃት/ኢህአዴግ ታሪክ እንደምናየው) በብሄር ላይ አተኩረውና መሳሪያ ይዘው የሚታገሉ ኃይሎች እንታገልለታለን ከሚሉት ብሄረሰብ ውጭ ለሁሉም የምትሆን ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ከልባቸው ለመገንባት ይፈቅዳሉ ወይ? ህብረ ብሄር የሆኑና አገራዊ አጀንዳዎች ያነገቡ የትጥቅ ትግል የሚያካሄዱ የተለያዩ ድርጅቶች ትግሉ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ሲደርስ እርስ በርሳቸው ከመጋጨት
የሚከለክላችው ምንድነው? የሚሉና ሌሎች ተመሳሳይ ጥያቄዎች ለመመለስ እንደሚፈልግ ዜጋ ነበር በጥሞና የምከታተለው። በዚያ ቃለ መጠይቅ ውስጥ ታጋይ ፍሰሀ ከተናገራቸው ነገሮች እስካሁን ትዝ የሚሉኝና ዴምህትን በቅርብ እንድከታተል ያደረጉኝ (የቀጥታ ጥቅስ ሳይሆን እኔ እንደገባኝና በጥቅሉ) የሚከተሉት ሁለት አቋሞች ነበሩ:
ሀ)ዴምህት እንደ ድርጅትና፤ (በተለይ ስሙን ብቻ ለተመለከተ) በትግራይ ብሄረሰብ ስም የሚንቀሳቀስ ቢመስልም ድርጅቱ ግን ሙሉ በሙሉ ኢትዮጵያዊ ድርጅት ነው። ህወሀት የትግራይን ህዝብ በተለይ ጠርንፎ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር ለማጋጨት ስለሚፈልግ እኛ የትግራይ ልጆች የትግራይን ህዝብ ከህወሀት የተለየ ኢትዮጵያዊ አቅጣጫ እንዲይዝ ለማድረግ ለጊዜው በስሙ መንቀሳቀስ ከስልት አኳያ ይጠቅማል ብለን እንጂ በድርጅታችን ውስጥ ትግራዋይ ያልሆኑ የሌሎች ብሄረሰብ ተወላጅ ኢትዮጵያውያን ይገኛሉ ስለዚህ በስም እንጂ በተግባር ኢትዮጵያዊ ድርጅት ነን:
ለ) መሰረታዊ ትግላችን ህወሀት/ኢህአዴግን ጥለን እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መመስረት ነው። ይህን ለማድረግ ደግሞ እኛ ብቻችንን የምናደርገው ሳይሆን ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ድርጅቶች ጋር በጋራ የምንሰራው ስራ ነው፤ ስለዚህም ሰፋ ያለ የድርጅቶች ህብረት እንዲፈጠር ማገዝና መስራት ቀዳሚ ስራችን አድርገን የምንወስደው ነው፤ የሚሉት አቋሞች ነበሩ።
ከእስር ቤት ወጥቼና የትግል ስልት መቀየር አስፈላጊ መሆኑን አምኜ ከጓዶቼ ጋር ሆኜ ግንቦት 7ን ከመሰረትን በኋላና የትግል እስትራቴጂያችን “ሁለንተናዊ ትግል” ነው ብለን ካወጅን በኋላ ከዚህ ሁለንተናዊ ትግል ውስጥ አንዱ የሆነውን በመሳሪያ የታገዘ ትግል እንዴት ነው የምናስኬደው በሚለው ጉዳይ ላይ ከሁለት አመታት በላይ ስንመክርበት ቆይተን ጓዳችን አንዳርጋቸው ይህን ስራ እንዲሰራ ወክለነው ወደዚህ ወደኤርትራ መምጣት ከጀመረ ጀምሮ ነበር ስለዴምህት በቅርብ ማወቅ የጀመርነው። ከሞላ ጎደል አንዳርጋቸው ስለ ዴምህት የነገረን ከላይ ፍሰሀ በቃለመጠይቁ ያነሳቸው አቋሞች አሁንም የድርጅቱ አቋሞች መሆናቸውን ነበር። በዚህ በመበረታታትም ይመስለኛል አንዳርጋቸው ከዴምህት አመራርና ታጋዮች ጋር የቅርብ ግንኙነት እንደመሰረተ የምናውቀው። አርበኞች ግንቦት 7 በውህደት ከተመሰረተ በኋላና እኔም እዚህ ከመጣሁ በኋላ ይህን የቅርብ ግንኙነት አጠናክረን ለመቀጠል ነበር ስንሞክር የነበረው የሞላ መክዳት እስከሚፈጠር ድረስ። ሞላም ከከዳ በኋላ እኛ በጊዜው ምክትል ሊቀመንበር ከነበረው ከመኮንን ጋር በግል ብዙ ጊዜ እየተገናኘን ለረጅም ሰዓታት ከመወያየታችንም በላይ ባንድ ወቅት ከሙሉ አመራሩ ጋር ረጅም ጊዜ የወሰደ ስብሰባ አድርገን ባጠቃላይ ስለትግሉና ስለሁለቱ ድርጅቶች ግንኙነት በሰፊው ተወያይተናል። በኛ በኩል ከነኝህ ውይይቶች በመነሳት ዴምህት በሞላ ምክንያት የተፈጠሩትን ችግሮች ቀርፎ ጠንክሮ እንደሚወጣ ምንም አልተጠራጠርንም። ምንም እንኳን ሂደቱ ከጠበቅነው በላይ ጊዜ ቢወስድም በሂደቱም ሆነ በውጤቱ (እስካሁን ከሰማናቸው የጉባኤው ውሳኔዎች) ደስተኞች መሆናችንን በዚህ አጋጣሚ መግለጽ እወዳለሁ።
ምንም እንኳን ይህ የጉባኤያችሁ የመዝጊያ ፕሮግራም የደስታ ፕሮግራም ቢሆንም አሁን በሀገራችን እየተካሄደ ያለውና በጣም በፍጥነት እየተቀያየረ ያለው ሁኔታ ሁላችንንም ከዚህ በፊት ስንጓዝ ከነበረበት አካሄድ በተለየና በጣም ባስቸኳይነት ስሜት እንድንሰራ የሚገፋፋ ሁኔታ ስለተፈጠረ፤ ይህን አጋጣሚ ተጠቅሜ በሀገሪቱ ስላለው ሁኔታና ይህም በትግላችን ላይ ባጠቃላይ፤ በተለይ ደግሞ በዴምህት ላይ ይዞ የመጣው የተለየ ሀላፊነት ላይ አንድ ሁለት ነጥቦች ለማንሳት ይፈቀድልኝ።
ሀገራችን አሁን ያለችበት ሁኔታ ምን ይመስላል? ከኛ ምን ይጠብቃል?
ሁላችንም እንደምናውቀው በአሁኑ ሰዓት ሀገራችን በህዝባዊ እምቢተኛነት እየተናወጠች ነው። ከዘጠኝ ወራት በፊት ጀምሮ በኦሮምያ ክልል የተጀመረውና በፍጹም ሊበርድ ያልቻለው ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያካተተው የህዝባዊ እምቢተኝነት እንቅስቃሴ የብዙ ህዝብ ህይወት ቀጥፎም እንደቀጠለ ነው። ይህ እንቅስቃሴ ካለፉት ሁለት ወራት ወዲህ አድማሱን ወደ አማራ ክልል አስፍቶ በተለይ ጎጃምና ጎንደር ሰፊ ህዝባዊ አመጽ የሚደረግበት ቀጠና አድርጎታል። በነኝህ ሁለት ዞኖች በኅወሀት/ኢህአዴግ እየተፈጸመ ያለው ወደር የማይገኝለት አፈናና ግድያ ትግሉን ሊያስቆመው አልቻለም። ከሰሞኑ ደግሞ ተዳፍኖ የቀረ ይመስል የነበረው የኮንሶ እንቅስቃሴ አገርሽቶ ብዙ ሰላማዊ ሰዎችን እየገበረ ይገኛል። ይህ ሁኔታ ክረምቱ ከወጣና ትምህርት ቤቶች ከተከፈቱ በኋላ ከኦሮምያና ከአማራ ክልሎች በተጨማሪ በሌሎችም የደቡብ ክልል ወረዳዎችና እንደ ጋምቤላና አፋር ባሉ ክልሎች ይሰራጫል ተብሎ ይጠበቃል። ይህ በሀገራችን ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ መጠነ ሰፊ ህዝባዊ እንቅስቃሴ ብዙ ትርጉም ያለውና እኛንም እንደ ታጋይ ድርጅቶችና የህዝቡን ትግል እንደሚደግፉ ኃይሎች እስካሁን ስንሄድበት የነበረውን አካሄድ በደንብ መርምረን ለጊዜው የሚመጥን አካሄድ እንድንቀርጽ ያስገድደናል። ከዚህ አንጻር ይህ አዲስ ኩነት በህዝቡ የትግል ስሜት ላይ፤ ህወኃት/ኢህአዴግ ለዚህ የህዝብ ትግል በሚሰጠው መልስ ላይና፤ እኛ እንደታጋይ ድርጅቶች ሁለቱንም ከግምት ወስደን በምንሰጠው መልስ ላይ ያላቸውን አንድምታዎች በአጭሩ ላቅርባቸው።
በመጀመሪያ የሀገሪቱን ፖለቲካ በቅርብ እንከታተላለን የሚሉትን ሳይቀር ጉድ ያስኘው፤ ህወኃት/ኢህአዴግ በልማት ፕሮፓጋንዳ፤ በአፈናና በትር፤ ቅስሙን ሰብሬ የፍርሀት ቆፈን ውስጥ አስገብቼዋለሁ፤ ህዝቡ ከኛ ሌላ አማራጭ ፖለቲካ ሊያይ እንኳን የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል ለዚህም ማሳያው በ2007ቱን የይስሙላ ምርጫ 100% ማሸነፌ ነው፤ ይህንንም ኦባማ ሳይቀር የአለም ታላላቅ ሀገሮች መስክረውልኛል ብሎ በትእቢት በተወጠረበት ወቅት ነው ህዝቡ ምንም አይነት ፍርሀት የማያሸንፈውና ከሚፈልገው ነጻነት የሚያስቆመው ምንም ምድራዊ ኃይል እንደሌለ ደረቱን ለጥይት ሰጥቶ የሞቱ ጓደኞቹንና ልጆቹን እየቀበረ ትግሉን የቀጠለው። ይህ ለገዢው ኃይልና ለተባባሪዎቹ ብቻ ሳይሆን ህወኃት/ኢህአዴግን በተለያየ መንገድ ለሚቃወሙ ተቃዋሚ ድርጅቶችም ግልጽ ያደረገው የኢትዮጵያ ሕዝብ ያለነጻነት መኖር እንደሰለቸው፤ ለነጻነቱ ህይወቱን ለመስጠት ዝግጁ እንደሆነ፤ በዚህ ትግሉ ህወሃት/ኢህአዴግን ገርስሶ መጣሉ የማይቀር ብቻ ሳይሆን ከዚያም በኋላ ራሱ በመረጣቸው መሪዎች መተዳደር የሚፈልግ፤ ሰው ሆኖ ሰብአዊ መብቱ ተከብሮ፤ ከሁሉም ኢትዮጵያዊ ጋር በእኩልነት መኖር እንጂ ካሁን በኋላ በምንም አይነት የጉልበት አገዛዝ እንደማይተዳደር ያወጀበት ነው ብለን ልንወስድ እንችላለን። ይበልጥ የሚገርመው ደግሞ በዚህ የትግል ሂደት እንደተፈራውና ህወኃት/ኢህአዴግ አጠንክሮ ሲሰራበት የቆየው የብሄር ክፍፍል ሀገሪቷን ወደ ቀውስ ሳይሆን፤ የተለያዩ ብሄረሰቦች አንዳቸው ለሌላው በደል የሚያስቡበትና ነጻነታቸውን በግል ሳይሆን በጋራ ትግል እንደሆነ የሚያገኙት በማመን ትግላቸውን በጋራ የነጻነትና ያንድነት መንፈስ ማስተሳሰራቸው ነው። ምንም እንኳን የዚህ ትግል የመጨረሻው ውጤት ምንነት ገና ያልተጻፈ ቢሆንም፤ ይህ ለሀገሪቱ የወደፊት እጣ ፈንታ እጅግ አወንታዊ የሆነ ክስተት ነው።
ሁለተኛውና ይህን ሁኔታ በአጽንኦት እንድንመለከተው የሚያስገድደንና እኛም የምንሄድበትን አካሄድ በጥሞና እንድንመረምር የሚያደርገን ከዚህ ጋር የተያያዘው ክስተት ህወኃት/ኢህአዴግ ለዚህ የህዝብ ትግል እየሰጠ ያለው መልስና እንዴት ሊሄድበት እንዳሰበ የሚያመለክቱት አደገኛ አዝማሚያዎች ናቸው። ምንም እንኳን የህዝቡ ትግል ባብዛኛው ሰላማዊ የነበረ ቢሆንምና የህዝቡ ጥያቄም በድርድርና በሰላማዊ መንገድ ሊፈታ እንደሚችልና እንዲፈታ ከተለያየ አቅጣጫ ጥያቄዎች ቢቀርቡም፤ (ለምሳሌ እንደነ ጀነራል ጻድቃንና አበበ ጆቤ ያሉ ለስርዓቱ ቅርበት ያላቸው ሰዎችም በጽሁፍ ያቀረቡት ቢሆንም) መንግስት የመረጠውና የሚያውቅበት ብቸኛ አካሄድ ባንድ በኩል ፍጹም ያረጀና ካሁን በኋላ ምንም ሰሚ የሌለውን ፍጹም የተምታታ የሽንገላ አካሄድ፤ (ዋና መስመራችን ትክክል ነው ግን ትንሽ የአሰራር ስህተቶች ሰርተናል እሱን ደግሞ እናርማለን…ወዘተ) በይበልጥ ግን ችግሩን ይበልጥ በማጦዝ በመሳሪያ ኃይልና በጉልበት ለመጨፍለቅ፤ አልፎም ችግሩን የዴሞክራሲና የነጻነት ፍለጋ ትግል አድርጎ ሳይሆን በጣም በሚገርምና ለወደፊቷ ኢትዮጵያ እጅግ አደገኛ በሆነ መንገድ ትግሉ የኦሮሞና በተለይ የአማራ ህዝብ በትግራይ ህዝብ ላይ የተነሳና በትግራይ ህዝብ ላይ “የዘር ማጥፋት” ለማካሄድ የሚደረግ እንቅስቃሴ አድርጎ ሰፊ ፕሮፓጋንዳ መክፈቱ ነው። ይህ ህወኃት “ስልጣኔ ሊነካ ነው” ብሎ ሲያስብ የትግራይን ህዝብ ከጎኑ በማስፈራራት ለማሰለፍ የሚያደርገው የተለመደ መሰሪ አካሄዱ እንደሆነ እኛ በምርጫ 97 ወቅት በተቃዋሚው ጎራ ተሰልፈን ፖለቲካው ውስጥ የነበርን ሰዎች ያየነው፤ እኩይና ኢትዮጵያን ለማጥፋት የሚፈልግ ለሀገሪቱ ምንም በጎ የማይመኝ የውጭ ኃይል የሚያደርገው እንጂ፤ ከዚህ ህዝብ ጋር ወደፊት አብሬ እኖራለሁ ብሎ የሚያስብ ሀገራዊ ኃይል ሊያስበው እንኳን የማይገባ እጅግ አደገኛ አካሄድ ነው።
በምርጫ 97 ወቅት የህወኃት የደህንነት ክፍል ሌሊት ሌሊት ጸረ ትግራይ የሆኑ ፓንፍሌቶች በተቃዋሚው ስም እያወጣ ይበትን እንደነበር እናውቃለን። “እቃ ወደ ቀበሌ ትግሬ ወደ መቀሌ” የሚል ያነጋገር ፈሊጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀመው የህወሀት ባለስልጣን የነበረ ሰው በቪኦኤ ቀርቦ ነው ግን ይህንን ማን እንዳለው ሳይናገር “ተቃዋሚዎች እንዲህ ይላሉ” ብሎ የነዛው እሱ ነው። እራሳቸው ያሰራጩትን ከፋፋይ የጸረ ትግራይ ፓንፍሌቶች “ሚዲያ ላይ ወጥተን በጋራ እናውግዝ” ስንላቸው ስራቸውን ስለሚያውቁት እምቢ ይሉ የነበሩት እነሱ ነበሩ። ኢንተርሀምዌ የሚባል አስከፊውን የሩዋንዳን ጭፍጨፋ የሚያስታውስ ቃል በኢትዮጵያ ያስተዋወቀው በአሳፋሪ ሁኔታ በምርጫ መሸነፉ ያስደነገጠው፤ ክፋት እንጂ ለሀገሪቱ ምንም ጥሩ ራዕይ ያልነበረው፤ የህወሀት መሪ የነበረው መለስ ነበር። ይህንን መለስ ከቤተመንግስት ሆኖ የተፋውን መርዝ ነበር ስዩም መስፍን እንደ በቀቀን በምርጫ ክርክሩ ወቅት ሊያስተጋባ የሞከረውና የከሸፈበት። ይህ ያንጊዜ የትግራይ ሰዎችን ለማሰባሰብና ተቃዋሚውን ለማስጠላት፤ ይበልጥ ደግሞ ፈረንጆቹን ለማጭበርበርና የምንወስደውን የኃይል እርምጃ ዝም ብለው እንዲመለከቱት ጠቅሞናል ያሉትን አደገኛና ፍጹም ሀላፊነት የማይሰማው “ከኔ በላይ ሰርዶ አይብቀል” የሚለውን አህያማ ፍልስፍና የሚያስታውስ አካሄድ ነው አሁንም ለሁለተኛ ጊዜ ስልጣናቸው በህዝብ ትግል መነቃነቅ ሲጀምር እንደገና ይዘው ብቅ ያሉት። መቼም ከሰሞኑ እነ አባይ ጸሀዬና ስዩም መስፍን የመሳሰሉ የህወኃት ቱባ ባለስልጣናት የሚናገሩትን እጅግ አሳፋሪና የሚያቅለሸልሽ፤ ፍጹም ሀላፊነት የማይሰማው ንግግር “እንዴ እነዚህ ሰዎች እኛ ከስልጣን ከምንወርድ ሀገሪቱ ትጥፋ ብለው የሚያምኑ ሰይጣኖች ናቸው እንዴ?” ብሎ ያልታዘበና ያላዘነ የኢትዮጵያ ወዳጅ ያለ አይመስለኝም። ይህ ግን እንደገና “እንዲሰራላቸው” በፍጹም መፍቀድ የለብንም።
ይህ አዲሱ “የዘር ማጥፋት” ሟርት በምርጫ 97 ጊዜ ከነበረው ጋር የሚያመሳስለው ሁለቱም የተፈበረኩት የህወኃት መሪዎች በአራት ኪሎ ላይ በጉልበት ያገኙት ስልጣን ሲነቃነቅ ያንን ለመከላከልና የትግራይን ህዝብ አስፈራርተው ከጎናቸው ለማሰለፍ ያደረጉት እኩይ ስራ መሆኑ ነው። በሁለቱም ጊዜ በትግራይ ህዝብ ላይ እንደ ህዝብ የተቃጣ፤ አይደለም የተቀነባበረና ተግባራዊ የሆነ፤ የታሰበ እንኳን ጥቃት አልነበረም። የለም። በምርጫ 97 ጊዜ ለዚህ የዘር ማጥፋት ሙከራ በማስረጃነት የቀረበውን የአቶ ኑር ሁሴንን ምስክርነት ፍርድ ቤት ሆኖ ለሰማ እነኝህ ሰዎች የሚሰሩትን ያውቃሉ? በእርግጥ ህዝቡን ለማባላት ይፈልጋሉ? ይህን በዘር ላይ የተመሰረተ የጥላቻ እሳትስ አንዴ ከለኮሱት በኋላ እነሱን ሳይበላ ያልፋል ብለው የሚያስቡ ደንቆሮዎች ናቸው? ብሎ ነው የሚገረመውና ለሀገሪቱም የሚፈራላት። የአሁኑን የህወሀት ሟርት ለማስረዳት የሚቀርበው ማስረጃ ተብዬው ደግሞ ባንዳንድ ትግሉ በሚካሄድባቸው የአማራና የኦሮምያ ክልሎች አንዳንድ የትግራይ ብሄረሰብ አባላት የሆኑ ግለሰቦች ንብረት ላይ የሀይል እርምጃ ተወስዷል የሚል ነው። የሰላም ባስ መቃጠልም እንደ ማስረጃነት ይቀርባል።
በመጀመሪያ አንድ ነገር ያለምንም ማሽሞንሞንና ምክንያታዊ ለማድረግ ሳይሞከር ግልጽ መሆን ያለበት ነገር አለ። በማንም ኢትዮጵያዊ ላይ በብሄር ማንነቱ ምክንያት ብቻ የሚደርስ ምንም አይነት የኃይል እርምጃ ብቻ ሳይሆን ምንም አይነት ትንሽም እንኳን የመብት መጣስ ሁላችንም አጥብቀን ከልባችን ልናወግዘው የሚገባን ጉዳይ ነው። ይህንን የምናደርገው ደግሞ ለግዜያዊ የፖለቲካ ፍጆታ ሳይሆን እንደሰው ልጆችና እንደ ኢትዮጵያውያን በማንም ሰው ላይ የሚደርስ ኢፍትሀዊ በደል ውስጣችንን ስለሚያመን ሊሆን ይገባል። በተለይ በዚህ የትግል ወቅት በፍጹም ልንረሳው የማይገባው ዋና ነገር ይህ ትግል ከምንም በላይ ለፍትህ የሚደረግ ትግል መሆኑን ነው። ህወሀት/ኢህአዴግን የምንታገለው መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ (የትግራይን ህዝብ ጨምሮ) ፍትህ ስለከለከለ ነው። ፍትህን አውቀው እየረገጡ ለፍትህ የሚደረግ ትግል ፍጹም አላማውን የሳተ የእውር ድንብር ትግል፤ ሲያልፍም ጥላቻን ብቻ ሰንቆ ለጉልበትነት የሚጠቀም ፍጹም አጥፊ ጸረ_ኢትዮጵያ ጉዞ ነው የሚሆነው። ከዚህ ለፍትህ ካለን ፍጹም የማያወላዳ አቋም ነው በኦሮሞ ወገኖቻችንም ሆነ በአማራ፤ በጋምቤላ ሆነ በኮንሶ፤ በቤንሻንጉል ሆነ በአፋር፤ በትግራይ ሆነ በጉራጌ፤ በክርስቲያኖች ሆነ በሙስሊሞች፤ በቡድኖች ላይ ሆነ በግለሰቦች፤ ላይ የሚደርሱ በደሎች ግፎችና የአድሎና የዘረፋ ስራዎችን ሁሉ የምናወግዘው። በጋራ ታግለን እጅ ለእጅ ተያይዘን ለሁላችንም የምትሆን፤ ሁላችንንም እንደ ኢትዮጵያውያን በእኩልነት የምታይና የምታስተናግድ ሀገር እንገንባ የምንለው። ለዚህ ነው ከህወሀት/ኢህአዴግ ጋር የሞት የሽረት ትግል ውስጥ የገባነው።

ይህንን ለፍትህ የሚደረግ የህዝብ ትግል የሰዎችን እንሰሳዊ የሆነ የራስ የመከላከል ስሜት አነሳስተውና በዚህም ጊዜያዊ ድጋፍ ባንዳንድ ወገኖች ዘንድ እናገኛለን፤ ይህንንም ለጊዜያዊ የፖለቲካ ጉልበትነት እንጠቀምበታለን ብለው የሚያስቡ አክራሪና አጥፊ ኃይሎች ትግሉን ወደ ጥላቻ ትግል ለማስቀየስ የሚሞክሩ ሊኖሩ እንደሚችሉ እናውቃለን። እንደነዚህ አይነት ጥቂት ኃይሎች በህዝቡ ትግል ውስጥ ተመሽገው የሚወስዷቸው እርምጃዎችንና የሚያካሂዷቸውን የጥላቻ መርዛማ ፕሮፓጋንዳ ህወኃት/ኢህአዴግን ስለተቃወሙ ብቻ ዝም ብለን “የህዝቡ ትግል አካላት ናቸው” ብለን የምናልፋቸው ሊሆኑ በፍጹም አይገባም። እንዲህ አይነት እኩይ ኃይሎችን ማውገዝ ብቻ ሳይሆን አስቀያሚ ገጽታቸውን በሚያሳዩበት ጊዜ ሁሉ እነሱን ማጋለጥና ከህዝቡ ፍትሀዊ ትግል ማግለል ለእውነትና ለፍትህ፤ ኢትዮጵያችንን ከተጋረጠባት አደጋ ለመታደግ፤ ብሎም ለእውነተኛ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንታገላለን የምንል ኃይሎች ሁሉ ያለማሰለስ ልንሰራው የሚገባን ስራችን ነው።
ይህ ግልጽ ከሆነ በኋላ ግን የህወኃት እልቂት ጋባዥ መሪዎች የሚያቀርቡት ክስ በእርግጥ እውነትነት ያለው ነው? የሚለውን ከስሜት ነጻ ሆኖ ማየትና መሞገት፤ ስለዚህም የህወሀት የአጥፍቶ መጥፋት ፕሮፓጋንዳ ሰለባ እንዳንሆን (በተለይ ታፍኖና ሌላ ሀሳብ እንዳይሰማ የተከለከለው የትግራይ ህዝብ) መከላከል ያስፈልጋል። ከዚህ አንጻር በመጀመሪያ መታየት ያለበት በየት ቦታ ነው “የትግራይን ህዝብ የማጥፋት” እንቅስቃሴ አይደለም፤ ሙከራውስ የተደረገው? የሚለውን ማየት ተገቢ ነው። በቅርቡ በኢሳት ቴሌቪዥን ላይ ቀርበው ቃለምልልስ የሰጡት ሁለቱ ቆራጥ የትግራይ ልጆች (እነወዲ ሻምበል) በቃለምልልሱ ላይ እንደተናገሩት ይህ የአሁኑ የህዝብ እንቅስቃሴ እየተደረገ ያለው በዋናነት በኦሮሞና በአማራ ክልል እንጂ በጣም ብዙሀኑ የትግራይ ህዝብ በሚኖርበት የትግራይ ክልል አይደለም። በወልቃይት ህዝብ የማንነት ጥያቄ ዙሪያ እንኳን እስካሁን እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ብናይ፤ የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ ጥያቄ እኛ በታሪካችንም ሆነ በባህላችን አማሮች ነን፤ ይህ ያማራ ማንነታችን ይታወቅልን የሚል ጥያቄ ያነገበ እንጂ ለረጅም ጊዜ አብሮን ሲኖር የነበረውና የተዋለድነው የትግራይ ብሄረሰብ ህዝብ አይደለም ይጥፋልን፤ ካካባቢያችን ይውጣልን የሚል ጥያቄ እንኳን የለውም። ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሚታገሉ ሁሉም ኃይሎች (ምናልባት እዚህ ግቡ ሊባሉ የማይችሉ በጣም ጥቂት ጥግ የያዙ አክራሪዎች ካልሆኑ በስተቀር) እስከሚሰለች ድረስ ሁሌም የሚሉት ህወኃት የትግራይን ህዝብ አይወክልም፤ የትግራይ ህዝብ እንደሌላው ብሄረሰብ ሁሉ ታፍኖ የተያዘ ህዝብ ነው፤ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ይናፍቃል፤ ስለዚህም እንደህዝብ የለውጡ አካል ነው፤ በትግራይ ክልል እንደሌሎች ክልሎች ጎልቶ የሚታይ (እንደነ አረና ያሉ ድርጅቶች የሚያደርጉት ትግል እንደተጠበቀ ሆኖ) የህዝብ ጸረ_ህወኃት እንቅስቃሴ የማይታየው በትግራይ ያለውን መጠነ ሰፊ አፈና የሚያመለክት እንጂ የትግራይ ህዝብ ከሌላው ህዝብ የተሻለ ደልቶት ወይንም የመብት መከበር ስላገኘ አይደለም ነው የሚሉት። በሌላ አነጋገር የዴሞክራሲ ትግሉ ኃይሎች በጣም አብዛኛው አቋም፤ እንደነሳሞራ ያሉ የህወሀት አላዋቂና ዘራፊ መሪዎች የሚሉትን “ህወሀት ማለት የትግራይ ህዝብ ማለት ነው፤ ህወሀት ከጠፋች የትግራይ ህዝብ ይጠፋል…ወዘተ” የሚል ቀጣፊና ጸረ_የትግራይ ህዝብ ንግግር ፍጹም በመጻረር፤ ህወሀት ከትግራይ ህዝብ አብራክ የወጣ ጭንጋፍ የዘራፊዎች ቡድን እንጂ በፍጹም የትግራይን ህዝብ የማይወክል ሀይል እንደሆነ ነው።
በየትኛውም ክልል በሚደረገው ህዝባዊ ትግል ህወሀት/ኢህአዴግን ባጠቃላይ፤ ህወሀት በመንግሥት ስርዓቱ ላይ ባለው ትልቅ ሚና ደግሞ በተለይ፤ ይወገዝና ከጫንቃችን ይውረድልን የሚል ካልሆነ በቀር የትግራይን ህዝብ ያጠቃለለ አንድ መፈክር እንኳን ታይቶ አይታወቅም። የሰላም ባስ ሲቃጠል ድርጊቱ ያነጣጠረው በህወሀት የማፍያ የዝርፊያ ቡድን ላይ እንጂ በፍጹም በትግራይ ህዝብ ላይ አይደለም፤ ልክ በባህርዳር የዳሽን ቢራ ማከፋፈያ ሲቃጠል ያነጣጠረው የብአዴን ዘራፊዎች ላይ እንጂ እሱ እወክለዋለሁ የሚለውን የአማራውን ህዝብ እንዳልሆነ ሁሉ። ከእንደዚህ አይነት እርምጃዎች ባሻገር በዚህ በአሁኑ የትግል ሂደት “የዘር ማጥፋት እርምጃ” ማስረጃ ተብሎ የሚቀርበው በተወሰኑ የትግራይ ባለሀብት ግለሰብ ንብረቶች ላይ በተለይ በጎንደር ተወሰዱ የተባሉ እርምጃዎች ናቸው። ምንም እንኳን በጎንደር በነበረው እንቅስቃሴ ላይ የተሳተፉ ወገኖች በሰጧቸው ቃለመጠይቆች እንደሚሉት ተጠቁ የሚባሉት ንብረቶች የትግራይ ባለሀብቶች ስለሆኑ ሳይሆን እነኝህ ሰዎች በቀጥታ የህወሀት ወኪሎች የሆኑና ባካባቢው ከህወሀት የስለላ አካሎች ጋር በቅርብ የሚሰሩ ሰዎች ስለሆኑ ነው፤ እንጂማ የትግራይ ባለሀብቶችን ትግራዋይ ስለሆኑ ብቻ የማጥቃት እርምጃ ለመውሰድ ታስቦ ቢሆን፤ ከነኝህ ንብረቶችም ለማውደም እጅግ ይቀሉ የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ባለሀብቶች ንብረቶች በጎንደር ዙሪያ ሞልተው አልነበር ወይ? ባካባቢያችን አብረው ከሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ላይ በአንድ ሲቪል ሰው እንኳን የደረሰ ጉዳት አለ ወይ? የሚለው መከራከሪያ ምክንያታዊ ቢሆንም፤ ቢያንስ እንደ ህወሀት ላሉ (ሌሎችም አክራሪ ቡድኖች) እኩይ ሀይሎች መጠቀሚያ እንዳይሆን እንዲህ አይነቱ እርምጃ ከትግሉ አንጻር ከጥቅሙ ጉዳቱ ስለሚያመዝን በፍጹም መወሰድ የሌለበት ነውና መታረም ያለበት መሆኑን መቀበል ይገባል። ያም ሆኖ ግን እነኝህ እርምጃዎች በምን ሂሳብ ነው የዘር ማጥፋት እንቅስቃሴ የሚሆኑት? ልክ በጊዜው የህወሀት ታጣቂ በነበሩት በአቶ ኑር ሁሴን ላይ የድብደባ እርምጃ የወሰዱ ወጣቶች (በፍርድ ቤት በቀረበው ማስረጃ ዱላው መሳሪያ ለመቀማት ይሁን ለምን ባይታወቅም እሳቸውን ከዱላው ያስጣሏቸው ያካባቢው ወጣቶች የቅንጅት ደጋፊዎች ተብለው በዘር ማጥፋት የተከሰሱት ናቸው) ለዝርፊያ ብለው ይሁን በወጣትነት እድሜ በስሜት ተገፋፍተው እንዲህ አይነት እርምጃ ቢወስዱ እንዴት ነው ይህ የዘር ማጥፋት ስራ የሚሆነው? ጥቂት በትዕቢት የተወጠሩ የትግራይ ወጣቶች ቡና ቤት ውስጥ እየጠጡ ባካባቢያቸው ያሉትን ሌሎች ደንበኞች አላስቆም አላስቀምጥ ቢሉና በዚህ ድርጊት ከተበሳጩት ሌሎች ደንበኞች ጋር (ባጋጣሚ ትግራዋይ ያልሆኑ) ድብድብ ቢገጥሙ እንዴት ነው ይህ ግጭት ጥቂት የጠገቡ ወጣቶች የተነኮሱት ግጭት መሆኑ ቀርቶ የዘር ግጭት የሚሆነው?
ያንድ ሀገር ሰው፤ ያውም ህዝብን ለማስተዳደር በጉልበት እንኳን ቢሆን ስልጣን ላይ ያለ ኃይል፤ አይደለም ያልሆነ የውሸት ድራማ ፈጥሮ የሌለ የህዝብ ለህዝብ ጸብ ሊጭር፤ ህዝብን ከህዝብ ሊያባላ የሚችል ነገር እንኳን ቢፈጠር ክስተቱን የግለሰብ ጠቦች አድርጎ አለስልሶ ለማለፍ መሞከርና ባይሆን ክስተቱን የፈጸሙት ሰዎች ላይ ጠንካራ እርምጃ ወስዶ እንዲህ አይነት ክስተት ዳግም እንዳይፈጠር መከላከል ነው እንጂ የሚጠበቅበት እንዴት እንዲህ አይነቶችን ግጭቶች የዘር ግጭት እንዲሆኑ ለማባባስ ተግቶ ይሰራል? (ድሮ ትዝ ይለኛል ለጥምቀት በዓል ጊዜ በጭፈራ ወቅት የተለያዩ የብሄረሰብ ጭፈራዎች ሲደረጉ የጭፈራው ስሜት የሚፈጥራቸው የብሄረሰብ ግጭቶች ይከሰቱ ነበር። እነኝህ ግን ከጭፈራው ጋር የተገናኙ የወጣቶች የደም ትኩሳት የፈጠራቸው ክስተቶች ሆነው እዚያው ባካባቢው ፖሊስ ያልቃሉ። ለሚዲያ ፍጆታ እንኳን አይቀርቡም ነበር እንኳን እንደ ዘላቂ የብሄሮች የመጠፋፋት ጠላትነት ሆነው በመንግሥት መገናኛ ብዙሀንና በመንግስት ባለስልጣናት ለሚዲያ ፍጆታ ሊውሉ)። ይህን አይነቱን በፍጹም ሀላፊነት የጎደለው አካሄድ ነው እንግዲህ የህወሀት ጀሌዎች ከሰሞኑ ስራችን ብለው የተያያዙት።
ይህንን የሰሞኑን ሟርት ግን በምርጫ 97 ጊዜ ከተጠቀሙበት ሁኔታ የሚለያቸው ሁለት ወሳኝ ነገሮች አሉ። በምርጫ 97 ጊዜ ይህ ፕሮፓጋንዳቸው ያነጣጠረው ቅንጅት የሚባል በምርጫ ያሸነፋቸው አንድ የፖለቲካ ድርጅት ላይ ነበር። ብዙው የግጭቱ ክስተትም የነበረው በትላልቅ ከተሞችና ከህወሀት/ኢህአዴግ የአፈና ኃይሎች ውጭ ምንም ባልታጠቁ ሰዎች ላይ ነበር። ያሁኑን አካሄዳቸውን ግን ፍጹም አደገኛ የሚያደርገው አንድም ትግሉ በራሱ በህዝቡ የሚመራና በነኝህ ክልሎች ውስጥ ያሉትን በጣም አብዛኛውን ህዝብ ያሳተፈ መሆኑ ነው። ይህ ደግሞ የህወሀትን የፕሮፓጋንዳና የማጥፋት ዘመቻ ባንድ ድርጅት ላይ ሳይሆን በየክልሎቹ ባለው ህዝብ ላይ ያነጣጠረ እንዲሆን ያደርገዋል። ሁለተኛው ይህ የህዝብ እንቅስቃሴ የሚካሄደው በከተሞችም በገጠሮችም ስለሆነና በተለይ በገጠር ያለው ህዝብ (በተለይ በሰሜኑ ያገራችን ክፍል) በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የታጠቀ ስለሆነ እንደ 97ቱ ዝም ብሎ የሚገደል ሳይሆን በጎንደር እንዳየነው እራሱን በመሳሪያ ኃይልም ቢሆን ለመከላከል የተዘጋጀ ህዝብ መሆኑ ነው። ይህ አዲስ ሁኔታ የህወሀትን አጥፊ ፕሮፓጋንዳ ሰፊ ውጤት የሌለውና እንደ ምርጫ 97ቱ ጊዜ ለህወሀት የፖለቲካ ጥቅም በማስገኘት (የትግራይን ህዝብ ከጎኑ በማሰለፍ) ብቻ ይደመደማል ማለት በእሳት ላይ የሚጫወት ህጻን ልጅ የሚያደርገው አይነት የጨቅላነት አለማወቅ ነው። ወይም ደግሞ የህወሀት አይነት ስልጣኑን ቢያጣ ከሚያጣው ዝርፊያ በቀር ለሀገርና ለህዝብ ምንም ደንታ የሌለው የማፍያ ቡድን የሚሰራው፤ ለማጥፋት ያለውን ኃይል ውጤቱ ምንም ይሁን ምን እስከመጨረሻው ለመጠቀም ቅንጣት ታክል ሀፍረት የሌለው በአደገኛ ተስፋ መቁረጥና በህዝብና በሀገር ላይ የሚደረግ ግዴለሽ የቁማር ጫወታ ነው። ለዚህ ነው ይህንን ያሁኑን የጥፋት መንገዳቸውን በምንም አይነት መንገድ ባስቸኳይ ማስቆም የሚኖርብን።
እንዴት ነው ይህንን የህወሀት ቁማር ሃገራችንን ሳያጠፋት የምናስቆመው? ዴምህትም ሆነ የህወሀትን ምንነት የተረዱ የትግራይ ድርጅቶችስ ምን ይጠበቅባቸዋል?
ይህንን የህወሀት አጥፊ መንገድ እንዴት ነው የምንከላከለው የሚለው ለአንድ ወገን የሚቀርብ ጥያቄ ሳይሆን ሁላችንንም እንቅልፍ ሊነሳ የሚገባና በከንፈር መምጠጥ ሳይሆን በተግባር ልንቋቋመው የሚገባን የጊዜው ችግር ነው። በመጀመሪያ ለወያኔዎች ግልጽ ሊሆን የሚገባው አሁን ህዝቡ የገባበት ትግል በምንም አይነት የጥፋት ሟርት ተታሎ የሚተወው ሳይሆን እስከ ነጻነት ድረስ የሚገፋበት መሆኑን ነው። ይህ የማስፈራራት ጫወታ የተበላ እቁብ ነውና በዚህ የሚቆም ትግል የለም። ይህ ግልጽ ከሆነ በኋላ ግን ለፍትህ፤ ሀገርን ለማዳንና ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሚታገሉ ኃይሎች በሙሉ የፍትህ ትግሉ ያልሆነ አቅጣጫ እንዳይይዝ በሚያደርጓቸው የፕሮፓጋንዳ ስራዎችም ሆነ በተግባራዊ ትግሉ ወቅት ማድረግ የሚገባቸውን ጥንቃቄ ከላይ በትንሹ ጠቅሼዋለሁ። ዛሬ ይህን ንግግር የማደርገው ባብዛኛው የትግራይ ታጋዮች በሚገኙበት ስብሰባ እንደመሆኑና፤ ይህ ህወሀት ከስልጣኔ ይታደገኛል ብሎ እንዲፈጠር የሚፈልገው ግጭት ከሌሎቻችንም በላይ በስሜት አጣብቂኝ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ ብዬ ከማስባቸው የትግል ጓዶቻችን ጋር ስለሆነ (ከዚህ በፊት ካደረግናቸው ውይይቶች ይህንን የስሜት ጭንቀት ስለታዘብኩ) ሃሳቤን በተለይ የትግራይ ወገኖቻችንን በተመለከተና በተለይም ዴምህት ላይ ያለውን ሀላፊነት አጽንኦት ለመስጠት በዚያ ላይ ብቻ አተኩሬ፤ ከዚህም በላይ ሳላሰላቻችሁ እንዲሁም የረዘመው ንግግሬን በቶሎ ልቋጭ።
በዘር ማንነታቸው የትግራይ ብሄረሰብ አባላት ሆነው ህወሀትን የሚቃወሙና በተቻላቸው መጠንና በተለያየ የትግል ዘዴ፤ አንዳንዴ በግለሰብ ደረጃ በሌላ ጊዜ ደግሞ በተደራጀ መልክ፤ ሲመቻቸውና ሁኔታው ሲፈቅድላቸው እራሳቸውን በትግራይ ብሄረሰብ ዙሪያ ባጠነጠኑ ድርጅቶች ሌላ ጊዜ ደግሞ በህብረ ብሄራዊ ድርጅት ውስጥ በመሆን ሥርዓቱን የታገሉ ብዙ የትግራይ ተወላጆች ህወሀት ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ እንደነበሩና አሁንም እንዳሉ ይታወቃል። ቀድሞ ህወሀት ውስጥ ሲታገሉ የነበሩና እንዲያውም ባመራር ደረጃ ሲሰሩ የነበሩ እንደነ አረጋዊ በርሄ፤ ግደይ ዘራጽዮን፤ ገብረመድህን አርአያ፤ ተስፋዬ ቼንቶ…ወዘተ ያሉ አሁን ድረስ ህወሀትን የሚታገሉ ታጋዮች እንዳሉ ይታወቃል። እንደዚህ በሚዲያ ከሚታወቁት ውጭ በጣም ብዙም ባይባሉ ሌሎችም የቀድሞ የህወሀት ታጋዮች አሁን ግን በውጭ ሀገር ከዴሞክራሲ ትግሉ ጋር አብረው ያሉ እንዳሉ እናውቃለን። ህወሀት ከተመሰረተ ጀምሮ ያቀነቅን የነበረው ብሄር ተኮር ትግል ስለማይጥማቸው ህብረ ብሄራዊ ትግል ውስጥ (በተለይ በኢህአፓና ኢህአሰ ውስጥ) ገብተው ከከፍተኛ ያመራር ቦታዎች ጀምሮ እስከ ተራ አባልና ታጋይ ድረስ ሲታገሉ የወደቁ ብዙ የትግራይ ጓዶቻችን እንደነበሩ በጊዜው የነበርነው እናውቃለን፤ ስለ ብዛቱ ባላውቅም አሁንም እንኳን በኢህአፓ ውስጥ ያሉ የትግራይ ልጆች እንዳሉ አውቃለሁ። ህወሀት/ኢህአዴግ ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላም ቁጥራቸው እየቀነሰ ቢሄድም በህብረ ብሄራዊ ድርጅት ውስጥ ሆነን ነው ለዴሞክራሲ የምንታገለው ብለው እንደነ ዶ/ር ሃይሉ አርአያ፤ ሸዋዬ ኪሮስ፣ አስራት አብርሃ ያሉ የህወሀት ዘረኝ ቅስቀሳ ሳይበግራቸው ቀድሞ ቅንጅት በኋላም አንድነት ጋር ሆነው ለአላማቸው ጸንተው የቆሙ ምርጥ ኢትዮጵያውያን የትግራይ ልጆች አሉ። ከኔ በስተቀር ሌላ ትግራዋይ ድርጅት ሊኖር አይችልም ብሎ ህወሀት ፍጹም ጠርንፎ በያዘው በትግራይ ክልል እንኳን “ጸረ_ትግራዋይ” ፤ “የትምክህተኞች መሳሪያ” እየተባሉ፤ ከማህበረሰቡ እንዲነጠሉ እየተደረጉ ጥርሳቸውን ነክሰው ለእውነተኛ ዴሞክራሲ እንታገላለን ብለው ህይወት እየገበሩም በአረና ስር ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ ትግራውያን አሉ። በድርጅት ባይታቀፉም እንኳን ይህንን የህወሀት መሰሪ አካሄድ ቀደም ብለው ተገንዝበው ከቅድም ጀምረው ህወሀትን ሲያጋልጡና ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ሽንጣቸውን ገትረው እስከአሁን የሚከራከሩ እንደነ ዶ/ር ግደይ አይነት እውቅ ምሁራንም አሉ። የህወሀት ሁሉን ጠርንፎ የመያዝ አባዜ በተለይ ትግራዋይ የሆኑ ተቃዋሚዎቹን ከሌሎቹም በላይ እንደሚጠላ፤ በዘር ሀረጋቸው “ትምክህተኛ” ሊላቸው የማይችል ከትግራይ አብራክ የወጡ ልጆቹን ዘረኛ አካሄዱን ስለሚያጋልጡበት ከፍተኛ ማህበራዊና ቤተሰባዊ መገለል እንደሚያደርስባቸው ይታወቃል። ለዚህም ነው በዚህ ከባድ ፈተና ላይም ሆነው ለአላማ ሲሉ ህወሀትን የሚቃወሙ የትግራይ ወገኖችን፤ ህወሀት በትግራይ ህዝብ ስም በኢትዮጵያ ላይ እያደረሰ ካለው መከራ አንጻር በቁጥር በቂ ናቸው ማለት እንኳን ባይቻል፤ የነኝህን ቆራጥ ወገኖች ወኔ የምናደንቀው። የህወሀትን ሰይጣናዊ ተግባር ለማርከስ ግን ከነኝህ ወገኖቻችን ከዚህም በላይ ብንጠብቅ ተገቢ ነው። በተለይም ደግሞ ብዙሀኑ የትግራይ ምሁራን ይህ ድርጅት የሚያደርሰውን አደጋ እያዩ ህወሀትን ባይደግፉም እንኳን ዝም ብለው ከዳር ቆመው ማየታቸው ተገቢ ነው ብዬ አላምንም። የሚሰራው ወንጀል በስማቸው ስለሆነ ቢያንስ በስማችን እንደዚህ አትነግድ፤ እናንተ በስልጣን ማማ ላይ ሆናችሁ ስለዘረፋችሁ ሁሉም ትግራይን የሚወክል ጥቅም አስመስላችሁ ማህበረሰባችንን ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር አታጣሉት ብለው ደፍረው መናገራቸው ከሞራል ሀላፊነት አንጻር አስፈላጊ ነው ብቻ ሳይሆን ህወሀትን ለማረቅም ያለው አቅም በቀላሉ የሚታይ አይሆንም።
10

በእርግጥም በቅርብ ጊዜ ይህ የህወሀት አደገኛ አካሄድ እያሳሰባቸው ድምጻቸውን የሚያሰሙ ትግራውያን እየተበራከቱ መጥተዋል። ለምሳሌ በውጭ የሚገኙ 16 ታዋቂ የትግራይ ምሁራን ያወጡት መግለጫ፤ ወይም እንደ ሲራክ አማረ (ወዲ ሻምበል) ና ጥላሁን ወልደስላሴ አይነቱ በግልጽ በኢሳት ላይ ወጥተው እንዳደረጉት ይህንን የህወሀት አካሄድ የሚያወግዙ ንግግሮች በማድረግ ህወሀት የትግራይን ህዝብ ለዚህ እኩይ ተግባሩ ለማሰለፍ የሚያደርገውን ሙከራ ለማክሸፍ የሚያደርጉት ሙከራ አበረታች ነው። ይህ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ባለሙሉ ተስፋ ነኝ። ይህ ግን በፍጹም በቂ አይደለም። ከትግራይ ምሁራን ወገኖቻችንና ለኢትዮጵያ በጎ ከሚመኙ ትግራዋይ ወገኖቻችን ከዚህም በላይ ብንጠብቅ ተገቢ ነው። በነጻነትና በእኩልነት ታጋዮች በኩል ደግሞ እንዲህ አይነት ወገኖቻችንን ማበረታታት፤ መቅረብና አብረውን እንዲሰሩ ማድረግ፤ በረጅም ጊዜ የህወሀት ፕሮፓጋንዳ ምክንያት፤ ወይንም ደግሞ ባንዳንድ አክራሪ ኃይሎች አካባቢ በሚሰሙት የጥላቻ ወሬ ተወናብደው በሌላው ኢትዮጵያዊ ላይ ይዘውት ያሉት ጥርጣሬ ካለ ጥርጣሬውን ለመግፈፍ ቀርቦ መወያየትና የትግሉን እውነተኛ ኢላማ ማስረዳት ይጠበቅብናል። የህወኃትን የጥላቻ መርዝ ለማርከስ እጅግ ያስፈልጉናልና! ተግባር ከብዙ ቃላት በላይ ይናገራልና በዚያው ልክ ደግሞ በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል የሚደረገው ህዝባዊ ትግልና አመጽ ከህወኃት ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸውን ንጹሀንና ሰላማዊ የትግራይ ወገኖቻችንን እንዳይነካ መጠንቀቅና በስህተት እንኳን እንዲህ አይነት ክስተት ከተፈጸመ አጥብቆ በማውገዝ ትግሉ ሁሉንም የሀገሪቱን ህዝቦች (በህወሀት መዳፍ ስር እየማቀቀ ያለውን የትግራይ ህዝብን ጨምሮ) ነጻ ለማውጣት የሚደረግ ትግል መሆኑን ያለማሰለስ ለህዝቡ ማስረዳት ነው በትግሉ ደጋፊዎችና መሪዎች በመደጋገም እንዲሰራ የሚጠበቀው።
ዴምህት አሁን በሀገሪቱ በተፈጠረው ውጥረት ላይ ሊጫወት የሚችለው ልዩ ታሪካዊና ገንቢ ሚና
ስለሌሎች የትግራይ ድርጅቶችና ግለሰቦች ሚና ባጭሩ ይህን ያክል ካልኩ ዴምህትን በተመለከተ አንድ ሁለት ነገሮች ብዬ ላብቃ። ዴምህት ህወሀትን ከሚቃወሙት ከሌሎቹም የትግራይ ድርጅቶች በላይ ያለበት ሁኔታ በህወሀቶች ዘንድ የማይወደድ መሆኑ ይታወቃል። የህወሀትን መስመር ከስሩ የሚቃወም ድርጅት ብቻ ሳይሆን፤ ከሌሎችም በተለየ ይህ መሰሪ ስርዓት በአመጽ ካልሆነ እንደማይንበረከክ አምኖ የትጥቅ ትግል የጀመረ ድርጅት ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን ይህን ትግሉን ለማድረግ ህወሀቶች “የትግራይ ዋና ጠላት” ብለው ከሚፈርጁት የኤርትራ መንግሥት እርዳታ ይቀበላል መባሉ በራሱ ለህወሀት ድርብ ጠላት ያደርገዋል። ከዚያም በላይ ግን በኤርትራ በመታገዙ ምክንያት ብቻ የህወሀት ተቃዋሚ በሆኑት የትግራይ ተወላጆችም እንኳን በጥርጣሬ አይን ነው የሚታየው። ይህ ለዴምህት አካሄድ እንደ ተግዳሮት የሚታይ ቢሆንም፤ ዴምህት ያለበት ሁኔታ ደግሞ የወያኔን መሰሪና መርዛማ አካሄድ ለማርከስ የሚያስችል የተለየ ቦታ ላይ ያስቀምጠዋል። ያለ ምንም ማጋነን ህወሀትን የሚቃወሙ፤ ብዙ ጠንካራ ታጋይ የትግራይ ልጆች ባንድ ላይ የተሰባሰቡበትና የህወሀትን መሰሪ አካሄድ በኃይል ለመቋቋምም የሚያስችል አቅምና ፍላጎት ያለው ብቸኛ ድርጅት ዴምህት ነው ማለት ይቻላል። ስለዚህም በነጻነት ትግሉ ሂደት ከፍተኛ ሚና መጫወት የሚችል ድርጅት ነው። ያለበት ቦታ ደግሞ ልክ እንደሱ ለነጻነት የሚታገሉ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ድርጅቶች ያሉበት አካባቢ ስለሆነ በስማ በለው ሳይሆን ከነኝህ ድርጅቶች ጋር በቅርበት በመገናኘት ስለጋራ ትግሉ መምከር፤ መወያየት፤ አልፎም በጋራ አብሮ ለመታገል የሚያስችለው ሁኔታ ላይ ይገኛል። አብዛኛው የትግራይ ህዝብ በህወኃት አፈና ተለጉሞ በዴሞክራሲ ትግሉ ላይ እንደሌሎች ክልሎች በጣም በግልጽ የሚታይ አጋርነት ማሳየት ለጊዜው ባልቻለበት በአሁኑ ሁኔታና፤ ህወኃቶች ሆን ብለው ህዝቡን ከህዝብ ጋር ለማጋጨት ፕሮፓጋንዳ በሚያናፍሱበት በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ፤ እንዲሁም በአጋዚ ጦር በየቀኑ የሚያልቀው የአማራና የኦሮሞ ህዝብ የህወሀት/ኢህአዴግን ጦር በአብዛኛው የሚመሩትን የህወኃት መኮንኖች እያየ ልቡ ሲያዝንና ስሜቱ ሲጨነቅ፤ እንዲህ ያለ ትልቅ የትግራውያን ድርጅት ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር ሆኖ ለነጻነትና ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሲዋደቅ ሲያይ፤ በትግሉ ውስጥ ለሚሳተፈው ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚሰጠው የአጋርነትና የአለኝታነት ስሜት ከትግሉ ወቅትም ባለፈ ለምትፈጠረዋ የጋራ ሀገር ትልቅ አንድምታ ያለው ነው ብዬ አምናለሁ። አፉ በህወሀት ጥርነፋና አፈና ለተዘጋው የትግራይ ህዝብም፤ ከሚወደው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በዘላቂ ክር ከሚያስተሳስረው ባህሉና ታሪኩ ባልተናነሰ ላለፉት 25 አመታት ከአብራኩ የወጡት መሰሪ ልጆቹ በሚወዳት ሀገሩ ላይ ያዘነቡበትን መከራ እያየ የሚያዘነውን ያክል ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር ሆነው ሀገራቸውን ለመታደግ በሚወድቁት ልጆቹ ክፉኛ እንደሚኮራ ጥርጥር የለኝም። ከዚህ አንጻር ዴምህት ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር ሆኖ ለነጻነት፤ ለእኩልነትና ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሚያደርገው ትግል ለትግራይም ህዝብ ትልቅ ቤዛ እንደሚሆን ነው የሚሰማኝ።
በመጨረሻ ማለት የምፈልገው እኛ እንደ አርበኞች ግንቦት 7 ዴምህት ይህን ውስጣዊ መርሁ አድርጎ ለሚያደርገው ትግል በምንችለው አቅም ሁሉ ለመርዳት ከጎኑ መሆናችንንና፤ ዝግጁ ነኝ በሚልበት ጊዜም ከዚህ በፊት ጀምረን የነበርነውንና በሞላ መክዳት ምክንያት ተግባራዊነቱ የተስተጓጎለውን ትብብር እንደገና ለማስነሳትም ሆነ በሌላ በማንኛውም መልኩ ተባብረን፤ ሀገራችንን ከገጠማት አደጋ ለማውጣት ባስቸኳይነት ስሜት ለመታገል ያለንን ፍላጎት በዚህ አጋጣሚ እንደገና መግለጽ እፈልጋለሁ። እንዲህ አይነት ትብብር ሲፈጠር ደግሞ ጊዜያዊ ለሆነና ያጭር ጊዜ የሀይል ሚዛንን ባሰላ ስሌት፤ ወይንም ደግሞ ዝም ብሎ ህወሀት/ኢህአዴግን ለማስወገድ ብቻ ባለመ የስልት አሰላለፍ ሳይሆን፤ በጥርጣሬ አይን እየተያየንና እንደማይተማመን ባልንጀራ አንዳችን ያንዳችንን የውስጥ ግፊት በመጠየቅ ሳይሆን፤ ያችን ሁላችንም እንድትፈጠር የምንፈልጋትን ለሁላችንም እኩል የሆነች እውነተኛ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ማቆምን ግቡ ያደረገና በዚህ ጠንካራ አለት ላይ የቆመ የውስጥ መተማመን ያለበት ስትራቴጂካዊ ትብብር ማድረግን ኢላማው ያደረገ ትብብር እንዲሆን ያለንን ተስፋ በአጽንኦት እገልጻለሁ።
የወያኔን መሰሪ አካሄድ በጋራ እንመክት!
አንድነት ኃይል ነው

No comments:

Post a Comment