የወያኔ አረመኔያዊ ያገዛዝ ስርዓት በህዝባችን ላይ የሚፈጽመው አፈና ግድያና ዝርፊያ በመጠኑም በዘግናኝነቱም ይበልጥ እያገጠጠ ስለመጣ ለወትሮው እንዳላየ አይተው የሚያልፉትን ምዕራባውያን ለጋሾቹንና ወዳጆቹን ሳይቀር በጅጉ ማሳስብ ጀምሯል። ወያኔ ለምዕራባውያን ደህና ሎሌ በመሆን ወንጀሌን እንዳላዩ እንዲያዩልኝ ማድረግ እችላለሁ የሚለው አካሔዱ በውንብድና ተግባሩ ለከት የለሽነትና ዘግናኝነት ምክንያት ሙሉ ለሙሉ እየተሸረሸረበት ነው። ብዙዎቹ ምዕራባውያን ላለፉት ሁለት ወራት በተለይ በኦሮሚያ ውስጥ የሚካሄደውን ጭፍጨፋና አፈና ለማውገዝ የተገደዱበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
አሜሪካንን ጨምሮ የወያኔ ለጋሽ ሀገራት የሆኑት ምዕራባውያን ሰሞኑን በኦሮሞ ወገኖቻችን ላይ ወያኔ የከፈተውን የዕብሪት ጭፍጨፋ እስራትና አፈና አስመልክቶ ችግሩን በውይይትና በስልጡን መንገድ የፈታ ዘንድ የሚያሳስቡ ግልጽና ባንጻራዊ ደረጃ ሲታዩ ጠንከር ያሉ መግለጫዎችን አውጥተዋል።
የደረሰውም ጥፋት ተመርምሮ ጥፋተኛ ወገን እንዲጠየቅ የሚጠይቁና ችግሩም በሰላምና በውይይት እንዲፈታ እየጎተጎቱ ይገኛሉ። ባለፉት በርካታ ዐመታት ምዕብራባውያኑ የወያኔ ጉጅሌ ይህንን አቅጣጫ እንዲከተል ተጽዕኖ የመፍጠር አቅማቸውን ተጠቅመው ያደረጉት በቂ ግፊት እንደሌለ ይታወቃል። የአሜሪካ መንግስትና ያውሮፓ ሕብረት አባል ሀገሮች ዘግይተውም ቢሆን ሀገራችን ውስጥ የተካሄደውንና እየተካሔደ ያለውን ጭፍጨፋ ማውገዛቸውና ወደፊትም በዝርዝር ተመርምሮ ተጠያቂው እንዲታወቅ ያቀረቡትን ሀሳብ እንደ በጎ ጅምር እንመለከተዋለን።
ለሀገራችንና ለህዝባችን እጣ ፋንታ የምንጨነቅና የህዝቡ ጥቃት ያንገፈገፈን የሀገሪቱ ልጆች የችግሩ የመፍትሔ መጀመሪያ ይህ በጉልበቱ ህዝባችን ላይ የተጫነ መንግስት ነኝ ባይ የግፈኞች ጥርቅም በሃይል በሚደረግ ትግል ጭምር መወገድ አለበት ወደሚለው ውሳኔ የደረስነው የሰላም በርና ጭላንጭል ሁሉ በመዘጋቱ እንደሆነ ስንገልጽ ቆይተናል ። ላለፉት ሁለት ወራት በኦሮሞ ወገኖቻችን ላይ የተፈጸመውና ከመቶ ሀምሳ በላይ ወገኖቻችን ያለቁበት ጭፍጨፋ እንዲሁም በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች በሚኖሩ ዜጎቻችን ላይ እየተፈጸመ ያለው ተመሳሳይ ግዲያ እስራትና የተቀናቃኝን አድራሻ ደብዛ ማጥፋት እርምጃ የሚያሳየው ይህ ስርዓት የበለጠ ጥፋት ከማድረሱ በፊት በፍጥነት መወገድ ያለበት መሆኑ ላይ ያለን አቋም ለሁሉም ይበልጥ ግልጽ እየሆነ መምጣቱን ነው። እንደወያኔ ያለ ከህዝብ የተጣላ የፖለቲካ ሀይል የፖለቲካ ጥቅምን የሚያየው ከራሱ ህልውናና ደህንነት አንጻር እንጂ ከህዝቡ ሰላም ብልጽግናና ነጻነት ወይም ከሀገሪቱ የረጅም ጊዜ እጣ ፋንታ አንጻር አይደለም። የወያኔን ገዥዎች የሚያስጨንቃቸው የህዝቡ ኑሮ ሳይሆን የራሳቸው የዝርፊያ ስርዓት ባግባቡ መጠበቅ አለመጠበቁ ነው። ለዚህ ነው ስርዓታቸውን ለመጠበቅ የነጻነት ጥያቄ ኮሽታ በሰሙ ቁጥር የሚባንኑት። ለዚህ ነው በሰላም መብቱን የጠየቃቸውን ሁሉ መደዳውንና በጭካኔ በጥይት የሚረፈርፉትና የተረፋቸውን እንደ እንስሳ ወህኒ በረት ውስጥ የሚያጉሩት።
አርበኞች ግንቦት 7 የወያኔ ጸረ ህዛብና ጸረ አገር እርምጃ ሊቆም የሚችለው ላለፉት 25 አመታት ወያኔ በመካከላችን የገነባው የመከፋፈልና የልዩነት ግድግዳ ለመናድ ሁላችንም እጅ ለእጅ ተያይዘን በአንዳችን ላይ የሚፈጸመው ጥቃት በሁላችንም ላይ እንደ ተፈጸመ ቆጥረን በጋራ ስንንቀሳቀስ ብቻ ነው ብሎ ያምናል:: ዛሬ በኦሮሚያ ወገኖቻ ላይ እየተፈጸመ ያለው ሰቆቃና ግዲያ ትናንት በጋምቤላ ፤ በኦጋዴን ፤ በአፋር፤ በቤኔሻንጉል ፤ በደቡብና በአማራ ወገኖቻችን ላይ በፈረቃ ሲፈጸም የቆየና እየተፈጸመ ያለ መከራ መሆኑን የማይገነዘብ የለም:: በፈረቃ መገደል ፤ በፈረቃ ወህኒ መወርወር ፤ በፈረቃ መፈናቀል፤ በፈረቃ ለስደት መዳረግ የሁላችንም ዕድል ፈንታ ሆኖአል :: ይህንን ስቃይና መከራ ማስቆም ለፍትህና ለነጻነት የቆመ ዜጋ ሁሉ ግዴታ ነው::
ወያኔ የሰላም በሮችን በሙሉ ጠርቅሞ ሲዘጋ ለአገራቸው ጥቅም ሲሉ ዝምታን የመረጡ ምዕራባዊያን የህዝብ ብሶት ገንፍሎ አደባባይ ከወጣና ብዙዎች በአጋዚ ጦር ጨካኝ ግዲያ ህይወታቸውን ከገበሩ ቦኋላ ዘግይተውም ቢሆን መናገር መጀመራቸው መልካም ጅምር ነው:: ነገር ግን በእብሪት የተወጠሩ የወያኔ መሪዎች በባዕዳን አለቆቻቸው ቁጣ ከአቋማቸው ፍንክች ይላሉ ብሎ መጠበቅ መዘናጋት እንዳያስከትል መጠንቀቅ ተገቢ ነው:: : ችግሮችን ተነጋግሮ መፍታት ትልቅ አቅምና ችሎታን የሚጠይቅ የዘመናችን ሥልጣኔ ውጤት ነው:: በጠመንጃ ተጸንሶ በጠመንጃ የተወለደው ወያኔ ለእንዲህ አይነት ዕድገትና ሥልጣኔ አልታደለም::
አርበኞች ግንቦት 7 የወያኔ ስርዓት ሊወገድ እንጂ ሊጠገን የማይችል የተበላሸ ስርዐት መሆኑን ይገነዘባል::በመሆኑም በህዝባችንና በአገራችን ላይ የሚፈጸመውን ወንጀል ለማስቆም የጀመረውን ሁለገብ ትግል የወያኔ አገዛዝ እስኪወገድና ሠላምና ዲሞክራሲ በአገራችን እስኪሰፍን ድረስ አጠናክሮ እንደሚቀጥልበት ለወዳጅም ለጠላትም ያረጋግጣል ::
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!
No comments:
Post a Comment