ድርቁ አስፈሪ ገጽታ እየያዘ መሆኑ ተጠቆመ
በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተው ድርቅ አስፈሪ ገጽታን እየያዘ መሆኑን ዓለም አቀፍ ለጋሾች እየገለጹ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትና ከአርባ በላይ ለጋሾች በተጣመሩበት የጋራ የሰብዓዊ የዕርዳታ ጥሪ፣ በአገሪቱ 10.2 ሚሊዮን ሕዝብ የአስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ እንደሚያስፈልገው አስታውቀው ነበር፡፡ ይህ በተገለጸ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በድርቁ አጠቃላይ ይዞታ ላይ የተናጠል ዳሰሳ እየሠሩ የሚገኙ ለጋሽ ድርጅቶች፣ ችግሩ አስፈሪ ገጽታን እየተላበሰ እንደሆነ በመግለጽ ላይ ይገኛሉ፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ትኩረቱን የኢትዮጵያ አሳሳቢ ድርቅ ላይ ማድረግ ባለመቻሉ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
አገሪቱ ባለፉት ሃምሳ ዓመታት አይታው የማታውቅ የአየር ንብረት መዛባት ያመጣውን ድርቅ ለመቋቋም ለለጋሾች የ1.4 ቢሊዮን ዶላር የዕርዳታ ጥሪ ቢቀርብም፣ እስካሁን የተገኘው በጣም ትንሽ መሆኑ ተገልጿል፡፡ በዚህም ምክንያት ከፍተኛ የምግብ ችግር ስለሚያጋጥም ረሃብ እንዳይከሰት ፍራቻ አለ፡፡ በሚቀጥሉት ሦስት ወራት ውስጥ ችግሩ እንዲሁ ከቀጠለ የአስቸኳይ ምግብ ዕርዳታ ፈላጊዎች ቁጥርም ይጨምራል ተብሏል፡፡
የተለያዩ ዓለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማት ያነጋገሩዋቸው የዓለም የምግብ ፕሮግራም የኢኮኖሚ ባለሙያ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ፣ ነገር ግን እስካሁን የራሳቸውን የምግብ ክምችት ሲጠቀሙ የነበሩ ዜጎች ጥሪታቸውን እያሟጠጡ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም ከመጪዎቹ መጋቢት እስከ ሚያዝያ ባሉት ወራት የአስቸኳይ ዕርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ገልጸዋል፡፡ የአሜሪካ የግብርና ዲፓርትመንት በበኩሉ በአሁኑ ወቅት ለ10.2 ሚሊዮን ተረጂዎች ያስፈልጋል የተባለው አንድ ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ስንዴ ቢሆንም፣ በመጪዎቹ ጥቂት ወራት የሚያስፈልገው ስንዴ መጠን በእጥፍ እንደሚያድግ ትንበያ አቅርቧል፡፡
ዓለም አቀፍ ለጋሾች በተለያዩ ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ቀውሶች መጠመዳቸው፣ ለኢትዮጵያ ድርቅ ትኩረት እንዳይሰጡ እንዳደረገም የኢኮኖሚ ባለሙያው ይገልጻሉ፡፡
በሶሪያ፣ በደቡብ ሱዳን፣ በየመን፣ በማዕከላዊ አፍሪካና በመሳሰሉት አገሮች የተከሰቱ ግጭቶችና ሰብዓዊ ቀውሶች የበለጠ ትኩረት መሳባቸውና የኢትዮጵያ ችግሩን የመቋቋም አቅም፣ ዓለም አቀፍ ለጋሾች ቃል የገቡትን ወደ ተግባር እንዳይለውጡ ሳያደርጋቸው እንዳልቀረ፣ የዓለም የምግብ ፕሮግራም ባለሙያው ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ከሚያስፈልጋቸው 10.2 ሚሊዮን ተጎጂዎች ውስጥ፣ 2.1 ሚሊዮን ያህሉ በከፍተኛ ደረጃ በምግብ እጥረት የተጎዱ መሆናቸውን ባለሙያው ገልጸው፣ በአሁኑ ወቅት የዓለም የምግብ ፕሮግራም መርዳት የሚችለው ከአጠቃላዩ የድርቁ ጉዳተኞች አምስት በመቶውን ብቻ ነው ብለዋል፡፡
እየተባባሰ ያለው ድርቅ ከኢትዮጵያ መንግሥት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር ተዳምሮ አስፈሪ ሁኔታን እየያዘ ነው ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ የሚገኙ የሕፃናት አድን ድርጅቶች ጥምረት በበኩሉ፣ በአሁኑ ወቅት በይፋ ከተገለጸው 10.2 ሚሊዮን የተረጂዎች ቁጥር ውስጥ ከ5.75 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ሕፃናት መሆናቸውን አስታውቋል፡፡
በውኃና በመኖ እጥረት ምክንያት ቁጥራቸው ለጊዜው ያልታወቀ በርካታ እንስሳት መሞታቸውን፣ ሁኔታው በዚህ ከቀጠለም የእንስሳት ዕልቂት ሊከሰት እንደሚችል፣ በአጠቃላይ ችግሩ በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የገለጹት የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት የኢትዮጵያ ተጠሪ አማዱ አልሃውሪ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት በእንስሳት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፡፡ ለዚህም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንስሳቱን ለማዳን እንደሚንቀሳቀስ ተስፋ እንዳላቸው፣ ነገር ግን በቂ ገንዘብ አለመኖሩ ደግሞ እንደሚያሳስባቸው ተናግረዋል፡፡
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በምሥራቅ አፍሪካ በተለይ በኢትዮጵያ የተከሰተውን አደገኛ ድርቅ መቀልበስ ካልቻለ፣ ከወራት በኋላ የፀና ረሃብ ሊከሰት እንደሚችል ብዙዎችን አግባብቷል፡፡ ለጋሾች በተቻለ መጠን በመንግሥትና በረድኤት ድርጅቶች የቀረበውን የዕርዳታ ጥሪ በመስማት፣ ሕይወትን ማዳን እንዳለባቸው በሰብዓዊ ድርጅቶች እየጎተጎቱ ነው፡፡
የሕፃናት አድን ድርጅቶች ጥምረት በአሁኑ ወቅት በሥራ አስፈጻሚዎቻቸው አማካይነት በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎችን እየጎበኙ መሆኑን ለሪፖርተር በላኩት መረጃ አስታውቀዋል፡፡ በመጪው ሳምንት አጠቃላይ የድርቁን ሁኔታ በተመለከተ መግለጫ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ምንጭ፦ ሪፖርተር
No comments:
Post a Comment