Tuesday, January 5, 2016

የኖርዌይ ኤምባሲ ዜጎቹ በኦሮሚያ ሲንቀሳቀሱ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳሰበ

ኢሳት (ታህሳስ 25 ፥ 2008) ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ተቃዉሞ ጋር በተገናኘ መቀመጫዉን በኢትዮጵያ ያደረገዉ የኖርዌይ ኤምባሲ፣ ዜጎቹ በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ከተሞች በሚያደረጉት እንቀሰቃሴ ላይ ጥንቃቄን እንዲያደርጉ ሰኞ በድጋሚ አሳስቧል። ተቃውሞው ከቅርብ ጊዜ ተቃውሞ ረገብ ያል ቢመስልም በማንኛውም ሰአት በድጋሚ ሊከሰትና የደህንነት ስጋት ሊያጋጥም ይችላል ሲል ኤምባሲዉ ገለጿል። በዚሁ ክልል አሁንም ድረስ አለመረጋጋት መኖሩን የገለጸዉ ኤምባሲዉ ዜጎቹ ሊያደርጓቸዉ ያሰቧቸዉን ጉዞዎች ላይ የጥንቃቄ እርምጃን እንዲወስዱም ጠይቋል። በኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር በተገናኘ የተቀሰቀሰዉን ተቃዉሞ ተከትሎ ኤምባሲዉ ዜጎቹን እንዲጠነቀቁ ሲያሳስብ መሰንበቱ የሚታወስ ነው። መቀመጫቸዉን በኢትዮጵያ ያደረጉ የተለያዩ ሀገራት ተወካዮችና አለም አቀፍ ተቋማት ባለፈዉ ሳምንት በጉዳዩ ዙሪያ ከመንግስት ተወካዮች ጋር በአዲስ አበባ ምክክር ማካሄዳቸዉ ይታወቃል። በወቅቱ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሀላፊዎች ተቃዉሞዉ በቁጥጥር ሰር ዉሏል ቢሉም ከዉይይቱ በኋላ ኖርዌይ ዜጎቿን ስታሳስብ የመጀመሪያዉ ሀገር መሆኗን ለመረዳት ተችሏል። የአሜሪካ መንግስትና በርካታ አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች መንግስት ለተቃዉሞ አደባባይ በወጡ ሰዎች ላይ የወሰደዉን የሀይል እርምጃ መኮነናቸዉ የሚታወስ ሲሆን መንግስት ከድርጊቱ ተቆጥቦ የዜጎችን ሀሳብን በነጻነት የመግልጽ መብት እንዲያከብር አሳሰበዋል።

No comments:

Post a Comment