Thursday, January 21, 2016

አቶ ኃይለ ማርያም ምን ነካካቸው?

– ከተማ ዋቅጅራ
ጠቅላይ ሚንስትር ማለት፡- የቃሉ ትርጉም የሚንስትሮች ሁሉ የበላይ፣ ሁሉንም ሚንስትር የሚያዝ፣ ሁሉንም ሚንስትሮች ጠቅልሎ የሚመራ የሚለውን ትርጉም ይሰጠናል። እንደ ኢትዮጵያ፣ እንግሊዝ፣ ጃፓን የመሳሰሉት አገሮች የአገር መሪነት ድርሻ የጠቅላ ሚንስትሩ ነው። የአለማችን አብዛኛው አገራት የሚመሩት በፕሬዝዳንት ሲሆን ኢትዮጵያ ግን የምትመራው በጠቅላይ ሚንስትር ነው። በጠቅላይ ሚንስትር የሚመሩት አገሮች ሁሉ የሚመረጡት በህዝ የሚሾሙትም በህዝብ የሚያገለግሉትም የመረጣቸውን ህዝብ ስለሆነ ባለሙሉ ስልጣን ባለቤት ናቸው። በዚህ የተነሳ ሃገራቸውን የሚያስከብር ስራ ይሰራሉ ህዝባቸውንም የሚጠቅም ስራ ይሰራሉ። ከህዝባቸውን የተሰወረ ነገር አያደርጉም ህዝባቸውንም የሚጎዳ እና የሚያሳፍር ድርጊትም አይፈጽሙም። ስለዚህ ህዝቡ በመሪዎቻቸው ደስተኛ ነው።ኢትዮጵያ ግን እንደ እድል ሆኖ እንደዛ አይደለም። መሪው የሚመረጠው በህዝብ ሳይሆን በህውአት ሰዎች ነው። መሪ ተብዬዎች አገልግሎታቸውን የሚሰጡት ለኢትዮጵያን ህዝብ ሳይሆን ለመረጣቸው ፓርቲ ብቻ ነው። በዚህ ምክንያት ህዝባችን ቢገደል፣ ቢታሰር፣ ቢንገላታ፣ ቢራብ፣ ቢጠማ፣ የትኛውም አይነት መከራ ቢደርስበት የመረጣቸው ፓርቲን የማይነካ ከሆነ እንደ አገር መሪ ትንፍሽ ማለት አይችሉም። የኢትዮጵያ ዳር ድንበር ተደፍሮ አገር ተቆርሶ ለበአድ ሲሰጥ  እንደ አገር መሪ አንድ ስንዝር የአገሬ መሬት አይሰጥም ብለው ለአገር እና ለህዝብ የቆሙ መሆናቸውን የሚያሳዩበት ንግግር ማድረግ አልቻሉም።
አጋዚ ፌድራል የተባሉ የህውአት ወታደሮች ከጠቅላይ ሚንስትሩ ትዕዛዝ ውጪ ተልከው ህዝባችንን በዘግናኝ ሁኔታ  በጥይት እየመቱ ሲገድሉ የኢትዮጵያ ህዝብ ከዳር እስከዳር በተቃውሞ ሲናወጥ እንደ አገር መሪነቶ መናገር ሆነ ለሚወሰደው እርምጃ ሙሉውን ኃላፊነት መውሰድ የሚገባቸው አቶ ኃይለ ማርያም ሆነው ሳለ በተገላቢጦሽ መግለጫ የሚሰጡትም ሆኑ መግለጫ መስጠት ያለባቸውን አካል የሚመርጡት የህውአት ሰዎች መሆናቸውን ስናውቅ ቢያሳፍረን እና ቢያሳምመንም አቶ ኃይለ ማርያምን ምን እንበላቸው? እስቲ ስም አውጡላቸው የአገር መሪ ወይንስ የአገር አማራሪ?።

ከጎንደር ጀምሮ ጎጃም፣ ቤንሻጉል ጉምዝ፣ ጋንቤላ፣ ከፋ ድረስ የሚደርሰውን  የኢትዮጵያ መሬት ቆርሶ ለሱዳን ለመስጠት ህውአት እቅዱን ለማስፈጸም ሲሯሯጥ አቶ ኃይለ ማርያም እንደ አገር መሪ የኢትዮጵያን ድንበር ከሚደፈር ኢትዮጵያ ክብርም ከሚጠፋ እኔ ልጥፋ ብለው ለአገር ክብር እና ነጻነት ከመቆም ይልቅ ጥቂት ወደ ስልጣኑ ማለትም ለሹመት ያበቋቸውን ግለሰቦች አገልጋይ ሆነው ለማስደሰት ተብሎ እንዴት የአገር ክብርን የሚያክል አሳልፎ ይሰጣሉ? ታሪክ የማይሽረው ትልቅ ስህተት እየሰሩ መሆናቸውን የሚመክራቸው የቅርብ ወዳጅ እንዴት ያጣሉ? የአገር ጉዳይ የህልውና ጉዳይ መሆኑን ዘንግተውት ከሆነ ላስታውሶት እወዳለው። በአገር ጉዳይ ከመጣ ህዝቡ በሙሉ ከዳር እስከ ዳር ክተት እንደሚያውጅ እና ያለምንም መሪ የአገር ጠላትን ለመደምሰስ እንደሚነሳ እንዴት ማስታወስ ተሳኖት? የኢትዮጵያ ልጆች በአገር ለመጣ ጠላት ጣልያንን እንኳን በባዶ እግሩ ዘምቶ  ዶግ አመድ ማድረጉን እንዴት ማስታወስ ተሳኖት? አገር ተቆርሶ ለሱዳን ተሰጥቷል ተብሎ ህዝባችን ጆሮ የደረሰ ለታ የእርሶ  እጣ ፈንታ የጋዳፊ አይነት እንደሚሆን  ከወዲሁ ሊያውቁት እና ሊረዱት ይገባል።
ህዝባችን ለመብቱ ጥያቄ ሲያነሳ መልሱ ግድያ እና እስራት እንዲሁም ከአገር መሰደድ ሲሆን የእርሶ  መልስ ዝምታ ሲገርመን… የኢትዮጵያ ዳር ድንበር ተቆርሶ ለሱዳን ሊሰጥ ወያኔ ሲስማማ የርሶ መልስ ደግሞ የሱዳን መስካሪ በመሆን የኢትዮጵያን ገበሬ ወንበዴ ብለው መሳደቦ መገረማችን ሳያበቃ እንደው ለትውልዱ ከባድ መከራን ሊያመጣ የሚችለውን ውሳኔ በቀላሉ አስፈጻሚ ሆነው ሲናገሩ በህዝብ ህልውና ጉዳይ ላይ መፍረዶ እንደሆነ ተገንዝበውት ይሆንን? ደሞም ቀጥለው ህዝቡ ያልመከረበት ውሳኔ በየትኛውም ነገር ይሁን ተፈጻሚነት የለውም ብለው ሲዋሹ አይሰቀጥጦትም?(መንግስት ህዝቡን አማክሮ ውሳኔ የሰጠበት ግዜ አለ እንዴ?) የሱዳን መሪዎች እና ባለስልጣኖች ለአገራቸው ህዝብ እንዲሁም ለአገራቸው ጋዜጦች እና ለውጪ ሚዲያ ስለ ድንበሩ ከለላ በግልጽ በመጥቀስ ኢትዮጵያ የሱዳን መሬት ይዛ ያለአግባብ እየተጠቀመችበት እንደነበረ  የኢትዮጵያ መንግስት አምነው ለሱዳን በሰላም ሊያስረክቡ እንደሆነ በሰፊው እየተናገሩ ባለበት ግዜ  በዚህ ወሳኝ ሰዓት አቶ  ኃይለ ማርያም የህውአትን እቅድ አስፈጻሚ በመሆን ታሪካዊ ስህተቶችን እየፈጸሙ እንዳሉ ንጹ ህሊና አልያም አስታዋሽ ዘመድ ማጣታቸው ቢገርመንም የሚወስኑት ውሳኔ ግን የእርሶ ስልጣን ዘመን ሳይቋጭ ነገሮች ተገልብጠው ለፍርድ የሚቀርቡበት ግዜ እንደሆነ  ማስታወስ እፈልጋለው። ዛሬ ቤተ መንግስት ቁጭ ብለው የፓርላማ አባሎችን ሰብስበው የሚናገሩት ንግግር በሙሉ  የኢትዮጵያ ህዝብ በሚገባ እያዳመጠ እና እየተከታተለ እንደሆነ በመግለጽ የመጨረሻው የድንበር ውሳኔ እና  የህዝብ ግድያው አገርን  ለማጥፋት የተዘመተ ዘመቻ እንደሆነ ስለሚታወቅ ኢትዮጵያዊው ሁሉ ከዳር እስከዳር ክተት አውጆ ጠላትን ድል እንደሚነሳ ስነግሮት የኢትዮጵያን ህዝብ ጀግና እና በሃገር ድርድር የማያውቅ ስለሆነ ነው።
ታዲያ እስከዛው ድረስ እርሶን ማን እንበሎት የአገር መሪ ወይንስ የአገር አሳፋሪ? ብቻ ታሪክ የማይረሳው ትልቅ ስህተት እየሰሩ ነውና እንደ አገር መሪነቶ  ህዝብንና አገርን  የሚጠቅም ስራ ሰርተው ያልፉ ዘንድ ግዜው አሁን ነው ጥቂት ከቆዩ ግን ይረፍድቦታል።http://www.zehabesha.com/amharic/archives/50117
ከተማ ዋቅጅራ
19.01,2016
Email- waqjirak@yahoo.com

No comments:

Post a Comment