Thursday, January 14, 2016

በረሃብ ምክንያት በሰሜን ወሎ ወረዳዎች የሚኖሩ አርሶአደሮች ቀያቸውን እየለቀቁ ወደ ባህርዳር በመፍለስ ላይ ናቸው



ጥር ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአካባቢያቸው በተከሰተው ድርቅ የሚበሉትና የሚቀምሱት እንዳጡ የሚናገሩት ስደተኞች፣ ሰሞኑን ባህርዳር ገብተዋል፡፡ በየመንገዱ በመለመን የእለት ምግባቸውን ለማግኘት እየሞከሩ መሆኑን በፎቶ አስደግፎ ዘጋቢያችን የላከው መረጃ ያሳያል፡፡ የክልሉ መንግስት ምንም አይነት እገዛም አላደረገላቸውም፣ ማረፊያ ቦታም አላዘጋጀላቸውም ፡፡ አብዛኞቹ ስደተኞች ሴቶችና ህጻናት ናቸው። ህብረተሰቡ ለዜጎቹ እገዛ በማደረግ ላይ ቢሆንም፣የአለማቀፍ ድርጅቶችም ሊጎበኙዋቸው እንደሚገባ ዘጋቢያችን አስተያየቱን አስፍሯል። በሌላ በኩል ግን በኢትዮጵያ የተከሰተው ድርቅ ወደከፋ የረሃብ ደረጃ እየተሸጋገረ ነው በሚል በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሚያሰራጩት ወሬ ገንዘብ ለማግኛ እንጂ ትክክለኛ አይደለም በሚል ኮምሽነር ምትኩ ካሳ አስተባብለዋል፡፡ በቅርቡ በአዲስ መልክ የተቋቋመው የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮምሽነር አቶ ምትኩ ካሳ ማክሰኞ ዕለት የመንግስትን አንድ ኣመት የስራ ዕቅድ ይፋ ባደረጉበት ወቅት እንደተናገሩት ድርቁ ወደከፋ ደረጃ መሸጋገሩን የዓለም ምግብ ፕሮግራምን (ፋኦ) የመሳሰሉ ኣለም አቀፍ ድርጅቶች የሚያሰራጩት ወሬ ዕርዳታ ለማሰባሰብ እንዲጠቅማቸው እንጂ እውነታው እነሱ እንደሚሉት አለመሆኑን እነሱም ያውቁታል በሚል አስተባብለዋል፡፡ በተለይ በሀገር ውስጥ የሚገኙ መገናኛ ብዙሃንም ይህንኑ በማስተጋባት ላይ መሆናቸውን በመጥቀስ ወቀሳ አቅርበዋል፡፡ ኮሚሽነሩ ችግሩ ከመንግስት አቅም በላይ አልሆነም በሚል በተናገሩበት በዚሁ መድረክ፣ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለመንግስት ይፋዊ የእርዳታ ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ ባለመስጠቱ ትልቁን ድርሻ ብቻውን እየተወጣ ያለው መንግስት ነው በማለት እርስ በእርሱ የሚጋጭ ሃሳብ ሰንዝረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት 10 ነጥብ 2 ሚሊየን ዜጎች ለምግብ እጥረት መጋለጣቸውን ያስታወሱት ኮምሽነሩ፣ ድርቁን ለመከላከል ለቀጣይ አንድ ኣመት ብቻ 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር ወይንም 30 ቢሊየን ብር ገደማ እንደሚያስፈልግ ይፋ አድርገዋል፡፡ ከኣለም አቀፍ ረጂ ድርጅቶችና መንግስታት የተገኘው ድጋፍ እጅግ አነስተኛ ቢሆንም፣ መንግስት በራሱ አቅም እስካሁን 300ሚሊየን ዶላር ገደማ ወጪ መድቦ ችግሩን ለመቋቋም እየሰራ ነው ብለዋል፡፡ ቀሪውን 1 ቢሊዮን 100 ሚሊዮን ዶላር ማን እንደሚሸፍነው ግን ያሉት ነገር የለም። ዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች የተረጂውን ቁጥር ወደ 20 ሚሊየን የሚያደርሱት ሲሆን ችግሩን ለመቋቋም በመንግስት አቅም የሚደረገው ጥረት በቂ ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ ችግሩ በአጭር ጊዜ ሊባባስና ወደከፋ ቀውስ ሊሸጋገር እንደሚችል ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል፡፡ መንግስት የረድኤት ድርጅቶቹን ማሳሰቢያ ተከትሎ አፋጣኝ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ችግሩን ወደመሸፋፈን ማድላቱ በራሱ ቀውሱን ያባብሳል በሚል እየተተቸ ነው፡፡ በሌላም በኩል ኦክስፋም እና ዩኒሴፍ በቅርቡ ባወጡት የጋራ መግለጫ ድርቁን ተከትሎ በሁሉም ክልሎች ያለዕድሜ ጋብቻ እየጨመረ መምጣቱን ይፋ አድርገዋል፡፡ በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች የሚገኙ ወላጆች ልጆቻቸውን ለመታደግ ሲሉ ያለዕድሜያቸው ለመዳር እየተገደዱ መሆኑን እንዲሁም ሴቶችና ህጻናት ውሃ ፍለጋ ብዙ ርቀት ሲጉዋዙ ለጾታ ጥቃቶች እየተጋለጡ መሆኑን በቅርቡ ባካሄዱት ጥናት ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል።

No comments:

Post a Comment