Monday, January 4, 2016

ጥያቄአችን አንድ ይሁን (ይገረም አለሙ) ይገረም አለሙ



ወያኔዎች የኢትዮጵያን የመንግሥትነት ሥልጣን እንደያዙ በርካታ ኢትዮጵያውያን ወያኔዎቹ ራሳቸው ዓላማችን ብለው በሰነድ ያሰፈሩትንም ሆነ ስለ እነርሱ የሚያውቁ ሰዎች የመሰከሩትን ወደ ጎን በማለት እነዚህ ሰዎች ከጫካ ነው የመጡት እንኳን የሰው ልጅ አውሬ እንኳን ከጫካ ወጥቶ በአግባቡ ከተያዘ ተለማምዶ ከሰው ጋር ይኖራልና ግዜ ልንሰጣቸውና ልናግዛቸው ይገባል በማለት በቅርብም በሩቅም ሆነው እንደውም አንዳንዶች እነርሱው ጋር ገብተው ይበጃል ያሉትን ለመምከር ጠቃሚ ያሉትንም መንገድ ለማሳየት ብዙ ጥረዋል፡፡
ብረት አንስቶ መታገልና መንግሥት ሆኖ ሀገር መምራት የተለያዩ ናቸውና ወያኔዎች ይህን ተረድተው ከጠመንጃ አምላኪነት ወደ ለህግ ተገዢነት እንዲያድጉ ፣ ከአብዮተኝነት ወደ ዴሞክራሲያዊነት እንዲለወጡ ከታጋይነት ወደ ሀገር መሪነት እንዲሸጋገሩ የዘር ጥብቆአቸውን አውልቀው ኢትዮጵያዊ ካባ እንዲለብሱ ወዘተ ለማስቻል አመቺ ሆኖ ባገኙት መንገድና ዘዴ ሁሉ የቻሉትን ያደረጉ ወገኖች ያስገኙት ውጤት በማይለወጠው የወያኔ ሕገ አራዊት መበላት ነው፡፡
ወያኔ በሀይል የያዘውን ሥልጣን በህዝብ ፈቃድ ለማረጋገጥና ሀገሪቱን ወደ ዴሞክራሲያዊ አቅጣጫ ለማምራት በጠመንጃ የተገኘ ሥልጣን በሀይል ይጠበቃል ከሚለው እምነት ወጥቶ ምርጫ ለማካሄድ ፈቃደኛ እንዲሆን አለበለዚያም በተለያየ መንገድ አስገድዶ ነጻ ምርጫ በኢትዮጵያ አንዲለመድ ለማድረግ በርካታ ኢትጵያውያን ጥረዋል፤ ሕዝቡም በየግዜው መስዋዕትነት ከፍሏል ፡፡ የመጀመሪያው የ1987 ምርጫ መአህድና ኦነግ በመጨረሻ ሰአት ራሳቸውን ከምርጫ አግልለው ይሄ ነው የሚባል የምርጫ ሂደት ሳይታይ ብዙ ህዝብም ምርጫ መኖሩን አንኳን ሳያውቅ ምንም አሻራ ሳያኖር አለፈ፡፡

በሁለተኛው የበ1992 ምርጫ ከ10 በላይ የሚሆኑ የተቀዋሚ ፓርቲ አባላት የፓርላማ ወንበር በማግኘታቸው ጥረቱ መስመር ሊይዝ ወያኔም እየተማረ ሊሄድ ነው አሰኝቶ ተቀዋሚዎች ጠንክረው ቢሰሩ ወያኔን በምርጫ ማሸነፍ ካልሆነም ሥልጣን መጋራት ይቻላል የሚለው አስተሳሰብ እንዲጎለብት አስችሎ ነበር፡፡ በዚህ መነቃቃት የተነሳሱ ወገኖች በተቻለ አቅም ያለፉ ችግሮችን በተለይ ተለያይቶ ለምርጫ መቅረብን ለማስወገድ ቅንጅትን መስርተው ባካሄዱት ምርጫ 97 በአጠቃላይ ተቀዋሚው በወያኔ የታመነ ከ200 በላይ ወንበር ለማግኘት ሲችል ውጤቱን ተከትሎ በተፈጠረው አለመግባባት አያሌ ኢትዮጵያውያን ተገደሉ፣ ታሰሩ ተሰደዱ ንብረት ወደመ፡፡ ይህ የምርጫ 97 ሂደት አንድም ህዝቡ ለወጥ መፈለጉንና ነጻ ምርጫ ቢካሄድ በድምጹ ለውጥ ማምጣት መቻሉን ሁለትም ወያኔ በሀይል የተገኘ ስልጣን በስመ ዴሞክራሲ አይለቀቅም (በጠመንጃ ይጠበቃል) ከሚለው አምነቱ የሚላቀቅ አለመሆኑን ያሳየ ነበር ፡፡
በምርጫ ስልጣኑን ማስጠበቅ እንደማይችል ከምርጫ 97 በግልጽ የተማረው ወያኔ ምርጫ 97ትን ያየ እንከን የለሽ ምርጫ እያለ አይጫወትም ያለ በሚመስል ሁኔታ ምርጫ በኢትዮጵያ የሱን ስልጣን ለማደስ የሚውል ብቻ እንዲሆን የሚያበቃውን ስራ ሲሰራ የምርጫ 97 ውጤት መክሸፍ እንዴትነትና ምንነት በውል ሳይመረምሩ የተገኘውን ወንበር ብቻ በማየት ወይንም የየራሳቸው ምክንያት ኖሮአቸው በምርጫ 2002 የተወዳድሩ አንድ ወንበር ብቻ አገኙ፡፡ ወያኔ ከዚህም ልምድ ተምሮ በሀይል የተገኘ ሥልጣን በሀይል የጠበቃል መርሁን አጠንክሮ የፓርላማውን ወንበር ለመጠቅለል በበቂ ተዘጋጅቶ በምርጫ 2007 ተቀዋሚ የሚባል ፓርላማ ደጅ እንዳይደርስ ለማድረግ ቻለ፡፡ በመሆኑም ወያኔን ምርጫ ለማለማመድ ሀያ አራት አመት ሙሉ የተደረገው ጥረት ውጤቱ ዜሮ ሆነ፡፡ ከሀያ አራት ዓመቱ ልፋት ከንቱነት በላይ የሚያሳዝነውና የሚያስቆጨው በየምርጫው በተለይ በምርጫ 97 የተከፈለው መስዋዕትነት ነው፡፡
ጦርነትን ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን ጦርነትን መስራትም እንችላለን የሚሉትንና የሰላማዊ ትግል ልምድም እውቀትም የሌላቸውን ወያኔዎች ሰላማዊ ትግልን በተግባር በማለማመድ ሀገራችን ለዘመናት ከተጓዘችበት የጠመንጃ ትግል ማላቀቅ ይኖርብናል ያሉ ወገኖች ፓርቲ እየመሰረቱ ለመንቀሳቀስ ሞክረዋል፡፡ በርግጥ ፖለቲከኞቹ ራሳቸው ሰላማዊ ትግል ብለው ፓርቲ ሲመሰርቱ የሀገሪቱን የቀደመ ታሪክ የወቅቱን ነባራዊ ሁኔታ የህዝቡን ሥነ- ልቦና ስልጣን ላይ ያለውን ሀይል ማንነት በሚገባ አጥንተው ከዚህ አንጻር በሀገራችን ደረጃ በደረጃ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ የሰላማዊ ትግል አይነቶችን ለይተው አውቀውና በበቂ ተዘጋጅተው የጀመሩ ባይሆኑም የወያኔ ባህርይ ግን በዚህ ደረጃ ላይ ያሉ ፓርቲዎችን እንኳን በህጋዊ አግባብ ማስተናገድ አልቻለም፡፡ በሂደት እያደጉና እየጎለበቱ እንዳይሄዱ ማድረግ አይደለም ሲጀምሩ የነበራቸውን አቅም አንኳን ይዘው እንዳይቀጥሉ በህግም በጉልበትም እያዳከመ ጠንካራ ተቀዋሚ ቢኖር መሀል መንገድ ድረስ ሄደን እንቀበለው ነበር በማለት ሲሳለቅና ሲመጻደቅ ኖረ፡፡ በመሆኑም በሀያ አራት ኣመታት ውስጥ ወያኔን ከሰላማዊ ትግል ጋር ለማለማመድ የተደረገው ጥረት ያስገኘው ውጤት ወያኔን የለየለት አምባገንን ማድረግና ግንባር ቀደም የህዝብ ታጋዮችን ጨምሮ አያሌ ኢትዮጵያዉያንን በእስር በስደት በሞት ማጣት ነው፡፡
ወደ ኋላ መለስ በማለት ለማንም ግልጽ የሆነውን ይህን ጉዳይ ማንሳቴ፤
አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ወያኔዎችን የሚቃወመው እነርሱን በመጥላት ወይንም እነርሱ እንደሚሉት የቀድሞውን ሥርዓት በመናፈቅ ወይንም እነርሱ የሚሉትን የብሄር ብሄረሰቦች መብት መረጋገጥ በመጥላት ሳይሆን ከኢትዮጵያዊነት ያፈነገጠው ተፈጥሮአቸው በምክርም በተሞክሮም የማይለወጥ በመሆኑ እንደሆነ ለማሳየት፡፡ ወያኔዎች የምሁራንን ምክር ተቀብለው ፣ የህዝብን ጩኸት አዳምጠው፣ የፖለቲከኞችን ተቃውሞ ሰምተውና አማራጭ ሀሳብ ተቀብለው ከደደቢት ህልማቸው ቢወጡና እንደ ኢትዮጵያ መንግስት ማሰብና መስራት ቢጀምሩ ከዴሞክራሲም ጋር እርቅ ቢፈጥሩ ከሚቃወማቸው የሚደግፋቸው በበዛ ነበር፡፡ ከዛ በኋላ ሊኖር የሚችለው ተቃውሞም ቢሆን በሌሎች ዴሞክራቲክ ሀገሮች እንደሚታየው በተወሰኑ ጉዳዮች በተለይም በአፈጻጸም ላይ የተመሰረተና በሰለጠነ የፖለቲካ አካሄድ የሚከናወን በሆነ ነበር፡፡
ሌላው ይህን ጉዳይ ወደ ኋላ ሄጄ ማንሳቴ ወያኔ በምንም ሁኔታ ከተነሳበት ዓላማም ሆነ ወደ ግቡ ከሚያደርገው ጉዞ ዝንፍ የማይል መሆኑ በተግባሩ የተረጋገጠ መሆኑን ለማስታወስና ከዚህ በኋላ በወያኔ አገዛዝ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ፣ሰብአዊ መብትን ማስከበር፣ምርጫን የህዝብን ድምጽ ወደ ስልጣን መቀየሪያ መሳሪያ ማድረግ፣ በጥቅሉ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እውን ማድረግ ይቻላል የሚል ተስፋ የተሟጠጠ በመሆኑ ጥያቄአችን አንድ እሱም ነጻነት የሚል መሆን አለበት የሚል አጽንኦት ለመስጠት ነው፡፡
ከላይ በጥቂቱ ለማሳየት የተሞከሩት ወያኔን ከበርሀ ፋኖነት ወደ መንግስትነት ለመለወጥ የተደረጉ ጥረቶችና ያስገኙት ውጤቶች የሚያሳዩት ወያኔ ከደደቢት እሱነቱ መቼም በምንም የማይለወጥ መሆኑን ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ራሳችንን ለውጠን ወያኔን ለመቀበልና ለአገዛዙ ይሁንታ ለመስጠት አይቻለንም፡፡ ይህን ለማድረግ ኢትዮጵዊነታችንን ከውስጣችው አንጠፍጥፈን ማውጣት ያስፈልገናል ፤ ህሊናቸንና ሆዳችንን ቦታ ማቀያየር ይጠበቅብናል፤ ከዴሞክራሲ ከህግ የበላይነት ከሰብአዊ መብት ወዘተ ጋር መለያየት ግድ ይላናል፡፡ ይሄ ደግሞ የማይሆን ብቻ አይደለም ፈጽሞ የማይታሰብ በመሆኑ ነው አትዮጵያውያን ሀያ አራት ዓመታት ሙሉ የሚገደሉት የሚታሰሩት የሚሰደዱት በተለያዩ የወያኔ ባዶ ስድስት የጭካኔ ዘዴዎች የሚሰቃዩት፡፡
በርግጥ ከላይ የተጠቀሰውን አድርገው አዲስ ማንነት ፈጥረው ለወያኔ ያደሩ አልፎ ተርፎም ከጳጳሱ ቁሱ እንዲሉ ሆነው በወያኔ ተልእኮ አስፈጻሚነት የተሰለፉ ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው በሀገር ውስጥም በውጪም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አሉ፡፡ ወያኔ ከዓላማው ዝንፍ ከመስመሩም ፈቀቅ እንዳይል የእነዚህ ሰዎች ተግባር አስተዋጽኦ አድርጓል ማለት ይቻላል፡፡ እንደውም ከዓላማው ዝንፍ አለማለቱና የሚፈጽማቸው ኢ-ሰብአዊ ተግባራት ሲታዩ ለተለያየ ዓላማና ፍላጎት በተለያየ መንገድ እጅ የሰጡትን ሰዎች በማየት ሌላውስ ለምን እጅ አይሰጥም ወይንም ሰጥ ለጥ ብሎ አይገዛም በሚል የእልህ አስተሳሰብ እየተጓዘ ያለ ነው የሚያስመስሉት፡፡
ታዲያ ወያኔ ራሱን ለውጦ የህዝብ አካል መሆን ካልቻለ፤ ህዝቡ ወያኔን መሆን አይደለም መምሰል ቀርቶ በመንግስትነት እንዲቀበለው የሚያስችል ምንም ነገር ከሌለ አንድና ብቸኛ ምርጫው መገላገል ነው፡፡ በወያኔ አገዛዝ ስር የፍትህ፣ የሰብአዊ መብት፣ የሀብት ተጠቃሚነት የዴሞክራሲ ወዘተ ጥያቄዎች ማንሳት ግዜው አልፎበት አሁን ጥያቄው የነጻነት ጥያቄ ሆኗል፡፡ በሆኑም ወያኔን ለመለወጥም ለማለማመድም እቅጣጫ ላማሳየትም ከተደረገው የሀያ አራት አመታት ጥረት መክሸፍ በኋላ በሁሉም የሀገሪቱ ማዕዘን በሁሉም ኢትዮጵያዊ ( ከወያኔዎች በስተቀር ) መነሳት ያለበት ጥያቄ የነጻነት ጥያቄ መካሄድ ያለበት ትግል ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የመመስረት ትግል መሆን ይገባዋል፡፡ ይህን ማድረግ ካልቻልን ዛሬም ካለፈው አልተማርንም ለወደፊትም ምንም ራእይ የለንም ማለት ነው፡፡
Tigray People Front, TPLF

No comments:

Post a Comment