Tuesday, January 5, 2016

ኢሳት ዜና

ኢሳት (ታህሳስ 25 ፥ 2008) የሶማልያ የወደብ ከተማ የሆንችዉን ኪስማዩ ከሶማሊያዉ ታጣቂ ሀይል አል-ሸባብ ለማስለቀቅ ኢትዮጵያ ተጨማሪ ወታደሮችንና ታንኮችን ወደ ስፍራዉ ማሰማራቷ ተገለጠ። የታጣቂ ሀይሉ ጠንካራ ይዞታ እንደሆነች የሚነገርላትን ኪስማዩ ለማስለቀቅም በአካባቢዉ በማንኛዉም ሰአት ከባድ ዉጊያ ይቀሰቀሳል የሚል ስጋት መኖሩን የሀገሪቱ ባለስልጣናት አስታዉቀዋል። እሑድ ወደ ወደባማ ከተማዋ የገቡት በመቶዎች የሚቆጠሩት የኢትዮጵያ ወታደሮች በታጣቂ ሀይሉ ቁጥጥር ስር የምትገኘዉን ከተማ ነጻ ለማዉጣት መጠነ-ሰፊ ዉጊያን እንደሚያካሂዱ የጁባላንድ ግዛት ምክትል ፕሬዝደንት አብዱላሂ ሼክ-ኢስማኤ ለመገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል። በአካባቢዉ ሰፍሮ የሚገኘዉ የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ሀይል ለኢትዮጵያ ወታደሮች እገዛን እንደሚያደረግም ሀላፊዉ አስረድተዋል። የኢትዮጵያ ወታደሮች ሀላፊነት የሚቆጣጠሩት ኮሎኔል ተስፋዬ በታጣቂ ሀይሉ ስር ለአመታት በቁጥጥር ስር የምትገኘዉን ከተማ መልሶ ለመያዝ በቂ ዝግጅት መደረጉንና የኬኒያና የቡሩንዲ ሰላም አስከባሪዎች እገዛን እንደሚያደርጉ ገልፀዋል። ከወራት በፊት ኢትዮጵያ ለተመሳሳየ ተልእኮ አንድ ሺ ወታደሮችን ወደ ሀገሪቱ አሰማርታ እንደነበር የሚታወስ ነዉ። ይህንኑ ስጋት ለመቀነስም ኢትዮጵያ ተጨማሪ ወታደሮችን ወደ ሶማሊያ በማሰማራት ከባድ ዉጊያ ዉስጥ መሆኗን የሶማሊያ ባለስልጣናት ይፋ አድርገዋል። የአል-ሸባብ አመራሮች ለማደን ከአርባምንጭ ከተማ ሰው አልባ የጦር አዉሮፕላኖችን በሶማሊያ ስታሰማራ የቆየችዉ አሜርካ ተልእኮዋን እንዳቋረጠች ሰሞኑን ይፋ ማድረጓም ይታወቃል። በኢትዮጵያ የሚገኘዉ ወታደራዊ ጣቢያ በአሁኑ ሰአት የሚያስፈለግ ሆኖ ባለመገኘቱ እንዲዘጋ ከመንግስት ጋር ስምምነት መደረሱን ተገልጿል። ለሶስት አመት ያህል ጊዜ ወታደራዊ ዘመቻን ሲያካሂድ የቆየዉ ይኸዉ ጣቢያ ወደፊት ስራዉን ይቀጥል አይቀጥል የተገለጸ ነገር የለም።

No comments:

Post a Comment