Monday, August 29, 2016

በአማራ ክልል የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ተከትሎ አብዛኞቹ አካባቢዎች ከህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ ነጻ እየወጡ ነው ተባለ ኢሳት (ነሃሴ 23 ፥ 2008)



በአማራ ክልል የተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ አድማሱ አስፍቶ መላው ሰሜን ጎንደርን፣ ደቡብ ጎንደርን፣ ምዕራብ ጎጃምን፣ አዊን እና ምስራቅ ጎጃምን ከህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ ነጻ እያወጣ መሆኑ ተገለጸ። 
በጎንደር፣ ደባርቅ፣ ዳባት፣ ገደብየ፣ አምባጊወርጊስ፣ ጎንደር፣ ደምቢያ፣ አዲስ ዘመን፣ በለሳ፣ ወረታ፣ ዓለም በር፣ ደብረ ታቦር፣ ጋሳይ- ክምር ድንጋይ፣ ነፋስ መውጫ፣ ሳሊ፣ ጨጭሆ፣ ጎብጎብ፣ ፍላቂት፣ ደራ ሐሙሲት፣ ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ የአገዛዙ መዋቅር እየፈራረስ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል። 
በተመሳሳይ ሁኔታ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ምዕራብ ጎጃም ባሉ ከተሞች ማለትም ባሕር ዳር፣ ፒኮሎ፣ ዱርቤቴ፣ አቸፈር፣ ቋሪት፣ ፍኖተ ሰላም፣ ብርሸለቆ- ጃቢጠናን፣ ቡሬ፣ ሽንዲ፣ ደምበጫ፣ የጨረቃ፣ አንበር፣ ሎማሜ፣ ፈረስ ቤት፣ አዴት ይልማና ዴንሳ፣ ጎንጅ ቆለላ፣ ሞጣ፣ ጉንደወይን ከፍተኛ የሆነ ሰላማዊ ሰልፍና የቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ ተካሄዷል። 
በየጊዜው የሚደረገው ሰላማዊ ሰልፍ እና በቤት የመቀመጥ አድማ መደረጉ የአገዛዙን ባለስልጣናት ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ እንደከተታቸው ለማወቅ ተችሏል።
በዛሬው ዕለት በባህርዳር የቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ ወደ አደባባይ ተቃውሞ በመቀየሩ ወደ ከተማዋ የሚወጡና የሚገቡ መንገዶች መዘጋታቸው ታውቋል። በከተማዋ የተኩስ ዕሩምታ ይሰማ እንደነበር የገለጹት የኢሳት ምንጮች፣ ቁጥራቸው ያልታወቀ ሰዎች ላይ የሞትና የመቁሰል አደጋ መድረሱ ተነግሯል። 
በከተማው የተቀሰቀሰው ተቃውሞ አይሎ ህዝቡ ወደ አደባባይ በመውጣቱ፣ የመንግስት ሃይሎች በሰላማዊ ሰልፈኛው ላይ ተኩስ በመክፈት ሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ ጉዳት አድርሰዋል። 
ህዝባዊ ማዕበሉን የፈሩት የመንግስት ሹማምንቶች በህወሃት/ኢህአዴግ ጦር እየተጠበቁና አንዳንዶቹም እየሸሹ እንደሆነ ለማወቅ ለኢሳት ከደረሰው መረጃ ለመረዳት ተችሏል። 
ይህ በእንዲህ እንዳለ አዊ ዞን ውስጥ የምትገኘው የቻግኒ ከተማ በከባድ ሕዝባዊ ተቃውሞ እየተናጠች እንደምትገኝ ታውቋል። ወደ አደባባይ የወጣው ሰላማዊ ሰልፈኛ፣ በሕወሓት/ኢህአዴግ ካድሬዎች ላይ ጥቃት ሊሰነዝር ይችላል በሚል ስጋት የካድሬ ቤቶችና የአገዛዙ መስሪያ ቤቶች ጭምር በመከላከያ ሰራዊት ጥበቃ እየተደረገላቸው እንደሚገኙ ኢሳት ያነጋገራቸው እማኞች ከስፍራው ገልጸዋል። ትናንት ከፍተኛ ህዝባዊ ተቃውሞ ሲያደርጉ የነበሩ የእንጅባራ (ኮሶበር)፣ ዳንግላ እንዲሁም በጎንደር ስማዳ ህዝብ ዛሬም ለሁለተኛ ቀን ተቃውሞ ሲያደርጉ እንደዋሉ ለማወቅ ተችሏል። 
በዛሬው ዕለት በጎንደር ሃሙሲት እና ወረታ መሃል፣ ጉማራ ድልድይ ላይ በመንግስት ሃይሎች እና በአርሶደአሮች መካከል በተደረገው የተኩስ ልውውጥ 7 ፌደራል ፖሊሶች እና 4 አርሶአደሮች መሞታቸው ለኢሳት የደረሰው መረጃ ያመለክታል።
ከሳምንታት በፊት በጎንደር ከተማ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ተዛምቶ መላውን የምዕራብ ጎጃም፣ የአዊ እና የምስራቅ ጎጃም አካባቢዎች ማዳረሱ ህወሃት/ኢህአዴግ የሚመራውን መንግስት ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ከቶታል።

No comments:

Post a Comment