“ጥሪ በህውሃት ስር እያገለገልክ ላለኸው የመከላከያና የፖሊስ ሰራዊት” –
የአንድ አገር የመከላከያ ሰራዊት ዋና ተግባር የአገርን ብሄራዊ ጥቅም የማስጠበቅና በኃይል የመጣን የውጪ ወራሪ ኃይል በመመከት የአገርን ዳር ድንበርና ሉዓላዊነት ማስከበር እንደሆነ ይታወቃል ።
በዚህ በህውሃት የአገዛዝ ዘመን ግን ከላይ የጠቀስነውን ብሄራዊ ዓላማና ተግባር ማከናወን ሳይሆን በተቃራኒው የራሱን ሰላማዊ ዜጐች በማሸበርና በጐዳና ላይ ያለ ርህራሄ የጅምላ ፍጅት በመፈፀም ላይ መሆኑን ሁላችንም በከፍተኛ ሃዘንና ቁጭት እያስተዋልነው እንገኛለን ።
ላለፉት 25 ረጃጅም የሰቆቃ አመታት ህውሃት በዘር ተደራጅቶና በመሳሪያ አፈሙዝ በጉልበት ስልጣን ተቆናጦ በአገራችን ታሪክ ታይቶም ሆነ ተሰምቶም በማይታወቅ ሁኔታ ዓለም ዓቀፋዊ የሰብዓዊ መብት ህግጋትን በጣሰ መልኩ ሰላማዊ ዜጐችን ዒላማ ያደረገ የጭካኔ ፍጅት መፈፀሙን አጠናክሮ ቀጥሏል ። በዚህም የተነሳ ህዝባችን በአልሞት ባይ ተጋዳይነት ከዚህ የጅምላ ፍጅት እራሱን በመከላከል ላይ ይገኛል ።
የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዓለም አቀፍ ህብረት ይህንን በሰላማዊ ዜጐች ላይ እየተፈፀመ ያለውን የጐዳና ላይ ፍጅት እያወገዘ በማናቸውም መልኩ ህዝባችን ለነፃነቱ በሚያደርገው የአልሞት ባይ ተጋዳይነት ትግል ጐን በሙያችንም ሆነ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ በትግል አጋርነት የምንቆም መሆናችንን እናሳውቃለን ። በዚህ አጋጣሚም በአሁኑ ሰዓት በአገልግሎት ላይ ላለው የመከላከያ ሰራዊት ያለማሰለስ ከህዝብ ጋር በመወገንና ህዝብን ከአላስፈላጊ ፍጅት እንዲታደግ ጥሪ ያቀርባል ።
ሰላምና ነፃነት ለኢትዮጵያ ህዝብ !
የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዓለም አቀፍ ህብረት
No comments:
Post a Comment