ጭቆናን ለማጥፋት የሚደረግ ትግል ኖሮ አያውቅም
ህዝብ ቋቱ ሲሞላ ነው አልችልም፤ በቃኝ ያለው
አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ የተናገረው የሚያስደንቅ ነው
http://www.addisadmassnews.com/index.php?option=com_
በሦስት መንግስት ውስጥ አልፈዋል - ታዋቂው ምሁርና አንጋፋው ፖለቲከኛ ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም፡፡ በአገራቸው ፖለቲካ ውስጥ ዛሬም በሽምግልና ዕድሜያቸው ንቁ ተሳታፊ ናቸው፡፡ በሰብአዊ መብት ተሟጋችነታቸውም ይታወቃሉ፡፡ ፕ/ር መስፍን ወ/ማሪያም በኦሮሚያና በአማራ ክልል በተነሱ ተቃውሞዎችና ግጭቶች፣ በተቃውሞዎቹ መንስኤና ባህሪያት እንዲሁም በመንግስት ምላሽ አሰጣጥና በችግሮቹ መፍትሄ ዙሪያ ሃሳባቸውንና ዕይታቸውን ለአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ በቃለ-ምልልስ መልክ አጋርተውታል፡፡ እነሆ፡-በእርስዎ ዕይታ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ለተቀሰቀሱ ተቃውሞዎች መንስኤው ምንድን ነው?
የህዝቡ ጥያቄ 25 ዓመት የፈጀ ነው፡፡ አንድ የፖለቲካ ቡድን በፈለገው መንገድ የህዝቡን ግንኙነት በጎሳ ብቻ እንዲሆን፤ በኑሮውም (በቤት፣ በመሬት፣ በስራ፣ወዘተ---) መቶ በመቶ ቁጥጥር አድርጎ ሰውን ነፃነት የነሳበት፤ ጋዜጣ፣ መፅሄት፣ ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥን በአንድ አገዛዝ ስር የወደቀበት ጊዜ ነው ያለፈው፤25 ዓመት፡፡ አሁን ግን እዚህ ላይ ሲደርስ የታመቀው መተንፈሻ ሲያጣ ገንፍሎ ፈነዳ። እየሞቀ … እየሞቀ … እየሞቀ ሲሄድ ድንጋይም ይቀልጣል፡፡ ቀልጦ ቀልጦ ሲሞቅ ይፈነዳል፡፡ እሳተ ገሞራ ሆኖ የሚወጣው የቀለጠው ነው፡፡ አሁን በሀገሪቱ የምናየው ይሄንኑ ነው፡፡
ተቃውሞዎቹ የተነሱት በምርጫ ሙሉ በሙሉ ማሸነፉን ባወጀ ማግስት መሆኑ አንደምታው ምንድን ነው?
ምን ምርጫ አለና! ይሄ መቶ በመቶ አሸንፈናል ያሉበትን ነው የምትለው?
አዎ! የ2007 ምርጫ----
በ“ወያኔ” ዘመን ምርጫ አልነበረም፤ የለም፡፡ ከደርግ ጊዜ የተሻለ አይደለም፡፡ በአፄ ኃይለስላሴ ጊዜ ደግሞ ከሁለቱም የተሻለ ነበር፡፡ ፓርቲዎች ባይኖሩም ምርጫው በጣም ጥሩ ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ ምርጫ የሚባል ነገር የለም፤እንዲሁ ለይስሙላ ነው።
በኦሮሚያ የተቃውሞው መነሻ ማስተር ፕላን ሲሆን በአማራ ክልል ደግሞ የወልቃይትና የኮሚቴው ጉዳይ ነው፡፡ እርስዎ እውነተኛ ምክንያቶቹ እነዚህ ናቸው ብለው ያምናሉ?
ኦሮሚያ ለተነሳው ተቃውሞ ምክንያቱ ማስተር ፕላን ነው ተባለ… ማስተር ፕላኑ ከዚህ በፊት አልነበረም? አዲስ ነው? ቤቶች ሲፈርሱ አልነበረም? ሰዎች መንገድ ላይ እንዲሁ እንደዋዛ ሲጣሉ አልነበረም? አሁን በቃ ቋቱ ሞላ፤ ይሄ ነው ምክንያቱ። ቋቱ ሲሞላ ህዝብ አልችልም፤ በቃኝ ነው ያለው፡፡ ከእንግዲህ ወዲህ ግፍ መቀበል አንችልም ነው፡፡ የወልቃይትም ጉዳይ ቢሆን በተለይ የታሰረው ኮ/ል ደመቀ ጎበዝ ሰው ነው፡፡ እሱ ነው ይሄን ነገር የጫረው፡፡ ግን የወያኔ ኮሎኔል ነው እሡ፡፡ በስርአቱ የነበረ የስርአቱ መሳሪያ ሆኖ የቆየ ሰው ነው፡፡ እንግዲህ ቋቱ ሲሞላ እሱም በቃኝ አለ፤ ሌሎችም በቃን እንዲሉ አደረገ፡፡ እና ምንም አዲስ ነገር የለም። ሁሉም ቋቱ ሲሞላ ነው ወደዚህ ደረጃ የደረሰው፡፡ የማስተር ፕላንና የወልቃይት ጉዳይ ብቻ አይደለም።
አሁን ያለው ተቃውሞና ግጭት ከቀጠለ የአገሪቱ እጣ ፈንታ ምን የሚሆን ይመስልዎታል?
ይሄ የሚያስፈራ ጥያቄ ነው፡፡ “ወያኔ” ተቃዋሚ ድርጅቶች እንዳይዳብሩ እንዳይበረቱ አድርጎ፣ አሁን ተቃዋሚ አለ የማይባልበት ደረጃ ላይ ነው ያለው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በእንደዚህ አይነቱ ጊዜ ድምፃቸው ሊሰማ የሚችል፣ የሚከበሩ የሚደመጡ ሽማግሌዎች እንዳይኖሩ አድርገዋል፡፡ አሁን ታዲያ ማንን ይስማ? ወያኔ አሁን ቢሰማ፣ የሚሰማው ፈረንጆቹን አሜሪካንን፣ እንግሊዝን ነው፡፡ ቸርችል በ2ኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ ያለው አንድ ጥሩ አባባል ነበር፡- “let dog eat dog.” (እርስ በርሳቸው ይባሉ ምንም አይደለም) ፈረንጆቹም በተመቻቸው ሁኔታ እንድንሆንላቸው ይፈልጋሉና ምንም አያደርጉም። ስለዚህ አስታራቂ ሊኖር አይችልም፡፡ ወያኔም የሚሰማው ጡንቻው መሳሪያው ብቻ ነው፡፡ ያንን መሳሪያ እስከያዝኩ ድረስ አልሸነፍም በሚለው አስተሳሰቡ ፀንቷል፤ከደርግ አልተማሩም፡፡ ደርግ የትየለሌ መሳሪያ ነበረው፤ህዝብ ግን አልነበረውም። ህዝብ ከሌለ የትም መድረስ አይቻልም፡፡ እነሱም ይሄንን አልተረዱትም፡፡ አሁንም ለእርቅ፣ ለሰላም የተዘጋጁ አይመስለኝም፡፡ እንደ በፊቱ በጡንቻችን ረግጠን እንቀጥላለን፤ብለው ነው የሚያስቡት። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ደግሞ አገዛዙና ህዝቡ ደም ተቃብቷል። ይሄ ወደ ኋላ የሚመለስ አይመስለኝም። እየባሰ እየከረረ የሚሄድ ይመስለኛል፡፡
በዚህ መሃል ግን አጠቃላይ የትግራይ ተወላጆች ጉዳይ አለ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ በተገቢው መንገድ ውይይት እየተደረገ አይደለም፡፡ ልንወያይበት ልንነጋገርበት የሚገባ ነገር ነው፡፡ የትግራይ ተወላጆች በደቡብ በኩል በጎንደር፣ በወሎ ወንድሞቻቸው ድሮ ችግር ሲመጣ የሚሄዱበትን ቦታ ሁሉ አሁን ጠላት እንዲሆኑ አድርጓል ወያኔ፤ በሰሜን በኩል ያሉ ኤርትራውያን ወንድሞቻቸውን ጠላት አድርጓል። የትግራይ ህዝብ በዚህ መሃከል ነው ያለው፤ እንደ ቡሄ ዳቦ፡፡ አሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለው፡፡
ለዚህ ችግር መፍትሄው ምንድን ነው ይላሉ?
ህዝቡ ራሱን ሊያወጣ ይችላል፡፡ ህወሓትን በመቃወምና ከሌላው ጋር በአጋርነት በመቆም ከዚህ አጣብቂኝ ራሱን ሊያወጣ ይችላል፡፡ “ትግሬ ህውሓት ነው፤ ህውሓት ትግሬ ነው” የሚባለው ለኔ ትክክል አይደለም፡፡
ህዝባዊ ተቃውሞው ባለቤት የለውም፣ እንቅስቃሴዎቹ ጎልቶ የወጣ መሰረታዊ ጥያቄ የላቸውም የሚሉ አስተያየቶች ይደመጣሉ፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?
እንቅስቃሴው ዋና እምቡጥ የለውም የሚለው ጉዳዩን ካለመገንዘብ የመጣ ነው፡፡ 25 ዓመት ሙሉ ሲጠራቀሙ የመጡ በርካታ ጥያቄዎች ናቸው የእምቡጡ መሰረቶች፡፡
በየተቃውሞዎቹ የሚነሱ የማንነትና የብሄር መብት ጥያቄዎችስ አቅጣጫቸው ወዴት ነው?
የማንነት ጥያቄ የተምታታ ነው፡፡ እንኳን በአጠቃላይ በህዝቡ ቀርቶ ተማርን በሚሉት፣ አስተማሪ ነን ምሁራን ነን በሚሉትም ዘንድ ብዙ ውዥንብር አለ፡፡ ኢትዮጵያ መቼም የምታስደንቅ ሀገር ነች፤ በዚህ ውዥንብር፣ ተማርኩ የሚለው ሰው ሁሉ በተወናበደበት ጊዜ ሯጩ ፈይሳ ሌሊሳ የተናገረው ነገር የሚያስደንቅ ነው፡፡ ብዙ ምሁራንን ዜሮ ያደረገ ንግግር ነው የተናገረው፡፡ “እኔ ኢትዮጵያዊ ኦሮሞ ነኝ” ነው ያለው፡፡ ሌሎቹ የማይሉትን ነው የተናገረው፡፡ ምሁራ ነን የሚሉት ሁለቱን ማገናኘት አይፈልጉም፡፡ ይሄ አትሌት ግን ድርቅ ያለውን እውነት አውጥቶታል፡፡ ሁሉም ሰው እርስ በእርሱ የተጋባባት፣ የተዋለደባት ሀገር ነች ኢትዮጵያ፡፡ ብዙዎች ዛሬ አለን የሚሉት ማንነት ሲፋቅ ሌላ ማንነት ይወጣዋል፡፡
በብሄር ተቧድኖ የሚቀርቡ ተቃውሞዎችና ጥያቄዎች ሀገሪቱን አደጋ ላይ አይጥሏትም?
አደጋ ሊፈጥር ይችላል፡፡ ግን እንደ ፈይሳ አይነት ሰዎች በብዛት የሚኖሩ ከሆነ ምንም አይፈጠርም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ እውነት የሚገባቸው እንደ ፈይሳ ያሉ ሰዎች ካየሉ ስጋት አይኖርም፡፡ ዘር ከፋፋዮች ከሆነ የሚመሩት የተሰጋው ሊደርስ ይችላል፡፡ እንደኔ ግን 90 በመቶ የሚሆነው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ኦሮሞ፣ እንደ ፈይሳ የሚያስብ ነው ብዬ ነው የማምነው፡፡ እኔ የማገኛቸው ኦሮሞዎች ሁሉ እንደዛ ናቸው፡፡
ከ97 ምርጫ በኋላ ያለው የተቃዋሚዎች እንቅስቃሴ እንዴት ይገለጻል?
“ወያኔ” ብልሃት ብሎ ሃገር ውስጥ ተቀናቃኝ ቡድኖች እንዳይፈጠሩ እንዳያድጉ አደረገ፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ ተቃዋሚዎቹን ከሃገር አስወጣቸው። አንዳንዱ ፈርቶ ስደት ወጣ፡፡ ያኔ ኢህአዴግ ይጠቅመኛል ብሎ ያመጣው ብልሃት አሁን የሚጎዳው ነገር ሆኗል። ትልቁ የተቃዋሚ ጎራ ያለው ውጭ ሃገር ነው፡፡ አሜሪካ፣ አውሮፓ፣ አውስትራሊያ ደቡብ አፍሪካ ነው የተቃውሞው መቀመጫ፡፡ ተቃውሞው በጣም ከመጠንከሩ የተነሣ አሁን እነሱም ወደ ውጭ ሃገር ሄደው መስራት አልቻሉም፡፡ እዚያም ተቃውሞ ይገጥማቸዋል። የበለጠ ሊቆጣጠሩት የማይችሉት ተቃውሞ ነው ከውጭ ሃገር እየገጠማቸው ያለው። እዚህ ሊቆጣጠሩት ይችሉ የነበረውን ተቃውሞ ገደልን ብለው ወደ ውጪ እንዲሄድ አደረጉት። ወደ ውጭ የገፉት ተቃውሞ ደግሞ ጊዜውን ጠብቆ እነሱኑ ሽባ አደረጋቸው፡፡ ሆቴል እየተከተሉ ማዋረድ ሆነ ነገሩ። ‹‹ተንጋሎ የተፋው ለራሱ ከረፋው›› አይነት ነገር ነው የሆነው፡፡ የተፉት መልሶ መጣባቸው፡፡ አሁን ያንን ሊያቆሙት አይችሉም። እነሱ ካልተለወጡ ያኛው እየተባባሠ ይሄዳል እንጂ በምንም መንገድ አይለወጥም፡፡ ሊደርሱበት ሊቆጣጠሩት አይችሉም።
በአገር ውስጥ ያለው የተቃውሞ እንቅስቃሴስ?
አገር ውስጥ ስላሉ የፖለቲካ ቡድኖች ምንም የምናገረው ነገር የለም፡፡ ማን አለና ነው የምናገረው? ማንም የለም፡፡ ሠማያዊም ሌላውም የሉም፤ የሚረቡ አይደሉም፡፡ አላማቸውም ሌላ ነው፡፡
በሦስት ስርዓቶች ውስጥ ያሣለፉ እንደመሆንዎ ተቃውሞዎች በንጉሡ፣ በደርግና በኢህአዴግ መንግስታት ያላቸው አንድነትና ልዩነት እንዴት ይገለጻል?
በአፄ ኃይለስላሴ ጊዜ ህዝቡ አልተንቀሳቀሰም። ተቃዋሚ የሚባለው ተማሪውና አስተማሪው ነበር፡፡ እሱም በአብዛኛው የዩኒቨርሲቲ ተማሪና የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ነው፡፡ ህዝቡ ግን አብዛኛው የአፄ ኃይለስላሴ ደጋፊ ነበር፡፡ ግፉንም በደሉንም አልተረዳም ወይም የበደሉ አካል ነበር ማለት ይቻላል። ጭቆና፤ ጨቋኝና ተጨቋኝ በሚል ርዕስ በመፅሃፌ ገልጨዋለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ጭቆናን ለማጥፋት የሚፈልግ የለም፤ትግሉ ሁሉ ተጨቋኙ ጨቋኝ ለመሆን ነው፡፡ ጨቋኙ ደግሞ ጨቋኝ መሆኔን አልለቅም እያለ ጨቋኝ ለመሆን ተጨቋኝና ጨቋኙ ይታገላሉ እንጂ ጭቆናን ለማጥፋት የሚደረግ ትግል ኖሮ አያውቅም፡፡ አሁንም የሚደረገው ጨቋኙን ወያኔን አውርደን፣ እኛ ጨቋኝ እንሁን ነው፡፡ ጭቆናን እናስወግድ የሚል ትግል አይደለም፡፡
በዚህ ሁኔታ ውስጥ ተጨቋኙ ከጨቋኙ ጋር የተባበረ ነው፡፡ ፈልጎ ነው ያንን የሚያደርገው፡፡ ስንት ሺህ ሰው ባለበት 5 ፖሊሶች አንዱን መንገድ ላይ ይዘው ይደበድቡታል፡፡ እንደዚያ ሲያደርጉ 1ሺ ሰው ምንም አያደርግም፡፡ ይሄ ለኔ የጨቋኝ ተጨቋኝ ስምምነት ነው፡፡ “ለምን ትመታዋለህ?” የሚል የለም። ያ ሁኔታ እስካለ ድረስ ጭቆና ይቀጥላል፡፡
መንግስታቱ ለተቃውሞዎች የሚሰጡት ምላሽስ በንጽጽር ምን ይመስላል?
በአፄ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ ከመጠን ያለፈ የኃይል እርምጃ አይታሰብም፡፡ ንጉሱ የኢትዮጵያ ስምም ሆነ የሳቸው ስም በውጭ ሀገራት በክፉ እንዲነሳ አይፈልጉም፡፡ ራሳቸውን ስለሚያከብሩ ሀገሪቱንም ያከብራሉ፡፡ ለራሳቸው የሚሰጡት ክብር ነው ሀገሪቱን እንዲያስከብሩ የሚያደርጋቸው፡፡ አሁን ያ የለም። የአትሌት ፈይሳ ድርጊት በስንት የዓለም ሚዲያ ነው የተነገረው? ግን ምን ተሰማቸው? ፈይሳ የበለጠ ነገሩን አፈነዳው፡፡ ይሄ ውርደት ግን አይሰማቸውም። ይሄ ህዝቡ የሚደበደበውና አስከሬኑ በየሚዲያው የሚታየው ያሳፍራቸዋል? በአፄ ኃይለስላሴ ጊዜ ይሄ በጣም የሚያሳፍር፣ ሀገሪቱን ህዝቡን ክፉኛ የሚያዋርድ ነገር ነበር፡፡ ንጉሡ ይሄን አይፈልጉትም ነበር፡፡ ፖሊስ ከተማሪ ጋር ይጣላ የነበረው በዱላ ነው እንጂ በመትረየስ አልነበረም፡፡ እንግዲህ የሁለቱ የአፀፋ መልስ አሰጣጥ ከክብር ጉዳይ የሚመነጭ ነው፡፡ አፄ ኃይለሥላሴ ታሪካቸውን ራሳቸውን የሚያስከብሩ ስለነበሩ ክብራቸውን ይጠብቃሉ፡፡ አሁን ያሉት ራሳቸውንም ህዝቡንም አያከብሩም፤ታሪካቸውንም አያከብሩም፤ የሚታያቸው ጡንቻ ብቻ ነው፡፡
በአፄ ኃይለሥላሴ ጊዜ የሰብአዊ መብት ጉዳይ በጨዋነት የተያዘ ነው እንጂ በወረቀት ላይ ብቻ የሰፈረ አልነበረም፡፡ ይሄን ማድረግ ሀጢያት ነው፤ ብልግና ነው፤ ነውር ነው---ነበር የሚባለው፡፡ ከሥነ-ምግባር የሚመነጭ ሰብአዊነት ነበር፡፡ ጡንቻ የተጀመረው በደርግ ዘመን ነው፡፡ በጥይት መጋደል ተጀመረ። እውነት ለመነጋገር ከሆነ፣ ያንን ያመጣው ደርግ አልነበረም፡፡
የስልጣን ተቀናቃኝ ሆነው የገቡት ኢህአፓና መኢሶን ነበሩ ግብግቡን የጀመሩት፡፡ እነዚህ አካላት የሶስትዮሽ ድብድብ ሲገጥሙ መሳሪያ ያደረጉት ወጣቶችን ነበር፡፡ #ወያኔ”ም የኢህአፓ የመኢሶንና የደርግ ርዝራዥ ነው፡፡ እምነታቸውም የጡንቻ ነው፤ እስካሁን የሰሩትም በዚያው ነው። የሚለያየው የያዛቸው የውጭ እጅ ብቻ ነው፡፡ ሶቭየት ህብረት ደርግን መሳሪያ እየሰጠ ለግድያ ነፃ አድርጎት ነበር፡፡ እነዚህ ደግሞ በአሜሪካ ይደገፋሉ። አሜሪካ ደግሞ ግልፅ ግድያ አይፈልግም ነገር ግን እነዚህ በኃይል እየወጡ ጉልበታቸውን እያሳዩ ነው፡፡
በእንዲህ ያለ የፖለቲካ ቀውስ ወቅት የምሁራን ሚና ምን መሆን አለበት?
መጀመሪያ ፍርሃት መወገድ አለበት፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ለህዝብ ነፃነት መቆም ያለባቸው ምሁራን፣ የኪነ ጥበብ ሰዎች እንዲሁም ጋዜጠኞች ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ ግን አሁን በፍርሃት ቆፈን የተያዙ ናቸው፡፡ እነዚህ ራሳቸውን ነፃ ካላወጡ ሌላው ነፃ አይወጣም። የምሁራኑ በዚህ ውስጥ ነው ያለው፡፡
በአገሪቱ ላይ መረጋጋት እንዲፈጠር መፍትሄው ምንድን ነው ይላሉ?
ከኃይለኛ ጋር ስትጋፈጥ መፍትሄው ሁሉ የሚኖረው በኃይለኛው እጅ ነው፡፡ መፍትሄው ሁሉ ያለው በ“ወያኔ” እጅ ነው፡፡ ከ“ወያኔ” በስተጀርባ ደግሞ በአሜሪካ እጅ ነው፡፡ ከዚያ ውጭ የኢትዮጵያ ህዝብ ወያኔን ልስበር ካለ መጥፎ ነው፤መጫረስ ነው የሚሆነው፡፡ በተለይ ደግሞ ወያኔን ትግሬ እያደረጉ፣ ትግሬን ሁሉ ወያኔ እያደረጉ የሚኬድበት ሁኔታ መታረም አለበት፤ አደገኛ መርዝ ነው፡፡ ሀገሪቱን አደጋ ላይ የሚጥል ነው፡፡ መፍትሄው ግን በ“ወያኔ” እጅ ነው ያለው፤ ህዝቡን ማዳመጥ አለባቸው፡፡
No comments:
Post a Comment