Friday, September 9, 2016

በጀርመን በርሊን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ሰላማዊ ሰልፍ አካሄዱ ኢሳት (ጳጉሜ 4 ፥ 2008)


ነዋሪነታቸው በጀርመን በርሊን ከተማና አካባቢዋ የሆነ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ መንግስት በንጹሃን ሰዎች ላይ የሚፈጸመውን ግድያና አፈና በመቃወም አርብ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ አካሄዱ። 
በበርሊን ከተማ በሚገኘው የሃገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፊት ለፊት ተሰባስበ የነበሩት ኢትዮጵያውያን የተለያዩ መፈክሮች በማስተጋባት የጀርመንንና ሌሎች ሃገራት መንግስታት በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ ጉዳይ ልዩ ትኩረትን እኝዲሰጡ ጠይቀዋል። 
በዚሁ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ የተለያዩ አላማ ያላቸው የፖለቲካ ድርጅቶችና የህብረተሰብ ክፍሎች ልዩነታቸውን ወደ ጎን በመተው በተቃውሞ በአንድነት መቆማቸውንና የታሰበውን መልዕክት በተገቢው ሁኔታ እንዳስተላለፉ ከስፍራው ለኢሳት የደረሰ መረጃ መልክቷል። 
በገዢው የኢህአዴግ መንግስት የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዲቆሙ ጥያቄን ሲያቀርቡ ያረፈዱት ሰልፈኞቹ፣ ሰላማዊ ሰዎች እያቀረቡ ላሉት ህጋዊ ጥያቄ ድጋፋቸውን እንደሚሰጡ መግለጻቸውን የሰልፍ አስተባባሪዎች ከዜና ክፍላችን ባደረጉት ቃለምልልስ ተናግረዋል። 
በርሊን ከተማ ለሚገኙ የተለያዩ አለም አቀፍ ድርጅቶች የተቃውሞ መልዕክታቸው እንዲደርስ ማድረጋቸውን የገለጹት የሰልፉ አዘጋጆች በተቃውሞው ሰላማዊ ሰልፍ ወቅት በርካታ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ የስርዓት ለውጥ እንዲመጣ ድምጽ ሲያሰሙ እንደነበርም ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስረድተዋል። 
ከፍራንክፈርት ከተማና ሌሎች ከተሞች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የተለያዩ ትራስፖርቶችን በመጠቀም በተቃውሞ በመሳተፍ የተሳካ መልዕክት እንዳስተላለፉ አዘጋጆች ገልጸዋል። 
“የአማራ ደም የኦሮሚ ደም ነው፣ የኦሮሞ ደም የአማራ ነው” የሚሉ መፈክፎችን ጨምሮ፣ “አንከፋፈልም፣ አንድ ነን” የሚሉ ድምጾች በኢትዮጵያውያኑ ዘንድ ሲያስተጋባ ማርፈዱን የሰልፉ አስተባባሪ አባል የሆኑት አቶ ታደሰ ቶላ ለኢሳት አስታውቀዋል። 
በሃገሪቱ ያሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችንና ግድያዎችን በመቃወም ሃሙስ በሶስት የአውሮፓ ሃገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በየሃገሪቱ ያሉ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችን በመቆጣጠር ተቃውሞ ማካሄዳቸው ይታወሳል። 
በተመሳሳይ ቀን ነዋሪነታቸው በዚህ አሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ከተማና አካባቢዋ የሆነ ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ቅጥር ግቢ በመግባት ተቃውሞን ያሰሙ ሲሆን፣ ባለኮከቡ ባንዲራ በማወረድ በአረንጓዴ፣ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ አላማ መተካታቸውን መዘገባችን ይታወሳል። 
ከሁለት አመት በፊት በዚህ ኤምባሲ ላይ ተመሳሳይ ተቃውሞ ተካሄዱ የኢምባሲው አንድ ባልደርባ ተኩስ መክፈቱ አይዘነጋም። የአሜሪካ መንግስት ግለሰቡን በ24 ሰዓት ውስጥ ከሃገሪቱ እንዲወጣ ማድረጉም የሚታወስ ነው።

No comments:

Post a Comment