ሰሞኑን በባህርዳር ከተማና አካባቢ በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ግድያ የተፈጸመባቸው ሰላማዊ ሰልፈኞች በጸጥታ ሃይሎችና በተለያዩ ተቋማት ላይ ሃይል በመጠቀማቸው እርምጃው እንደተወሰደባቸው መንግስት አስታወቀ።
የመንግስት የኮሚኒኬሽን ሚኒስትሩ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ከአልጀዚራ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ውይይት በባህር ዳር የተሳተፉ ሰላማዊ ሰልፈኞቹ በጸጥታ ሃይሎች እና በተቋማት ላይ ቦምብ ጭምር በመወርወራቸው የጸጥታ ሃይሎች የመከላከል እርምጃ ወስደዋል ብለዋል።
የሟቾችን ቁጥር ለመግለጽ ያልፈለጉት አቶ ጌታቸው፣ 30 ሰላማዊ ሰልፈኞች ተገድለዋል የሚለውን የአልጀዚራን ዘገባ አጣጥለዋል ፥ የአልጀዚራ የጋዜጠኞች ስነምግባርም ተጠራጥረዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በኢትዮጵያ እየተፈጸመ ያለው ግድያ በአለም አቀፍ ገለልተኛ አካል ማጣራት እንዲካሄድበት ሲል ያቀረበን ጥያቄ ለምን የኢትዮጵያ መንግስት እንዳልፈቀደ የተጠየቁት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ መንግስት ህዝባዊ አመጽ በተቀሰቀሰባቸው የአማራና ኦሮሚያ አካባቢዎች በችግሩ ዙሪያ ከህዝብ ጋር ሆኖ እየሰራ ስለሆነ የአለም አቀፍ አጣሪ ቡድን አያስፈልገንም ሲሉ ጥያቄውን ውድቅ አድርገዋል።
“ለኢትዮጵያውያን ተጠያቂ የኢትዮጵያ መንግስት እንጂ የአለም አቀፍ ማህበረሰብ አይደለም” ያሉት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ መንግስትና ህዝብ ተመካክረው ችግሮቹን ይፈታሉ ሲሉ ተከራክረዋል።
በተጨማሪም ከሳምንት በፊት የኢትዮጵያ መንግስት ለምን የኢንተርኔት አገልግሎትን እንዳቋረጠ የተጠየቁት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ የኢትዮጵያ መንግስት የኢንተርኔት የፍሰቱን (ባንድ ዊድዝ) መቀነሱን እንጂ አለማቋረጡን ገልጸው፣ ሆኖም በማህበራዊ መገኛኛ ብዙሃን የተሳሳተ መረጃ ሲሰራጭ እንደነበርና ይህም መቆም እንደነበረበት አብራርተዋል። የአልጀዚራ ጋዜጠኛዋንም ማህበራዊ መገኛኛ ብዙሃን ምን እንደሚሰራ አታውቂም ሲሉ ወርፈዋል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ኢንተርኔት መዘጋቱን የኢንተርኔት ትራፊክ የምርመራ ሪፖርት ያቀረበው ኳርትዝ አፍሪካ ድረገጽ በበኩሉ፣ ከሳምንት በፊት የኢትዮጵያ መንግስት ኢንተርኔትን ዘግቶ እንደነበር ሆኖም በሁሉም የአገሪቷ ክፍሎች ይሁን በተወሰኑ አካባቢዎች ማወቅ እንዳልቻለ ገልጿል።
ከቀናት በፊት በባርዳር ከተማ በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በተፈጸመ ግድያ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር በከተማዋ ብቻ 55 መድረሱን የከተማዋ ነዋሪዎች ለኢሳት ማስታወቃቸው ይታወሳል።
በአልጀዚራ የተዘጋጀው ውይይት ኢትዮጵያዊው የታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር ህዝቅዔል ገቢሳንና የሂውማን ራይትስ ዎች ተመራማሪ የሆኑት ሚስተር ፊሊክስ ሆንር የተሳተፉበት እንደነበር ታውቋል።
No comments:
Post a Comment