-ሰልፉ በወልቃይት የማንነት ጥያቄ ላይ መነሻውን ቢያደርግም መድረሻውና ዓላማው እጅግ ሰፊና ሀገራዊ ሆኖ መገኘቱ ብሄርና ሀይማኖት ሳይለይ ከዳር እስከ ዳር የሁሉንም ኢትዮጵያውያን ቀልብ ሊሰርቅና አመኔታ ሊያገኝ ችሏል።
-ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ከሚወክለው የሰንደቅ ዓላማ አመራረጥ ጀምሮ በበሳል ሰዎች ለመስተባበሩ ቅንጣት ታህል የማያጠራጥረው የትናንትናው ሰልፍ፤ በህወኃት ሴራ በመጠኑም ቢኾን በኢትዮጵያውያን መካከል በተቀበረው የቂም በቀል ስራይ ላይ ውሃ በመቸለስ- በተናጠል የሚደረግን የነጻነት ትግል ወደአንድነት ለማምጣስት መሰረት የተጣለበት ነው።
አዎ፣“ወልቃይት አማራ ነው!፣ በኦሮሞ ወንድሞቻችን ላይ የሚፈጸመው ግድያ ይቁም! የሙስሊም ኮሚቴዎች ይፈቱ!” የሚሉ ጥያቄዎችና መፈክሮች መስተጋባታቸው የሚነግረን ሀቅ ፦ በወልቃይት ማንነት ላይ መነሻ ያደረገው ሰልፍ -ዓላማው ሀገራዊና ሰፊ መሆኑን ነው።
-የመንግስት ሚዲያዎች ሰልፉ የተለመደ የመልካም አስተዳደር ችግር እንደኾነ በማስመሰል ዓላማውን ለማሳነስ መሞከራቸው አይገርምም። እንደውም ኮከብ የሌለው ባንዲራ ተውለብልቦ ሳለ ከእስከዛሬ ልምዳቸው በመነሳት ፦”ህገ መንግስቱን የጣሱ ጥቂት ነውጠኞች..” አለማለታቸው ነው የሚገርመው። ያን ያላሉትና እነ አቦይ ስብሀት ነጋ በተወገዙበት ሰልፍ ራሳቸውን ከሰልፈኛው ህዝብ ጋር ለማጣጣም የሞከሩትም ለምን እንደሆነ ግልጽ ነው- ጎንደር በሚገባቸው ቋንቋ ስላናገራቸው ነው። “ወደሽ ነው ገጣቢት?” አሉ እማማ ዘርፌ?
-የመንግስት ሚዲያዎች ሀቁን ሊሸፋፍኑት ቢሞክሩም እድሜ ለማህበራዊ ሚዲያውና እንደ ዋዜማ፣ ኦ፣ ኤም፣ ኤን ፣ኢሳት፣ ቪኦኤ፣ደቸቨለ፣ ህብር... ለመሣሰሉ ሚዲያዎች፤ የሰልፉ መሰረታዊ ጥያቄም ሆነ ሰፊ ዓላማ ለህዝቡ በተገቢው መንገድ ተደራሽ ሆኗል።
እንደ ተጨማሪ
ቀንዱ ዕይታውን እንደከለለው በሬ ስለዛሬው ምቾታቸው ብቻ ሳይሆን ስለ ነገውና ከነገ በስቲያው አርቀው እንዲያዩ ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ሲመከሩ የቆዩት የህወኃት/ ኢህአዴግ መሪዎች ከተቀረቀሩበት ጠባብ ኩሬ መውጣት ተስኗቸው በ“ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” ፖለቲካ አብዛኛውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጫፍ እስከጫፍ ሲያስከፉትና ሲያሳዝኑት ኖረዋል። እነ ኢቲቪ መንደርተኞቹን እነ መለስ ዜናዊን “የአፍሪካ መሪ” እያሉ ሲያሞካሹ ቢቆዩም፤ ሕዝቡ ግን እንኳን የአፍሪካ የኢትዮጵያም መሪ እንዳልነበሩ ለማረጋገጥ የህወሀትን ከሥልጣን መወገድ አልጠበቀም። ከበርካታ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በቢል ቦርድ የተሰቀለ ምስላቸው የተነቃቀለውና ፎቷቸው በእሳት እየተለበለበ ወደ አመድነት የተቀየረው ገና ሦስተኛ የሙት ዓመታቸው ሳይከበር ነው። ሰፊ ሕዝብ መንደርተኛን ገዥ “የኔ መሪ ነበር” ብሎ ሊያስታውሰው አይፈቅድምና።አዎ፣ቅርብ ዓላሚ ሩቅ ሊያድር አይችልም።እናም መታሰቢያዎቹ ከጅምሩ ተወገዱ።
በትናንትናው የጎንደር ሰልፍም የህወሀት መስራችና የመጀመሪያ ሊቀ-መንበር የአቦይ ስብሀት ምስል ሲቃጠል ዐይተናል። ሁኔታውን ሲከታተል የነበረው አንድ ጓደኛዬ ፦”የመለስስ ቢቃጠልና ቢነቀል ከሞተ በኋላ ነው፤ የሽማግሌው የአቦይ ስብሀት ምስል የተቃጠለው ግን በቁማቸው ዐይናቸው ዕያዬ በመኾኑ ደስ ብሎኛል” አለኝ።
በእርግጥም ላለፉት 25 ዓመታት ሲገዟት በቆዩት ሀገር ላይ በቁማቸው እያሉ ይህ መሆኑ፤ በሰማንያዎቹ አጋማሽ ላይ ለሚገኙት አቦይ ስብሀት ልብ የሚያደማ ሀዘን ነው። እርግማን ነው።በቁም መሞት ነው።ከላይ እንደጠቀስኩት የዚህ ሁሉ ምክንያት እንደ ዶሮ መቀመጫ መጥበብ ነው። መቼም “ለሰፈሬ” ከሚል ጠባብ አስተሣሰብ በመነሳት ከኋላ ሆነው በእነ አባይ ወልዱ አማካይነት ያስጨረሱት የወልቃይት ሕዝብ ሐውልት ሊያቆምላቸው አይችልም።
No comments:
Post a Comment