በአለም በሰብዓዊ መብት መከበር ዙሪያ የሚሰሩ 14 የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ምክር ቤት በኢትዮጵያ ላይ ጠንካራ እርምጃን እንዲወስድ የጋራ ጥያቄን ሃሙስ አቀረቡ።
ለምክር ቤቱ ጥያቄያቸውን ያቀረቡት እነዚሁ ድርጅቶች ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ መንግስት የሚፈጸሙ ግድያና አፈና በአስቸኳይ እንዲቆምና ድርጊቱ በገለልተኛ አለም አቀፍ ተቋማት/ቡድን ማጣራት እንዲካሄድበት አሳስበዋል።
ከፊታችን ማክሰኞ ጀምሮ 33ኛ ልዩ መደበኛ ጉባዔውን በጄኔቫ ስዊዘርላንድ የሚያካሄደው የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በአለም ዙሪያ ባሉ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ዙሪያ የሁለት ሳምንት ምክክርን ያካሂዳል ተብሎ ይጠበቃል።
ጥያቄያቸው ለምክር ቤቱ ያቀረቡት 14ቱ አለም-አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በልዩ ጉባዔው ወቅት በኢትዮጵያ መንግስት የሚፈጸመው ግድያ ልዩ አጀንዳ ሆኖ እንዲቀርብ ዘመቻ መክፈታቸው ታውቋል።
ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ መንግስት የጸጥታ ሃይሎች በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች እየወሰዱ ያለው ከመጠን ያለፈ የሃይል እርምጃ እንዲቆም ጠንካራ ውሳኔን ማስተላለፍ ይኖርበታል ሲሉ 14ቱ ድርጅቶች ለምክር ቤቱ ባቀረቡት የጹሁፍ ጥያቄ አመልክተዋል።
ከህዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተገናኘ ለእስር የተዳረጉ ጋዜጠኞች የፖለቲካ አመራሮችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ግለሰቦች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መፈታት እንዳለባቸው ድርጅቶቹ አሳስበዋል።
በመንግስት ሲፈጸሙ የነበሩ ግድያዎች፣ አፈናዎች እስራቶችና የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችም በአለም አቀፍ ገለልተኛ ቡድን ምርመራ እንዲካሄድበትና ድርጊቱን የፈጸሙ አካላት ለህግ እንዲቀርቡ ሲሉ ተቋማቱ ለምክር ቤቱ ጠይቀዋል።
የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ባለፈው ወር በአማራና ኦሮሚያ ክልል እየተፈጸሙ ያሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በመኮነን ድርጊቱ በገለልተኛ ቡድን እንዲጣራ ለኢትዮጵያ መንግስት ይፋዊ ጥያቄ ማቅረቡ ይታወሳል።
ይሁንና፣ መንግስት ለጥያቄው ተባባሪ እንደማይሆን በመግለጽ ድርጊቱ በሃገር በቀል አካላት ማጣራት እንደሚካሄድበት ምላሽ ሰጥቷል።
ሃሙስ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጥያቄያቸውን ያቀረቡት 14ቱ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ትሟጋች ተቋማት የኢትዮጵያ መንግስት በተለያዩ ጊዜያት ለፈረማቸውና ላጸደቃቸው የተባበሩት መንግስታትና የአፍሪካ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ ተገዢ እንዲሆን ጫና እንዲደረግ አክለው ጠይቀዋል።
ሂውማን ራይትስ ዎች፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ፍሪደም ሃውስ፣ አለም አቀፍ የጸረ-ስቃይ ተቋም፣ እንዲሁም መቀመጫቸውን በተለያዩ ሃገራት ያደረጉ ድርጅቶች ከ14ቱ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት መካከል እንደሚገኙበት ለመረዳት ተችሏል።
የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ እየተፈጸመ ያለውን ግድያና አፈና በመኮነን ረቡዕ ከሃገሪቱ የሚሰጥ የአስቸኳይ ጊዜ የገንዘብ ድጋፍ እንዲቋረጥ መወሰኑ ይታወሳል።
No comments:
Post a Comment