Friday, September 9, 2016

ከኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባርና ከአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ የወቅቱን የኢትዮጵያ ሁኔታ በማስመልከት የተሰጠ መግለጫና ለሁሉም ነፃነት ፈላጊ ወገኖች የቀረበ ጥሪ

ከኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባርና ከአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ የወቅቱን የኢትዮጵያ ሁኔታ በማስመልከት የተሰጠ መግለጫና ለሁሉም ነፃነት ፈላጊ ወገኖች የቀረበ ጥሪ
ኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባርና ከአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ የወቅቱን የኢትዮጵያ ሁኔታ በማስመልከት የተሰጠ መግለጫና ለሁሉም ነፃነት ፈላጊ ወገኖች የቀረበ ጥሪ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ለነፃነት፣ ለፍትህ፣ ለእኩልነትና ለትክክለኛ ዲሞክራሲ የሚያደርጉት የብዙ ሺህ ንፁሃን ዜጎችን የሕይወት መስዋዕትነት የጠየቀ የተቃዉሞ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ከመቀጠልም አልፎ ወደከፍተኛ ደረጃ ተሸጋግሯል፡፡ የዛሬዉ የሕዝባችን ትግል የአገዛዙን የከፋፍሎ መግዛት ግንብ ንዶ በተባበረ መንፈስና በአንድ ድምፅ የጋራ ጠላቱ የወያኔ አገዛዝና አልጠግብ ባይ ዘራፊ መሪዎቹ ብቻ መሆናቸዉን በማያሻማ ቋንቋ ከሚገልፅበት ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን በተግባር አሣይቷል፡፡ ለዚህ ደግሞ አስረኛ ወሩን የያዘዉ የኦሮሞ ሕዝብ የነፃነት ትግልና በጎንደር የተቀጣጠለዉና ወደሌሎችም የአማራ ክልል አካባቢዎች በፍጥነት የተዛመተዉ የአማራ ሕዝብ የነፃነት ትግል ተሣታፊዎች ያነሷቸዉ መሠረታዊ ጥያቄዎች፣ ያስተላለፏቸዉ መልዕክቶችና ያነገቧቸዉ ታሪካዊ መፈክሮች ጉልህ ምሥክሮች ናቸዉ፡፡ ከዛሬዉ በዝርፊያ ላይ የተመሠረተ የምቾት ኑሯቸዉ ባሻገር ማየት ለተሣናቸዉ ከፋፋይ የወያኔ መሪዎች የሕዝባችን የአብሮነት ስሜት ዱብ ዕዳ እንደሆነባቸዉና ዕረፍትም እንደነሳቸዉ ባለሥልጣን ተብዬዎቻቸዉ በሚቆጣጠሯቸዉ የመገናኛ ብዙሃን እየቀረቡ ከሚያስተላልፏቸዉ የተስፋ መቁረጥ መልዕክቶች በላይ ማረጋገጫ አይኖርም፡፡ ለዚህ ደግሞ ወንድማማች የሆኑትንና የአንዱ ደም የሌላዉም ደም፣ የአንዱ ጥያቄ የሌላዉም ጥያቄ መሆኑን በአደባባይ የገለፁትን የአማራና የኦሮሞ ሕዝቦች “መታረቅ የማይችሉ ባላንጣዎች” አድርጎ ለማሣየት ከመሞከርም አልፎ እነዚህን ሁለት ትልልቅ ሕዝቦች በ“እሳትና ጭድ” አስመስሎ ለመግለፅ የሞከረዉን የወያኔ ባለጊዜ እንደምሳሌ መጥቀስ ይቻላል፡፡
በአጠቃላይ አነጋገር እየተካሄደ ያለዉ የሕዝቦቻችን የነፃነት ትግል በማያሻማ መንገድ ካረጋገጣቸዉ እዉነታዎች አንዱ ኢትዮጵያ በጠመንጃ ኃይል የያዙትን የመንግሥት ሥልጣን ተጠቅመዉ የአገርንና የህዝብን ሃብት ከመዝረፍና ራሳቸዉንና ደጋፊዎቻቸዉን ከማበልፀግ ዉጭ ለአገርም ሆነ ለሚገዙት ሕዝብ በማያስቡና የአገር ህልዉና፣ የዜጎች ሰላም፣ ደህንነትና አንድነት ምንም በማይመስላቸዉ ራስ ወዳድ ግለሰቦች መዳፍ ሥር የወደቀች አገር መሆንዋን ነዉ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦችም ቢሆኑ መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶቻቸዉን በጥቂት ባለጊዜዎች የተገፈፉ፣ እጅግ በጣም ዉስን ለሆኑ የገዢዉ ቡድን አባላትና ደጋፊዎች ምቾት ሲባል ከቤት ንብረታቸዉ እንዲፈናቀሉ ተደርገዉ በዘመናዊ ባርነት ሥር ታፍነዉ የሚገዙ፣ ሰብዓዊ
መብታችንና ነፃነታችን ይከበር ብለዉ ሲጠይቁ ደግሞ ያለምንም ርህራሄ እንዲታሠሩ፣ እንዲሰደዱ ብሎም የሞትን ፅዋ እንዲጎነጩ የተፈረደባቸዉ አሳዛኝ ሕዝቦች መሆናቸዉ የአደባባይ ምስጢር ነዉ፡፡

የወያኔ መሪዎች ታሪክ ይቅር የማይለዉና ወደር የማይገኝለት የጭካኔ ወንጀል በሚገዙት ሕዝብ ላይ እየፈፀሙ ለመሆናቸዉ የሰሞኑ ዘግናኝ ድርጊታቸዉ ጉልህ ማስረጃ ነዉ፡፡ እንደሚታወቀዉ በዜግነታቸዉ ሊኖራቸዉ የሚገባዉን መብት በሰላማዊ መንገድ ስለጠየቁ ብቻ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ዜጎች ወያኔ በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች በከፈታቸዉ ስዉርና ግልፅ የማሰቃያ ማዕከላት የስቃይ ኑሮ እንዲገፉ ተደርገዋል፤ እየተደረጉም ነዉ፡፡ እነዚህ የማሰቃያ ማዕከላት ደግሞ የሕዝብ አለኝታ የሆኑ የፖለቲካ መሪዎችን፣ ታዋቂ ጋዜጠኞችን፣ የእስልምና ሃይማኖት መሪዎችንና ለሕዝቡ የነፃነት ትግል ራሳቸዉን አሳልፈዉ የሰጡ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ ታጋዮችን የያዙ ናቸዉ፡፡ እነዚህ ምርጥ የሕዝብ
ልጆች ከታጎሩባቸዉ የስቃይ ማዕከላት ወጥተዉና ከሚወዱት ሕዝብ ጋር ተቀላቅለዉ የነፃነት አየር የሚተነፍሱበት ቀን ይናፍቀናል፤ ደህንነታቸዉ ደግሞ እጅግ ያሳስበናል፡፡ ይህን የአፈና ሥርዓት ከሥሩ መገርሰስ የትግላችን ዋነኛዉ የትኩረት አቅጣጫ እንዲሆን የተስማማነዉም የዚህ ዓይነቱን የዜጎች ስቃይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማስቀረት ጊዜ የማይሰጠዉ ጉዳይ በመሆኑ ነዉ፡፡

በተለይም የወያኔ መሪዎች ሰሞኑን ያሳዩንን በቅልንጦ እስር ቤት ታጉረዉ በራሳቸዉ የፀጥታ ኃይል አባላት ቁጥጥር ሥር የነበሩ እስረኞችን በአልሞ ተኳሽ ቅልብ ወታደሮቻቸዉ በጥይት አስፈጅተዉ ድርጊታቸዉን ለመሸፈን ደግሞ አስክሬኖችን ከህንፃዎች ጋር በእሳት በማጋየት የወሰዱትን የጭካኔ እርምጃ ስናስብ ይህን ሥርዓት በተባበረ ትግል የመገርሰሱ እንቅስቃሴ ከእስከአሁኖቹ የፖለቲካ አካሄዶቻችን በጣም የተለየና እጅግም የፈጠነ መሆን እንዳለበት ይሰማናል፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ የነፃነት ታጋዮች ከየሥፍራዉ በጅምላ ታፍሰዉ ታስረዉበት የነበረዉ የቅልንጦ እስር ቤት ቃጠሎ ከተሰማ ከአምስት ቀናት በላይ ተቆጥረዋል፡፡ ከአዲስ አበባ በተወሰኑ ኪሎሜትሮች ርቀት ላይ የሚገኘዉ የቅልንጦ እስር ቤት 
የሕወሐት/ኢሕአዴግ መንግሥት ከፍተኛ ጥበቃ ከሚያደርግላቸዉ የንፁሃን ዜጎች ማሰቃያ ማዕከላት (high security prisons) አንዱ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ በዚያ የስቃይ ማዕከል አካባቢ የሚደረጉ ማናቸዉም እንቅስቃሴዎች ከገዢዉ ቡድን የፀጥታ ኃይል አባላት ዕይታ ዉጭ አይደሉም ማለት ነዉ፡፡ ይሁን እንጂ ቃጠሎዉን አስመልክቶ በገዢዉ ቡድን የተሰጠ ይህ ነዉ የሚባል ይፋዊ መግለጫ ካለመኖሩም በላይ ሕዝባችን ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸዉ፣ በስስት ዓይን የሚያያቸዉና የሚሣሣላቸዉ የፖለቲካ እስረኞች ሕይወት በምን ሁኔታ ላይ እንደገሚገኝ ለኢትዮጵያ ሕዝብም ሆነ ለእስረኞቹ የቅርብ ቤተሰቦች በይፋ የተገለፀ ነገር የለም፡፡ በሌላ በኩል ግን የሟቾች ቁጥር ወደ ስልሣ መድረሱ በማህበራዊ መገናኛዎች እየተገለፀ ነዉ፡፡ መንግሥት ነኝ ብሎ ራሱን የሚጠራዉ የጥቂቶች ቡድን በቁጥጥሩ ሥር የነበሩትን ዜጎች ማንነት የሚያዉቅ እንደመሆኑ መጠን የሟቾችን ማንነትና ቁጥራቸዉን ይፋ አለማድረጉም ሆነ በአልሞ ተኳሾች ጥይትም ሆነ በእሳት ቆስለዉ በሕይወት የተረፉትን እስረኞች ለቤተሰቦቻቸዉ አለማሣየቱ “ምን ዓይነት ሚስጢር ለመደበቅ ነዉ?” የሚል ጥያቄ ከማስነሳትም አልፎ ድርጊቱ የተፈፀመዉ በመንግሥት ተብዬዉ የወያኔ ቡድን እዉቅናና ትዕዛዝ መሆኑን ያመለክታል፡፡ ይህ ደግሞ የወያኔ መሪዎችን ሰዉ-በላነትና በጠመንጃ ኃይል ቀጥቅጠዉ ለሚገዙት ያልታደለ ሕዝብ ያላቸዉን ንቀትና ፍፁም ጥላቻ ከማሣየት ዉጭ ሌላ ትርጉም የሚሰጠዉ ጉዳይ አይደለም፡፡

ስለሆነም የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባርና የአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ንቅናቄ የሚከተለዉን ጥሪ ስናቀርብ ሁሉም ወገኖች ጥሪያችንን በቀና መንፈስ በመቀበል የየበኩላቸዉን እርምጃ እንደሚወስዱ በመተማመን ነዉ፡-
1. በኢትዮጵያ ሕዝቦች የተጀመረዉን የነፃነት ትግል አጠናክሮ ከመቀጠልና ወያኔን በማስወገድ ትግሉን በሕዝባዊ ድል ከመደምደም ዉጭ ለአገራችንና ለሕዝቦቻችን የሚበጅ ሌላ አማራጭ የለም፡፡ ስለዚህ እጅግ በሚያረካ መንገድ የተጀመረዉ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አንድነትና በፀረ-ወያኔ ትግል ላይ ከልብ የመተባበር እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡ የሕዝቦቻችን መተባበርና አብሮ መታገል ማለት ለወያኔ መሪዎች ሞት በመሆኑ ወያኔ በአልሞት ባይ ተጋዳይነት አንዳንድ የማስመሰያና የጊዜ መግዣ እርምጃዎችን ሊወስድ እንደሚችል ይጠበቃል፡፡ ከእርምጃዎቹም መካከል፡- አንዱን ሕዝብ በሌላዉ ሕዝብ ላይ ማነሣሣት፣ ሰሞኑን በአንዳንድ የመገናኛ ብዙኃን እንደተሰማዉ የአንዱን ሕዝብ የተወሰኑ ጥያቄዎች “ተገቢ ጥያቄዎች ናቸዉ መፍትሔ ሊሰጣቸዉም ይገባል” በማለት አንዳንድ መለስተኛ የጥገና ለዉጦችን በማድረግ በቆራጥነት የተነሣዉን ሕዝብ ለማለዘብ መሞከር፣ አንዳንድ ታዋቂነት ያላቸዉን የልዩ ልዩ ማህበረሰብ አባላት በመጠቀም የነፃነት ጥያቄ አንግቦ የተነሣዉን ሕዝብ “በብሔራዊ ዕርቅ” ስም ከወያኔ መንግሥት ጋር እንዲስማማ ለማድረግ መሞከር፣ እና ሌሎችንም የማዘናጊያ እርምጃዎች መጥቀስ ይቻላል፡፡ እነዚህ ሁሉ የማዘናጊያ አቀራረቦች ከምንም በላይ “እምቢ ለነፃነታችን” ብለዉ የተነሡትን ሕዝቦቻችንን በቆራጥነት ለጀመሩት የነፃነት ጥየቄ ተገቢ ምላሽ ለማግኘት ጠንክረዉ ከመታገል ሊያቆሟቸዉ አይገባም እንላለን፡፡ በአጠቃላይ የወያኔ ገዢ ቡድን ከሥልጣን መወገድና በትክክለኛ ዲሞክራሲያዊ መንገድ በሚመሠረት የመንግሥት ሥርዓት መተካት ለምንም ዓይነት ድርድር የማይቀርብ የመጨረሻ ግባችን መሆኑን ለአፍታ እንኳን ሳንዘነጋ ትግላችንን የበለጠ አጠናክረን መቀጠል እንደሚገባን ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡
2. የወያኔ ገዢ ቡድን ከሚታወቅባቸዉ መሠሪ ባህሪያት አንዱና ዋነኛዉ አንዱን ሕዝብ የሌላዉ ሕዝብ ጠላት አድርጎ የማቅረብና በሕዝቦች መካከል ምንም ዓይነት መተማመን እንዳይኖር ለማድረግ መሞከር ነዉ፡፡ ይህን ዘዴ ደግሞ በአንዳንድ አጎራባች የኦሮሚያና የደቡብ ሕዝቦች፣ የኦሮሚያና የሶማሌ ሕዝቦች፣ ወዘተ መካከል ተጠቅሞበታል፡፡ ይኸዉም ሆን ብሎ የድንበር ግጭቶችን በማነሣሣትና አንዱን ወገን አስታጥቆ ሌላዉን እንዲያጠቃ በማድረግ ቀጥሎም ራሱን አስታራቂ ዳኛ አድርጎ በመሰየም “የኢሕአዴግ ሥርዓት ከሌለ አገር ሰላም ሆና ልትቀጥል አትችልም” የሚል ልብ-ወለድ ስሜት እንዲፈጠር ሰፊ የተንኮል ሥራ በተለያዩ ማህበረሰቦች መካከል ሲሠራ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ ሕወሐት ለመሠሪ ዓላማዉ ዛሬም ይህን አያደርግም ማለት አንችልምና ሕዝባችን ተገቢዉን ጥንቃቄ ሁሉ እንዲያደርግ አበክረን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡ በተለይም ላለፉት ሃያ-አምስት ዓመታት የኢትዮጵያን መንግሥት ሥልጣንና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ቁልፍ የኃላፊነት ቦታዎች በበላይነት የተቆጣጠሩት የሕወሐት መሪዎች፣ አባላትና ደጋፊዎች የሚቀርቡባቸዉን ተገቢነት ያላቸዉ ቅሬታዎችና የሕዝቦችን የመብት ጥያቆዎች ሳይቀር ሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች በትግራይ ሕዝብ ላይ እንደሕዝብ የሚያነሱት “የትግሬ ጥላቻ” የወለዳቸዉ ጥያቄዎች ለማስመሰል ሲሞክሩ ታይተዋል፤ አሁንም በተለያዩ መንገዶች ይህንኑ ለማድረግ ሲሞክሩ ይታያሉ፡፡ የወያኔ መሪዎች ከዚህም አልፈዉ በመሄድ እነሱ በሥልጣን ላይ ከሌሉ የትግራይ ሕዝብ እጅግ ለከፋ ችግር እንደሚዳረግ (በሌላ አባባል እነሱ አሁን በሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ እያደረሱ ያሉት ዓይነት የጭካኔ እርምጃ እንደሚወሰድበት) አድርገዉ ለማሣየት ይሞክራሉ፡፡ እዉነታዉ ግን ከዚህ በጣም የራቀ ነዉ፡፡ የትግራይ ሕዝብ የዛሬዎቹ የወያኔ መሪዎች ከመፈጠራቸዉ በፊት ከኢትዮጵያዉያን ወገኖቹ ጋር ለብዙ ዘመናት በአንድ የጋራ አገር ዉስጥ በሰላም፣ በፍቅር፣ በመተሳሰብና በወንድማማችነት አብሮ የኖረ ሕዝብ ነዉ፡፡ ላለፉት ሃያ-አምስት ዓመታት የታዩት የወያኔ መሪዎች ጭፍን ተግባራት ሕዝቦቻችንን ክፉኛ አለያይተዉ አራራቁ እንጂ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ፣ ከመሃል እስከ ጠረፍ በኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል እንደ ሕዝብ የመጠላላት ወይም በጠላትነት ስሜት የመተያየት ሁኔታ ኖሮ አያዉቅም፡፡ ስለሆነም አሁን በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች እንዲሁም በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች እየተካሄዱ ያሉት ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች የትግራይን ሕዝብ ጭምር ከጥቂት የወያኔ ባለጊዜዎች አፈናና ጭቆና የሚያላቅቁ የነፃነት ትግሎች ናቸዉ፡፡ አስር ወራትን ያስቆጠረዉ የኦሮሞ ሕዝብ ትግልና በጎንደር የተጀመረዉ የአማራ ሕዝብ ፀረ-ወያኔ ትግል የአንዳንድ የትግራይ ተወላጆችን ድጋፍ ያገኘዉም በኢትዮጵያ ሕዝቦች እየተካሄደ ያለዉ የነፃነት ትግል የወያኔ መሪዎች ለማስመሰል እንደሚሞክሩት “የትግሬ ጥላቻ” የወለደዉ ጭፍን እንቅስቃሴ ባለመሆኑ ነዉ፡፡ ስለዚህ እየተካሄደ ያለዉ ትግል ሁሉንም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ለነፃነት የሚያበቃ ፍትሃዊ ትግል መሆኑ ታዉቆ የትግራይን ጭቁን ሕዝብ ጨምሮ ሁሉም ነፃነት ፈላጊ ወገኖች በንቃት እንዲሳተፉበት የጋራ ጥሪያችንን ደግመን ደጋግመን እናቀርባለን፡፡
3. ከምናያቸዉና ከምንሰማቸዉ የዕለት-ከዕለት ድርጊቶች እንደምንረዳዉ አገራችን እጅግ አደገኛ ወደሆነ ሁኔታ እየሄደች ነዉ፡፡ ይህን አደገኛ ሁኔታ መለወጥ የማንችል ከሆነ ደግሞ የኢትዮጵያ ህልዉና ጥያቄ ዉስጥ የሚገባበት ጊዜ ሩቅ ላይሆን ይችላል፡፡ ይህን አገራዊ ጥፋት በአንድ ወገን የተናጠል ጥረት ብቻ ማስቀረት አይቻልምና የሀገራችን ጉዳይ ያገባናል የምንል ወገኖች ሁሉ የየበኩላችንን ድርሻ መወጣት ይኖርብናል፡፡ በአሁኑ ወሳኝ ወቅት በተለያዩ መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች ዉስጥ በልዩ ልዩ ሙያዊም ሆነ ፖለቲካዊ ኃላፊነቶች ላይ የሚሠሩ የሲቪልና የልዩ ልዩ ወታደራዊ ክፍሎች አባላትም የዚያች አገር ጉዳይ ከሚያገባቸዉ ወገኖች መካከል እንደሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ስለዚህ አሁን በሥልጣን ላይ ካለዉ የወያኔ/ኢሕአዴግ መንግሥት ጋር በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎችና የሥራ ድርሻዎች ላይ የምትሠሩና ከሕዝቡ ወገን ለመሠለፍ የሚያግዳችሁ ምንም ዓይነት የወንጀል ድርጊት በሕዝብ ላይ ያልፈፀማችሁ ሲቪል የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም የአገር መከላከያና የፖሊስ ሠራዊት አባላት የምታገለግሉት ሥርዓት አገሪቱን ወደጥፋትና ወድቀት እየወሰዳት መሆኑን ተረድታችሁ ከተሣሣተ የታሪክ ጎራ በመዉጣት ለነፃነት የሚደረገዉን ሕዝባዊ ትግል እንድትቀላቀሉ ጥሪያችንን እናቀርብላችኋለን፡፡
4. ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃነትና የዲሞክራሲ መብት መከበር በየፊናችሁ የምትታገሉ የወያኔ/ኢሕአዴግ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ሁሉ ያለፉት ሃያ-አምስት ዓመታት የተናጠል ጉዟችን ምንም ያህል ርቀት እንዳላስኬደንና የምንፈልገዉን ዉጤት ለማግኘት እንዳላስቻለን ተረድታችኋል ብለን እናምናለን፡፡ ስለሆነም ያለፉት ሃያ-አምስት ዓመታት ዉጤት-አልባ ሂደቶቻችንን ላለመድገም ይልቁንም ካለፉት ስህተቶቻችን ተምረን ወደምንፈልገዉ ግብ ለመድረስ የሚያስችለንን ተግባራዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ ይቻል ዘንድ ተቀራርበን በመነጋገር በተቃዉሞዉ ጎራ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶችን ሁሉ ያካተተና ሰፊ መሠረት ያለዉ ዲሞክራሲያዊ ትብብር ለመመሥረት የተጀመረዉን ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ተባብረን እንድናሰፋ ጥሪያችንን እናቀርብላችኋለን፡፡
ነፃነትና ፍትሕ ለሁሉም!!
የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር እና የአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ
ጳጉሜ 2008 ዓ. ም.
ኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባርና ከአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ የወቅቱን የኢትዮጵያ ሁኔታ በማስመልከት የተሰጠ መግለጫና ለሁሉም ነፃነት ፈላጊ ወገኖች የቀረበ ጥሪ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ለነፃነት፣ ለፍትህ፣…
OROMODEMOCRATICFRONT.ORG

No comments:

Post a Comment