Wednesday, September 7, 2016

የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ የሚሰጠው የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ እንዲቋረጥ ወሰነ ኢሳት (ጳጉሜ 2 ፥ 2008)



የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ መንግስት ይፈጸማል ያለውን ግድያና የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመቃወም ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ እንዲቋረጥ መወሰኑን ረቡዕ ይፋ አደረገ። 
ህብረቱ ባለፈው አመት ያቋቋመው ልዩ የአስቸኳይ ጊዜ የገንዘብ ድጋፍ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለሌሎች የአፍሪካ ሃገራት በሚሊዮን የሚቆጠር ዩሮ ገንዝብ ድጋፍ ለማድረግ ያለመ እንደነበር ህብረቱ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል። 
ይሁንና፣ በኢትዮጵያ መንግስት እየተፈጸመ ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ህብረቱ ኢትዮጵያን ከአስቸኳይ ጊዜ የገንዘብ ድጋፍ እንድትወጣ ምክንያት መሆኑን ኢውሮ አክቲቭ የተሰኘ መጽሄት የአውሮፓ ህብረትን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል። 
የኢትዮጵያ መንግስት ህብረቱ በሚሰጠው ልዩ የአስቸኳይ ጊዜ የገንዘብ ድጋፍ ከፍተኛ ድርሻን ተሰጥቷት እንደነበር ያወሳው የአውሮፓ ህብረት በአሁኑ ወቅት በሃገሪቱ ያለው የሰብዓዊ መብት ረገጣና የሰላማዊ ሰዎች ግድያ ድጋፉን እንዳታገኝ ማድረጉን ገልጸዋል። 
የህብረቱ ባለስልጣናት ለኢትዮጵያ ሊሰጥ የነበረው ድጋፍ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እንዲቀር መደረጉን ለኢሮ አክቲቭ መጽሄት አስረድተዋል። የኢትዮጵያ ዋነኛ የልማት አጋራት የሆነው የአውሮፓ ህብረት በሃገሪቱ እየተካሄዱ ያሉ ህዝባዊ ተቃውሞዎችና የፖለቲካ ሁኔታዎች በቅርቡ እየተከታተለ እንደሆነ ገልጾ፣ በከፍተኛ የህብረቱ ባለስልጣናት ዘንድ ጉዳዩ ለኢትዮጵያ መንግስት ተወካዮች መቅረቡን አክሎ አስታውቋል። 
የአውሮፓ ፓርላማ ባለፈው አመት በጸደቀው የውሳኔ ሃሳብ የአውሮፓ ህብረት ከኢትዮጵያ በሚሰጠው ድጋፍ ላይ የማስተካከያ እርምጃን እንዲወሰድ ውሳኔ ማስተላለፉ ይታወሳል። 
በኦሮሚያ ክልል እየተፈጸመ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ግድያ የኮነነው የህብረቱ የፓርላማ ቡድን በመንግስት ተፈጽመዋል ያላቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በገለልተኛ አካል ማጣራት እንዲካሄድበት መጠየቁም ይታወቃል። 
በአማራና በኦሮሚያ ክልል ለወራት የዘለቀውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የአሜሪካ መንግስትን ጨምሮ የአውሮፓ ህብረትና የተለያዩ አለም አቀፍ አካላት መንግስት የሃይል እርምጃን ከመውሰድ እንዲቆጠብ በማሳሰብ ላይ ናቸው። 
ይሁንና፣ የአውሮፓ ህብረት እየተፈጸሙ ያሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በማውገዝ ከሃገሪቱ የሚሰጥ የአስቸኳይ ጊዜ የገንዘብ ድጋፍ እንዲቋረጥ ሲወሰን የመጀመሪያ የኢትዮጵያ አጋር ሆኗል። 
ህብረቱ እንዲቋረጥ የወሰነው ይኸው የአስቸኳይ ጊዜ የገንዘብ ድጋፍ እስከመቼ ድረስ ሊቆይ እንደሚችል የሰጠው ዝርዝር መረጃ የሌለ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግስት እስካሁን ድረስ የሰጠው ምላሽ የለም።

No comments:

Post a Comment