Sunday, September 18, 2016

ውድ ያገራችን ጀግኖች ለነጻነታችሁ የምታደርጉት ተጋድሎ ወደር የማይገኝለት መሆኑን ስንነግራችሁ በኩራት ነው። ይህን ተጋድሎአችሁን በጠመንጃ ሃይል ለማፈን የወያኔ አገዛዝ የሚወስደው ፋሽስታዊ እርምጃ አልበቃ ብሎት፣ አሁን ደግሞ የስነ ልቦና ዘመቻ ከፍቶባችኋል። አባቶቻችሁን ፣ እናቶቻችሁን፣ ወንድሞቻችሁንና እህቶቻችሁን በየመድረኩ እየጠራ እናንተን እንዲያወግዙ እየስገደደ ነው። አድሎአዊነትና ኢፍትሃዊነት አንገሽግሾአችሁ ያቀጣጠላችሁትን የነጻነት ትግል ለማራከስ፣ ታሪካችሁን ለማቆሸሽ ላይና ታች እያለ ነው። የእናንተ ታሪክ ግን እንደ ገዳዮቻችን ታሪክ የሚቆሽሽ አይደለም። ማንም ምን ቢል የእናንተ ስራ ወደር የማይገኝለት ዘለላም ለትውልድ ሲተላለፍ የሚኖር ነው። የእናንተ ትግል ለራሱ ክብርና ነጻነት የሚቆጭ የሰው ልጅ ሁሉ ሊያደርገው የሚገባ እውነተኛ ትግል ነው። ለዚህ ነው የህይወት መስዋትነት ቢከፈልበት የሚያንስበት እንጅ ከቶውንም የሚበዛበት የማይሆነው ። በዚህ ወሳኝ የታሪክ ወቅት ለራሳችሁ፤ ለወገናችሁና ለአገራችሁ ስትሉ ከጨካኝ ሥርዓት ጋር ግብግብ ገጥማችሁ በምትከፍሉት መስዋዕትነት የአሁኑ ብቻ ሳይሆን የሚመጣውም ትውልድ እንደሚኮሩባችሁ አትጠራጠሩ። የህወሃት ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ የጭቆና ዘመኑን ለማራዘም ዛሬ በወላጆቻችሁ ላይ የፈለገውን ጫና ቢፈጥር እናቶቻችሁና አባቶቻቸሁ ለምን ወለድኩት፣ ለምን ወለድኳት ሳይሆን እንኳንም ወለድኩት እንኳንም ወለድኳት ብለው ገድላችሁን የሚዘክሩበትና በናንተ ጀግኖች ልጆቻቸው መስዋዕትነት የሚኮሩበት ወቅት ሩቅ አይሆንም ። ውድ ያገራችን ልጆች የእስከዛሬው የሰው ልጆች ታሪክ እንደሚመሰክረው በምድር ላይ ለነጻነት የሚደረግን ትግል ያክል ክቡር ዋጋ የሚያወጣ ነገር የለም። ዛሬ ነጻነታቸውን ያገኙ አገሮች፡ አሁን የሚሳሱለትን ነጻነት ለማግኘት ከፍተኛ የህይወት መስዋትነት ከፍለዋል፤ ዛሬም በተለያዩ የአለም ክፍሎች የህይወት መስዋትነት የሚከፍሉ ጀግኖች አሉ። እናንተም ከእነዚህ ጀግኖች አንዱ ሆናችኋልና ድስ ሊላችሁና ልትኮሩ ይገባል። በአረሜኔው የአጋዚ ጦር በየአደባባዩ የሚፈሰው የእናንተ ደም ኢትዮጵያ አገራችሁንና ላለፉት 25 አመታት በዘረኞች የባርነት ቀንበር ሥር እየማቀቀ የሚገኘውን ወገናችሁን አርነት የሚያወጣ መሆኑን ፍጹም አትጠራጠሩ። ። እናት አገራችን ኢትዮጵያ እናንተን በብዙ ምጥ ወልዳለችና ፣ እናንተም በነጻነት መልሳችሁ ልትወልዷት ደማችሁን እያፈሰሳችሁላት እንደሆነ ሁሌም አትዘንጉት ። ውድ ያገራችን ልጆች እየከፈላችሁት ያለው የህይወት መስዋዕትነትና እየፈሰሰ ያለው ደማችሁ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የገዥዎቻችን መሣሪያ በመሆን ደማችሁን እያፈሰሱ ያሉትን ሳይቀር ነጻ ያወጣቸዋል። ደማችሁ ከገዳዮቻችሁ ደም በላይ ወፍራም ነውና ፤ ሞታችሁ ከገዳዮች ህይወት በላይ ዋጋ አለው። ለነጻነት ሲባል በምትከፍሉት መስዋዕትነት እናንተ በህይወት ባትኖሩም ህያው ናችሁ፣ እነሱ ግን በህይወት እየኖሩ በቁም የሞቱ ናቸው። ደማችሁን እያፈሰሳችሁ ያላችሁ ሁሉ፣ እስካሁን ለፈጸማችሁትም ሆነ ለወደፊት ለምትፈጸሙት ገድል እጅግ ከፍተኛ ክብር ይገባችሁዋል። በአገራችን ነጻነት እውን እስኪሆን የጥይቱንም የፕሮፓጋንዳውንም ናዳ ተቋቁማችሁ ትግላችሁን ዳር እንደምታደርሱ ኢትዮጵያ ታምናለች። እናንተን እንዲገድሉ ከታዘዙት ወታደሮች መካከል አንዳንዶች የአለቆቻቸውን ትእዛዙ በመጣስ ከእናንተ ጎን ቆመዋል። የመግደያ መሳሪያቸውን እየጣሉ የእናንተን ፈልገ ተከትለዋል። ኢትዮጵያ በእነዚህ ወታደሮች ድርጊት ኮርታለች። ለወደፊቱም ብዙ ወታደሮች እንደሚቀላቀሉዋችሁ ልንነግራችሁ እንወዳለን። አሸናፊነትን እየተቀናጃችሁ በሄዳችሁ ቁጥር የዳር ተመልካቾችና ተሸናፊዎች ወደ እናንተ ይመጣሉ። ምን ጊዜም ከናንተ ጋር የሆነው ንቅናቄያችን አርበኞች ግንቦት 7 አፈሙዛቸውን ማስታገስ ተስኖአቸው በናንተ የነጻነት ቀንድሎች ላይ የጭካኔ እጃቸውን ለሚሠነዝሩት የወያኔ ጀሌዎች እና አዛዦቻቸው መምከርም ማስጠንቀቅም የሚፈልገው ነገር አለ ። ጀግኖቻችን በዚህ የለጋ እድሜያቸው ደማቸውን የሚያፈሱት እናንተንም ነጻ ለማውጣት ነው። እናንተ የእነሱን ደም ማፍሰሳችሁን በቀጠላችሁ ቁጥር፣ ህይወታችሁንም ሞታችሁንም እያራከሳችሁት ትሄዳለችሁ። እስካሁን ያረከሳችሁት ይበቃል፤ ከዚህ በሁዋላ ግን በእርኩሰት ላይ እርኩሰት አትጨምሩ። ልብ በሉ! ህዝብን ያሸነፈ ሃይልና ጉልበት በየትኛውም ዘመን ኖሮ አያውቅም ! ወደፊትም አይኖርም ! በህዝብና የአገር ሃብት ዘረፋ ልባቸው ያበጠው አልቆቻችሁ ይህንን ሃቅ መረዳት ተስኖአቸው እናንተን በገዛ ወገኖቻችሁ ላይ አዝምተዋችኋል። እናንተ ግን ከህዝብ አብራክ የወጣችሁ ያገሪቱ መከላኪያ ሠራዊት ፤ የፖሊስና የደህንነት አባላት እንጂ ለጥቂት ባለሥልጣናት የሥልጣን ዕድሜ ማራዘሚያ በወገኖቻችሁ ላይ ጭፍጨፋ ለማካሄድ የተቀጠራችሁ የባዕድ ቅጥረኞች /mercenaries / አይደላችሁም። ስለዚህ በእብሪትና በጥጋብ ተወጥሮ በገዛ ወገናችሁ ላይ ያዘመታችሁን የህወሃት ጦር አዛዦች ትዕዛዝ አትቀበሉ። የአገር ዳር ድንበር ከውጭ ወረራ ለመከላከል እንጂ ፍትህ የሚጠይቀውን ወገኔን ለመግደል አልተቀጠርኩም በላቸው! የተሸከምከው ጠመጃና የታጠከው ጥይት የገዛ ወንድሞችህን ለመግደል እንዳልሆነ ንገራቸው። እምቢ ካሉ ለአንተና ለልጆችህ ነጻነት ጭምር ከሚታገሉ የአገርህ ልጆች ጎን ለመሰለፍ ህዝቡን ተቀላቀል! የህዝብ አለኝታነትህንና ወገናዊነትህን በተግባር አረጋግጥ ! ይህ ሳይሆን ከቀረ ነገ የአሸናፊነቱ ደወል ሲደወል ዛሬ ደማቸውን በምታፈሳቸው እምቡጦች ጫማ ስር ትወድቃለህ ። ስለዚህ ወቅቱ ሳይዘገይ ሚናህን ለይና ከህዝብ ጎን ቁም! የህዝብ ጥሪ ተቀብለህ ከህዝብ ጎን ከቆምክ ፣ ህዝብ ከጎንህ ይቆማል። የአገሬ ልጅ ሆይ የጠመንጃህን አፈሙዝ በገዢዎቻችን ላይ አዙር! ካልሆነልህ ደግሞ መሳሪያህን ጥለህ ራሳህን ከገዳዮች ጎሬ ለይ! ህዝብ አንቅሮ የተፋውን የህወሃት አገዛዝ ዕድሜ ለማራዘም በወገን ላይ ጦርነት ያወጃችሁ የሥርዓቱ ቅምጥሎችም አፈሙዙን ሰከን አድርጋችሁ በጊዜ ከነጻነት ሃይሎች ጎን እንድትሰለፉ ካልሆነም የግድያ ትእዛዝ ከመስጠት ራሳችሁን እንድታርቁና አርበኞች ግንቦት 7 ወገናዊ ጥሪ ያቀርብላችኋል። ህዝባችን ለነጻነቱ የሚከፍለው መስዋዕትነት እንዲራዘም የሚደረግ ማንኛውም ሃላፊነት የጎደለው እርምጃ ይዋል ይደር እንጂ በህግም በታሪክም የሚያስጠይቅ መሆኑን ለአፍታም አትዘንጉ ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!! የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ ርዕሰ አንቀጽ

No comments:

Post a Comment