Monday, September 5, 2016

ኢህአዴግ “እታደሳለሁ” ማለቱን ተቃዋሚዎች አጣጣሉት

“መንግሥት የሀገሪቱን መሰረታዊ ችግር አልተገነዘበም”

   የሰሞኑ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ መግለጫ፤ የወቅቱን የሀገሪቱን ችግሮች በአግባቡ የፈተሸና ለውጥ ሊያመጣ የሚችል አለመሆኑን የገለፁት ተቃዋሚዎች፤ በሀገሪቱ በተከሰቱት ችግሮች ዙሪያ ያስቀመጧቸውን የመፍትሄ ሃሳቦች ከግምት ውስጥ ያስገባ የሰጠ አይደለም ብለዋል፡፡ 
መንግስት የአገሪቱን መሰረታዊ ችግር ባለመገንዘቡ፣ አሁንም መፍትሄ ለማምጣት ቁርጠኛ አለመሆኑን ከተሰጠው መግለጫ መረዳታቸውን ተቃዋሚ ፓርቲዎች አስታውቀዋል፡፡ 
በሀገሪቱ በተለይ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ለተፈጠሩት ችግሮች መፍትሄው ውይይትና ብሄራዊ እርቅ ማካሄድ ብቻ እንደሆነ ሲወተውቱ መቆየታቸውን የጠቆሙት ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ፤ መንግስት የመፍትሄ ሃሳቦቹን አለመቀበሉን እንዳልተቀበላቸው ከመግለጫው አረጋግጠናል ብለዋል፡፡ 
“ኢህአዴግ እታደሳለሁ ማለቱ ጊዜውን ያልጠበቀ ነው፤ ከዚህ በኋላ ቢታደስም ለውጥ አያመጣም” ሲሉ ፓርቲዎቹ የተሃድሶ ፕሮግራሙን ነቅፈውታል። 
የኢዴፓ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደ፤ በሀገሪቱ ለተፈጠሩ ተቃውሞና ግጭቶች የብሄራዊ መግባባትና እርቅ ማካሄድ መፍትሄ እንደሆነ ፓርቲያቸው በተደጋጋሚ ሲያሳስብ እንደነበር አስታውሰው፤ መንግስት እንደተለመደው ማሳሰቢያዎቹን ችላ ማለት ውጤቱ የከፋ ነው ብለዋል፡፡ 
ኢዴፓ፤ የግጭት መንስኤዎች እንዲጠኑ፣ የኃይል እርምጃ እንዲቆም በተደጋጋሚ መጠየቁን የጠቀሱት ዶ/ር ጫኔ፤ መንግስት የመፍትሄ ሃሳቦቹን ያልተቀበለው አሁንም በጉልበት ሰላም አሰፍናለሁ የሚል አቋም በመያዙ ነው ብለዋል። “የኢህአዴግ የሰሞኑ መግለጫ የህዝብን ቁጣ የሚያባብስ ነው” ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ መንግስት የተፈጠሩትን ችግሮች ለመፍታት ዝግጁ እንዳልሆነ ለመገንዘብ መቻላቸውን ገልፀዋል፡፡ “ኢህአዴግ ለህዝብ ተቃውሞዎች መንስኤ የሆኑ ጉዳዮችንም በአግባቡ አልተረዳም” ያሉት ዶ/ር ጫኔ፤ “ምላሹ ለተቃውሞው የሚመጥን ያልሆነው ለዚህ ነው” ሲሉ አስረድተዋል፡፡ 
አንድ ፓርቲ “እታደሳለሁ” ሲል ሚኒስትሮችን ከስልጣን ማንሳት ሳይሆን የፖሊሲ ለውጥ እንዲያደርግ ነው የሚጠበቀው፤ ኢህአዴግ ይሄን ለማድረግ ፈቃደኛ አይመስለኝም ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ አሁን የተፈጠሩት ችግሮች ግን በፓርቲው መታደስ ብቻ የሚቀረፉ አይደሉም ብለዋል፡፡ 
ሰማያዊ ፓርቲ በበኩሉ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ የሰጧቸው መግለጫዎች፤ ችግሩን በጥልቀት አለመገንዘባቸውንና መፍትሄ አለማስቀመጣቸውን ያረጋግጣሉ ብሏል፡፡ መንግስት ችግሮቹን በሰላም ከመፍታት ይልቅ በኃይል ለመቆጣጠር ጥረት እንደሚያደርግ ገልጿል ያሉት የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ነገሠ ተፈረደኝ፤ ወታደሩ እርምጃ እንዲወስድ መታዘዙ ለፖለቲካ ችግር ፖለቲካዊ መፍትሄ ለመፈለግ መንግስት ቁርጠኛ አለመሆኑን ያስገነዝባል ብለዋል፡፡ 
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የሚሊዮኖችን ተቃውሞ 300 እና 400 ሰዎች የሚረብሹበት ነው ማለታቸው በኢህአዴግ በኩል እውነታውን ላለመቀበል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ይጠቁማል - ብለዋል ምክትል ፕሬዚዳንቱ፡፡ 
ኢህአዴግ ከዚህ በኋላ ጥገናዊ ለውጥ ቢያደርግም በህዝብ ተቀባይነት አግኝቶ ለመቀጠልና ለውጥ ለማምጣት እንደሚቸገር አቶ ነገሰ ጠቁመው፤ ለውጥ ሊያመጣ የሚችለው ብቸኛ መፍትሄ፣ የህዝብ መንግስት ማቋቋም የነበረ ቢሆንም አሁን የህዝቡ ጥያቄ ከዚህም አልፎ ሄዶ “የስልጣን ልቀቅ” የሚል ሆኗል ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም በውጭም በውስጥም ያሉ ተቃዋሚዎች፣ ራሡን ኢህዴግን ጨምሮ እንዲሁም የሃይማኖት አባቶችንና የሃገር ሽማግሌዎችን ያካተተ ህዝባዊ መንግስት መቋቋም አለበት ይላሉ፤ አቶ ነገሠ፡፡ “ህዝባዊ መንግስት መቋቋሙ አንዱ ተሸናፊ ሌላው አሸናፊ፤ አንዱ ጨቋኝ ሌላው ተጨቋኝ እንዳይሆን ያደርጋል” የሚሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፤ ህዝባዊ መንግስት መመስረት ብቸኛው አማራጭ ነው ባይ ናቸው፡፡
የመኢአድ ፕሬዚዳንት ዶ/ር በዛብህ ደምሴ በበኩላቸው፤ የጠ/ሚኒስትሩ መግለጫ መንግስት የፓርቲያቸውን የመፍትሄ ሃሳቦች እንዳልተቀበለ አስገንዝቦናል ብለዋል፡፡ የህዝቡን ችግርና ብሶት በተገቢው መልኩ ያልተረዳ፤ መፍትሄም ያላስቀመጠ የተለመደ አይነት መግለጫ ነው ሲሉም አጣጥለውታል፡፡
‹‹የችግሩ መፍትሄ የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ አካላትን ማወያየት ነው›› የሚል አቋም ፓርቲያቸው ሲያንፀባርቅ መቆየቱን የጠቀሱት ዶ/ር በዛብህ፤ መንግስት ለማወያየትም ሆነ ስልጣንን ለማጋራት ድፍረቱ እንደሌለው አረጋግጠናል ብለዋል፡፡ አሁን መንግስት እያስቀመጠ ያለው ጊዜያዊ ማስታገሻ እንጂ መሠረታዊውን ችግር ለመፍታት የተቀመጠ አቅጣጫ እንደሌለ የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ፤ ኢህአዴግ ከዚህ በኋላ በህዳሴ ወይም በጥገናዊ ለውጥ ይሻሻላል ወይም የተፈጠሩትን ችግሮች ይፈታል የሚል እምነት እንደሌላቸው ገልፀዋል፡፡ 
መድረክ ፓርቲ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ ‹‹የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ነው›› ብሏል፡፡ የኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበርና የመድረክ አመራር አባል አቶ ሙላቱ ገመቹ፤ መግለጫው ሃገሪቱ አሁን ያለችበትን ሁኔታ ያልተረዳና ሚዛን የማይደፋ ነው ብለዋል፡፡ “በሁሉም ቦታ አመፁን ተቆጣጥረናል፤ አሁን ሠላም ነው” ማለታቸውን በመጥቀስም፤ ይሄ ከእውነታው ጋር የሚቃረን ነው ብለዋል፡፡ 
ጠ/ሚኒስትሩ፤ የወልቃይት-ጠገዴ ጉዳይ በሁለት ክልሎች መፈታት ነበረበት ማለታቸውን የነቀፉት አቶ ሙላቱ፤ የኮሚቴው አባላት ለበርካት ጊዜያት በየክልሎቹ መመላለሳቸውን ብቻ ሳይሆን ወደ ፌደሬሽን ም/ቤት ለማመልከት ሲመጡ መታሰራቸውንም ጭምር እንደሚያውቁ ጠቁመው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሄን ሃቅ መካዳቸው አግባብ አይደለም” ብለዋል፡፡ 
መድረክ ፤የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም ሲጠብቅ እንደነበር የተናገሩት አቶ ሙላቱ፤ ጥገናዊ ለውጥ የትም አያደርስም፤ ኢህአዴግ የችግሩን ሁኔታ በአግባቡ የተረዳ አይመስለኝም ሲሉ ተችተዋል፡፡ 

No comments:

Post a Comment