Monday, September 5, 2016

አነጋጋሪው የፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ መጽሐፍ ምጥን ዳሰሳ



- የኦሮሞና የአማራ ህዝብ በደምና ስጋ ብቻ ሳይሆን በባህል፣ በኅሊናና በመንፈስ ዳቅሏል፤ ተዋህዷል
· አንዳንዶች፤ ‹‹አፄ ምኒልክ ጡት ቆረጡ፤ 5 ሚሊዮን ኦሮሞ ገደሉ›› እያሉ የሚነዙት የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ነው
· አማራውን እወክላለሁ ብሎ ያወጀ ንጉሠ ነገስትስ ይኖር ይሆን?

-

   ነዋሪነታቸው በአሜሪካ የሆነው ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ጂግሳ፤ በቅርቡ የኦሮሞ የአማራና የተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ እውነተኛና ትክክለኛ የዘር ምንጭ ምን እንደሆነ ከ5ሺ ዓመታት በላይ ወደኋላ ተጉዘው፣ ማስረጃ አስደግፈው፣ ምንጭ ጠቅሰው፣ እስካሁን ድረስ የምናውቀውን የኢትዮጵያን ታሪክ የሚሽር፣ አዲስ የኢትዮጵያ ታሪክ በዝርዝርና በጠራ አቀራረብ የሚገልጽ ድንቅ መጽሐፍ አቅርበዋል፡፡ እስካሁን የነበረውን ታሪክ ከስር መሰረቱ ገለባብጦ፣ በአዲስ ታሪክ የሚተካ መጽሐፍ አግኝቼና አንብቤ አላውቅም፤ስለዚህም በጉጉት ነው ያነበብኩት፡፡  

ደራሲው ከኦሮሞና አማራው እውነተኛ የዘር ምንጭ በተጨማሪ ትርጉማቸው በትክክል ለማይታወቅ፣ አደናጋሪና አሳሳች ለሆኑ በርካታ ርዕሰ ጉዳዮች፣ በመረጃ አስደግፈው ትክክለኛ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ለአብነት ያህል ሐበሻ ማለት ምንድነው? ሀበሻ የሚለው ቃል እንዴት መጣ? እውነት ኢትዮጵያውያን ሀበሻ ናቸው? ትርጉሙስ አዎንታዊ? ወይስ አሉታዊ? አማራ መላ ኢትዮጵያን የገዛ ስርወ መንግስት ነበር? ንግስተ ሳባ በእርግጥ በኢትዮጵያ ምድር የኖረች ናት? ወይስ አፈ-ታሪክ? ለኦሮሞ ቋንቋ ምቹና  አመቺው የላቲን ፊደላት ወይስ የግዕዝ? ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ምን አይነት ሰው ነበሩ? እውነት ጡት ቆርጠዋል? አስቆርጠዋል? 5 ሚሊዮን ኦሮሞዎችንስ ፈጅተዋል? ደራሲው መልስ አላቸው፡፡
የዚህ ዳሰሳ፣ ዓላማ በአንዳንድ ነጥቦች ላይ አፅንኦት መስጠት ነው፡፡ በእርግጥ አንዳንድ ታሪኮች ልብ ወለድ ወይም አፈ ታሪክ ይመስላሉ፡፡ ለምሳሌ የኦሮሞና የአማራ እንዲሁም የመላው ኢትዮጵያውያን አባት የሆነውና ፈላስፋው ደሼት (ደሴት) አፈጣጠር፣ ደሼት ከክርስቶስ ልደት 1400 ዓመታት በፊት ወንዝ እያየ ሲመሰጥ፣ በውሃው አረፋ ላይ የማርያምን፣ የኢየሱስንና የተወላጆቹን ወደ ቤተልሔም የመራቸውን ኮከብ ምስል ማየቱ፣ በማስረጃ ተደግፎ ቢቀርብም አምኖ መቀበል ግን ያስቸግራል፡፡ እነዚህን ነጥቦች በቦታቸው አነሳቸዋለሁ፡፡
ደራሲው አዲሱን የኢትዮጵያ ታሪክ ሲጽፉ በማጣቀሻ ዋቢነት የተጠቀሟቸው ምንጮች፤ በመጽሐፍ መደብሮች በሚገኙ የአማርኛና እንግሊዝኛ ሥነ - ጽሑፎች እንደሆነ፣ ከእነዚህ ጽሑፎች ውስጥ ሱዳን ኑቢያ ጀበል ኑባ በተባለ ስፍራ በአንድ የኢትዮጵያ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲን ፍርስራሽ አጠገብ ተቀብረው ከዛሬ 50 ዓመት በፊት መራሪስ አማን በላይ በተባለ መናኝ ወጣት የተገኙ፣ አጥረውና ወደ አማርኛ ተተርጉመው “መጽሐፈ ሱባኤ” እንዲሁም “የኢትዮጵያ ትንሳኤ ታሪክ” በሚሉ ርዕሶች የታተሙ ጥንታዊያን የግዕዝ ብራና ቅጠሎች እንደሚገኙባቸው በመቅድማቸው ገልጸዋል፡፡ በአጠቃላይ መጽሐፍ ቅዱስና ሌሎች 40 ያህል ማጣቀሻ ምንጮች መጠቀማቸው ታውቋል፡፡
ኦሮሞና አማራ ከየት እንደመጡ፣የዘር ሐረጋቸው ከየት እንደሆነ በትክክል አይታወቅም፡፡ ኦሮሞ ከአማራ ጋር ስላለው ዝምድናም እጅግ ግራ መጋባት አለ ይላሉ፤ ፕሮፌሰር ፍቅሬ፡፡ ኦሮሞዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዛሬ 500 ዓመት ገደማ ከእስያ ተነስተው በማዳጋስካር አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ የመጡ የውጭ ወራሪ ተደርገው አጉል ስም ተሰጥቷቸዋል፡፡ ኦሮሞ መጤ ነው ወይስ አገር በቀል? በማለት ደራሲው ይጠይቃሉ፡፡ ስለ አማራ ማንነትም ቢሆን ሁሉም የታሪክ ሊቃውንት እርግጠኞች አይደሉም ይላሉ፡፡ አማሮች ከኦሮሞ ቀድመው ከደቡብ አረቢያ የፈለሱ ናቸው የሚሉ ታሪክ ጸሐፊዎች አሉ፡፡ አማሮች እንደ ሴማዊ ይባስ ብሎም እንደ ሐበሻ ይታያሉ፡፡ እውን አማሮች እነዚህን ናቸው? አማሮች ንጉሠ ነገሥት፣ ንግሥተ ነገስታት ሆነው ላለፉት 3000 ዓመታት እንደገዙት እንደ ሰለሞን ስርወ መንግስት አባላት ተቆጥረዋል፡፡ አማሮች ይህን ሁሉ ነበሩ? የኦሮሞና የአማራ እውነተኛው ምንጭ ከየት ነው?
አማራው በሰለሞናዊው ስርወ መንግስት ውስጥ ዋናው የሥልጣን ባለቤት እንደነበር ተቆጥሮ እስከ ዛሬ ድረስ ለዘር ጥቃት ሲጋለጥ ሲፈናቀል፣ ሲሰቃይና ሲገደል ኖሯል፡፡ ምንም እንኳ ከነበረው ከማንኛውም መንግስትና ወታደራዊ ስልጣን ከተገለለ 40 ዓመታት ያለፉ ቢሆንም አሁንም ስልጣን ላይ እንዳለ እየተቆጠረ የዘር ጥቃት ሰለባ ሆኖ ይገኛል፡፡
በእርግጥ አንዳንድ የጎሳና የፖለቲካ ቡድኖች እርስ በርሳቸው ሙሉ በሙሉ ተፃራሪ ሆነው ሳለ፣ ኅብረትና አንድነት ለመፍጠርና ስልጣን የመያዝ ፍላጎታቸውን ለማሳካት፣ አማራን እንደ ጋራ ጠላታቸው ቆጥረው፣ ፀረ-አማራነትን የመሰብሰቢያና የመጠናከሪያ ብልሃት አድርገውታል፡፡ አማራን የጋራ ጠላታቸው አድርገው ባይተባበሩ፣ ባይዋሃዱና አንድነት ባይፈጥሩ ኖሮ የትግላቸው ውጤት ፍፁም የተለየ ይሆን ነበር በማለት አብራርተዋል፡፡
እውን አማራው ላለፉት 3000 ዓመታት ዋናው የኢትዮጵያ ገዢ ኃይል ሆኖ ያውቃል? አማሮች የአማራ ስርወ መንግስት የሚል መስርተው፣ ኢትዮጵያን የገዙበት አጋጣሚ አለ? አማራውን እወክላለሁ ብሎ ያወጀ ንጉሠ ነገስትስ ይኖር ይሆን? ለመሆኑ ላለፉት 700 ዓመታት ኢትዮጵያን የገዛው ኦሮሞ ነው ወይስ አማራው? በኢትዮጵያ ስርወ መንግስታት ውስጥ የአማሮች ተሳትፎ ምን ያህልና እስከ ምን ድረስ ነበር? አማራ የሚባል ህዝብስ አለ ወይስ የለም? የዚህ መጽሐፍ ዓላማ፣ በእነዚህ መደናገሮችና ጥርጣሬዎች ላይ ምርምር ማድረግና ብርሃን ፈንጥቆ፣ እውነቱን ማጥራት ነው ብለዋል፤ደራሲው በመጽሐፉ መቅድም ላይ፡፡
ደራሲው በዋቢነት የተጠቀሙት ማጣቀሻ መጽሐፍት በእጃቸው የገቡት ከ6 ዓመት በፊት ነው፡፡ እነዚህን መጽሐፍት ካገኙ በኋላ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ የነበራቸው ግንዛቤ ሙሉ በሙሉ መቀየሩን ይናገራሉ። ታሪካችን በጊዜ ክፍተት ውስጥ ሲያልፍ በተቃራኒ ሀሳቦች የመቀየጥና የመድበስበስ አደጋ አጋጥሞታል። አሁን ግን ሀቁ ፍጥጥ ብሎ ወጥቷል፡፡ እነዚህ አዳዲስ መረጃዎች፤በመቶዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ኢትዮጵያን ስለገዙ ኦሮሞ ንጉሶችና ንግስቶች እንዲሁም ሁለቱም ጎሳዎች ኦሮሞና አማራ ለኢትዮጵያ ስልጣኔ ስላበረከቱት አስተዋጽኦ ያትታሉ በማለት ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለተባለችው አገር መስራች የሆነው ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኢትዮጵ፤ ለኦሮሞ ለአማራና ለሌሎችም ኢትዮጵያውያን ሁሉ ቀደምት አማት መሆኑ በእነዚህ መጻሕፍት ተገልጿል ይላሉ፡፡ አማሮች ሴማዊ፣ ኦሮሞዎች ኩሻዊ ናቸው እየተባለ ሲነገረን ያደግነው ውሸት ነው። ሁለቱም ጎሳዎች ኩሻውያን ናቸው፡፡ ሁለቱም ደሼት ወይም ደሴት ከተባለ አንድ አባት፣ ሁለቱም ከአንድ አካባቢ ከጎጃም፣ ሁለቱም ከአንዲት አገር ኢትዮጰያ የተገኙ ናቸው ሲሉ አብራርተዋል፡፡ ሁለቱ ህዝቦች አንድ ዓይነት የዘር ሐረግ፣ አንድ ዓይነት  ታሪክና አንድ ዓይነት ዕጣ ፈንታ ስለሚመሩ አንድ ላይ ተቀላቅለዋል። የሥጋ ዝምድና እንዳላቸው በደንብ በመገንዘባቸው፣ አማሮች፣ ባለፉት ጊዜያት የኦሮሞን ባህልና የአኗኗር መንገዶች ተጋርተዋል፡፡ አንዳንዶች እንደሚመኙት፤ አማሮች እብሪተኞች ቢሆኑና ኦሮሞን ቢንቁ ኖሮ የኦሮሞን ባህልና ልማድ ተቀብለው እየተጋቡ፣ራሳቸውን አያዋህዱም ነበር፡፡ ኦሮሞዎች ባህላቸውንና ልማዳቸውን በአማሮች ላይ በግድ አልጫኑባቸውም፡፡ አማሮች ናቸው ወደውና ፈቅደው የተቀበሉት፡፡ የኦሮሞና የአማራ ህዝብ በኢትዮጵያ በደምና ስጋ ብቻ ሳይሆን ላለፉት 3500 ዓመታት በባህል፣ በኅሊናና በመንፈስ ተዳቅሏል፤ ተዋህዷል በማለት አንዳንድ ዘረኞችና ተንኮለኞች ሁለቱን ጎሳዎች ለማጋጨት የሚነዙት አሉባልታ እንደማይሰምር አስረድተዋል፡፡
ኦሮሞና አማራ የዘር አወራረዳቸው አንድ ነው። ከኖህ ልጅ (ካም) እና ከልጁ ከኩሽ ይጀምራል፡፡ ካም ኩሽን ወለደ፤ ኩሽ ሰባን (ወንድ ነው) ወለደ፣ ሰባ ኑባን ወለደ፤ ኑባ ጋናን ወለደ፤ ጋና ኢታናን ወለደ፤ ኢታና ናምሩድን (የባብኤል ማማን የሰራውን) ወለደ፤ ናምሩድ አዳማን ወለደ (የዛሬዋ ናዝሬት አዳማ ከተማ መጠሪያዋና ያገኘችው፤ ከዚህ ነው) አዳማ ራፌልብን ወለደ፤ ራፌልብ ቀንአን ወለደ፤ ቀንአ ጌራን ከፍተኛውን ካህንና የሳሌምን (የኢየሩሳሌምን ንጉሥ መልከጸዴቅን) ወለደ፡፡ ጌራ ወይም መልከጸዴቅ በጣና ሐይቅና በግዮን (አባይ) ወንዝ አካባቢ ከ400 ዓመት በፊት የኖረውን ኢትዮጵ ተብሎ እንደገና የተሰየመውንና በቢጫ ወርቅ በተሞላ ቦታ ሰፋሪውን ኤት-ኤልን ወለደ፡፡ ኢትዮጵ ማለት፤“ለእግዚአብሔር የቢጫ ወርቅ ስጦታ” ማለት ነው፡፡
ኢትዮጵ. ሲና ከተባለችውና በኋላ እንቆጳግየን (የግዮን ቢጫ ወርቅ ጌጥ) ተብላ ከተጠራችው አዳማ ሚስቱ 10 ወንዶችና ሦስት ሴቶችን ወለደ፡፡ ወንዶቹ ልጆች አቲባ፣ ቢኦር፣ ተምና፣ አቴር፣ አሻን፣ አጅዚብ፣ በሪሻ፣ ቴስቢ፣ ቶላና አዜብ ይባላሉ፡፡ ሴቶቹ ደግሞ ሎዛ፣ ሚልካና ሱባ ናቸው፡፡ እነዚህ የኢትዮጵ ልጆችና ልጆቻቸው እጅግ ብዙ ጎሳዎችና ነገዶች ሆነው የሁሉም ኢትዮጵያውያን አባትና እናት ሆነዋል፡፡
ከእነዚህ የጥንት አባቶቻችን ውስጥ አንዱ የኦሮሞና የአማራ እንዲሁም የሁሉም ኢትዮጵያውያን መሰረት የሆነው ደሼት (ደሴት) ነው፡፡ የደሼት ውልደት ለየት ያለ በመሆኑ ተረት ይመስላል፤ ነገር ግን ሀቅ ነው ይላሉ ፕሮፌሰር፡፡ የቤላም (በልዓም) የልጅ ልጅ የሆነችው ነቢይትዋ እናቱ ሸምሼል መነኩስት ነበረች፡፡ ከወንድ ርቃ ግዮን ወንዝ አካባቢ በገዳም መንፈሳዊ ሕይወት ትመራ ነበር፡፡ አንድ ቀን እርቃኗን ወንዝ ውስጥ ገላዋን ስትታጠብ የወንድ ዘር ፍሬ በማኅፀኗ ገባና ደሼት (ደሴት) ተፀነሰ፡፡ ኦሮሞ፣ “ሕይወት ሁሉ ከውሃ ተገኘ” ብሎ የሚያምነው ለዚህ ነው፡፡ ይህ የሆነው ከ3500 ዓመት በፊት ስለሆነ ማስረጃው ሁሉ ጠፍቷል፡፡ የተወሰነ እውነት ብቻ በጎጃም በሚኖሩና ራሳቸውን “እነማይ” ብለው በሚጠሩ ኦሮሞዎችና አማሮች አዕምሮ ውስጥ ዛሬም አለ፡፡ “እነማይ” ማለት ከውሃ የተገኘ ሰው ማለት ነው፡፡ በእርግጥ  በግዕዝ፣ በትግሪኛና በመጠኑም በአረብኛ “ማይ” ውሃ ማለት ነው፡፡
የኢትዮጵና የደሼት ዝርያዎች ቀደም ሲል ኢትዮጵያ ውስጥ ይኖሩ ከነበሩ ኩሻውያን ጋር እየተጋቡ ራሳቸውን አባዝተው፣ በ4000 ዓመታት ውስጥ ያሁኖቹን ኢትዮጵያውያን አስገኝተዋል፡፡ አማራና ኦሮሞን ጨምሮ ለበርካታ ኢትዮጵያውያን ነገዶች አባት የሆኑት አራት የደሼት ልጆች፡- ማጂ፣ ጂማ፣ መንዲና መደባይ ናቸው። ማጂ፣ ማራ (አማራ)ን እና ጀማ (ዠማ)ን ወለደ፡፡ ጀማ (ዠማ)ዎች በዛሬው ሸዋ ውስጥ በነገዳቸው ስም በሰየሙት ዠማ ወንዝ ዳር የሰፈሩት ናቸው፡፡ ጂማ፡- ገንቲን፣ አወንቲንና ማራን ይወልዳል፡፡ ኦሮሞ፡- ከመደባይ፣ ከጂማና ከመንዲ ተገኘ፡፡ ኦሮሞዎች፤ኦሮሞ ከመባላቸው በፊት መደባይ ነበር የሚባሉት፡፡ ከ2950 ዓመት በፊት በቀዳማዊ ምኒልክ ዘመን እንኳ ኦሮሞዎች መደባይ እየተባሉ ይጠሩ ነበር፡፡ መደባይ በአሁኑ ወቅትም አለ፡፡ መደባይ ዛና ከ36ቱ የትግራይ ወረዳዎች አንዱ ነው፡፡
ቆየት ብሎ የ“ማራ” ልጆች “አ-ማራ” ወይም “ሃ-ማራ” እየተባሉ መጠራት ጀመሩ፡፡ “ሃማራ” ብሎ የጠራቸው ግዕዝ ተናጋሪው አግአዚ ነበር፡፡ “ማራ” የተባለው ቃል የተለያዩ ትርጉሞች አሉት፡፡ መነሻው ግን የሱባ ቃል ነው፡፡ በሱባ ቋንቋ “ማ” ማለት “እውነት” ማለት ነው። “ራ” ደግሞ “ብርሃን” ማለት ነው፡፡ በዚህ መሰረት “ማራ” ማለት “እውነተኛ ብርሃን” ማለት ነው፡፡ “ሱባ፣ ልነሰብ (ሰብአዊ ቋንቋ) ቀዳማዊ ምኒልክ ሥልጣን እስከያዘበት ጊዜ ድረስ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቋንቋ ነበር፡፡ ነገሥታቱ ትዕዛዞቻቸውንና መመሪያዎችን የሚጽፉበትና የሚያውጁበት የመንግሥት የስራ ቋንቋ ነበር፡፡ ቀዳማዊ ምኒልክ መደባዮችን በከፊል የጨፈጨፈውና የመንግስት የሥራ ቋንቋ የነበረውን የሱባ ቋንቋ መጻሕፍት ያቃጠለው ኢትዮጵያን ወደ አይሁድ ምድርነት ለመቀየር የነበረውን መሰሪ ዕቅድ በመቃወማቸው ነበር፡፡ መደባዮች ባህልና ቋንቋቸውን ለማስጠበቅ መጤ የአይሁድ ባህልና ቋንቋ አንቀበልም በማለታቸው ቀዳማዊ ምኒልክን ተከትለው ከእስራኤል ከመጡ 40 ሺህ አግአዚና ከ28 ሺህ ጀቡስቶች (ኢያቡሳውያን) ወታደሮች ጋር ከፍተኛ ውጊያ ገጥመው ተሸነፉ፡፡ ቀዳማዊ ምኒልክ በሚያሳዝን ሁኔታ መደባዮችንና መጻህፍቶቻቸውን አጠፉ፡፡ የንጉሡን መንግስት እንዲያገለግሉና የአግአዚን ባህል እንዲላበሱ የተገደዱት መደባዮች፤ የታላቅ አባቶቻቸውን የኢትዮጵና የደሼትን የሱባ ቋንቋ እርግፍ አድርገው ትተው የግዕዝ ተናጋሪዎች ሆኑ፡፡ ቀዳማዊ ምኒልክ አግአዚዎችን ስልጣን ላይ አውጥቶ የሰለሞን ስርወ መንግስት የተባለውን መንግስት በኢትዮጵያ መሰረተ፡፡
አንዳንድ መደባዮች በጥንቱ የሱባ ቋንቋ የተጻፉ መጽሐፎቻቸውን ደበቁ ወይም ለንጉሡ አስረከቡ፡፡ ንጉሡም የወረሳቸውን በእጁ የገቡትን መጻሕፍት በሙሉ አቃጠላቸው፡፡ ከዚህ ቀጥሎ የሰፈረው ታሪክ “ተረት ይመስላል” ካልኩት የሚመደብ ነው፡፡ በዚህ ድርጊት ያዘነ አንድ መደባይ፣ መጽሐፉን ለንጉሡ አላስረክብም ብሎ ለላሚቱ አበላት፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ላሟን ሲያርዷት የተወሰነ ጽሑፍ በስጋዋ ላይ ማግኘቱ ተዘግቧል፡፡ እሱና ልጆቹ አንዳንድ ፊደላት ገጣጥመው ለመተርጎምና ስለ ታሪካቸው ፍንጭ ለማግኘት በመሞከራቸው መደባይን “ኦሮሞ” ብሎ መጥራት ተጀመረ፡፡ በጥንቱ የሱባ ቋንቋ “ኦሮሞ” ማለት “እውቀት ገላጭ፣ ተርጓሚ በሰው ልብ ውስጥ ያለውን የሚያነብ ብልህ ሰው” ማለት ነው፡፡
ኦሮሞዎች በመላዋ ኢትዮጵያና በብዙ የአፍሪካ አገሮች ተሰራጭተው ይገኛሉ፡፡ ወደ ሰሜን ወደ ጎንደርና ትግራይ ክልሎች ተጓዙ፡፡ በስተደቡብ ወደ ወለጋና ኢናሪ (አሁን ሊሙ) አቅኑ ይላሉ፤ ደራሲው፡፡ ቀስ በቀስ ቁጥራቸው ሲበረክት ደግሞ ወደ ባሊ (አሁን ባሌ) ሶማሊያ፣ በቦረና በኩል ወደ ኬንያ፣ ሩዋንዳን አልፈው እስከ ኒጀር፣ ማዳጋስካር፣ ማሊ፣ ናይጄሪያ ዘለቁ፡፡ የሩዋንዳ ቱትሲዎች ኦሮሞ መሆናቸውን ያምናሉ፡፡ ኢትዮጵያዊ መልክም ይታይባቸዋል፡፡ ሁቱዎቹ  ሊያጠቋቸው ሲፈልጉ፤ “ወደ አገራችሁ ኢትዮጵያ ተመለሱ” ይሏቸው ነበር፡፡ በኦሮምኛ “ማሊ” ማለት “ምንድነው?” ማለት ነው ሲሉም  አብራርተዋል፡፡
ከክርስቶስ ልደት በፊት በ1000 ዓ.ዓ ገደማ ወንድማማቾቹ ጀማና የማራ (አማራ) ልጆች ከነባር ጋፋት ህዝቦች ጋር መዋጋት ሰለቻቸውና ወደ ምስራቅ አቀኑ፡፡ እዚያም የጀማ ልጆች ዛሬ ሸዋ በሚባለው ውስጥ አንድ ወንዝ አገኙና፤ ለአባታቸው ማስታወሻ እንዲሆን ጀማ ብለው ጠሩት (አሁን ዠማ ይባላል፡፡) ማራ (አማራ)ዎች የሰፈሩባቸውን ቦታዎች ሸበል በረንታ፣ ዑሬራ፣ ግራርጌ፣ አዲስጌ፣ ገመራ (አሁን መራቤቴ) አማራ ሳይንት፣ ሊኮ (አሁን ወሎ) ባቢባ ገነቴ (አሁን የጁ) እያሉ ሰየሟቸው” በማለት የአማን በላይን “የጥንቷ ኢትዮጵያ ትንሳኤ ታሪክ” የተባለ መጽሐፍ (ገጽ 202) ዋቢ አድርገው አቅርበዋል፡፡
እዚህ ላይ ምናልባት ሰምታችሁ የማታውቁትን (ለእኔ እንደዚያ ስለሆነ ነው) ታሪክ ላጫውታችሁ፡-ለካንስ ጃማይካዎች ኢትዮጵያን በፍቅር የሚወዷትና የሚያመልኳት፤ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ቀይ ባንዲራዋን በኩራት የሚያውለበልቡት (የሚያስሩት) ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ኢትዮጰያዊ ደማቸው እየሳባቸው ነው፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ ጀማዎች (ዠማዎች) የግራኝ ወረራን አጥብቀው በመቃወማቸው፣ አሕመድ ግራኝ ክፉኛ ጎዳቸው፡፡ ግራኝ ደጋፊዎቹ ስለነበሩት አረቦች በመርከብ ጭኗቸው በባርነት ሸጧቸው፡፡ የአጋጣሚ ጉዳይ ሆኖ የተጫኑባቸውን መርከቦች ስፔናዊያን ማረኳቸውና ዛሬ በስማቸው ጃማካ ወይም ጃማይካ ተብሎ በሚጠራው አገር በባርነት ኖሩ ይላሉ፤ፕሮፌሰር ፍቅሬ “የጥንቷ ኢትዮጵያ ነገሥታት ታሪክ” (ከገጽ 53-55) የሰፈረውን መረጃ ዋቢ በመጥቀስ፡፡
አማራ ኃይለኛና ጠንካራ ተዋጊ ወታደር ነው፤የፈለገውን ወደ ሥልጣን ያወጣል፣ ያልፈለገውን ደግሞ ተዋግቶ ከስልጣን ያወርዳል፡፡ “በሙያው፣ በትምህርት (ቅኔ ቤት) በንግድ፣ በግብርና በጽህፈት ስራና ከሁሉም በላይ ደግሞ በአብዛኛው በውትድርና ሙያ ተክኗል” ይላሉ ፕሮፌሰር፡፡ ለምሳሌ “አክሱማይ ገና ትንሽ ልጅ ሳለ (6 ወይም 7 ዓመት በነበረበት ወቅት) የግብፅ ፈርኦን ሆኖ ራምዜስ ውም ራሚሱ በሚል የንግስና ስሙ ሲነግስ፣ ከ2850 ዓመት በፊት ዙፋኑን ለመጠበቅና ሱዳንን በስሟ ያስጠራችውን እናቱን ሳዶንያን አጅበው ከኢትዮጵያ ወደ ግብፅ የሄዱት 350ሺህ አማሮች ነበሩ፡፡ እነሱም እስከ ዛሬ በስማቸው በሚጠራው አማርና ደልታ በተባሉ ቦታዎች መኖር ጀመሩ፡፡ (ኢንተርኔት ውስጥ ገብተው ሊያረጋግጡ ይችላሉ) ይህ ከሆነ ከ1800 ዓመት በኋላ ላሊበላ ከኢየሩሳሌም ወደ ኢትዮጵያ  ሲያቀና ወደ ግብፅ ጎራ አለ፡፡ ከዚያም በአማርና ደልታ ከሚኖሩ አማሮች፣ በሺህዎች የሚቆጠሩትን ወደ ኢትዮጵያ ይዞ መጥቶ፣ ባላንጣው የነበረውን የዛጉዬ ንጉሡ-ነገሥት ሂርጴን በጦርነት ድል አድርገው ላሊበላን የኢትዮጵያን ንጉሠ-ነገሥት አደረጉት፡፡
አማሮች ሌሎች የሚጠቀሱ ብዙ ታሪኮች አሏቸው። ከእነዚህ ውስጥ አንዱን እነሆ፡- ኒውዮርክ ታይምስ እ.ኤ.አ ቅዳሜ ጥቅምት 21 ቀን 2006 ዓ.ም የዘገበው ነው፡፡ “ባግዳድ ጥቅምት 20-2006፤ ከሺአይት ጸሐፊ ከማከታዳ አልስዳር ጋር ግንኙነት ያላቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሚሊሻዎች በደቡባዊ ምስራቅ አማራ ከተማ አርብ ዕለት የአካባቢውን ፖሊስና የሺአይት ሚሊሽያ ተቃዋሚ የሆኑትን አጥቅተው ፖሊስ ጣቢያውን ደምስሰዋል፡፡ አካባቢውን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረዋል፡፡ ሰማዩን በጪስ የሸፈኑ ቦምቦችም አፈንድተዋል” በማለት ዘግቧል፡፡ “አማራ” የሚል ቃል አነበብኩ እንዴ? ብለው ዓይንዎን ሊጠራጠሩ ይችላሉ፡፡ በእርግጥ “አማራ” የሚል ቃል አንብበዋል፡፡ ታሪኩ እንዲህ ነው፡፡
ከክርስቶስ ልደት በፊት በዘጠነኛው ዓመተ ዓለም የቀዳማዊ ምኒልክ የልጅ፣ ልጅ፣ ልጅ የሆነው አክሱማይ፤ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት አክሱም ከተማን ቆረቆረ፡፡ ግዙፉን ግንባታ ለማከናወን መሐንዲሶችን፣ ባለ እጆችንና ግንበኞችን ከመላው ኢትዮጵያ መረጠ፡፡ ሴት ልጁን ረብላን ለባቢሉኑ (አሁን ኢራቅ) ንጉሥ ለናቡከደነፃር በጋብቻ ሰጠ፡፡ አማራ ወታደሮች ሪብላን አጅበው ወደ ኢራቅ ተጓዙ፡፡ ሪብላ በኢራቅ በስሟ ከተማ ቆረቆረች፡፡ አማራ ወታደሮችም “አማራ” የተባለች ከተማ በስማቸው መሰረቱ፡፡ ሪብላ ከተማ በመሬት ነውጥ ተደመሰሰች። “አማራ” ከተማ ግን እስከ ዛሬ በስምዋ ትገኛለች፡፡ ኒውዮርክ ታይምስ፣ “አማራ” በሺአይት ሙስሊሞች ተያዘች በማለት የዘገበው ያኔ ከ2025 ዓመታት በፊት በአማራ ወታደሮች የተቆረቆረችዋን ከተማ ነው፡፡
ፕሮፌሰር ፍቅሬ በኢትዮጵያዊነታቸው በጣም ይኮራሉ፤ ኢትዮጵያንም በጣም ይወዷታል፡፡ በዚህ አቅማቸው ኦሮሞ ወዳጆቻቸው እንደሚገረሙ ጽፈዋል። “አያት ቅድመ-አያቶቼ ልዩ የሆነውን ቅርሳቸውን የተወልን የኢትዮጵያን ዳር ድንበር አዘልለው መሆኑን አውቃለሁ፡፡ ስለዚህ ራሴን “ኦሮሚያ” በምትባል ጠባብ ቦታ ላይ መወሰን አልፈልግም፡፡ ምክንያቱም ጠቅላላዋ ኢትዮጵያ በመላው  ቀመትዋና ስፋትዋ የእኔ፣ የኦሮሞ ወንድሞቼና እህቶቼ እንዲሁም የሌሎችም ኢትዮጵያውያን ናት፡፡ …. ስለዚህ፣ እኔ ፍቅሬ ቶሎሳ ጂግሳ የሳሌም (ኢየሩሳሌም) ንጉሥና የእግዚአብሔር ከፍተኛ ካህን የነበረው የመልከጸዴቅ ልጅ፣ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥትና የዓለማቱ ፈጣሪ ከፍተኛ ካህን የነበረው የኢትዮጵ ልጅ፣ እንዲሁም ነብይና ፈላስፋ የነበረው የጎጃም ንጉሥ የደሴት ልጅ ነኝ፡፡ አዎ! ኦሮሞዎችን፣ ሃዲያዎችን፣ ከምባታዎችን፣ ሶማሌዎችን፣ አፋሮችን ጉራዎችን…. እና ሌሎቹን ኢትዮጵያውያን ጨምሮ እንደ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እኔም የእነዚህ ሁሉ ልጅ ነኝ›› በማለት ኢትዮጵያዊ የመሆን ኩራታቸውን መንስኤ አብራርተዋል፡፡ ለዛሬ ዳሰሳዬን በዚሁ ላብቃ፡፡ ሳምንት እመለስበታለሁ፡፡
(ይቀጥላል)

No comments:

Post a Comment