Friday, September 16, 2016

ጥቂት አንቀጾች ስለመምህርነትና የኢትዮጵያ ፓለቲካ Tadesse Biru Kersmo.


Bilderesultat for tadesse biru kersmoእኔ በግሌ መምህርነትን የሚያህል ሙያ ያለ አይመስለኝም። ከልጅነቴ ጀምሮ መሆን እመኝ የነበረውን በኋላም የሆንኩት መምህር ነው። “መምህር” የሚያስደስተኝ መጠሪያም ነው።
መምህር መሆን ማለት የሁል ጊዜ ተማሪ (lifelong learner) መሆን ማለት ነው። የጥሩ መምህር ሥራ “ያለቀለት እውነት” መስበክ ሳይሆን ተማሪዎች ራሳቸው የራሳቸውን እውነት እንዲያገኙ መርዳት ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ የፋርሱ ካሊብ ጅብራን “ነብዩ” በተሰኘው መጽሀፍ ያለው ያሰፈረው በጣም የምወደው አንቀጽ ሙሉውን እዚህ ላስቀምጥ።

“መምህር ከእምነቱና ከፍቅሩ ይሰጥሃል እንጂ ጥበቡን አይደለም። የከዋክብት መርማሪ ስለሔዋው ያለውን ማስተዋል ይነግርህ ይሆናል ግን ማስተዋሉን ሊሰጥህ አይችልም። በሔዋው ሁሉ ያለውን ዜማ ዘማሪው ያዜምልሃል፤ ዜማውን የሚያደምጥ ጆሮ ወይም የሚያስተጋባውን ድምፅ ሊሰጥህ አይችልም። በሂሳብ ጥበብ የላቀው የሚዛንና የመለኪያን ወሰኖች ሊነግርህ ይችላል፤ ነገር ግን ወደዚያ ሊመራህ አይችልም።”
[በነገራችን ላይ፤ ነቢያት መምህራን ሆነው የመጡት ያለምክንያት አይደለም። ነገሥታት ሆነው በመምጣት እምነታቸው ማወጅ ይችሉ ነበር፤ ወይም ካድሬዎች ሆነው በመምጣት ሰዎች መነዝነዝ ይችሉ ነበር። የመረጡት ግን መምህራን ሆነው በመምጣት person specific approach በመጠቀም ደቀመዛሙርትን በማፍራት እያንዳንዱ ደቀመዝሙር የነቢዩን እውነት ራሱ እንዲያገኝ ወይም ያገኘ እንዲመስለው አደረጉ]
ይህንን የመሰለ ትልቅ ማኅበራዊ ቦታ የተሰጠው መምህርነትን የህወሓት አገዛዝ ምን ያህል እንዳረከሰው በዓይኖቻችን እያየን ነው። የዛሬዎቹ መምህራን ራሳቸው በነፃነት ማሰብ አይችሉምና ተማሪዎቻቸውን በነፃነት ማሰብን ሊያለማምዱ አይቻላቸው።
በሁሉም በላይ የሚያናድደኝና የሚያሳፍረኝ ሥርዓቱ መምህራንን የሚያይበት እይታ ነው። ሥርዓቱን መምህራንን የሚመለከተው በቀላሉ ሊደለሉ እንደሚችሉ አድርባዮች ስብስብ ነው። መምህራን በድህነት መኖራቸው የሥርዓቱ ተመጽዋች አድርጓቸዋል። [በግል ኮሌጆች በማታ የምንሰጠውን ክፍል “ድህነት-ቅነሳ” እንለው ነበር] ሥርዓቱ “ካድሬ-በርካሽ” ሲፈልግ ዓይኖቹን የሚያማትረው ወደ ትምህርት ቤቶች ነው። በክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች በኋላፊነት የመመደብ እድል፤ ኮንዲሚነም የማግኘት ተስፋ (ያውም ተስፋ ብቻ) እና የደመወዝ ጭማሪ ቁጥራቸው በቀላሉ የማይገመት መምህራንን ተለማማጭ አድርጓቸዋል። “ወይን ለኑሮ” እንደ ኑሮ ዘይቤ ሥር ከሰደደባቸው የሥራ መስኮች አንዱ መምህርነት ነው።
ይህ በዘመነ ወያኔ የመጣ እንጂ ቀድሞ እንዲህ አልነበረም። የኢትዮጵያ መምህራን በለውጥ ሂደት ውስጥ ፋና ወጊዎች ነበሩ። መምህራን የብዙ ነገሮች መረጃዎች ያሏቸው ሰዎች ናቸው ተብሎ ይታመን ነበር። በማኅበረሰቡም ተሰሚነት ያላቸው በመሆኑ ማኅበራዊ ስሜትን የመቆጣጠር ችሎታ ነበራቸው። የመምህራን መልዕክት ማኅበራዊ እንቅስቃሴን መፍጠርም ሆነ የተፈጠረውን እንቅስቃሴ ማብረድ ይችል ነበር። መምህራን ነበሩ በሕዝብ ልብ የተደበቀውን ብሶት አንብበው ስሜት በሚሰጥ መልክ አቀናብረው ከመፍትሄ ሃሳብ ጋር መልሰው ለኅብረተሰቡ የሚያቀርቡት።
ዛሬ ያ ሁሉ “በነበር” የቀረ ይምሰል እንጂ ተመልሶ መምጣቱ አይቀርም። ከህወሓት የባርነት አገዛዝ ነፃ መውጣት የምንጀምረው መምህራን ነፃ ሰዎች መሆናቸው ማረጋገጥ ሲችሉ ነው። በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ መምህራን ያልተሳተፉበት አብዮት ግቡን አይመታም።
ይህንን ማስታወሻ በምፅፍበት ወቅት የኢትዮጵያ መምህራን በአሰልቺ የሥርዓቱ “የንዝነዛ ስልጠና“ ውስጥ ናቸው። አሰልጣኞቹ ራሳቸው ስለማያውቁት ነገር ነው የሚናገሩት፤ በእያንዳንዱ የስልጠና አዳራሽ ”ጆሮ ጠቢዎች” አሉ። ጆሮጠቢዎቹ ከአሰልጣኞቹ የባሱ ደነዞች ናቸው። እነሱ ሥራ ተስጥቷቸዋል፤ ከመምህራኑ ጥቂቶች በስሜት ሲናገሩ ለመቅለብና ሪፓርት ለማድረግ ተዘጋጅተዋል። በዚህ ስልጠና የመምህራኑ መናገር የጆሮጠቢዎቹ ሲሳይ ከመሆን ያለፈ አንዳች ፋይዳ አይቻየኝም። የህወሓት ካድሬዎችን ተከራክሬ አሳምናለሁ ብላችሁ አትልፉ። እንደምታውቁት ለመማር የማይፈልግን ሰው ማስተማር በጣም፣ እጅግ በጣም ከባድ ነው፤ እንደዚሁም ለመስማት ላልተዘጋጀ ሰው መናገር ራስን ማድከም ነው።
ይልቁንም የስልጠናውን ጊዜ በአግባቡ ለመጠቀም አፎቻችን ዝም ይበሉ፤ ዝምታ ፍጹም የሆነ ዝምታ “በስልጠና” አዳራሾች ሁሉ ይስፈን። አዕምሮዎቻችን ግን 2009 የትምህርት ዓመት የውጤታማ ትግል ዘመን እንዴት ማድረግ እንደሚቻል ያሰላስሉ፤ ስትራቴጂዎችን ይንደፉ፤ ታክቲኮችን ይቀምሩ። አዕምሮዎቻችን በየትምህርት ቤቶቻችን ሕዝባዊ እምቢተኝነትን እንዴት እንደምናደራጅ፤ እንደምን ያሉ አሪፍ አሪፍ አሻጥሮችን በሥርዓቱ ላይ እንደምትሠራ ያሰላስሉ !!!
መልካም ጊዜ
16/09/2016

No comments:

Post a Comment