Tuesday, October 18, 2016

ኬንያ ከኢትዮጵያ ጋር በምትዋሰንበት የድንበር ዙሪያ ወታደሮቿን አሰማራች ኢሳት (ጥቅምት 7 ፥ 2009)


የኢትዮጵያ ወታደሮች እሁድ የኬንያ ድንበር አቋርጠው መግባታቸውን ተከትሎ ኬንያ ከኢትዮጵያ በምትዋሰንበት የድንበር ዙሪያ ወታደሮቿን አሰማራች።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ታጣቂዎችን ፍለጋ በሚል ወደ 100 አካባቢ የሚጠጉ የኢትዮጵያ ወታደሮች ዕሁድ ከሰዓት በኋላ ማርሳቤት ተብሎ ወደሚጠራ ግዛት መግባታቸውን የግዛቲቱ ባለስልጣናት ሰኞ ለመገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።
የማርሳቤት ግዛት ፖሊስ ኮማንደር የሆኑት ማርክ ዋንጀላ የኢትዮጵያ ወታደሮች የኬንያ ድንበርን ጥሰው በገቡ ጊዜ በአንድ ወጣት ላይ ግድያ መፈጸውማቸውን እንዳስታወቁ ዴይሊ ኔሽን ጋዜጣ ዘግቧል።

ኢትዮጵያ ወታደሮቿ ለማዝመት የተገደደችውም የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኦነግ ታጣቂዎች በቅርቡ ጥቃትን በመፈጸም በርካታ ወታደሮችን መገደላቸውን ተከትሎ እንደሆነ የፖሊስ ሃላፊው አስረድተዋል።
ይሁንና የኬንያም ሆነ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በኦነግ ታጣቂዎች ስለተገደሉ ኢትዮጵያውያን ወታደሮች ቁጥር የሰጡት ዝርዝር መረጃ የሌለ ሲሆን፣ የኬንያ ወታደሮች የኢትዮጵያ ወታደሮች እንቅስቃሴ ጉዞ እንደገቱም ታውቋል።
በሁለቱ ሃገራት ድንበር ዙሪያ ዘጠኝ ኪሎሜትር ያህል የሚሸፍን የሶሎሎ መንደር ውጥረት ነግሶ እንደሚገኝ የማርሳቤት ግዛት ፖሊስ ኮማንደር ማርክ ወንጀላ ለዴይሊ ኔሽን ጋዜጣ አክለው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በቅርቡ ተግባራዊ ያደረገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ ወታደሮቹን የኦነግ ታጣቂዎችን ለመዋጋት በሚል የኬንያ ድንበርን አቋርጦ ሲያስገባ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑም ታውቋል።
የኬንያ የድንበር ተቆጣጣሪ ባለስልጣናት የኢትዮጵያ ወታደሮች በየጊዜው ይፈጽሙታል ያሉትን የድንበር መጣስ ድርጊት ለማስቆም የሃገራቸው መንግስት ጠንካራ ዕርምጃን እንዲወስድ ሲያሳስቡ መቆየታቸው ይታወሳል።
በሁለቱ ሃገራት መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ተከትሎ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኢትዮጵያና ኬንያ የድንበር ውዝግባቸውን እንዲፈቱ ባለፈው አመት ስምምነት እንዲደርሱ ማድረጉም ይታወቃል።
የኢትዮጵያና ኬንያ ስምምነቱን ቢፈራረሙም አሁንም ድረስ የጋራ ድንበራቸው ውጥረት የሰፈነበት እንደሆነ ይነገራል። እሁድ የተፈጸመውን የድንበር መጣስ ድርጊት በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግስት እስካሁን ድረስ የሰጠው ምላሽ የለም።

No comments:

Post a Comment