Wednesday, October 26, 2016

አርበኞች ግንቦት 7 ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ለኢትዮጵያ የመከላከያና ፓሊስ ሠራዊት አባላት የተደረገ ጥሪ


የተከበራችሁ የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት አባላት፤ የፌደራልና የክልል ፓሊስ አባላት፤ የአጋዚ ልዩ ኮማንዶ ጦር አባላትና ሌሎች የሥርዓቱ ታጣቂዎች። አገራችን በለውጥ ሂደት ውስጥ ባለችበት በዚህ ወሳኝ ወቅት ለእናንተ ቀጥታ መልዕክት ማስተላለፍ የሚገባ ሆኖ ስላገኘሁት ይህንን አጭር መልዕክቴን በጥሞና እንድታዳምጡኝ፤ የሰማችሁ ላልሰሙት እንድታደርሱልኝ እጠይቃለሁ። 
የአገር መከላከያ ሠራዊት አባል መሆን ከፍተኛ ክብር ያለው ሙያ እንደነበር የምታውቁት ነው። ለሀገር ዘብ መቆም መልካም ዜጎች ሁሉ የሚመኙት ተግባር ነው። አንድ ሰው ቃለ መሀላ ፈጽሞ የመከላከያ ሠራዊት ዩኒፎርም ከለበሰ በኋላ ተራ ዜጋ አይደለም። አገሪቷ በዜጎቿ ማየት የምትፈልጋቸውን መልካም እሴቶችን ሁሉ በወታደሮቿ ማየት ትሻለች፤ ለሕዝብ ተቆርቋሪነት፣ ሀገር ወዳድነት፣ ፍትሀዊነት፣ ጀግንነት፣ ታማኝነት በወታደሮቿ ማየት ትሻለች። ለዚህም ነው በብዙ አገሮች ውስጥ ያሉ ሕፃናት “ስታድጉ ምን መሆን ትፈልጋላችሁ?” ሲባሉ ከሚሰጧቸው መልሶች ግንባር ቀደሙ “ወታደር” የሚሆነው። በሀገራችንም ዘመናዊ ጦር ከመደራጀቱ በፊት አያት ቅድም አያቶቻችን ራሳቸውን በወታደርነት አሰልጥነው፤ ወራሪ ሲመጣ በየጎበዝ አለቆቻቸው እየተቧደኑ ዘመናዊ ጦሮችን ሳይቀር ተዋግተው በማሸነፍ የአገራችንን ሉዓላዊነት አቆይተውልናል። ዘመናዊ ጦር ከተደራጀ ወዲህም እስከ ህወሓት አገዛዝ የነበሩ አስተዳደሮች ብዙ እንከኖች ቢኖርባቸውም እንኳን የመከላከያ ሠራዊትን የአገር መከላከያ ሠራዊት አድርገውት ቆይተዋል። የሠራዊቱን ክብርና ሞገስ ለመጠበቅም የተቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል። ይህ ጥረት ግን በህወሓት የአገዛዝ ዘመን ሙሉ በሙሉ ተቀልብሷል። 
የፓሊስ ሠራዊት ሥራ ለሕዝብ የዕለት ተዕለት ኑሮ ዋስትና መስጠት ነው። ዜጎች በሰላም ከቤታቸው ወጥተው በሰላም የመመለሳቸው ዋስትና ከወገናቸው ከፓሊስ ሊያገኙ ይሻሉ። ሕዝባዊ ፓሊስ የወሮበሎች፣ የሌቦችና የማጅራት መቺዎች ጠር፤ የድሆችና ደካሞች አጋር ነው። ሕዝባዊ ፓሊስ የፍትህ ጠበቃ ነው። እንዲህ ዓይነቱን ፓሊስ በህወሓት የአገዛዝ ዘመን ማየት አልቻልንም። 
የህወሓት አገዛዝ የተከበሩትን የውትድርናና የፓሊስ ሙያዎችን አዋርዶ ለሀገርና ሕዝብ ደህንነት ሳይሆን ለአንድ ቡድን ሥልጣን መከበር የቆሙ ኃይሎች እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። አሁን ያለው የኢትዮጵያ መከላከያና የፓሊስ ሠራዊትን ስናስብ በአዕምሮዓችን የሚመጡት የሚከተሉት ሀቆች ናቸው። 
1. የጦር ሠራዊቱ፣ብቃትና ዕውቀት እንዲሁም የሀገር ፍቅር ባላቸው ጄኔራሎችና የጦር መኮንኖች የሚመራ ሳይሆን በተቃራኒው ምንም ዓይነት ወታደራዊ ትምህርት በሌላቸው ከሽምቅ ውጊያ ቡድን አዛዥነት ወደ ዘመናዊና መደበኛ ጦር አዛዥነት በድንገት ያደጉ፤ ራሳቸውን ከዘመናዊ ሠራዊት አደረጃጀትና አመራር ጋር ያላዋሃዱ፤ ከሀገር ጥቅም ይልቅ የራሳቸው የግል ጥቅም የሚበልጥባቸው፤ የማይጠረቁ ስግብግቦች፤ ታማኝነታቸው ለሀገር ሳይሆን አባል ለሆኑባቸው ፓርቲዎች የሆኑ ግለሰቦች ናቸው። 
2. ዛሬ ያለው የኢትዮጵያ ሠራዊት በወያኔ የስለላ መረብ ተተብትቦ ወይም በእነርሱ ቋንቋ “ተጠርንፎ” በግድ የተያዘ እንደቁም እስረኛ ሊቆጠር የሚችል በከፍተኛ ምሬትና በደል ውስጥ የሚገኝ ሠራዊትመሆኑን እናውቃለን። የሠራዊቱን ክብር በሚነካ፤ ስብዕናን በሚያዋርዱ ዘለፋዎችና በግምገማ ናላው እንዲዞር፣ሞራሉ እንዲላሽቅ የተደረገ ሠራዊት ነው።የህወሓት ጄኔራሎችና ካድሬዎች የሚያወርዱበት ዘለፋና ስድብ የዕለት ተዕለት ቀለቡ የሆነ፤ ሞራሉም የላሸቀ ሠራዊት ነው።
3. አንድ ተራ የህወሓት ካድሬ ወይንም የበታች ሹም የዘረኛው ሥርዓት በሚሰጠው ልዩ ግምትና ስልጣን ከሌሎች ብሔሮችና ብሔረሰቦች የመጡ በማዕረግም በዕውቀትም የበላይ የሆኑንትን ሻለቆችና ኮሎኔሎችን የሚያንጓጥጡበት፣ የሚያዋርዱበትና የሚያሸማቅቁበት፤ አመራሩ በወታደራዊ እዝና ወታደራዊ ስነምግባር መሠረት የሚመራ ሳይሆን በብሄር የበላይነት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ዲሲፕሊንና ውህደት የሌለው ሠራዊት ነው። በብሔር የተከፋፈለ በመሆኑ በውስጡ ያለው ጓዳዊ ስሜት በእጅጉ የላላ ሠራዊት ነው።
4. የፍትህ ጥያቄ የሚያነሱ የሠራዊቱ አባላት ለህወሓት ካድሬዎች ስላልጣማቸው ብቻ ያለ ወታደራዊ ህግና አግባብ በአንድ የህወሓት ካድሬ ትዕዛዝ ብቻ ደብዛቸው ሊጠፋ እንደሚችል ስለሚያውቁ በከፍተኛ የፍርሃት እና በራሳቸው ላይ እምነት እንዲያጡ የተደረጉ ናቸው።
5. ይህ ሠራዊት ለወያኔ ጠባብ አጀንዳ በየግንባሩ ዘመቻ እንዲሄድ ሲገደድና ሲማገድ የህወሓት ካድሬዎችና ጄኔራሎች የሕይወትና የደም ግብር እንዳይከፍሉ ከአደጋ እንዲጠበቁ የሚደረግበት ዘዴና ስልት የተቀየሰበት የዘረኝነትና የአድሎ ሥርዓት ውስጥ የተጣደ ሠራዊት ነው።
6. ሠራዊቱ ሲቆስል፣ ደሙን ሲያፈስ፣ ፈንጂ ሲረግጥ፣ ሕይወቱን ሲገብር የህወሃት ቅምጥል ጄኔራሎችና መኮንኖች ቅጥ ባጣ አስረሽ ምችው በየከተማው እንደሚባልጉ የሚያውቅ ሠራዊት ነው።
7. ጫማና የደንብ ልብስ ከዚያም አልፎ የሚበላዉን ምግብ ከሚከፈለዉ ትንሽዋ ደሞዙ ላይ እየተቆረጠበት እናት አባቱን ለመጦር እና ልጆችን ለማሳደግ ፈተና ውስጥ የሚገባ፤ ለበርካታ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የተዳረገ ሠራዊት ሆኖ ሳለ በአንፃሩ የህወሓት ጄኔራሎችና ከፍተኛ መኮንኖች በኮንትሮባንድ ንግድና በዘረፋ ሲከብሩ፤ ንግዳቸውን በግላጭ ሲያጧጥፉ፤ ባለብዙ ህንፃዎች ባለቤቶች በመሆን በዘመድ አዝማዶቻቸዉ ስም ጭምር ሀብት ሲያካብቱ፤ የህዝቡን መሬት ያላግባብ ሲቀሙና ሲቀራመቱ፤ በሰላም አስከባሪ ኃይል ስም በተባበሩት መንግስታት በየሀገሩ እየተመደቡ በወር እስከ 25,000 የአሜሪካ ዶላር ተከፋይ ሆነው ሲቀማጠሉ በሚገባ እያስተዋለ የሚገኝ ሠራዊት ነው።
8. በተጨማሪም እንደው ድንገት ለምርጦቹ የሚደርሰው የሰላም ማስከበር ተሳትፎ ግዳጅ ሲሄድ ሊያግኝ ከሚገባው የኪስ ገንዘብ ላይ አብዛኛውን ለራሳቸዉ ጥቅም በማዋል እና ሀገሪቷ ከዚህ ከሰላም ማስከበር ልታገኝ የሚገባትን ጥቅማ ጥቅም በራሳቸዉ በህዉሃት ጄኔራሎችና አመራሮች የግል ኪስ በማስገባት ራሳቸውንና ዘመድአዝማዶቻቸዉን እያበለጸጉበት ይገኛሉ።
9. ሠራዊቱ ከትንሿ ደመወዙ ለመለስፋ ዉንዴሽን፣ ለአባይ ግድብ ግንባታ፣ ለተለያዩየ ተሃድሶ መዋጭዎች፣ ለአመት በአል ድግሶች መዋጮ እንዲፈል የሚገደድ ምስኪን ነው። አላዋጣም፤ ገንዘብ የለኝም ብሎ ቢል ጸረ ሰላም ወይንም ሌላ ስም ተሰጥቶት ለተለያዩ አይነት ቅጣቶች ይዳረጋል። ሕገ መንግሥቱ በግልጽ ቢከለክልም እንኳን በሰራዊቱ ውስጥ የድብቅ የሕወሀት አደረጃጀት ፈጥሮ በሰራዊቱ ውስጥ የልጅና የእንጀራ ልጅ ስሜት ፈጥሮ የሚከፋፍል እኩይ ኃይል ነው ይህን ሰራዊት የተቆጣጠረው።
በፌዴራል ፖሊስና በአጋዚ ልዩ ኮማንዶ ውስጥ ነግሶ የሚታየው ሁኔታ ከላይ ከዘረዘርናቸው የተለየ አይደለም። ሠራዊቱ የአዛዦቹ አገልጋይ በመሆን የበይ ተመልካች የሆነበት መዋቅር ነው። ሞት፣ የአካል መጉደልና ድህነት ለሠራዊቱ አባላት፤በአንፃሩ ምቾችና ድሎት ግን ለአዛዦቹ እንዲሆን ታቅዶ የተደራጀ ሠራዊት ነው። 
ኢትዮጵያ በየዘመኑ እያደገና እየዘመነ የመጣ ሞያን፣ ችሎታንና ወታደራዊ ሳይንስን አዳብሎ የታጠቀና ከተለያዩ የአገራችን ክፍሎች የተዉጣጣ ዘመናዊ የአገር መከላከያ ተቋም የነበራት አገር ነበረች። ዘረኞቹ የወያኔ መሪዎች አዲስ አበባን ሲቆጣጠሩ ይህንን ዘመናዊ የአገርና የወገን መከታ የሆነዉን ሠራዊት አፍርሰዉና ለእናት አገሩ የተዋደቀዉን ሠራዊት ለማኝ አድርገዉት ነዉ በህወሓት የበላይነት የሚመራ አዲስ የመከላከያ ሠራዊት የገነቡት። ይህ ህወሓት የገነባዉ ሠራዊት በአደረጃጀቱም ሆነ በቀን ከቀን ስራዉ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅምና ፍላጎት ጋር በምንም መልኩ የተገናኘ አይደለም። ይህንን መከላከያ ሠራዊት የፈጠረዉ ህወሓት፣ የሚመራዉና የሚቆጣጠረዉ ህወሓት፤ ሠራዊቱ በሚወስዳቸዉ እርምጃዎች ሁሉ ዋነኛዉ ተጠቃሚም የህወሓት/ኢህአዴግ ጥቂት ዘራፊ መሪዎች ብቻ ነዉ። 
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሆይ! 
ህወሓት/ኢህአዴግ ለኢትዮጵያና ለሕዝቦቿ የደገሰዉ የጥፋት ተልዕኮ ካልተሳካ አንተን እንደለመደዉ ሜዳ ላይ በትኖና ባንተ ትከሻ ላይ እንደመዥገር ተጣብቆ የዘረፈዉን የአገር ሀብትና ንብረት ይዞ አገር ለቅቆ እንደሚጠፋ ምንም ጥርጥር የለዉም። ለዚህ የሽሽት ጉዞዉ ደግሞ ለረጂም ግዜ ተዘጋጅቷል። በቢልዮኖ ዶላሮች የሚቆጠር ሀብት በውጭ ሀገሮች አስቀምጧል። በዚህ ሠራዊት ዉስጥ የአገሩን ዳር ድንበር የጠበቀ እየመሰለዉ የህወሓት መሳሪያ ሆኖ የራሱን ወገኖች ከሚገድለዉ ኢትዮጵያዊ ዉስጥ ከአስር ዘጠኙ የህወሓት/ኢህአዴግን መወገድ የሚናፍቅ ዜጋ ነዉ። ችግሩ ይህ ሠራዊት ልክ እንደ ሲቪል ወግኖቹ በዘርና በቋንቋ ተለያይቶ የተደራጀ በመሆኑ እርስ በርስ ተገናኝቶ መነጋገርና መወያየት አለመቻሉ ነው። 
ይህ ሙሉ በሙሉ በህወሓት ቁጥጥር ስር የሚገኘዉ ሠራዊት ባለፉት ሀያ አምስት ዓመታት የወሰዳቸዉን ፀረ ሕዝብና ፀረ አገር እርምጃዎች አንድ በአንድ ስንመለከት ይህ ተቋም በሚወስዳቸዉ እርምጃዎች የሚጎዳዉ የሠራዊቱ ጡንቻ የሚያርፍበትን የኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የሠራዊቱ አባላት እራሳቸዉም የራሳቸዉ እርምጃ ሰለባዎች ናቸዉ። ታድያ ለምንድነዉ ይህ ሠራዊት ከ25 አመት በላይ እሱን እራሱን፣እናቱን፣አባቱን፣ እህቱንና ወንድሙን የሚጎዳ እርምጃ የሚወስደዉ? የአገርን ዳር ድንበር ከባዕዳን ወራሪዎች ለመከላከል የተደራጀና የታጠቀ መከላከያ ሠራዊት ለአዛዦቹ መታዘዝ እንዳለበት ከማንም የተሰወረ አይደለም። ሆኖም አንድ የአገሬን አንድነትና የወገኖቼን ደህንነት እጠብቃለሁ ብሎ ቃለ መሃላ የፈጸመ የመከላከያ ሠራዊት አባል ደህንነቱን መጠበቅ የሚገባዉን ሕዝብ በነጋና በጠባ ግደል ተብሎ ትዕዛዝ ሲሰጠዉ ትዕዛዙን ከመፈጸሙ በፊት ማንን ነዉ የምገድለዉ ለምንስ ነዉ የምገድለዉ ብሎ እራሱን መጠየቅ አለበት።
ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘመናዊ የባርነት አዋጅ ታዉጆበታል። ህወሓት ይህንን አዋጅ ተግባራዊ ለማድረግ የሚሯሯጠዉ አንተን ከሕዝብ አብራክ የወጣኸዉን የሕዝብ ልጅ በመጠቀም ነዉ። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትና የፖሊስ ሀይል ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነጻነትና እኩልነት ይዋጋል እንጂ እሱንና ወገኖቹን የህወሓት ባሪያ የሚያደርግን አዋጅ አያስፈጽምም። ይህ አገርንና ሕዝብን ለመጠበቅ ህገ መንግስታዊ አደራ የተሸከመ ሠራዊት የታጠቀዉን መሳሪያ ማዞር ያለበት በወንድሞቹና በእህቶቹ ላይ ሳይሆን ሠራዊቱንና ኢትዮጵያን በትኖ ለመጥፋት ዝግጅት እያደረገ ባለዉ በጠላቱ በህወሓት ጥቂት ዘራፊ የሲቪልና ወታደራዊ መሪዎች ላይ ነዉ።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት ሆይ! 
የኛ ፍላጎት ፍትህ፣ነፃነት፣ እኩልነትና ዲሞክራሲ የሰፉኑባት ኢትዮጵያ እዉን ሆና ማየት ነዉ። እርግጠኞች ነን የእናንተም ፍላጎት ከዚህ የተለየ አይደለም። እነዚህን እኛም አናንተም የምንፈልጋቸዉን እሴቶች ቀምቶን ሁለታችንንም እንደ ባሪያ ረግጦ የሚገዛን ዘረኛዉ የህወሓት/ኢህአዴግ ሥርዓት ነዉ። እናንተና እኛ ይህንን አንድ ላይ የሚረግጠንን ሥርዓት ጎን ለጎን ቆመን በጋራ መታገል ነዉ ያለብን እንጂ እርስ በርስ መተላለቅ የለብንም። ደግሞም ሁለት ፍትህ፣ነፃነትና እኩልነት የናፈቃቸዉ ወንድማማቾች ነፃነታቸውን ቀምቶ የሚረግጣቸዉን ኃይል አንድ ላይ ሆነዉ ይፋለሙታል እንጂ እርስ በርስ አይተላለቁም። በዚህ የነጻነት ትግል ላይ የምንሳተፍ ወገኖችህ ወንድሞቻችንን በመግደል አናንተም እኛን ወንድሞቻችሁን በመግደል የሚገኝ ነገር ቢኖር ባርነትና የአገር አንድነት መፍረስ ብቻ ነዉ። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አገሩንና ወገኖቹን የሚጠብቅ ኃይል ነዉ እንጂ ጠላቶቹ ግደል የሚል ትዕዛዝ በሰጡት ቁጥር በገዛ ወገኖቹ ላይ የሚተኩስ ኃይል አይደለም። 
አንተ የኢትዮጵያ መለዮ ለባሽ ሆይ! 
ዛሬ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በጋምቤላ፣ በአፋር፣ በኮንሶ፣ በቤኒሻንጉልና ኦጋዴን ዉስጥ እህቶችህ “ወንድም ጋሼ” ድረስልን ብለዉ እየተጣሩ ነዉ፤ ወንድሞችህ “ጋሽዬ” አድነን እያሉህ ነዉ፤ አባትህና እናትህ “ልጄ አንተ እያለህ እንዴት እንዲህ ይደረጋል?” ብለዉ እየጮሁ ነዉ። መቼ ነዉ የምትደርስላቸዉ? መቼ ነዉ ከእስርና ከጥይት የምታድናቸዉ? መቼ ነዉ ተስፋ የምትሆናቸዉ?
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትና ፓሊስ አባላት ሆይ! 
የህወሓት አገዛዝ ልትጠብቀው ከሚገባህ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ደም እያቃባህ ነው፤ የውጭ ወራሪን ሳይሆን ፍትህ የናፈቀውን የገዛ ራስህን ወገን እንድትወጋ እያደረጉህ ነው፤ አገርህ ለጥቂቶች ብቻ የምትታለብ ጥገት ሆና ለማቆየት አንተን በመሣሪያነት እየተጠቀሙብህ ነው። የነፃነት ኃይሎች ትግል የገጠሙት ከህወሓት ዘራፊ ወታደራዊና ሲቪል መሪዎች ጋር እንጂ ከአንተ ጋር አይደለም። እነሱ ሁኔታው አላምር ሲል መሸሻ አዘጋጅተዋል፤ እድሜ ልካቸውን በልተው የማይጨርሱት ሀብት በውጭ አገራት አከማችተዋል። ያ ቀን ከመምጣቱ በፊት ግን አንተ የገዛ ወገንህን ገድለህ እንድትጨርስ፤ አሊያም በገዛ ወገንህ ተገድለህ እንድትጠፋ ይሻሉ። እንደምታውቀው በገባንበት ትግል አንተ ብቻ ተኳሽ፤ አንተ ብቻ ገዳይ አይደለህም። የነፃነት ኃይሎች ሊገላቸው የመጣን ኃይል ከመግደል አይመለሱም። በአሁን ሰዓት እንኳን ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የሠራዊቱ አባላት በነፃነት ኃይሎች ተጋድሎ መውደቃቸውን ታውቃለህ። ይህ መሆኑ ያሳዝነናል፤ ልትገድለን ስትመጣ ግን ባዶ እጃችንን አንጠብቅህም። እርስ በርስ የሚያጋድለን የህወሓት አገዛዝ ማብቃት አለበት። አንተ የዚህን እኩይ ስርዓት ትዕዛዝ አልቀበልም፤ ከድንበር መጠበቅ ውጭ የሀገሬን ህዝብ አልገልም ያልክ ቀን፤ ይህ ጦርነት ይቆማል። እንደልባቸው የሚያዙት ጦር እንደሌለ ሲያውቁ የሀገሪቱን የፖለቲካ ችግር በጉልበት ሳይሆን በፖለቲካዊ መንገድ ለመፍታት ይገደዳሉ። ለነጻነትና ለእኩልነት እየተዋደቁ ያሉት ወገኖችህ ልክ እንዳንተ ይህ በአንድ ሀገር ህዝቦች መሀከል የሚደረግ ጦርነት እንዲቆም ይፈልጋሉ። በረሀ የገቡት ገበሬ ዘመዶችህ በሰላም አርሰው ልጆቻቸውን አሳድገው ጥሩ ዜጋ ማድረግ ይፈልጋሉ። መገደል፤ መታሰርና መሰቃየት ሰልችቶት በረሃ የገባው ወጣት ሀገሩ ሰላም ሆና፤ የነጻነት አየር እየተነፈሰ ትምህርቱን በነጻ አዕምሮ ተምሮ ለሀገሩ በጉልበቱና በእውቀቱ አስተዋጽኦ ማድረግ የሚፈልግ እንጂ የጦርነት አባዜ ኖሮበት አይደለም በረሃ የወረደው። ስለዚህ ይህን ጦርነት ማስቆም የምትችለው አንተ ነህ። ይህን የምታደርገው ደግሞ እንዳንተ ሰላምና ነጻነት የሚፈልገውን ወገንህን በመግደል ሳይሆን አንተንም መላው ህዝቡንም አዋርደው መግዛት የሚፈልጉትን ጥቂት ዘራፊዎች እምቢ ማለት ስትችል ነው።
ከዛሬ ጀምሮ የተገኘውን ሁሉ አጋጣሚ ተጠቅመህ ሥርዓቱን በመክዳት የነፃነት ኃይሎችን ተቀላቀል። የሕዝብ ወገኖችን እንድትወጋ ስትታዘዝ እንድትወጋቸው ከተላክባቸው የነጻነትና የእኩልነት ታጋዮች ጋር ተቀላቀል። በአገኘኅው አጋጣሚ ሁሉ በግልም በቡድን መሣሪያህን ወደ ጥጋበኛ ህወሓት አዛዦችህ አዙር። 
በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች ከነፃነት ኃይሎች ጋር የሚቀላቀሉ የሠራዊቱ አባላት የክብር አቀባበል ይደረጋል። ሠራዊቱን የሚቀበሉ የሚያስተናግዱ፣ የሚያቋቁሙ ቡድኖችን በየቦታው አደራጅተናል። ሕዝብ በህወሓት አገዛዝ ላይ እንጂ በአንተ በሠራዊቱ አባል ላይ የያዘው ቂም የለም። እንዲያውም አንተ ራስህ ትግሉን እንድትቀላቀል ይፈልጋል። በሕዝብና በአገር ላይ በደል ሲፈጽም የኖረው የህወሓት አገዛዝ ፍፃሜ ለማፍጠን በሚደረገው ትግል የአንተ አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። 
በኢትዮጵያችን ውስጥ እንዲኖር የምንፈልገው ሠራዊት ታማኝነቱ ለፓርቲ ሳይሆን ለሀገር የሆነ፤ ድንበሯን ከጠላት የሚከላከል፤ በሀገር ፍቅር ስሜት የነደደ፤ ሕዝብ የሚወደውና የሚያከብረው ሠራዊት ነው። ይህ ሠራዊት የሚገነባው በአንተው ነው። የህወሓት ወንበዴዎች ከዚህ በፊት እንዳደረጉት ሠራዊቱን የመበተን ዓላማም ሆነ ፍላጎት ያላቸው የነፃነት ኃይሎች የሉም። እነኝህ ብልሹ መሪዎቹ ተወግደውለት መዋቅሩ እንደተጠበቀ፤ ሹመትና የደሞዝ ጭማሪ በችሎታና ባደረገው አስተዋጽኦ ብቻ እንጂ ለአንድ ድርጅት ባለው ድጋፍ ወይም በዘውግ ማንነቱ ያልሆነ፤ ሙያውና ተጋድሎው ሀገሩን ከጠላት መጠበቅና የህዝቡን ደህንነት ማረጋገጥ የሆነ፤ በተልዕኮ ላይ ቢሰዋ ህዝቡ እንደጀግና የሚቀብረው፤ አካለ ስንኩል ቢሆን ህዝቡ በአክብሮት እስከ እድሜ ልኩ የሚጦረው፤ መለዮ ለብሶ በህዝቡ ውስጥ ሲገኝ ወጣቱ እንደሱ ለመሆን የሚመኘው አኩሪ የኢትዮጵያ ሠራዊት ሆኖ እንዲቀጥል ነው ፍላጎታችን። ይህ ምኞት እንዲሳካ ግን ዛሬ የምትፈጽፈው ተግባር ወሳኝ ነው።
ውድ የአገሬ መለዮ ለባሾች፤ 
ለዴሞክራሲ ሲሉ እየታገሉ በሞቱትና አሁንም በሚታገሉት የሕዝብ ኃይሎች ስም የማቀርብላችሁን ጥሪ አድምጡኝ። ነፃ ሊያወጣችሁ እየታገለ ባለ ሕዝብ ላይ ፈጽሞ አትተኩሱ። ሕዝብ ላይ መተኮስ ማለት፤ የነፃነት ታጋዮች ላይ መተኮስ ማለት፤ በገዛ ራሳችሁ ላይ መተኮስ ማለት እንደሆነ እወቁ። ጤነኛ አዕምሮ ያለው ሰው እንዴት በገዛ ራሱ ጭንቅላት ላይ ይተኩሳል? የእስከዛሬው በቅቶን ከእንግዲህ መንገዳችሁን አስተካክሉ። ከቻላችሁ ይህን የባርነት አዋጅ ለማስፈጸም ስንል ከሕዝብ ጋር አንዋጋም ብላችሁ በኅብረት ቆማችሁ ይህንን ጦርነት አስቁማችሁ ሀገሪቱን ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ሽግግር ለመውሰድ ታገሉ። ይህን ካልቻላችሁ የሕዝብን ትግል ተቀላቀሉ። በግልም ይሁን በቡድን መሠሪ የህወሓት ጄኔራሎችና አለቆቻችሁን በማስወገድ የጀግንነት ታሪክ ሥሩ። 
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትና ፓሊስ አባላት ሆይ! 
የኛ ፍላጎት ፍትህ፣ ነፃነት፣ እኩልነትና ዲሞክራሲ የሰፈነባት ኢትዮጵያ እዉን ሆና ማየት ነዉ። የእናንተም ፍላጎት ከዚህ የተለየ አይደለም።ከሕዝብ ጎን ቁሙ፤ ሕዝብ በጎናችሁ ይቆማል: 
ኢትዮጵያ አገራችን በክብር ለዘላለም ትኑር።

No comments:

Post a Comment