Friday, October 14, 2016

“የለውጥ ሃይሎች” ግልፅና ደፋር ውይይት ለመፍትሔና የጋራ ድል!! (“ታሳቢ ሦስት”) – ኤርሚያስ ለገሰ ለህዝብ የውይይት መድረክ የተዘጋጀ (ቺካጎ/ኢሊኖይ)


ኤርሚያስ ለገሰ
የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቭዥንና ራዲዮ(ኢሳት)
ጥቅምት/2016

  ማስታወሻ       

*ይህ ጽሁፍ ከራሴ ውጭ የምሰራበትን የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቭዥንና ሬዲዮ (ኢሳት)ን ጨምሮ የማንንም አቋም አያንፀባርቅም::
**“የአዲስ አበባ ነዋሪ” (“አዲስ አበቤ”) የሚለው ቃል ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሆኖ በአዲስ አበባ የሚኖር አሊያም ለወደፊት የመኖሪያውን አዲስ አበባ ለማድረግ የፈለገን በሙሉ የሚያጠቃልል ነው።

  1. መንደርደሪያ

revolution-satenaw-news
የዛሬ ሦስት ወራት አካባቢ ከኦሮሞ አክቲቪስት ገረሱ ቱፋ ጋር በኢሳት ስቱዲዮ ለአጭር ሰዓታት ኢ-መደበኛ ወግ ጠርቀን ነበር። ገረሱ በወጋችን መሀል “ለጋራ መፍትሔ ግልፅና ደፋር ውይይት የማድረጊያው ሰዓት አሁን ነው” በማለት ይናገር ነበር። መልሶ መላልሶም “የጋራ ችግር አለብን፤ ያልተነጋገርናቸው እና በይደር ያቆየናቸው ድፍረት የሚጠይቁ አጀንዳዎች ከፊታችን ተቆልለዋል። በግልፅና በሐቅ ተወያይተን መፍትሔ ልናበጅለት ይገባል” እያለ የቀጣይ ስጋቱን ይዘረዝር ነበር። የዛሬን ብቻ ሳይሆን የነገንም ጭምር። የነገንም ብቻ ሳይሆን የተነገወ ዲያውም። ለልጅና ልጅ ልጆቻችን!

ከቀናቶች በኋላ ይሄንኑ አባባል  በኦሮሞ ጉዳዮች ላይ ብዙ ምርምር ከሰራውና የወቅቱ የኦሮሞ ጥናት ማዕከል ፕሬዝዳንት ከሆነው ፕሮፌሰር ህዝቅኤል ጋቢሳ ሰማሁት። ርግጥ ከላይ ከተገለጠው የገረሱ አባባል ጋር ቃል በቃል የተገለጠ አይደለም። መንፈሱ ግን ተመሳሳይ ነው። አገር አደጋ ላይ ወድቃለችና የልባችንን አውጥተን እንነጋገር፤ እንመካከር የሚል ነው። ዛሬ አገራችን ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ የማያሳስበው ዜጋ ያለ አይመስለኝም። በሌላም በኩል ወርቃማ የለውጥ ሁኔታን በብስለት ካልያዝነው ከእጃችን ሊወጣ ይችላል የሚል ነው። የህዉሃት መራሹ መንግስት የአገዛዝ ፖሊሲ መሰረት ያደረገው የኢትዮጵያ የለውጥ ሃይሎች የማይተባበሩ፣ በፖለቲካ ስልጣን፣ ብሄርና ሃይማኖት ተከፋፍለው የውስጥ ሽኩቻ የሚያደርጉ የሚለው ክስ ወደ እውነት እንዳይቀየር ነው።

“ግልፅ ውይይት” የሚለው አባባል በጽሁፍና በቃል ሲገለጽ ቀላል ሊመስል ይችላል። ወደ ተግባር ሲገባ ግን እጅግ ከባድና ውስብስብ ጥያቄዎችን ማስነሳቱ አይቀርም። ከባድ የሚያደርገው ወደ ተግባር የማይቀየር ስለሆነ አይደለም። ይልቁንስ ከባድ የሚያደርገው ይህን አስተሳሰብ አቅጣጫ የሚለውጥ ውይይት ለማድረግ ለሚጠይቀው መስዋዕትነት ምን ያህል ተዘጋጅተናል የሚለው ይመስለኛል። የተለያዩ ጥቅሞችና ፍላጎቶችን ለማጣጣምና ለጋራ ድል (win- win) በሁላችንም ዘንድ ምን ያህል ፍቃደኛነቱ አለ የሚለውም በተዛማች ሊነሳ የሚችል ነው። ህወሐት የሚባል የጋራ ጠላት ላይ በሚደረገ ርብርብ (ትክክል እንደሆነ አምናለሁ) በተቀየሰ ስልት በአርምሞ የተያዙ ግን ደግሞ ሃራምባና-ቆቦ የሚመስሉ አመለካከቶች እንዴት ይስተናገዳሉ የሚለውም የውይይቱን ውስብስብነት ማሳየቱ አይቀርም። ወደ ነገይቷ ኢትዮጵያ መንግስታዊ አወቃቀርና ስርአት ስንገባ ደግሞ ይበልጥ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያስፈልግበት ሁኔታ እናያለን።
አሁን ያለንበት ወቅታዊ ሁኔታ በእርግጥም ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ የገባንበት ነው። ህዉሃት በዘረጋው የአንድ ብሔር የበላይነት ለማምጣት በዘረጋው የዘረኛ ፖሊሲ ምክንያት የአንድ አገር ልጆት ጣት እየተጠነቋቆሉ ወደ ሚፋጁበት ዘመን ላይ እየደረስን ነው። ኢትዮጵያ ወደ አገር አቀፍ የብጥብጥና ቀውስ ሁኔታ ውስጥ ገብታለች።ይህንን ቀውስ ለመሻገር “ተከድኖ ይብሰል” የሚባልበት አይደለም። ወቅቱ ከአንገት በላይ አፍአዊ አቋም የሚወሰድበት ብቻ ሳይሆን በቁርጥ ወደ ተግባር የሚያሸጋግር መሆን ይገባዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ የመንግስት ለውጥ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ አስተሳሰብ ለውጥም እየተደረገ በመሆኑ የሚኖረው ውይይትና ክርክር (Diccourse) ይሄንን በሚመጥን ዳራ (diccourse) መስተናገድ ይኖርበታል። ስለዚህ የስርአት ለውጥን በተመለከተ እርስ በራስ መነጋገር የሚገባን ኢትዮጵያውያን የምናመነጨው መፍትሔም ሆነ የውይይት አግባቡ ይህን ሊመጥን ይገባል።
እዚህ ላይ ከውይይቱ በፊት አጽንኦት ሊሰጠው የሚገባ ነገር በቅድሚያ ማንሳት ያስፈልጋል። በውይይቱ ወቅት ወጣ ያለ አስተሳሰብ ያላቸው ዜጎች ካሉ መስኪድ ሲኬድ እንዳቋረጠ አሊያም ቤተክርስቲያን እንደገባ ውሻ ሁሉም የማሪያም ጠላት እያለ ሊቀጠቅጣቸው አይገባም። በዚህ በሰለጠነው ዘመን በለውጥ ሃይሎች መካከል ያለ አስተሳሰብ መሸነፍ ያለበት በአስተሳሰብ ብቻ ነው። በመሆኑም ሰዎች የሚፅፉትና የሚናገሩትን በታጋሽነት መስማትና የሃሳብ እክብሮት መስጠት ያስፈልጋል። የግለሰቦችን አስተሳሰብ አክብሮ እንደ አመጣጡ መመዘንና መመርመር ለቀጣይ ነፃነት ዋስትና ይሰጣል። አስተሳሰብን በአስተሳሰብ ማሸነፍ የማይፈልጉ የለውጥ ሃይሎች ከጅምሩ ለለውጥ ያላቸውን አመለካከት መመርመር ያስፈልጋቸዋል።
የተነሳንበትን መንደርደሪያ ለመቋጨት ያህል “ግልጽና ደፋር ውይይት” ለማድረግ ወቅታዊ የፖለቲካ ሂደት የሚጠይቀውና መድረኩ መፈጠር እንዳለበት ለጥያቄ የሚገባ አይደለም። በይደርም ማቆየት አይቻልም። በዚህ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያን ፖለቲካ በቅርበት ከሚከታተሉ (የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ጭምር) ወዳጆቼ ጋር ስንነጋገር “ወቅቱ ነወይ?” የሚል ጥያቄ አንስተን ተከራክረናል። የድመትና አይነምድሯን ትርክት አንስተን ተጨዋውተናል። ሁላችንም እንደምናውቀው ከፍጥረታት ሁሉ ድመትን የምናደንቅላት አንድ ተፈጥሮአዊ ባህሪ አላት። ይህም አይነምድሯን መሬት ቆፍራ በጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ትቀብረዋለች። ቆሻሻዋ እንዳይታይ ተደጋግማ በመመላለስ አፈሩን በመጫር በአቅሟ ልክ አፈር ታለብስበታለች።
ከዚህ ጋር ተያይዞ “ወቅቱ አይደለም” የሚሉት ወዳጆቼ የሚያነሱት መከራከሪያ አሁን እየተፈጠረ ያለውን መቀራረብ ጥላሸት እንዳይቀባው አሊያም ወደኋላ እንዳይመልሰው ከሚል ፍርሃት የሚመነጭ ነው። በተለይም ለረዥም አመታት በታቀደ መልኩ በተሰራ “የመከፋፈል ፖለቲካ” ምክንያት ሁለት ጥግ ተቀምጠው የነበሩት የኦሮሞና አማራ የፖለቲካ ሃይሎች የጋራ ጠላታቸው የሆነው ህዉሃት ላይ ለመረባረብ ቅድሚያ በመስጠት በቅንጅት እየሰሩ ባለበት ሁኔታ ወደ ውይይትና ክርክር መግባቱ አገዛዙን ሊጠቅመው ይችላል የሚል ፍርሃት አላቸው።
የእነኝህ ሰዎች ፍርሃት መሰረት ያለው መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም። በፖለቲካ ሃይሎች መካከል በጠንካራ መሰረት ላይ መገንባት ያልቻለ መተማመን ባለበት ሁኔታ ከግምት የማይገቡ ጥቃቅን ድርጊቶች የቅራኔ ምንጭ ሊሆኑ ይችላሉ። የሚነሱት ቅራኔዎች በፍጥነት ምላሽ ካላገኙና ወደ አጠቃላይ ማህበረሰቡ ከተሸጋገሩ እርስ በራስ በመወነጃጀል ሀዲዱን ሊስቱ ይችላሉ። ደግነቱ በህዝቦች መካከል ያለው በደም የተሳሰረ ጠንካራ ግንኙነት የፖለቲካ ሃይሎችን የመግራት እድሉ ሰፊ ነው። ቢሆንም “ነቀፌታ ጠል” መሪዎች እየበዙ በሄዱ ቁጥር መልካም ግንኙነቶች እየሻከሩ መሄዳቸው አይቀርም። ትልቁን ስዕል ትቶ የሆነ ባልሆነው መዘራጠጥ የለውጥ ግፊቱን ሊቀንስ ይችላል።
በመሆኑም በለውጥ ሃይሎች መካከል ባለፉት ሩብ ክፍለ ዘመናት የፖለቲካ ሃይሎች ጉዞ ላይ ውይይትና ክርክር በማድረግ ተቀራራቢ አቋም መውሰድ ይኖርበታል። በዛሬና የነገን የኢትዮጵያን እጣ ፋንታ በሚወስኑ መሰረታዊ አቋሞችና ንጣፎች ላይ ሁሉን አሳታፊና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ፍርጥርጥ አድርጎ መነጋገር መጀመር እንዳለበት እምነቱ አለኝ። ይህ መደረግ ያለበት የትላንትና ላይ በመጨቃጨቅ ዛሬና ነገን ለመርሳትም አይደለም። ይልቁንስ በመተማመን ላይ የተመሰረተ አሳታፊና ዲሞክራሲያዊ ውይይት ማድረግ ልዩነቶችን ከማጥበብም አልፎ በተራ የመንደር ወሬና አሉባልታ መለያየት እንዳያመጣ ያደርጋል። በቀጣዩ አካሄድ ላይ ከስሜት በፀዳ ሁኔታ መስተካከል የሚገባቸውን በመለየት በቅን ልቦና ተቀብሎ ለመጓዝ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል። ትላንት ተፈጠረ የተባለን የአፍ ወለምታም ሆነ ተጨባጭ ስህተት መልሶ መላልሶ መውቀጥና ማመንዠክ የአገዛዝ ዘመኑን ከማራዘም ውጪ የሚፈይደው ነገር የለም። የድመቷ ባህሪ እዚህ ጋር ሊመጣ ይገባል። በሌላም በኩል ዛሬ ደግሞ “እከሌ ይሄን ተናገረ” በሚል በግለሰቦች አገላለጥ ላይ በመመስረት የሚታይ ፍንደቃ የትም አያደርስም። የተጠቀሱት ግለሰቦች ሰዎች ናቸውና ነገም ሌላ ነገር ሊሉ ይችላሉ። ሊወድቅም ይችላል። ለማንም ግልፅ እንደሆነው አሁን ያለንበት የትግል ምዕራፍ ተለዋዋጭ እና ከሁኔታዎች ጋር እየተዛመደ መሄድ ያለበት ነው። ከእነዚህ ነባራዊ እውነታዎች ጋር መጓዝ የማይችል መሪ መከተል ትግሉ ሄዶ ሄዶ የመምከን እጣ ፋንታ ሊደርሰው ይችላል።

በዚህ መሰረት ለውይይት መነሻ እንዲሆን ይህ ፅሁፍ ተዘጋጅቷል። ጽሁፉ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ጉዞ ያለፉትን ሩብ ክፍለዘመን መሪ ተዋንያን ለመነካካት ይሞክራል።  የመጀመሪያው ክፍል በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ለ25 አመታት ከፊት መስመር በመሆን አስከፊ አገዛዝ ስርአት ያሰፈነውን ህወሃት ይዳሰሳል። “የህወሃት የሩብ ክፍለ-ዘመን አዙሪት” በሚል ርዕስ እንዲቀርብ ተደርጓል። በክፍል ሁለት ሦስትና አራት በሚዘጋጁ መጣጥፎችና ክፍሎች የተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ሲቪክ አደረጃጀቶች፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት፣የኪነ-ጥበብና ሚዲያ ተቋማት የሩብ ክፍለ ዘመን ጉዞ ላይ ለማተኮር ይሞክራል። ከዚህም በተጨማሪ በአሁን ሰዓት በኢትዮጵያ የተቀጣጠለው ህዝባዊ ማዕበል ምን አይነት ባህሪ እንዳለው፤ በህዝባዊ ማዕበሉ ውስጥ ያለው የሃይል አሰላለፍ፤ ማዕበሉ የሚፈጥረው ለውጥ በምን መርሆዎችና እምነቶች (ለውጥ ለምን?፣ ለማን፣ ምን ለማግኘት፣ እሴቶቹ ምንድናቸው?) የሚመለከት ይሆናል። ይህም “ኢትዮጵያ ከህወሃት በኋላ እጣ ፈንታዋ ምን ሊሆን ይችላል” ወደሚለው የመጀመሪያው መጨረሻ ምዕራፍ ይወስደናል።

ማሳሰቢያ፡ የቺካጎው የውይይት መድረክ የሚኖረው ጊዜ ውስን በመሆኑ በዚህ ጽሁፍ ላይ የመጀመሪያው ክፍልም ሆነ በተከታታይ የሚዘጋጁት ጽሁፎች አልቀረቡም። በሌላ መጣጥፍ በተከታታይ የሚዳሰሱ ይሆናል። በመሆኑም በዚህኛው መድረክ ለመጣጥፎቹ መነሻ የሆኑኝ (“ታሳቢዎች”) ውስጥ አንደኛው ብቻ “ታሳቢ ሦስት” ለውይይት በሚያግዝ መልኩ ቀርበዋል። እነዚህ ለዶክመንቱ መነሻ የሆኑ ታሳቢዎች ለሚካሄደው ውይይት እንደመንደርደሪያ የሚያገለግሉ ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ።

ታሳቢ አንድ፦ የህዉሃት አገዛዝ ይወድቃል። የሚወድቀው ግን በከባድ መስዋዕትነት ነው። ከተከፈለው ያልተከፈለው መስዋዕትነት ይበልጣል።
ታሳቢ ሁለት፦ የኢትዮጵያ አንድነት እንደተጠበቀ ይቆያል። የለውጥ ሃይሉ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ አይደራደርም።
ታሳቢ ሦስት፦ የአዲስ አበባ ነዋሪ የስርአት ለውጥ ይፈልጋል። ህዝባዊ ማዕበሉን ለማቀጣጠል ዝግጅነቱ ከፍተኛ ነው።
ታሳቢ አራት፦የለውጥ ሃይሉ ከህወሃት የቀድሞ የጦር ጄነራሎችም ሆነ አመራሮች ብዙ መጠበቅ የለበትም።
ታሳቢ አምስት፦ ከአጭር ጊዜ አኳያ የተገኘው ድል በብስለትና በፅናት ካልተያዘ ሊዳፈን ይችላል።

በአጠቃላይ መልኩ አሁን ያለንበት ሁኔታ በአንድ በኩል የስርአት ለውጥ ተስፋ በቀኝ እጃችን የጨበጥንበት፤ በሌላ በኩል በአገር ደረጃ ውድቀትና መበታተን ሊያመጡ የሚችሉ ችግሮችን እየታዩ ያለበት ነው። ያለምንም ማጋነን ብርሃንና ጨለማ መሳ ለመሳ የተጋመዱበት ሁኔታ ላይ ነን። ብርሃን ጨለማን አሸንፎ አልወጣም። ጨለማም ብርሃንን የደፈቀበት ሁኔታ አልተፈጠረም። በመሆኑም ብርሃን ጨለማን አሸንፎ እንዲወጣ ከተፈለገ በአገሪቱ ጉዳዮች ላይ በድብቅና በሹክሹክታ ሳይሆን በግልፅና ሃላፊነት በሚሰማው መልኩ መወያየት ያስፈልጋል። ለመውደቅ እየተንገዳገደ ባለው የህዉሃት ዘመንና ከዛ በኋላ ስለሚኖረው ሁኔታ በጋራ መምከርንና ያለንን ሃይሉ በሙሉ ተጠቅመን በመፍትሄዎቹ ላይ መረባረብ ይኖርብናል። ይህንን ማድረግ ከተሳነን ተመልሰን ወደ ዜሮ የምንገባበት እና ታሪክ ይቅርታ የማይለን ስህተት ውስጥ ኢትዮጵያን ልንከታት እንችላለን።

በመሆኑም ያለውን የሰጠ ንፉግ አይባልምና ሁላችንም እንደ አቅማችን ለትብብርና የጋራ መስራት አስፈላጊ ናቸው የምለውን ጠቃሚ ሃሳቦች እንወርውር። እንወያይ ። እንመካከር። በመተማመን ላይ በተመሰረተ ሁኔታ ወደ ተግባር እንግባ። ይህንን ከግምት በምክተት እኔም እንደ አቅሚቲ የሚከተሉትን የመወያያ ነጥቦች ሰንዝሬያለሁ። ለዛሬው አስቀድሞ እንደተጠቀሰው ለጽሁፌ መነሻ ከሆኑኝ አምስት ታሳቢዎች ውስጥ አንዱ ብቻ (“ታሳቢ ሦስት”) የማቀርብበት ይሆናል። ሦስተኛው ታሳቢ አዲስ አበባን የተመለከተ ሲሆን “የአዲስ አበባ ህዝብ የስርአት ለውጥ ይፈልጋል ወይ?፤ ህዝቡ ምን አይነት ችግሮች አሉበት?፤ ነዋሪው ህዝባዊ እምቢተኝነቱን በተሞላ መንገድ እንዲቀላቀል ምን መደረግ ይኖርበታል?” የሚለውን ለውይይት መነሻነት አቀርባለሁ። ስለ አዲስ አበባ መነጋገር ስለ ኢትዮጵያ መነጋገር እንደሆነ እምነት ስላለኝ የውይይታችን አድማስ በመዲናችን ላይ ብቻ የታጠረ አይሆንም።

ታሳቢ ሦስት፦ የአዲስ አበባ ነዋሪ ስር-ነቀል የስርአት ለውጥ ይፈልጋል። ህዝባዊ ማዕበሉንም ለማቀጣጠል ዝግጁነቱ ከፍተኛ ነው።

3.1 የአዲስ አበባ ህዝብ ዘርፈ ብዙ ችግሮች
የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የኢትዮጵያ ህዝብ ስቃይና የጭንቀት ጽዋ ሞልቶ እንደፈሰሰ በግላጭ የሚያውቁት ሀቅ ነው። የአዲስ አበባ ህዝብ በዚህ የጭንቅ ወቅት በንዴትና በቁጭት በየቤቱ እንደሚብሰለሰል ይታወቃል። ህዝቡ በአራቱም ማዕዘናት በአገዛዙ የሚካሄደውን የህዝብ ፍጅት ከየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ከሚኖረው ወገኑ በላይ የመመልከት እድል ስላለው እና የግፉም ተቋዳሽ በመሆኑ ጭንቀቱም በዛው ልክ ነው። የሚሞተው ህዝብ ብቻ ሳይሆን አገር እንደሆነ ያውቃል። በመሆኑም የአዲስ አበባ ህዝብ በቁሙ እየሞተ ኢትዮጵያ እየፈረሰችና ላካራ እየተዘጋጀ ለሩብ ክፍለዘመን እና ከዛ በላይ ዘመን እየተመለከተ “ህዝባዊ ማዕበሉን” አይቀላቀልም ብሎ ማሰብ የሚችለው ከህዝቡ ስነ-ልቦና ርቆ የተቀመጠው ብቻ ነው። ተወደደም ተጠላም የኢትዮጵያ አንድነትና የጋራ ኑሮ መናጋት ከየትኛው የሀገሪቱ ክፍል በላይ የህልውና ጥያቄ የሚሆንበት ለአዲስ አበባ ህዝብ ነው። ይሄ መታበይ አይደለም!!
ኢትዮጵያ ከሌለች አዲስ አበባ የለችም። ኢትዮጵያ ከፈረሰች አዲስ አበባም ትፈርሳለች። እናም የአዲስ አበባ ነዋሪዎች “ኢትዮጵያ!” “ኢትዮጵያ!” የሚሉት ወደው እና ፈቅደው ብቻ አይደለም። እንደ ሰው የመኖር /ያለመኖር የህልውና ጥያቄ ከፊታቸው ስለተጋረጠ ነው። ስለዚህ የኢትዮጵያ የአንድነት ዋስትና ለእያንዳንዱ የአዲስ አበባ ዜጋ የህይወት ዋስትና ነው። የአዲስ አበባ ህዝብ ከመኖርና ያለመኖር ጥያቄ በመለስ ሌሎች በአገዛዙ የተነጠቋቸው መሰረታዊ መብቶች አሉን። ከነዚህ ውስጥ የመጀመሪያ እንደ ሰው የመቆጠር ነው። በዲሞክራሲያዊ ስርአት ውስጥ የሚኖሩ አገሮች “ለሠው ልጅ” ትልቅ ክብር ይሰጣሉ:: የአንድ ሀገር የማይተካው ሀብት የሠው ሀብት ነው:: በመሆኑም የአዲስ አበባ ነዋሪ ዋነኛ መሠረት የሆነው የግለሰብ መብት መከበር መቻል አለበት::
ህዉሓት ወደ ስልጣን ከመምጣቱ በፊት አዲስ አበባን እንደ ጠላት በመፈረጁ በመዳፉ ካስገባት እለት ጀምሮ የቆሰለ አውሬ ጠባይ ከማሳየት ተቆጥቦ አያውቅም። ቁጥሩ ቀላል ያልሆነ የአዲስ አበባ ህዝብ በደርግ ከደረሰበት ግድያ ግፍና መከራ፣ የመናገር የመጻፍና የመቃወም ዲሞክራሲያዊ መብት እጦት ምክንያት ህዉሓት ለመመልከትና እድል ለመስጠት ፍቃደኛ የሆነ ነበር። እርግጥ አንዳንዶች እኩይና ተናካሽ ባህሪውን አስቀድመው በመገንዘብ በአደባባይ ቢቃወሙም የተወሰኑት በሩን ገርበብ ከማድረግና በአርምሞ ለመመልከት በጎ ፍቃድ ታይቶባቸዋል። የሚያሳዝነው የከተማው ነዋሪ የህወሃትን መጥፎ ጽዋ ለመቅመስ ወራቶች አልፈጁበትም። ህወሓት በአዲስ አበባ ህዝብ ውስጥ መሞት የጀመረው ገና ሳይደላደል “የመከፋፈል ፖለቲካ” ይዞ መሆኑ የሚያከራክር አይደለም።
ለሁሉም ግልፅ እንደሆነው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በመሰለውና ያዋጣኛል በሚለው አደረጃጀት ውስጥ ቢታቀፍ መብቱ እንደሆነ ይገነዘባሉ። ይህንን የፖለቲካ መብቱንም ያከብራሉ። ዜጎች ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብታቸው ሳይሸራረፍ ተከብሮ በፈቀዱትና ባሻቸው የተናጠልና የጋራ አደረጃጀቶች እየተመሰረቱና ትሥሥራቸውን በሚያጎለብት መንገድ እንዲጓዙ የፀና ፍላጎት አለው። መነሻና መድረሻቸው በኢትዮጵያ አንድነት ውስጥ እስከሆነ ድረስ ተባብሮና ተጋግዞ በጋራ ስርአት እንዲመጣ ከመትጋት ውጪ ሌላ አማራጭ አለ የሚል አስተሳሰብም ሆነ እምነት የለውም።
በሌላ በኩል ህውሓት ለሩብ ክፍለዘመናት በግድ እንደጫነባቸው “የእኔን አመለካከትና አወቃቀር ካልተቀበላችሁ” የሚሉንን ማንኛውንም ግለሰብና ቡድኖች በማያወላዳ መልኩ ይታገላሉ። ከሰው በታች አድርጎ ሊገዛቸው የሚፈልገው ህዉሓትን የመሰለ ጠባብና ወንጀለኛ ቡድን ለማስወገድ የሚያደርጉት ትግል እዛው ሳለ የነገዊቷ ኢትዮጵያ ውስጥ መብትና ጥቅማቸውን ያለምንም መሸራረፍ እንደሚከበር በሚያረጋግጥ መልኩ የሚፈፅሙት ይሆናል። የሚያቀጣጥሉት ህዝባዊ እምቢተኝነት ለዘመናት የተጠራቀመ መከራና ስቃያቸውን ለአንዴና ለነገው በእኩልነት የተመሰረተ ቀጣይ ህይወታቸው ዋስትና የምናረጋግጡበት ነው። የምናደርገው ህዝባዊ ተቃውሞ የጠባቦች ቡድን የሆነውን ህዉሓት ወደ መቃብር እንደሚወስደው የሚያጠራጥር አይደለም። የጊዜ ጉዳይ ብቻ ይሆናል። ታዲያ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ትልቁ ጭንቀታቸው በዚህ መቃብር ላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ተስፋና ዲሞክራሲ እንዴት ይለመልማል የሚለው ነው። ስርአቱ ፍርስራሹን አራግፎ የሚነሳበት ሳይሆን በመቃብር ላይ እኩልነት ፍትህና ብሩህ ተስፋ ማንበብ መቻሉ ላይ ነው።
በትክክልም የአዲስ አበባ ህዝብ ከህዉሃት በኋላ የምትኖረው ኢትዮጵያ ከምንም በላይ ያስጨንቀዋል። የአዲስ አበባ ነዋሪ ለሩብ ክፍለ ዘመን በታቀደ የፕሮፖጋንዳ ስራ እንድትጠላና እንድትናቅ የተደረገችውን ኢትዮጵያ ከመሬት ላይ በማንሳት ኢትዮጵያዊነት ትንሳኤው እንዲመጣ ሃላፊነት አለበት። ዛሬ እንደታየው የአፍሪካ ማፈሪያ ሳይሆን የኩራት ምንጭ ሆና የምትታይበት ሁኔታ እንዲፈጠር ከፍተኛ አደራ አለበት። ይህንን ሚና ለመጫወት ደግሞ አዲስ አበባ ከክብሯ ጋር የሚመጥን ስልጣንና ሃላፊነት ሊኖራት ይገባል።
አስቀድሞ እንደተገለጠው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የህዉሓትን ጠባብ ፍላጎትና ጭቆና የተረዱት አስቀድመው ነው። ህዉሓት አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ የከተማውን ነዋሪ ባይተዋርነት እና ለእሱ ያደሩ ባለሟሎቹን መልምሎ ወደ አዲስ አበባ በማምጣት በግላጭና በስውር በምስለኔ ሲገዛ ቆይቷል። ዛሬም አዲስ አበባ እየተዳደረች ያለችው በህዉሓት መዋቅር በሚመለመሉ ከነዋሪው ጋር ምንም አይነት ትሥሥር የሌላቸው ምስለኔዎች ነው።
እነዚህ ከአዲስ አበባ ነዋሪ ስነ- ልቦና ተንፈራቀው የቆሙ የአገዛዙ ሀይሎችና ባለሟሎች የህዉሓትን ጥቅም ከማስጠበቅና ከማገልገል ውጭ የነዋሪውን ጥቅም የሚያስጠብቁና የህዝቡን ብሶት የሚያጤኑ አይደሉም። ነዋሪውን እንደ ድርና ማግ ያስተሳሰሩ ማህበራዊ አደረጃጀቶችን ለማፈራረስና እትብቱ ከተቀበረበት ቀዬ ለማፈናቀል ቅንጣት ያህል አላወላወሉም። ነዋሪውን ለማሰር፣ ለመግደል፣ ለመሰወር፣ በተደጋጋሚ ከስራ ለማባረር አንዳችም ማቅማማት አላሳዩም። አገሪቱ በብዙ ድካም ያፈራቻቸውን  የተማሩ ሠዎችን ከአመራር ገለል ለማድረግና እንዲሰደዱ በማድረግ አዲስ አበባን ብሎም ኢትዮጵያን የምሁር ምድረ- በዳ ሲያደርጉ አንዳችም ፀፀት አልተሰማቸውም። ጆሮውን በጥጥ የደፈነው አገዛዝ ነዋሪው አስከፊ በሆነ “የከተማ ረሃብ” ተመቶ ከቆሻሻ ገንዳ ውስጥ ትርፍራፊ እየፈለገ ሲበላ ከቁብ አልቆጠሩትም።
ይልቁንስ የእሱን መሬት አስለቅቀው ለራሳቸው እና ለጠባብ ቡድናቸው ቪላዎች በመገንባት ተንደላቀው በመኖር ላይ ይገኛሉ:: የተቀረውን መሬት ደግሞ  ለመጥራት በሚዘገንን በሚሊዮኖች በሚቆጠር ብር በመቸብቸብ ለግል ጥቅማቸው በማዋል ላይ ናቸው:: በመሀል አዲስ  አበባ  በተለይም በቦሌና ዙሪያዋ  “የአፖርታይድ ሰፈሮችን” ፈጥረዋል:: ድሀውን ህዝብ የጎዳና ተዳዳሪ እያደረጉት ይገኛሉ:: የአዲስ አበባ  የቀድሞውን መሠረትና  ስብጥር በማፍራረስ በምትኩ እነሱና ባለሟሏቻቸው እንደፈለጉ የሚፈነጩበት ሁኔታ ተፈጥሯል:: በከተማዋ ዋና ዋና  ቦታዎች በተለይም በመርካቶ እና አካባቢዋ  የሚገኙ ሱቆችና  የንግድ ተቋማትን በቁጥጥር ስር በማዋል የሞኖፖሊ የኢኮኖሚ ስርአት ፈጥረዋል:: በተለይም ከምርጫ 97 በኋላ  የንግድ ተቋማት ነባር ባለቤቶች የሆኑትን የከተማችንን ነዋሪዎች ባማስለቀቅ የእነርሱ ንብረት በሆኑት እንደ ኤፈርት የመሳሰሉ የማፍያ ቢዝነስ ተቋማት እንዲወረሱ አድርገዋል::
ዛሬ በአዲስ አበባችን ጠግቦ በመብላት ወደ ትምህርት ቤት የሚሄዱት እነርሱ እና  እነሱን ለማገልገል ፈቃደኛ የሆኑ ወዶ ገቦች ናቸው:: ሌላውነዋሪ ለልጆቹ የሠነቀው ተስፋ ተጨናግፎ የልጆቹ በረሀብ የታጠፈ አንጀት እየተመለከተ የሚቆዝምበት ሁኔታ  ተፈጥሯል:: የሚበላውን ያጣ “አዲስ አበቤ” ምን አይነት “ኢትዮጵያዊነት” ስሜት ሊሰማው እንደሚችልና ሀገሩን ሊረግም እንደሚችል መገመት ቀላል አይደለም። የስርአቱ ብርቅ ልጆች በስልጣን ብልግና በተገኘ ገንዘብ በመቶሺዎች ወጪ እየወጣላቸው በሀገር ውስጥና በውጭ በሚገኙ ዘመናዊ አስኳላ እያማረጡ የሚማሩበት ሁኔታ ተፈጥሯል:: ዛሬ በአዲስ አበባ ዲሞክራሲያዊ መብት የሆኑት በነፃነት የመናገር የመፃፍ ሠላማዊ ሠልፍ የማድረግ የመቃወም በነፃነት የመደራጀት እውነትን በአደባባይ መናገር የሃይማኖት ነፃነት የሚታሠቡ አይደሉም:: መምህራን በግዳጅ የፓርቲ መዋቅር ውስጥ ገብተው አባል ካልሆኑ የስራ  ዋስትና  እና  እድገት አይፈቅድም:: በቢሮክራሲውና  መንግስታዊ ተቋማት ውስጥ የሹመት ዘይቤና የሹመት መለኪያው ችሎታ  ሳይሆን ታማኝነት ዜግነት ሳይሆን የፓርቲ አባልነት ነው::
እነዚህ ከብዙ በጥቂቱ የተዘረዘሩ መከራዎች የሚያመለክቱን ነገር የአዲስ አበባ ህዝብ በጫንቃው ላይ የተሸከመው ጭቆና ከአቅሙ በላይ እየሆነ መሄዱንና መሰረታዊ የሆነ ለውጥ እንደሚፈልግ የታየበት ነው። ችግሮቹ የበለጠ እየተባባሱና ውስብስብ እየሆኑ የሚሄዱ በመሆናቸው የስርአት ለውጥ (የህወሃት መወገድን) የሚፈልጉበት ሁኔታ ተፈጥሯል። መሰረታዊ የሆነ አዲስ አቀራረብን ይፈልጋል። እንዲያም ሆኖ እንዲመጣ የሚፈለገው አዲስ ስርአት (ከህወሃት መወገድ በኋላ) ተመሳሳይ ስህተት እንዳይፈፀም የተለያዩ ስጋቶች አሉበት። እነዚህን መራር ሀቆች መጋፈጥ ጊዜው የሚጠይቀው ሆኖ ወጥቷል። በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ነዋሪ ለውጡን በተከፈተ ልብ ሊቀበለው የሚችለው እነዚህ ስጋቶች ሲቀረፉለትና የለውጡ አካል መሆን ሲችል ብቻ ነው። ከህወሃት በኋላ የሚቋቋመው አዲስ መንግስት ወደ 5 ሚሊዮን የሚጠጋውን የአዲስ አበባ ነዋሪ በአግባቡ የሚያስተናግድ፣ የህብረተሰቡን ዲሞክራሲያዊ መብት የሚያረጋግጥና የህዝብን ድምፅ የሚሰማ ከሆነ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ የአዲስ አበባን ብሎም የኢትዮጵያን የለውጥ እንቅስቃሴ ከግቡ ለማድረስ ጠንካራ አመራርና አደረጃጀት ይፈልጋል። የስርአቱ ለውጡ ስኬትም ሆነ ውድቀት ዋነኛውና መሰረታዊ ምክንያት የአመራር መሆኑ አይቀርም። ሌሎች የስኬትና ውድቀት ምክንያቶች በሙሉ የሚመነጩትና የሚንጠላጠሉት ከአመራር ጋር የተያያዙ ናቸው። በህዝባዊ እምቢተኝነቱ እና የለውጡ የእድገት ደረጃ ጋር ተለዋዋጭ የሚሆን ራሱን እየለወጠና እያደገ የሚሄድ አመራር የሚሰጥ ሃይል ያስፈልጋል። ደግነቱ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የመላው ኢትዮጵያ ዜጎች በመሆናቸው አመራር ለመፍጠር የሚካሄድ እንቅስቃሴ ፍሬ ማፍራቱ የአጭር ጊዘ ስራ ብቻ ይሆናል።

3.2   የአዲስ አበባ የለውጥ እንቅስቃሴ መሠረታዊ አቋሞችና እምነቶች
በአዲስ አበባ የሚቀጣጠለውን ህዝባዊ እምቢተኝነትና ከዛም በኋላ ያለውን እንቅስቃሴ ለመምራት የሚችሉ መሰረታዊ አቋሞችና እምነቶች መኖራቸው ግድ ይላል። ከዚህ አንፃር ቢያንስ ሦስት አቋሞችና እምነቶች መዞ ማውጣት ይቻላል።
  በመጀመሪያ ደረጃ ከሁሉም አስቀድሞ የአዲስ አበባ ህዝብ ለኢትዮጵያ አንድነትና ለብሔራዊ ጥቅማችን ቅድሚያ የሚሰጥ ለውጥ ይፈልጋል ይሄ ጉዳይ በተድበሰበሰ አባባልና ቀቢፀ-ተስፋ በሚመስል መልኩ መቅረብ የለበትም። የአዲስ አበባ ነዋሪ በመከራ፣ በፀረ- ዲሞክራሲ፣ በከተማ-ረሃብ፣ በምስለኔ…. ወዘተ ከመኖሩም ባሻገር ለኢትዮጵያ አንድነት ባሳየው የፀና እምነት ሲቀጠቀጥ ነበር። የኢትዮጵያ አንድነት አይናጋም በማለቱ በርካታ መስዋዕትነት ከፍሏል። ይህንን ሁኔታ እንደ መጥፎ ታሪክ ወደ ኋላ የሚያየው እንጂ ከፊት ለፊትም የሚጠብቀው ከሆነ ውጤቱ ከድጡ ወደ ማጡ መሄዱ አይቀርም። 5 ሚሊዮን ይጠጋል ተብሎ የሚገመተው የአዲስ አበባ ነዋሪ ህይወቱን ይሰጣል እንጂ የኢትዮጵያን አንድነት ለማናጋት አሊያም ለመገነጣጠል ፍላጎት ካላቸው እካላት ጋር የሚሞዳሞድበት አንዳችም ምክንያት የለውም።
የአዲስ አበባ ህዝብ “ኦሮሞን ገንጥለን ሀገር እንመስርት”፣ “አማራን ገንጥለን አዲስ ሀገር እንገንባ”፣ ትግራይ ሪፐብሊክ እናቋቁም “ኢትዮጵያ እከሌ የሚባለውን ብሄር በኮሎኒ ይዛለች” ወዘተ ከሚሉ ሃይሎች ጋር መነሻቸው ምንም ይሁን ምን ህወሃትን ታግሎ ለመጣል ከሚያደርገው ትግል ባልተናነሰ ይታገላቸዋል። ተደጋግሞ እንደተገለፀው የኢትዮጵያ አንድነት መናጋት ለአዲስ አበባ ህዝብ የአዲስ አበባ ነዋሪ የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ ነው። የምርጫ ጉዳይ አይደለም። የአዲስ አበባ ነዋሪ ሰማይ ዝቅ፣ ምድር ከፍ ቢል ከኢትዮጵያ ህዝብ አብሮ መኖርና አንድነት ላይ የሚደረደር አይደለም።
የአዲስ አበባ ነዋሪ የሚያራምደው ኢትዮጵያዊነት የሁሉም ብሔረሰቦች መብት በእኩል ደረጃ የሚታዩበት ነው።  በተግባርም እየታየ ያለው በመዲናይቱ የሚኖሩ ብሔረሰቦች እርስ በራስ በመጋባት፣ በማህበር በእድር እና ጉርብትና የተሳሰሩ ያለምንም ማጋነን “ትንሿ ኢትዮጵያ” የሚታይበት ነው። የአዲስ አበባ ነዋሪ የሚያራምደው ኢትዮጵያዊነት በዲሞክራሲያዊ ባህልና ከውስጥ የሚመነጭ ነፃነት ጋር ተዋህዶ የሚቀርበውን አማራጭ ነው። መብትና ግዴታዎችን ጠንቅቆ የሚያውቅና በሌሎች ላይ በሃይል ለመጫን የሚያስበውን ነው። ነዋሪው መብትና ግዴታዎቹ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎቹ መሆኑን በሚገባ የሚረዳ፤ መብቱን ለድርድር የማያቀርብና ሊገረሡ የሚፈልጉትን አጥብቆ ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የሚታገል ነው። በሌላም በኩል በሃላፊነትና የህግ የበላይነት ስሜት ለጋራ አላማ መሳካት ግዴታውን መወጣት የሚፈልግ ነው።
በአጭሩ የአዲስ አበባ ነዋሪ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወዳድ አካላቶች ጋር በመቀናጀት ሀገሩን የሚታደግ፣ ብሄራዊ ስሜትና አንድነትን ለመፍጠር ታሪካዊ ሃላፊነት የተሸከመ ህዝብ ነው። ተወደደም ተጠላ አዲስ አበባ የአገራችን ኢትዮጵያ አማካይ ብቻ ሳትሆን አስኳል ናት።

በሁለተኛ ደረጃ የአዲስ አበባ ነዋሪ ያለምንም መሸራረፍና ተጽእኖ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱ ላይ ለድርድር የሚያቀርበው ነገር አይኖርም። ህውሃት እንዳደረገው ይህን ሰፊና ታላቅ ህዝብ ወደ ጎን ትቶ በፓርቲ መዋጮ ለነዋሪው ጥላቻ ያላቸው ካድሬዎችን በማምጣት ለመግዛት መሞከር ፈፅሞ ተቀባይነት የሚኖረው አይደለም። በዚህ ሃሳብ ደግሞ እውነተኛ  የለውጥ ሃይሎች በሙሉ ልብ የሚቀበሉትና የሚስማሙበት በመሆኑ በተግባራዊነቱ ላይ ብዙም ችግር ላያጋጥም ይቻላል። የአዲስ አበባ ህዝብ የሚፈልገው ስነ-ልቦናውን የተገነዘበ፤ ነዋሪውን ያለአንዳች ልዩነቶችና መከፋፈል የሚያስተባብር፤ ለነዋሪው መስዋዕት ለመሆን ልብና መንፈሳቸውን ያዘጋጁ መሪዎችን ነው። ነዋሪው ያገለግሉኛል የሚላቸውን ሰዎች በፍፁም ነፃነት መምረጥ መቻል ይኖርበታል። ከዚህም በተጨማሪ አዲስ አበባ በአለም ከሚገኙ ጥቂት ታላላቅ ከተሞች ውስጥ በርካታ አለም አቀፍ ተቋማት የሚገኝባትና የአፍሪካ መዲና እንደመሆኗ መጠን ከዚህ ደረጃና ክብር የሚመጥን ብስለትና የትምህርት ዝግጅት የሚኖረው አመራር ሊኖራት እንደሚገባ የሚታለፍ አይደለም።
የአዲስ አበባ ነዋሪ በኢትዮጵያ አንድነት የሚያምኑትን ሃቀኛና በራሳቸው የሚተማመኑ መሪዎችን ያለምንም ጣልቃ ገብነት መርጦ ለስልጣን ማብቃት ይኖርበታል። የከተማዋን የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና ማህበራዊ ፖሊሲዎች የከተማዋን ነዋሪዎችና ምሁራን በማሳተፍ ማዘጋጀት የመሪዎቹ ሃላፊነት ይሆናል። በመዲናይቱ ዲሞክራሲያዊ ስርአት እንዲገነባ፣ የህግ የበላይነት እንዲከበር፣ የነዋሪው ድምጽ እንዲሰማና በአጠቃላይ የፖለቲካ ነፃነት እንዲከበር በሙሉ ስልጣን መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል።  አዲስ አበባ እንደ ኢትዮጵያ አስኳልነት የህዝቦቿ የመፃፍ፣ የመናገር፣ የመቃወም፣ መብትን የማስከበር፣ የሌሎች አማራጮችን ሃሳብ የማክበርና እውነትን የመሻት አርአያነቷን (Role Modeling) ሆና መገኘት ይኖርባታል። የፍፁም ዲሞክራሲያዊ መብት መከበርና የዘመናዊ መንግስት አመራር በአፍሪካ ተጠቃሽ ከተማ ልትሆን ይገባል። ይሄ የራስን ገቢ አመንጭቶ ከመጠቀምና የህዝብ ፍላጎትን አጢኖ ባይተዋር ሳያደርጉ ከመንቀሳቀስ ውጭ የሚታሰብ አይደለም።

በሦስተኛ ደረጃ ከላይ ከተቀመጡት በመለስ ባሉ ጉዳዮች ላይ በድርድር ሰጥቶ በመቀበልና በጋራ ድል ላይ በተመሰረተ ሁኔታ ምላሽ የሚገኙ ናቸው። ይህም በአንድ በኩል በፌደራል ደረጃ (ቀጣዩ መንግስት ፌደራላዊ እንደሆነ ታሳቢ ተወስዶ) መልስ የሚሰጥባቸው ይሆናሉ። በሌላ በኩል በአዲስ አበባ ላይ የባለቤትነትም ሆነ ልዩ-ጥቅም ጥያቄ ያለው የኦሮሞ ብሄረሰብ ጋር በውይይትና ድርድር የሚፈቱ ናቸው። በቀጣይ የሚገነባው ስርአት ዲሞክራሲያዊ እስከሆነ ድረስ፤ ስልጣን ከብረት አፈሙዝ ሳይሆን ከእውነተኛ ምርጫ እስከመጣ ድረስ የሚፈጥሩ ልዩነቶች ሊፈቱ አሊያም ሊጣጣሙ ይችላሉ። አዲስ አበባን በተመለከተ የሚደረጉት ድርድሮች አንደኛው ሌላኛው ላይ የበላይነት ለመያዝ ሳያሴር፤ ቂም በቀልና ጥቃትን መሰረት ካላደረገና የራስን ጥቅም ለማስከበር የሌላውን በተመሳሳይ ደረጃ ለማክበር ዝግጁነቱ ካለ እርስ በራስ መተማመን ስለሚፈጥር የሚመጣውን ለውጥ በእምነት ለመቀበልና ለተግባራዊ እርምጃው ሀላፊነት ወስዶ ለመንቀሳቀስ ከፍተኛ እድል ይፈጥራል። የሚደረገው ውይይትና ድርድር የአዲስ አበባ ነዋሪን ወሳኝነት የተገነዘበ ሊሆን ይገባል። በድርድሩ ወቅት የሚፈጠሩ ቅራኔዎች ካሉ እንኳን ቅራኔዎችን ለመፍታት የመንፈስም የተግባርም ዝግጅት በሁሉም የለውጥ ሃይሎች መካከል ሊኖር ይገባል።
ከላይ ከተጠቀሱት ሃቆች በመነሳት የአዲስ አበባን ህዝብ ሰብአዊና ህጋዊ መብቱን የሚያስከብርለት ጎዳና የሚቀይስለት የፖለቲካ ፓርቲ ያልሆነ አደረጃጀት ያስፈልገዋል፡፤ ይህ አደረጃጀት መሰረታዊ መነሻው የኢትዮጵያ አንድነት ተጠብቆ እንዲቆይ፤ ህዝቡ በህብረት በሰላምና ወንድማማችነት እንዲኖር ለማድረግ የሚቀየሱ ውጥኖችን ተቀብሎ በዚህ ውስጥ የአዲስ አበባን ለማረጋገጥ የሚሰራ ይሆናል። ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያ አንድነት መናጋት የለበትም ከሚሉ ሌሎች አደረጃጀቶች (የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ) አብሮ በጋራ የሚሰራበት የመግባቢያ ሰነዶችን ያዘጋጃል። የፖለቲካ ፓርቲዎቹ አደረጃጀት ምንም ይሁን ምን በኢትዮጵያ አንድነትና ሉአላዊነት ላይ የፀና እምነት ካላቸው ጋር ትብብር የሚሰራበት ሁኔታ ይቀይሳል። የአዲስ አበባ ብሎም የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል ከሚሉ ኢትዮጵያውያን ጋር በሙሉ ተቀራርቦ የሚሰራበትን ሁኔታ ያመቻቻል።

            3.3   የአዲስ አበባ የለውጥ እንቅስቃሴ አደረጃጀት
ከላይ የተጠቀሱትን የአዲስ አበባ ህዝብ ፍላጎቶች ለማስፈፀም የሚያስችል “የአዲስ አበባ  ነዋሪ ህዝባዊ እምቢተኝነት አስተባባሪ ግብረ-ሃይል የሚቋቋምበት ሁኔታ መፈጠር ይኖርበታል። አስተባባሪ ግብረ-ሃይል የአዲስ አበባ ነዋሪ (“አዲስ አበቤ መሆን የፈለገ በሙሉ”) አባቶች፣ ምሁራን፣ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት፣ የአዲስ አበባ መምህራን ማህበር፣ ህብረት ስራ ማህበር፣ ንግድ ም/ቤት የከተማ ገበሬዎች፣ ቢሮክራሲ፣ በውጭ የሚኖር አዲስ አበባ የኖረና የወደፊት ህይወቱን አዲስ አበባ ማድረግ የፈለገ ኢትዮጵያዊ በሙሉ…..ወዘተ የሚሳተፍበት ሊሆን ይገባል። ጊዜያዊ ግብረ-ሃይል (Ad-hoc Committee) በኢትዮጵያ አንድነትና ብሄራዊ ጥቅም፣ ራስን በራስ የማስተዳደር፣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የሰብአዊ ዲሞክራሲያዊ መብቶች የሚደራደርባቸውና መግባባት የሚፈጥርባቸው ቢጋር (TOR-Term of Reference) እና የድርድር ሰነዶች የሚዘጋጅ ይሆናል። ለመነሻ የሚዘጋጀው ቢጋር (TOR)  የሚከተሉት አራት አላማዎችን ለማሳካት ቢሆን ይመረጣል።
የመጀመሪያው፦ በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች የተቀጣጠለው ህዝባዊ እምቢተኝነት በአዲስ አበባም በማያቋርጥ ሁኔታ እንዲጀመር ማድረግ
ሁለተኛው፦ በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎችየተነሱትንና የሚነሱትን ህዝባዊ ማዕበሎች መደገፍና በትብብር መስራት። ከለውጥ ሃይሎች ጋር በመሰረታዊ ጉዳይ ላይ መተማመን መፍጠር።
ሦስተኛው፦ ከህዉሃት ውድቀት በኋላ በሚመሰረተው አዲስ ስርአት ውስጥ አዲስ አበባና ነዋሪዎች ስለሚኖራቸው ሰብአዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ሙሉ ለሙሉ መከበራቸው ንግፊት የሚያደርግ ይሆናል።
አራተኛው፦ በአዲስ አበባ የፌደራል ስርአት ምስረታና የጋራ አስተዳደር ሂደት የአዲስ አበባ ህዝብ ሚናውን በአግባቡ እንዲጫወት፤ በሚገነባው ዲሞክራሲያዊ ስርአት ላይ ከሌሎች የሂደቱ አካላቶች ጋር በመተማመን፣ በእኩልነትና በአንድነት የሚሰራበት፤ በሦስቱም የመንግስት አካላት ውስጥ በቂ ውክልና እንዲኖረው ማስቻል።
አስተባባሪ ግብረ-ሃይሉ በአዲስ አበባ የማያቋርጥ ህዝባዊ እምቢተኝነት እንዲቀጣጠልና ከሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ጋር በትብብር መተማመን ለመስራት የሚያስችለው የአጭር ጊዜና ከሁኔታዎች ጋር ተለዋዋጭ የሆነ ስትራቴጂ መንደፍ ይኖርበታል። ከአገር ቤትም ሆነ ከኢትዮጵያ ውጭ ህዝባዊ ማዕበሉን የሚያቀጣጥሉ የግልፅና ህቡዕ አደረጃጀቶች መፈጠር ይኖርበታል። ህዝባዊ ማዕበሉን የሚመሩት ሰዎች ጠንካራ ማህበራዊ ትሥሥር ያላቸው፣ ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተቋማትን የሚመሩ፣ የሚቀረፁ መልዕክቶችን በቀላሉና ቀስቃሽ በሆነ መንገድ የሚያስተላለፍና በአግባቡ የተደራጀ ትሥሥር መፍጠር የሚችሉ ሊሆን ይገባል። ግብረ-ሃይሉ እንደዚህ አይነት ኔትወርኮችን እስከ ቤተሰብ ድረስ የሚዘረጋበት ስትራቴጂና ታክቲክ መቀየስ አለበት። የሚቋቋመው ግብረ-ሃይል የተለያዩ ንዑስ አደረጃጀቶች በውስጡ የያዘ ሊሆን ይችላል። ከእነዚህ ንዑስ አደረጃጀቶች ውስጥ እንደ መነሻ የሚከተሉት ሊኖሩት ይችላሉ፦
  1. የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን አስተባባሪ ግብረ-ሃይል
ይህ ንዑስ ግብረ-ሃይል አለም አቀፍና አገር አቀፍ የሚዲያ ተቋማትን፤ ማህበራዊ ሚዲያዎችን (ድረ-ገፅ፣ ፌስቡክ፣ ቲውተር….ወዘተ)፤ የህትመት ሚዲያዎችን በመጠቀም የአዲስ አበባ ህዝባዊ ንቅናቄንና የመጪውን ጊዜ የማስተዋወቅ ስራ የሚሰራ ይሆናል። የአዲስ አበባ ብሎም የኢትዮጵያ የአንድነት አጀንዳ ሰፊ ውይይት እንዲደረግበት ሃሳቦችን የማፍለው፣ የሚዲያ ተቋማትን በተለያዩ መንገድ በመቅረብ ሽፋን የሚያገኙበት ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል። የለውጥ እንቅስቃሴውን ከሚደግፍ የሚዲያ ተቋማት ጋር (ለምሳሌ ኢሳት፣ OMN፣ ዋዜማና ሌሎች የአከባቢ ሚዲያዎች) በሳምንት አንድ ጊዜ መደበኛ ፕሮግራም የሚቀርብበት ሁኔታን የሚደራደር ነው።

የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ስራው የአዲስ አበባን የትላንት፣ ዛሬና ነገን ሁኔታ በሚዳስስ መልኩ የሚቀርብ ይሆናል። ላለፉት 26 ዓመታት በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ላይ የተፈፀሙ የፍትህ መታፈኖች፤ የመሬት ወረራዎችና የነዋሪዎች መፈናቀል፤ የነዋሪውን ሉአላዊ መብት ለመንፈግ የወጡ አዋጆች፣ ህጎችና መመሪያዎች፤ ህወሃትና የቤት ውስጥ አገልጋዮቹ የአዲስ አበባን ህዝብ ለመዝረፍ የሚያካሂዱት የሌብነት፣ ጉቦና የቅሌት እንቅስቃሴዎች፤ የአዲስ አበባ ነባር ከበርቴዎችና ነጋዴዎችን ከገበያ ለማውጣት የተደረጉ እንቅስቃሴዎችና ሌሎች ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መታፈኖችን የሚመለከት ይሆናል። የሚዲያ ስራው የትላንትና እና የዛሬን ችግር ብቻ ሳይሆን ነዋሪው በነገይቱ ኢትዮጵያ ተስፋ የሚሰንቅበትና ነገን ለማየት የሚናፍቅበት የሚያስችሉ የቅስቀሳ ስራዎች መሰረት ይኖርባቸው። ጋዜጠኞች፣ የኪነ-ጥበብ ሙያተኞችና ፀሃፊያን፣ የሚዲያ ተቋማትና ኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዎች በዚህ ቡድን ውስጥ እንዲሳተፍ መደረግ ይኖርበታል።

  1. የህግ-ነክ ጉዳዮች አስተባባሪ ንዑስ ግብረ-ሃይል
ይህ ንዑስ ግብረ-ሃይል የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የሆኑና የከተማዋ ብሎም የኢትዮጵያ አንድነት ጉዳይ ያሳስበናል የሚል የህግ ሙያተኞች የሚሰባሰቡት ነው። የህግ-ሙያተኞቹ አዲስ አበባ ባለፉት 26 አመታት እንድትተዳደርበት የተደረጉትን አዋጆች ቻርተሮችና መመሪያዎች በመዳሰስ፤ የነዋሪውን መብት ለመንፈግ የተወሰዱ እርምጃዎችን በመመርመር ለውይይት የሚረዳ ዶክመንት ያቀርባሉ። ከሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ቡድን ጋር በመቀናጀት ዲሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ ግልፅ ውይይት እንዲደረግበት ያደርጋሉ።
ከዚህ በመነሳት የአዲስ አበባ ነዋሪ ሉአላዊ መብቱ ሙሉ ለሙሉ የሚጠበቅበትን የቀጣይ ማኒፌስቶ ለውይይት መነሻ ያዘጋጃሉ። በማኒፌስቶው ላይ ነዋሪና ያገባኛል የሚሉ አካላቶች (Stake Holders) አቋማቸውን ሳይደባብቁ አፍረጥርጠው የሚያቀርቡበት ሁኔታ የሚመቻችበት ሁኔታ ይፈጥራል።
  1. የፋይናንስና ሎጀስቲክ ጉዳዮች አስተባባሪ ንዑስ ግብረ-ሃይል
ህዝባዊ እምቢተኝነትን ለማቀጣጠልና ከዛም በኋላ የሚኖሩ ግዙፍ እቅዶችን ለማስፈፀም የገንዘብና የቁሳቁስ ማሰባሰብ ስራ የሚታለፍ አይሆንም። የሚካሄደው ፍልሚያ ከአምባገነኖችና በጠራራ ፀሃይ የጅምላ ጭፍጨፋ ከሚያካሂዱና የጦር ሃይሉንና የደህንነቱን ከተቆጣጠሩ ቡድኖች ጋር በመሆን ሰፊ መስዋዕትነት መጠየቁ አይቀርም። ስርአቱን ለመገርሰስ ከሄድንበት ያልሄድንበት ረጅም መንገድ መኖሩን የተገነዘበ ሊሆን ይገባል። ህዝቡን ሊያነቃንቁ የማደራጀት ስራዎችን ለመስራት በአገዛዙ ላይ የስነ-ልቦና ጦርነት ለማካሄድ፤ በፍልሚያ ሂደት ጉዳት የሚደርስባቸውን የነፃነት ታጋዮች ለመደገፍ ገንዘብ ማስፈለጉ አይቀርም።
በመሆኑም በአለም አቀፍ ደረጃ በአዲስ አበባ ብሎም በኢትዮጵያ የሚካሄደውን ህዝባዊ እምቢተኝነት የሚደግፍ የፋይናንስና ሎጀስቲክ የሚያሰባስብ አስተባባሪ ኮሚቴ መደራጀት ይኖርበታል። ይህ በግልፅነትና ተጠያቂነት መርህ ሊቋቋም የሚገባው ሃይል የራሱን ዝርዝር እቅዶች አውጥቶ የሚንቀሳቀስ ሊሆን ይገባል።
ከላይ እንደተገለፀው ግብረ- ሃይሉ ከድህረ ህወሃት በኋላ በኢትዮጵያ ውስጥ በሚመሰረተው አዲስ ስርአት ውስጥ አዲስ አበባና ነዋሪዎቿ ስለሚኖራቸው ሰብአዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መብቶች ሙሉ ለሙሉ መከበር ግፊት ማድረግን እንደ አላማ መውሰድ ይኖርባቸዋል። በሌላ አነጋገር የአዲስ አበባ ነዋሪ የመደራደር አቅሙ እንዲጎለብት መብቃት ይኖርበታል። የአዲስ አበባ ህዝብ መብቃት (Empoernment) መሆን ያለበት ሌሎችን ለማጥቃት ሳይሆን ለህልውናው ሲል ነው። በለውጥ ሂደት ውስጥ አቅም ገንብቶ ያልቆየ ማህበረሰብ የመናቅና የሚፈልገው መብቱንም የመነሳቱ እድሉ ሰፊ ነው። በሚካሄደው ስር-ነቀል ለውጥና በመሰረታዊ አቋሞቹ ዙሪያ በየጊዜው ውይይትና ክርክር ማድረግ ያስፈልጋል። በሌሎች የለውጥ ሃይሎች ውስጥ የተያዘው አቋምም ቀርበውለት ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መወያየትና መከራከር ግዴታ ነው። የሚደረገው ውይይት በለውጥ ሂደቱ ላይ ጥላሸት ለመቀባት፤ አሊያም ጠብ የለሽ በዳቦ ለማለት አይደለም። የቀጣይቷ የሁሉም የሆነች ኢትዮጵያ አደረጃጀቷ ፌደራላዊ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የሚከተሉት ሦስት አደረጃጀት አማራጮች በአዲስ አበባ ህዝብ ተወስኖ የአዲስ መንግስት ምስረታው ላይ ሰንዶ የሚያቀርብበት ይሆናል። ለምሳሌ ያህል የሚከተሉት አማራጮች እንደ መነሻ ሊቀርቡ ይችላሉ።
አማራጭ አንድ፦ አዲስ አበባ የፌደራል መንግስቱ ዋና ከተሟነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ የሚፈጠረው አደረጃጀት ብሔር ተኮር ከሆነ ራሱን የቻለ ግዛት (State) መሆን
አማራጭ ሁለት፦ አዲስ አበባ የፌደራል መንግስቱ መዲናነት እንደተጠበቀ ሆኖ ተጠሪነቷ ለፌደራል መንግስቱ የሚሆንበት (Chartered City)
አማራጭ ሶስት፦ አዲስ አበባ የፌደራል መንግስቱ ዋና ከተማነት እንደተጠበቀ ሆኖ በኦሮሚያ ግዛት (State) ውስጥ የሚጠቃለልበት ይሆናል።
የሚቀርበው ቢጋር (TOR) ከላይ የተቀመጡትን አማራጮች እንደ መሰረታዊ መነሻ የሚወስድ ይሆናል ማለት ይህ አማራጭ ብቻ ነው ማለት አይደለም። ሌሎች ከአዲሱ ፌደራል መንግስት አወቃቀር እና ጆኦ-ፖለቲካው ጋር የሚፈልቁ አዳዲስ አደረጃጀቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ለነገሩ አደረጃጀት አንድን አላማና ስትራቴጂያዊ ግቦች ለማስፈፀም የሚፈጠር በመሆኑ ይሄና ይሄ ብቻ አወቃቀርና አደረጃጀት ያስፈልጋል የሚል ዶግማቲክ አስተሳሰብ ሊኖር አይችልም። እንደውም የአንድ አደረጃጀት ጥንካሬው የሚለካው ከተለዋዋጭ ሁኔታዎች ጋር መጣጣም መቻሉ ነው። የአዲስ አበባ ህዝብ ትግሉን ቀጣይነት የሚያሳድግ ከሆነና 5 ሚሊዮን ህዝቡን በጠንካራ መስረት ላይ ማደራጀት ከቻለ ከዚህ የተሻለ አዳዲስ አደረጃጀቶች በአማራጭነት የሚቀርብበት እድል ዝግ አይደለም

No comments:

Post a Comment