Sunday, October 23, 2016

ወታደራዊ መረጃ እና የጌታቸው አሰፋ “ልጆች” እጣ ፈንታ ከዶ/ር ታደሰ ብሩ



Bilderesultat for የጌታቸው አሰፋየአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሳሞራ የኑስ ቡድን የበላይነት መያዙ የሚያረጋግጥ ነው። ይህ በህወሓት የስለላ ተቋማት ሥራ ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ ምንድነው?
ህወሓትን በቅርበት የሚከታተሉ ሰዎች እንደሚያውቁት ከመለስ ዜናዊ “መሰዋት” በኋላ ድርጅቱ ውስጥ ሁለት ቡድኖች ጎልተው ወጥተዋል። አንደኛው ቡድን ማንኛውም ዋጋ ተከፍሎ ቢሆን የህወሓት ፈላጭ ቆራጭነት መጠበቅ አለበት የሚሉ፤ ህወሓት እና የትግራይ ሕዝብ አንድ ናቸው እያሉ በአደባባይ የሚሰብኩ፤ የይስሙላ ስልጣን ቢሆንም እንኳን የኃይለማርያም “ጠ/ሚኒስትር” ተብሎ መጠራት ምቾት የማይሰጣቸው፤ ለአገሪቱ የፓለቲካ ችግሮች ሁሉ መፍትሄው ጉልበት ነው ብለው የሚያምኑ ከፍተኛ የአስተሳሰብ ችግር ያለባቸው ሰዎች የተሰበሰቡበት ነው። የዚህ ቡድን መሪ ሳሞራ የኑስ ነው። ሌላኛው ቡድን ደግሞ የህወሓትን የበላይነት ለማቆየት የሚቻለው በዘዴና በጥበብ እንጂ በጉልበት አይደለም፤ ስለሆነም ትንሽ እንለሳለስ ባይ ነው። የዚህ ቡድን መሪ ጌታቸው አሰፋ ነው።
በመግቢያዬ እንዳልኩት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሚነግረን ነገር ቢኖር የጌታቸው አሰፋ ቡድን በሳሞራ የኑስ ቡድን መሸነፉን ነው። አሁን አገራችን ድርና ማጋቸውክፋት ብቻ በሆኑ ሳሞራ የዩኑስና ፀጋዬ በርሄን በመሳሰሉ የአዕምሮና ድኩማን እየተመራች መሆኑን ነው።
ሳሞራ የሚመራው የጦር ሠራዊት ብዙ የሚገርሙ ነገሮች አሉበት። ጄኔራሎች እስካሁን መዋጮ ከፋዮች የህወሓት አባላት ስለመሆናቸው ብዙ የተባለበት ስለሆነ ደግሞ ማንሳት ዋጋ የለው። ዛሬ በትንሹ ልዳስሰው የምፈልገው የወታደራዊ መረጃ ዋና መምሪያን ነው።
መከላከያ ሚኒስቴር ውስጥ ለጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ ተጠሪ የሆኑ አምስት ዋና መምሪያዎች አሉ፤ ከእነዚህ አንዱ ወታደራዊ መረጃ ዋና መምሪያ ነው። ይህ ዋና መምሪያ ሰዋዊ (human) መረጃ፣ ኤሌክትሮኒክስ መረጃ (INSAም እዚህ ውስጥ ይገባል)፣ ፀረ-መረጃ፣ የእዞች መረጃ፣ የክልሎች መረጃ፣ የድንበር ክትትል፣ የውጭ አገራት መረጃዎችን የሚባሉ መምሪያዎች፣ ዋና ክፍሎችና ክፍሎች አሉት። ወታደራዊ መረጃ ሲባል የሚሊታሪ ኢንተለጀንስ ሊመስል ይችላል። እውነታው ግን ከዚህ በጣም፣ በጣም የተለየ ነው። የሳሞራ “ወታደራዊ መረጃ” የማይመለከተው ጉዳይ የለም። የወታደራዊ መረጃ human intelligence ለምሳሌ በሁሉም የሴክተር መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ኤጀንቶች አሉት። በሌላ አገለጽ የሳሞራ ሰላዮች የግብርና ሚኒስቴርንም የትምህርት ሚኒስቴርንም፣ መስጊዶችንና ቤተክርስቲያኖችን፣ ሆቴሎችንና ዮኒቨርስቲዎችን ይሰልላል። ይህ የጌታቸው አሰፋ ተቋም ሥራ ቢሆንም የወታደራዊ መረጃ “ባለሙያዎች” “የኛ ያልሆነ የስለላ ሥራ በአገሪቱ ውስጥ የለም” ባዮች ናቸው። ከሁሉ የሚብሰው በክልሎች፣ በዞንና በወረዳዎች ነው። በመከላከያ ስር 4 እዞች አሉ፤ ሰሜን እዝ፣ ማዕከላዊ እዝ፣ ምዕራብ እዝ እና ደቡብ ምስራቅ እዝ ይባላሉ። የክልሎች ወታደራዊ መረጃዎች የሚሄዱት ለእዝ አዛዦች ነው። ይህ አሠራር የእዝ አዛዦች ከክልሎች ፕሬዚዳንቶች በላይ መረጃና ስልጣን እንዲኖራቸው አድርጓል። በውጭ አገራት ኤምባሲዎችም ውስጥ የሚሊታሪ አታሼዎች ሥራ ከዚህ ዋና መምሪያ ጋር የተሳሰረ ነው።
የወታደራዊ መረጃ ዋና መምሪያ አዛዥ ሜ/ጄ/ ገብሬ ዴላ ይባላል። ዴላ እውነተኛ የአባቱ ስም አይደለም፤ የትውልድ ሥፍራዉ ትግራይ አምባላጌ ያለ የአካባቢ መጠሪያ ነው። ሜ/ጄ/ ገብሬ ዴላ የሳሞራ የቅርብ ወዳጅ ነው፤ ስለ ኢንተለጀንስ እውቀት ባይኖርም ከሳሞራ ያላነሰ ክፋት አለው፤ በሳሞራ መልካም ፈቃድ ከክፍለ ጦር አዛዥነት ወደ ወታደራዊ መረጃ ዋና መምሪያ ኃላፊነት የተተኮሰ ሰው ነው።
ከገብሬ ዴላ ጋር ሲነፃፀር ጌታቸው አሰፋ የተሻለ ግንዛቤ አለው፤ የህወሓት አገዛዝ ችግር ውስጥ መግባቱ ያውቃል፤ ሆኖም ግን በደነዞች ተበልጦ ተሸንፏል። አሁን ሳሞራ የአገዛዙን መሪ ጨብጧል፤ ከመረጃ አንፃር ደሞ መሪነቱን ገብሬ ዲላ ወስዷል። ድሮም የገብሬ ቢሮ በጌታቸው ቢሮ ሥራዎች ጣልቃ ይገባ ነበር፤ አሁን “ጣልቃ መግባት” ሳይሆን በአዋጁ መሠረት ህጋዊ ሥራው ሆኗል።
የገብሬ ዲላ ሰዎች ቀጥለው ምንድነው የሚያደርጉት? ጌታቸው አሰፋ ቀጥሎ የሚመጣውን ገምቶ መንቀሳቀስ ከአሁኑ ጀምሯል ብዬ አምናለሁ። ራሳቸውን “የኢንተለጀንስ ባለሙያዎች” አድርገው የሚቆጥሩ፤ ሁሉ በእጃቸው የሚመስላቸው የጌታቸው አሰፋ “ልጆች” አደጋ ውስጥ ናቸው፤ ገብሬ ዲላ ተፎካካሪ አይወድም፤ ሶሞራ ደሞ ከእርሱ በላይ ሰው በዓለምም ላይ ያለ የማይመስለው ግብዝ ነው። የሶሞራ መንግሥት የህወሓት አገዛዝን ውድቀት ያፋጥናል፤ ከመሞቱ በፊት ግን የሁልጊዜ ተፎካካሪውን የጌታቸው አሰፋ ቢሮ ሰላዮችን ይበላቸዋል። የጌታቸው አሰፋ ቢሮ ሰዎች ራሳችሁን ለማዳን ያላችሁን አጭር ጊዜ ተጠቀሙበት።
ከዶ/ር ታደሰ ብሩ

No comments:

Post a Comment