Wednesday, October 26, 2016

የአርበኞች ግንቦት 7 ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የታወጀ የዘመናዊ ባርነት አዋጅ ና በሕዝባዊ ትግሉ የሚወሰዱ እርምጃዎችና ዋና ዋና ዒላማዎች


መግቢያ
ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ፤

በሀገራችን ኢትዮጵያ የተከሰተው ስር የሰደደ የፖለቲካ ቀውስ በሰለጠነ የውይይትና የድርድር መንገድ እንዲፈታ ለሀገር ደህንነት ከሚያስቡ የአገር ሽማግሌዎችም ሆነ ከተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ወዳጆቹ ጭምር የቀረበለትንና የሚቀርብለትን ጥሪ አሌ ብሎ፤ ይህ እኩይ የጥቂት ሽፍቶች ሥርዓት ለ25 ዓመታት ሲያካሄድ የቆየውን የሕዝብና የሀገር ሀብት ዝርፊያ ከማቆም ይልቅ “ሀገሪቷን መዝረፍ ካልቻልኩ አቃጥያት እጠፋለሁ” ብሎ የመጨረሻው የሆነውን የጥፋት መንገድ ከሰሞኑ “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ” በሚል ስያሜ ባወጀው “የባርነት አዋጅ” ለሁሉም ግልጽ አድርጓል። ይህንን የወያኔ የዘራፊዎች ቡድን ለረጅም ጊዜ በቅርብ ስንከታተልና በተግባርም ስንፈትነው ለቆየነው የነፃነት ኃይሎች ይህ እርምጃው ስንጠብቀውና ስንዘጋጅበት የነበረ ስለሆነ በእውነቱ በፍጹም አልገረመንም። ትንሽም ቢሆን ያስገረመን ይህንን የመጨረሻ ጥይቱን እንደዚህ በቶሎ መጠቀሙ ነው። የመጨረሻ ጥይቱ ነው የምንለው ከዚህ በኋላ ሊጠቀምበት የሚችለው ምንም ሌላ መሳሪያ እንደሌለው ስለምናውቅ ነው።
በእርግጥ በዚህ አዋጅ ውስጥ አገዛዙ ሊወስዳቸው ያሰባቸው እርምጃዎች አብዛኛዎቹ ከዚህ በፊትም እራሳቸው ካወጧቸው ህጎችና ህገመንግስቱም ውጪ ያለምንም ከልካይ ሲተገብሯቸው የነበሩ እርምጃዎች ናቸው። የመንግሥትን ስልጣን ከተቆጣጠሩ ጀምሮ በስልጣናቸው በመጣ ጉዳይ አንድም ጊዜ ህጋቸውን አክብረው አያውቁም። ያለህግ ሲያስሩ፤ ያለህግ ሲገድሉ፤ ያለህግ የመገናኛ ብዙሀንን ሲዘጉና ሲያፍኑ፤ ከህግ ውጪ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን ሲያፈርሱና ያላፈረሱትን ደግሞ እራሳቸው የመረጡላቸውን መሪዎች ሲያስቀምጡ ነው እስካሁን የዘለቁት። ከዚህ አንጻር ይህ አዋጅ ቀድሞውንም ኢህጋዊ የሆነ ስራቸውን ይበልጥ ኢህጋዊ በሆነና አይን ባወጣ መንገድ፤ ለፈረንጆች ማባበያ ያጠለቁትን የህጋዊነት ጭምብል አውልቀው እርቃናቸውን ከመታየታቸው ባሻገር ብዙ አዲስ ነገር የለውም። ይህን አዋጅ ከዚህ በፊት ሲያደርጉት ከነበረው በተለየ እንድንመለከተው የሚያደርገን ከአዋጁ እናገኝበታለን ብለው የሚያስቡትና ዘላቂነት ይኖረዋል ብለው የገመቱት በሕዝባችን ላይ ሊያሳርፉት የፈለጉት፤ ዘላቂነት ያለው የተገዢነት ስነ ልቦና ውስጥ ሕዝቡ እንዲገባ የሚያደርጉት ሙከራ ላይ ነው።
በተግባር ይህ አዋጅ ተግባራዊ እየሆነ ባለበት ሁኔታ ምንም አይነት የፖለቲካ መፍትሄ ሊኖርም ሊሞከርም የማይችል እንደሆነና ግልጽ አድርጓል። የህወሓት አገዛዝ ከጉልበት ውጭ ምንም ሌላ መንገድ የማያውቅ አጥፊ ኃይል እንደሆነ ለወዳጅም ለጠላትም ያሳወቀበት አዋጅ ነው። ይህን አዋጅ ሲያውጁ ሰው ሆኖ መኖርን የናፈቀውና ካሁን በኋላ ያለነፃነት በፍጹም አልኖርም ብሎ ፍርሀትን በሚገርም ጀግንነት አሸንፎ ውድ ሕይወቱን እየከፈለና እየታገለ ያለውን፤ ከሞላ ጎደል መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ እንደገና በፍርሀት ቆፈን ውስጥ መልሼ ከትቼ ከቀድሞውም የባሰ ባርነት ውስጥ ዘፍቄ እገዛዋለሁ ብሎ አምኖ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ካሁን በኋላ ባርነትን የሚሸከምበት ምንም ጫንቃ የለውም። በዚህ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ሕዝብ በፍጹም በፍጹም ተመልሶ የባርነት ሕይወት ውስጥ ሊኖር አይፈቅድም። ስለዚህ ከዚህ በኋላ የፍትህና የነፃነት ኃይሎች ዋና ተግባር ያላቸውን አቅም ሁሉ አስተባብረውና ነፃነት የራበውንና የጠማውን ሕዝባቸውን ከጎናቸው አሰልፈው፤ ጊዜውና ሁኔታው የሚፈቅደውን ተለዋዋጭና ተለማጭ የትግል ስልት እየተጠቀሙ ይህ አዋጅ በፍጹም ተግባራዊ እንዳይሆንና እንዳይሳካ ማድረግ ነው። ይህን የባርነት አዋጅ ለማስፈጸም በመሪነትና በዋና አስፈጻሚነት የሚንቀሳቀሱት ኃይሎች፤ ይህ የባርነት አዋጅ በኢትዮጵያ ሕዝብ ጫንቃ ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ እንዲተገበርና እንዲሳካ ለማድረግ የሚሞክሩ ወይንም ከዚህ ዘራፊ ሥርዓት ጋር በጥቅም ተሳስረው ከዚህ የባርነት አዋጅ ጋር የሚተባበሩ ማናቸውም ኃይሎች ሁሉ ከአሁን ጀምሮ የሕዝባዊ ትግሉ ቀንደኛ ዒላማዎች መሆናቸውን ግልጽ አድርጎ መንቀሳቀስ ይገባል። በዚህ ሕዝባዊ ትግል ላይ የሚሳተፉ የሕዝብ ወገኖችም ሆነ ይህንን ዘራፊ ሥርዓት የሚያግዙ ኃይሎች በደንብ እንዲረዱት የሚያስፈልገው ይህን አዋጅ አከሸፍነው ማለት የወያኔ ሥርዓት አከተመለት ማለት እንደሆነ ነው። ይህ አዋጅ ተሳካ ማለት ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ ላልተወሰነ ጊዜ በባርነት መቀመቅ ውስጥ ሊኖር ተፈረደበት ማለት ነው። ለዚህ ነው አሁን የገባንበት ትግል የመጨረሻው የሞት ሽረት ትግል ነው የምንለው።
ለመሆኑ ይህ አዋጅ የሚደነግገው ምንድን ነው? ለምንድን ነው በፍጹም እንዲሳካ የማንፈቅድለት “የዘመናዊ ባርነት አዋጅ” ነው የምንለው?
“ባርነት” የሰውን ልጅ ሰው የሚያደርገውን መሠረታዊ ነጻነቱን ገፍፎ፤ ፈንጋዩ ከሚሰጠው ፈቃድ ውጭ በራሱ ምንም የሚወስነው ነገር እንዳይኖር ከልክሎ፤ ያለውን የጉልበትም ሆነ የማሰብ አቅሙን ሁሉ በባርነት ለሚያሳድረው ባለቤቱ ሀብት መፍጠርና አገልግሎት መስጠት ላይ ብቻ እንዲያውል የሚያደርግ ሥርዓት ነው። ባርያ የኔ የሚለው ንብረት የለውም፤ በገዛ ራሱ ሰውነትና አዕምሮ ላይ ሥልጣን የለውም። የሰው ልጅ እንዲህ ዓይነቱን ማንነቱን የሚነጥቅ በደል እሺ ብሎ በፈቃደኝነት አይቀበልም። ስለዚህ ይህን እንዲቀበል በጉልበት ማስገደድን ይጠይቃል። ይህን ለማድረግ ደግሞ ባርያ ፈንጋዮች የመጀመሪያ ሥራቸው ባርያ የሚያደርጉትን ሰው ከሰውነቱ የሚመነጨውን የነፃነትና ሰው የመሆን ፍላጎት በጉልበትና በሰቆቃ መንጠቅ ነው። አንዴ ይህን የውስጥ ማንነቱን ከነጠቁትና ባርያውን ወደ እንሰሳነት ከቀየሩት በኋላ እንደፈለጉት ለማድረግ በቀጣይነት ጉልበት መጠቀምም አያስፈልጋቸውም። በሕይወት የሚያቆየውን የሚበላውን መጥነው እየሰጡ እስከሚሞት ድረስ ጉልበቱን እየበዘበዙ ለራሳቸው ሀብት ማጋበስ ነው። ይህን በቀጣይነት ለማድረግ ባርያው ለራሱ ጥቅም እንዳያስብ መሆን አለበት። የሚያስበውን የሚነግሩት እነሱ፤ የሚሰማውን ወሬና ከማን ጋር መነጋገር እንዳለበት የሚወስኑለት እነሱ፤ የሚንቀሳቀስበትን ቦታ የሚወስኑለት እነሱ፤ መቼ መተኛትና መነሳት እንዳለበት የሚፈቅዱለት እነሱ፤ ምን ሥራ መሥራት እንዳለበት የሚፈቅዱት እነሱ፤ በሕይወት መኖርና አለመኖሩን የሚፈቅዱለት እነሱ፤ ባጠቃላይ ሕይወቱ በነሱ ፈቃድ ላይ የተመሰረተች እንጂ ከዚያ ውጭ ሕይወት እንደሌለው እንዲቀበል ማድረግ አለባቸው። ይህን ለማድረግ ከሚጠቀሙት ጉልበት በተጨማሪም ሰውየው ይህ ኑሮው በግድ የተጫነበት ሳይሆን በተፈጥሮ የተለገሰው እጣ ፈንታው እንደሆነ እንዲያምን ይጥራሉ። ይህን የሚያደርጉት ሰዎች በቁጥር ትንሽ ስለሆኑ በባርነት የሚኖሩት ሰዎች ተባብረው ከገቡበት የባርነት ቀንበር ራሳቸውን እንዳያላቅቁ ይህ የማይቻል እንዲሆን በባርያዎቹም መሀከል ልዩነት መፍጠርና አንዱ ባርያ ሌላውን የሚጠብቅበት መንገድ ማመቻቸትም አንዱ የመግዥያ መሣሪያቸው ነው። የተወሰኑትን ጥቂት ባርያዎች በአንጻራዊነት ቀለል ያለ የቤት ውስጥ ሥራ እያሠሩና ከሌሎች ባርያዎች በተለየ ከጌቶቻቸው የተረፈ ፍርፋሪ ምግብ እያበሉ እራሳቸውን እንደባርያ እንዳያዩና ሌላውን የመስክ ሥራ እየሠራ የሚፈጋውን ባርያ እየናቁና እንዳያምጽ የመቆጣጠር ሥራ ያሠሯቸዋል። ለሌላውም ባርያ “የጥሩ ባርያነት” አርአያ አድርገው ያቀርቧቸዋል። የሰው ልጅ እዚያ ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ ያገራችን ሰዎች አገሩን ላጣ ሰው እንሚተርቱት “ቢጭኑት አህያ ቢጋልቡት ፈረስ” የሆነ እንሰሳ ይሆናል ማለት ነው። 
የወያኔ ጥቂት ዘራፊ መሪዎች ይህን አዋጅ ሲያውጁና በተግባር እናሳካዋለን ብለው ሲገምቱ በትግሉ ነጻነቱን እያወጀ ያለውን የኢትዮጵያን ሕዝብ እዚያ ባርነት ደረጃ ላይ እናደርሰዋለን ብለው ገምተው ነው። በዚህ አዋጅ ላይ እነሱ ከፈቀዱለት ሰው ውጭ ያለ ኢትዮጵያዊ ምን መናገር እንደሚችል፤ ምን ማሰብ እንደሚችል፤ ከማን ጋር እንደሚያወራ፤ ምን ዜና እንደሚሰማ፤ ምን ማንበብ እንዳለበት፤ የት የት ቦታ መንቀሳቀስ እንደሚችል፤ ምን ሥራ እንደሚሠራ፤ በስንት ሰዓት ከቤቱ ወጥቶ በስንት ሰዓት እቤቱ መግባት እንደሚችል፤ የራሱን ንብረት እንዴትና መቼ ማንቀሳቀስ እንደሚችልና ይህንን እነሱ ከፈቀዱለት ውጭ በራሱ ፍላጎትና ተነሳሽነት ምንም ዓይነት ነገር ቢያደርግ ሕይወቱን እስከመንጠቅ ድረስ የሚደርስ እርምጃ እንደሚወስዱበት በዚህ የዘመናዊ ባርነት አዋጃቸው አውጀዋል። በቃሊቲ፣ ቂሊንጦ፣ ዝዋይና ቁጥራቸው ተዘርዝሮ በማያልቅ የማጎርያና የማሰቃያ እስር ቤት ያሰሯቸውን ዜጎች ከንጋት 11 ሰዓት እስከ ቀን 11 ሰዓት ድረስ ውጭ ወጥተው ጸሀይ እንዲሞቁና እግራቸውን እንዲያፍታቱ ከመፍቀድ በቀር ቀሪውን ሰዓት በተቆለፈ ቤት ውስጥ እንዲቀመጡ እንደሚያደርጉት ሁሉ በዚህ አዋጅም በሀገሪቱ ድንበር 50 ኪሎ ሜትር ሬድየስ እና ከዋና ዋና መንገዶች በግራና በቀኝ 25 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚኖር ኢትዮጵያዊ ሁሉ (ይህ ባገሪቱ ያሉትን ሁሉንም ከተሞችና ትናንሽ መንደሮች ከሞላ ጎደል ያካልላል) ከምሽቱ 12 ሰዓት እስከ ንጋቱ 12 ሰዓት ድረስ እራሱን በገዛ ቤቱ ውስጥ እንዲያስር የወሰነ እጅግ የሚገርምና በዛሬ ዘመን ሊታሰብ የማይችል የጅምላ እስር አዋጅ ነው። ይህ አዋጅ ከተሳካለት ማንም ኢትዮጵያዊ፤ ከነሱና ከቡችሎቻቸው በቀር፤ እራሱን ከጥቃት ለመከላከል የሚያስፈልገውን ማናቸውንም ዓይነት መሣሪያ እንዳይይዝ የሚከለክልና ያለውንም የሚቀማ ስለዚህም ለዘላለሙ በፍርሀትና በድንጋጤ እንዲኖር፤ በራስ የመተማመን ስሜቱን እንዲሰልብ ያለመ አዋጅ ነው። ይህ አዋጅ ከተሳካ እነሱ የኢትዮጵያውያንን ጉልበት እንደፈለጉ እየመዘበሩ የሚደልቡበት፤ ሌላው ኢትዮጵያዊ በገዛ ሀገሩ የበይ ተመልካች ብቻ ሳይሆን ጉልበቱንና የሀገሩን ሀብት ለነሱ እየገበረ የሚኖርበትን የዘመናዊ ባርነት ሥርዓት እንዲቀበል የሚያደርግ ነው። በዚህ ስድስት ወራት ውስጥ ይህንን ፍላጎታቸውን በኃይል ካሳኩ ከዚያ በኋላ አዋጁን ቢያነሱት እንኳን፤ ማሰሩንና መግደሉን ቢያቆሙት እንኳን፤ ይህ ቅስሙ የተሰበረ ሕዝብ ሰጥ ለጥ ብሎ ይገዛልናል ብለው አምነው የሚወስዱት እርምጃ መሆኑን ላንድ አፍታ እንኳም መዘንጋት የለበትም።
ለመሆኑ እንዲህ አይነት እርምጃ በዛሬው ዓለምና በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ሊሠራ ይችላል ብለው እንዴት ገመቱ?
አሁን ያለውን የኢትዮጵያ ሕዝብ የደረሰበትን የነፃነት ፍላጎት ደረጃና ባጠቃላይ የዓለማችንን ሁኔታ በክፍት ልቦና ለሚመለከት ሰው በሀገራችን ያለውንና እነሱ ራሳቸው የፈጠሩትን የፖለቲካ ቀውስ በዚህ ዓይነት አዋጅ እንፈታዋለን ብለው ማሰባቸው በራሱ በነሱ በሞራ በተሸፈነ ትንሽ ጭንቅላት ውስጥ የሚርመሰመስ የራሳቸው የተለየ የቅዠት ዓለም ውስጥ የሚኖሩ፤ ይህ የቅዠት ዓለማቸው ግን ከእውነተኛው ዓለም እውነታ ጋር ሲጋጭባቸው የሚሠሩትን እስከማያውቁ ድረስ የሚምታታባቸው እብዶች መሆናቸውን ነው የሚገልፀው። በመጀመሪያ፣ በዚህ አዋጅ አማካይነት እየታገሉት ያሉት ከማን ጋር እንደሆነ በፍጹም አላወቁም። በነሱ የቅዠት ዓለም፤ ትግላቸው ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ሳይሆን እነሱ “ጥቂት” ከሚሏቸው የነሱን “የልማትና የሕዳሴ ጉዞ” ከሚቃወሙ ወይንም ካልተዋጠላቸው ግለሰቦችና ድርጅቶች ጋር ነው። ከእነኝህ ጥቂት ግለሰቦችና ድርጅቶች ጋር ለሚደረግ ትግል ግን ለምን በመላው ሕዝብ ላይ ጦርነት ማወጅ እንዳስፈለጋቸው መቼም በትክክል በሚሰራ አዕምሮ ታስቦ የሚደረግ አይደለም። ከመላው ሕዝብ ጋር በሚደረግ ትግል ደግሞ እነኝህን እርምጃዎች በመውሰድ እናሸንፋለን ወይንም ያለሕዝብ ትብብር እነኝህን እርምጃዎች ተግባራዊ እናደርጋለን ብለው እንዴት ሊያምኑ እንደሚችሉ በሙሉ አዕምሮው ለሚያስብ ሰው ለመገመት አስቸጋሪ ነው። ሕዝቡ ቤቱ ውስጥ ያለው ቴሌቪዥን ላይ ምን እንደሚሰማ ለመቆጣጠር ቀደም ብሎ በሕዝቡ ትግል የፈረሰው “የአንድ ለአምስት” ጥርነፋ አሁንም ይሠራል ስለዚህም ልጅ አባትና እናቱን፤ ወላጆች ደግሞ ልጆቻቸውን ይሰልሉልኛል ብለው በቅዠት ዓለማቸው ካላመኑ በስተቀር ዛሬ እውነታው በምድር ላይ የለም። ለመሆኑ፣ በሀገሩ ውስጥ ያለውን የሳተላይት መቀበያ ሳህን ሁሉ ከየቤቱ ጣርያ ላይ ለማውረድ የሚያስችል የሰው ኃይል አለን ብለው እንዴት ሊያምኑ ቻሉ? በየመንግሥት መሥሪያቤት ያለውና በግል ድርጅቶች ውስጥ የሚሠራውን ሠራተኛ ሁሉ “በሥራ መለገም ወንጀል ነው” ብለው ሲደነግጉ ይህንን እንዴት እናስፈጽማለን ብለው ገምተው ነው? ዳሽን ቢራና ፔፕሲ አልጠጣም፤ የህወሓት ንብረት በሆነው ሰላም አውቶብስ አልሄድም፤ ገንዘቤን በህወሓትና እሱን በሚያገለግሉ ባንኮች ውስጥ አላስቀምጥም፤ የመሶቦ ሲሚንቶን አልገዛም ብቻ ሳይሆን በባርነት ታስሬ የምኖርበትን ቤት ከናካቴው አልሰራም ብሎ ያመረረን ሕዝብ እንዴት አድርጎ ነው ፔፕሲንና ዳሽን ቢራን ሊግተው ያሰበው? እንደው እዚህ ግባ የማይባል ደሞዝ ከፍለው መሣሪያ ያስታጠቁት የወታደርና የፖሊስ ኃይል ለዚህች ደሞዙ ብሎ ራሱንና ወገኖቹን ለዘላለማዊ ባርነት ለመዳረግ የሚተጋ ግዑዝ ኃይል ነው ብሎ ቢያስብ እንኳን፤ ይህ ቢበዛ ከ200ና 300ሺ በላይ የማይደርስ ኃይል የሀገሪቱን ድንበር የመጠበቅ ሥራውን ሁሉ ትቶና ከድንበር ላይ ነቅሎ ለዚህ አዋጅ ማስፈጸሚያ ሥራ ቢያውለው እንኳን፤ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል የተነሳንና እንዳስፈላጊነቱ በመሣሪያ ኃይል እራሱን ለመከላከል ያደራጀን በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሕዝብ እንዴት አድርጎ ያሸንፋል ብሎ ጤነኛ አዕምሮ ያለው ሰው ሊያምን ይችላል? ከዛሬ በኋላ እንኳንስ ሠራዊቱን በፍላጎት ለመልቀቅ እረፍት እንኳን መውስድ አትችልም ተብሎ በኃይል ተሰንጎ እንዲዋጋ የታወጀበት ሠራዊት ከሕዝቡ ጋር ጦርነት መግጠሙን ሲያውቅ አይደለም ከልቡ ሊዋጋና ሊያሸንፍ ከሕዝቡ ጋር ወግኖ መልሶ አዛዦቹንና ከሕዝብ ጋር የሚያዋጉትን የሀገርና የሕዝብ ጠላቶች ሊወጋ እንደሚዘጋጅ፤ ይህን እንኳን ማድረግ ቢያቅተው ከነመሣሪያው ጠፍቶ ሊሰወር እንደሚችል በትዕቢት የተወጠረና ማሰብ ያቆመ ጭንቅላት ካልሆነ በስተቀር በትክክል ለሚያስብ ሰው እንዴት ይሳነዋል? በመቶ ሺ እስኴር ኪሎ ሜትሮች በሚቆጠር አካባቢ የሚንቀሳቀስን በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሕዝብን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ስንት ሚሊዮን ተባባሪዎቹን ተማምኖ ነው ሊቆጣጠረው የሚችለው? በሌላ አነጋገር የማሰብ ኃይላቸው ፍጹም ተመናምኖ ያለቀው የአገዛዙ መሪዎች እንኳን ይህንን አዋጅ ያለሕዝብ ትብብር እጃቸው ላይ ባለው ኃይል እናሳካዋለን ብለው ያምናሉ ለማለት በጣም አስቸጋሪ ነው። ሕዝቡ ደግሞ በዛሬ ዘመን በራሱ ላይ ባርነትን ለመጫን ይተባበራል ብሎ መገመት በፍጹም የሚቻል አይደለም። ይልቁንም ወያኔዎች የተማመኑበት የሚመስለው በተለመደ ባዶ ድንፋታቸው ሕዝቡን አስፈራርተው፤ ወይንም የተወሰኑ ሰዎችን ገድለውና አስረው በዚህ እርምጃቸው ሕዝቡ ከተሸማቀቀ በኋላ ለነጻነቱ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ያቆማል ብለው ነው እየቆመሩ ያሉት። የዚህ ክፉ ቁማር ውጤት ግን እነሱ የጠበቁት ሳይሆን እስካሁን ዘርፈው ያካበቱትን ንብረት ሳይበሉ ተሰባብረው የሚወድቁበትን፤ የኢትዮጵያ ሕዝብም በዚህ ዘረኛና ዘራፊ ሥርዓት መቃብር ላይ እውነተኛ ነጻነቱን የሚቀዳጅበት የመጨረሻው ሂደት እንደሚሆን አያጠራጥርም።
ይህ ግን ስለተመኘነው የሚመጣ ሳይሆን በሥራችንና በትግላችን እውን የምናደርገው ድላችን ነው የሚሆነው! 
በሕዝባዊ ትግሉ የሚወሰዱ እርምጃዎችና ዋና ዋና ዒላማዎች
ቀደም ብዬ እንዳልኩት የወያኔ መሪዎች ይህን በፍጹም ሊሳካ የማይችል እርምጃ መውሰዳቸው ሳይሆን የሚገርመው ይህንን የመጨረሻ የተስፋ መቁረጥ እርምጃቸውን እንዲህ በቶሎ መውሰዳቸው ነው የሚገርመው። እንዲህ ዓይነት ፍጹም በቅጡ ያላሰቡበት እርምጃ ውስጥ የከተታቸው ደግሞ በዚህ ባጭር ጊዜ ሕዝባዊ ትግሉ የወሰዳቸው እርምጃዎች ከሚጠበቀው በላይና ባልተጠበቀ ፍጥነት ውጤታማ በመሆናቸው ነው። ባንድ በኩል በሀገር ውስጥ የሚደረገው የሕዝባዊ እምቢተኝነት እንቅስቃሴ ባጭር ጊዜ ትግል የበሰሉ ወጣት አመራሮችን አፍርቶ በየጊዜው የሚቀያየሩና በምድር ላይ የሚፈጠሩ ሁኔታዎችን ከግምት እያስገባ የሚሄድ ተለዋዋጭ የትግል ስልቶችን በመጠቀም ሕዝቡን በሰፊው ያሳተፈ ቀጣይነት ያለው ትግል ማካሄድ በመቻላቸው ነው። ከዚህ ጋር ተያያዥነት ያለው ትልቁ ነገር ይህ ህዝባዊ እምቢተኛነት እንቅስቃሴ በአንድ የሀገሪቱ ክፍል ብቻ ሳይሆን በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል በፍጹም ባልተጠበቀና የወያኔን ዘረኛ መሪዎች ባስደነገጠ መልኩ በደል ባስተሳሰረው የአንድነት መንፈስ መካሄዱ ነው። የወያኔን ዘረኛ መሪዎች ብርክ ያስያዛቸው ጎንደር ላይ የአማራ ሕዝብ ተገልብጦ ወጥቶ ወያኔን ወጊድልኝ ከማለቱ ባሻገር የበቀለ ገርባን ምስል ይዞ “የኦሮሞ ደም ደማችን ነው” የሚል መፈክር እያሰማ መውጣቱና ከኦሮሞ ሕዝብ ትግል ጋር አጋርነቱን ማሳየቱ ነው። በኢሬቻ በዓል ላይ የኦሮሞ ወጣቶች “የአማራ በደል የኛም በደል” ነው ብለው በጎንደርና በጎጃም ለሚደረገው ትግል ወገንተኛነታቸውን ማሳየታቸው ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በሁሉም ክልሎች ሕዝቡ ለሚያደርገው ሰላማዊና የሰለጠነ ትግል የወያኔ መሪዎች መልስ ጥይት መሆኑን በዓይኑ እየተመለከተ ሲሄድና በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ የትግል ጓዶቹን እየቀበረ ሲሄድ፤ አረመኔን በሰለጠነ ትግል ብቻ ማስቆም እንደማይችል አውቆ የሕዝባዊ እምቢተኝነት ትግሉን በሕዝባዊ አመጽ ለመደገፍ እየወሰደ ያለው ዝግጅትና መለስተኛ እርምጃዎች ናቸው። 
ዛሬ በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች ለመሞት ብቻ ሳይሆን ለመግደልም የቆረጡ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ አርበኞች በረሀ የወጡበት ጊዜ ነው። ዛሬ የአርበኛ ታጋይ አበራ ጎባውን ዓይነት ጀግና ተዋጊዎችና አዋጊዎች ብዙ የአጋዚ ጦር ደምስሰው የሚሰዉ ብርቅዬ የኢትዮጵያ ልጆች ይህን ሥርዓት ከስሩ ለመመንገል የተዘጋጁበት ጊዜ ነው። እንዲህ ዓይነቶች ጀግኖች በኦሮሚያ የተለያዩ ቦታዎች፣ በአርባ ምንጭ፣ በቴፒ፣ በኮንሶ፣በጋምቤላ፣ በአፋር የጀንግንነት ተግባራትን ፈጽመው አሳይተውናል። ዛሬ የህወሓት አገዛዝ የሚመራው ጦር እየከዳ እንዲህ ዓይነት ጀግኖችን የሚቀላቀልበት ወቅት ነው። ዛሬ የብዙ ጊዜ እንቅስቃሴያችን ፍሬውን ለማፍራት የተዘጋጀበት፤ ትግሉን ከዳር ለማድረስ ሁኔታዎች የተመቻቹበት ጊዜ ነው። የወያኔ መሪዎች ይህንን ጠንቅቀው አውቀዋል። ለዚህ ነው ይህንን የመጨረሻ የተስፋ መቁረጥ እርምጃዎችን እየወሰዱ ያሉት።
ይህ በጥሩና በአመርቂ ሁኔታ እየተካሄደ ያለ ትግል ግን እመጨረሻው ምዕራፉ ላይ ሳይደርስ በፍጹም መቆም የለበትም። “የነብርን ጅራት አይይዙም፤ ከያዙም አይለቁ” የሚለውን የአበው ብሂል እዚህ ላይ ይሠራል። ሕዝባዊ ትግሉን እዚህ ካደረስነው በኋላ ከዳር ሳናደርሰው መመለስ ከቶ አይቻለንም። ማድረግ ያሉብን ነገሮች ደግሞ ግልጽ ናቸው። አሁን በመላ አገራችን የተቀጣጠለው ሕዝባዊ ትግል እስካሁን ከነበረው በላይ አጠናክሮ መቀጠልና አዲስ ለተፈጠረው ሁኔታ የሚመጥኑ አዳዲስ እርምጃዎችን መውሰድ ይገባል። የትግል ዒላማዎቻችንን ከዚህ በፊት ከነበሩት በተጨማሪ ይህንን የባርነት አዋጅ ለመተግበር የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ላይ ሁሉ ማነጣጠር ይኖርበታል። ከዚህ አንፃር ይህንን የባርነት አዋጅ ለማክሸፍና ትግላችንን ከዳር ለማድረስ የሚከተሉትን ተጨባጭ እርምጃዎች በቀጣይነት እንወስዳለን፤
1. ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ነፃነትን የሚሻ ሁሉ ከሚመስለው ጋር ይደራጅ ስንል ቆይተናል፤ አሁን ከመደራጀትም አልፎ ራሱን ለመከላከል ከዚያም አልፎ ለሚደርስበት ጥቃት ተመጣጣኝ ምላሽ ለመስጠት ይዘጋጅ። ከእንግዲህ ባይሆን ገድሎ መሞት እንጂ “በሰላምተኝነት” መሞት የለም። ራስንና ሕዝብን ከህወሓት ሽብር ለመከላከል በየቦታው የተደራጁ ቡድኖች አሉን፤ ተጨማሪ ቡድኖች እናደራጃለን፤ በተቻለን ሁሉ እንደግፋለን። ነፃነት የጠማው ኢትዮጵያዊ ሁሉ እነዚህ ቡድኖች ይደግፍ፣ ይቀላቀል። በቡድን ብቻ ሳይሆን በግልም ጭምር ለህወሓት አመፃ የአመፃ ምላሽ ይስጥ። 
2. ይህ የባርነት አዋጅና የአዋጁ ባለቤት ህወሓት በስልጣን ላይ እስካለ ድረስ መንገዶች “መሠረተ - ልማቶች” ሳይሆኑ መሠረተ - ጥፋቶች ናቸው፤ አውራ ጎዳናዎች አስጠቂዎቻችን ናቸው። በእነዚህ መንገዶች እየተጓጓዘ ነው የአጋዚ ጦር ወገኖቻችንን እየፈጀ ያለው። ስለሆነም መንገዶችንና መዝጋት ብቻ ሳይሆን ማፍረስም ተቀባይነት ያለው ሥራ ነው፤ ከነፃነታችን የሚበልጥ አንዳችን ቁሳዊ ሀብት የለም። ለግንባታው ከነፃነት በኋላ እንደርስበታለን። የሕዝብ ጠላት የሆነ መንግሥት ንብረት ሁሉ የጠላት ንብረት ስለሆነ እናወድመዋለን፤ “የመንግሥት ንብረት የሕዝብ ንብረት ነው” እያሉ የሚያሞኙንን አንሰማም። 
3. የታወቁ የሥርዓቱ ቀንደኛ አራማጆች ብቻ ሳይሆኑ ይህንን የባርነት አዋጅ ለማስፈፀም የሚራራጡ ግለሰቦች፣ ቡድኖችና ተቋማት ሁሉ ጠላቶቻችን ናቸው። እነዚህ ሁሉ የትግላችን ዒላማዎች ናቸው። በየሠፈሩ አዋጁን የሚያስፈጽሙ ስማቸው ተለይቶ ይፋ ይደረጋል፤ የፃነት ኃይሎች በእነዚህ ኃይሎች ላይ እርምጃ ይወስዳሉ። 
4. የጦርና የፓሊስ ሠራዊት አባላት - በተለይም የአጋዚ ጦር አባላት - ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለእናንተ ገደብ የለሽ ሥልጣን የሰጠ በመሆኑ የምትጠቀሙ አይምሰላችሁ። እናንተ ዜጎችን በመግደላችሁ፣ በማሰራችሁና በማሰቃየታችሁ የሚጠቀሙት አለቆቻችሁ ጄኔራሎች እና የህወሓት/ኢህአዴግ ሹማምንት ናቸው። አዋጁ ከሌላው ሕዝብ ያላነሰ እናንተንም ባርያ የሚያደርግ ነው፤ የዓመት እረፍት እንኳን መውሰድ እንኳን መውሰድ እንዳትችሉ የተገደባችሁ መሆኑን እወቁ። በአዋጁ ተፈፃሚነት ለእናንተ የሚተርፋችሁ የእድሜ ልክ ፀፀትና ከሕዝብ ጋር የምትገቡት ቁርሾ ነው። የእናቶችና የሕፃናት ዋይታና ለቅሶ ይሰማችሁ፤ ህወሓት/ኢህአዴግ እናንተን ተጠቅሞ የኢትዮጵያም ሕዝብ በባርነት እየገዛ መሆኑ ይታያችሁ። ከኢህአዴድ መወገድ በኋላ የሚመጣው ሥርዓት እናንተን የሚጠቅም እንጂ የሚጎዳ አለመሆኑን አውቃችው ከአገዛዙ ጋር ያላችሁን ግኑኝነት በጥሱ። ዛሬውኑ ወስኑ ! በወገኖቻችሁ ላይ ላለመተኮስ ለራሳችሁቃል ግቡ !!! የመሣሪያዎቻችሁን አፈሙዝ በሙስና ወደደለቡት አለቆቻችሁ አዙሩ፤ አልያም ሥርዓቱን ከድታችሁ የነፃነት ኃይሎችን ተቀላቀሉ። ሥርዓቱን ለሚከዱ የሠራዊቱ አባላት የክብር አቀባበል እናደርጋለን፤ በየቦታውም ይህን የሚያስተባብሩ አካላትን አደራጅተናል። ይህን ዕድል ከመጠቀም ይልቅ ሥርዓቱን ለማቆየት የወሰናችሁ የሠራዊቱ አባላት የምትዋጉት የጠላት ጦርን ሳይሆን የራሳችሁን ሕዝብ መሆኑን መሆናችሁን እወቁ። በምንም ዓይነት ሕዝብን ማሸነፍ አትችሉም። 
5. የጦርና ፓሊስ ሠራዊት አባላት ቤተሰቦችና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በሠራዊቱ ላይ ጫና ያሳድር። ሠራዊቱ ከኢትዮጵያ አብራክ የወጣ ነውና የኢትዮጵያ ሕዝብን ይሰማል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ለህወሓት ሹማምንት ድሎት ሲባል በገዛ ልጆቹ መገደልና መረገጥ የለበትም። ሠራዊቱ የህወሓት/ኢህአዴግ ሠራዊት መሆኑ እንዲያበቃ ሁለገብ ጥረት እናደርጋለን። 
6. በአገዛዙ የስለላ መዋቅሮች የምትሠሩ ወገኖቻችን ኃላፊነት አለባችሁ። ማንን እየተከላከላችሁ፤ ማንን እያጠቃችሁ እንደሆነ አስተውሉ። ለራሳችሁ ደህንነት እና ለህሊናችሁ የሚበጃችሁ ከሕዝብ ጎን መቆም ነውና ዛሬውኑ ወስኑ፤ እናንተም ወደ ሕዝብ ትግል ስትመጡ ለመቀበል ዝግዱ ነን፤ ይህን እድል አታስመልጡ። በተመሳሳይም የኢህአዴግ አባላት ጎራችሁን ለዩ። አምርሮ ለዘመተብን ጠላት የመረረ ምላሽ ለመስጠት ተዘጋጅተናል። 
7. ህወሓት/ኢህአዴግ ከመነሻው ጀምሮ በአርሶ አደሩ እየነገደ ያለ እኩይ ኃይል ነው። ዛሬ የመንግሥትን ሥልጣን የያዙት ኃይሎች አርሶ አደሩ እየተራበና እየታረዘ ጠግቦ የሚያድር አስመስሎ ለዓለም የሚናገሩ ውሸታሞች ናቸው። ከዚህም በተጨማሪ መሬትን እየቀሙ ለራሳቸውና ለወዳጆቻቸው የሚያድሉ በልተው፣ ገፈው፣ በዝብዘው የማይጠግቡ ሆዳሞች ናቸው። ከእንግዲህ የኢትዮጵያ አርሶ አደር በባርነት ለሚገዛው አገዛዝ ግብር፣ መዋጮ፣ የምርጥ ዘርም ሆነ የማዳበሪያ እዳ አይከፍልም፤ ካድሬዎች ለሚጠሩት ስብሰባ አይወጣም፤ ራሱ በመረጣቸው የአገር አስተዳዳሪዎች እንጂ በሥርዓቱ ካድሬዎች አይተዳደርም፤ ለዳኝነት ወደ አገዛዙ ፍርድ ቤት አይሄድም። 
8. በማናቸውም የመንግሥት ሥራ ላይ የተሠማራ የመንግሥት ሠራተኛ ሥራውን በአግባቡ ሠራ ማለት ይህንን የባርነት አዋጅ አስፈፃሚ ሆነ ማለት እንደሆነ ይወቅ። እያንዳንዱ ነፃነቱን የሚወድ የመንግሥት ተቀጣሪ የዕለት ተዕለት ሥራውን ሲፈጽም የሥራው ውጤት ህወሓት/ኢህአዴግን የሚያዳክም እንጂ የሚያጠናክር እንዳልሆነ እርግጠኛ ይሁን። ሕዝባዊ እምቢተኝነትና ሕዝባዊ አሻጥር በሁሉም ቦታዎችና በሁሉም የሥራ ዓይነቶች ተግባራዊ ይሆናሉ። በባርያ ፈንጋይ ላይ አሻጥር መፈፀም በምድር የሚያስመሰግን በሰማይም የሚያፀድቅ ተግባር እንደሆነ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ያውቃል፤ በጣሊያን ፋሽስት የወረራ ዘመን የመንግሥት ሠራተኞች የነበሩ የውስጥ አበርኞች አብነቶቻችን ናቸው። ሕዝባዊ አሻጥር የኢትዮጵያ በህወሓት አገዛዝ ሥር ያለ መንግሥት ሠራተኛ የሥራ ባህል ይሆናል። 
9. ኢትዮጵያዊያ በአገራችን በነፃነት መኖር የምንችለው ይህን የባርነት አዋጅ በማክሸፍ የህወሓት/አገዛዝን አስወግደን የሕዝብ ይሁንታ ያለው መንግሥት ስንመሠርት ብቻ እንደሆነ እያንዳንዱ ወጣት ይወቅ። ሕዝባዊ እምቢተኝነት፣ ሕዝባዊ አመጽና ሕዝባዊ አሻጥር የወጣቱ ትውልድ ባህል ይሆናሉ። ከእንግዲህ የወጣቱ ሙሉ አካላዊና አዕምሮዓዊ ጉልበት ይህንን አዋጅ በማክሸፍ ሥራ ላይ ይውላል። በየቦታውና ጊዜው ተስማሚ የሆነ የትግል ስልት በመቀየስ የዚህን አስከፊ ሥርዓት ፍፃሜ ለማፍጠን የተለያዩ አደረጃጀቾችን በሥራ ላይ አውለናል። ወጣቶች የራሳቸው ፈጠራና አካባቢያዊ ግብዓቶችን በመጠቀም የህወሓት አገዛዝን በኃይል ለመከላከል የሚያደርጉትን ጥረት እንደግፋለን፤ እናበረታታለን። 
10. በየአካባቢው አካባቢያዊ ጥያቄዎች ሊኖሩን ይችላሉ፤ አካባቢያዊ ጥያቄዎችን ለትግል ማንሳት የሚበረታታ ነው፤ ያም ሆኖ ግን ትግላችን የሚደጋገፍና ወደ ጋራ ድል የሚያመራ እንዲሆን የተቻለንን ሁሉ ጥረት እናደርጋለን። በተለያዩ ማኅበረሰቦችና በተለያዩ እምነት ተከተያዮች መካከል የተፈጠረውን መግባባትና መተጋገዝ ለማዳበር ጠንክረን እንሠራለን። አገራዊ ኅብረት ለመፍጠር ቀንና ሌሊት እንተጋለን። 
11. በውጭ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንም ሙሉ ጉልበታቸውና ኃይላቸውን የህወሓት አገዛዝን ማዳከም ብቻ ሳይሆን ማጥፋት ላይ እንዲያተኩሩ እንሠራለን። በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የባርነት አዋጅ ታውጆበታልና በውጭ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንም ምላሽ የመረረ ይሆናል።

በመጨረሻም ማሳሰብ የምሻው ነጥብ አለ። ይህ የህወሓት ዘራፊ ቡድን በአንድ በኩልና በዋናነት ይህንን የባርነት አዋጁን በጉልበት ለማስፈጸም ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሰላም የሚፈልግ ለማስመሰል እሱ ከመረጣቸውና ባፈና መዋቅሩ ውስጥ ከቦ እያስፈራራ ካስቀመጣቸውና በተግባር ሽባ ካደረጋቸው የፖለቲካ ሰዎች ጋር እደራደራለሁ የሚል የተለመደ ማደናገሪያውን ለማስኬድ እየሞከረ እንደሆነ እያየን ነው። ይህ አካሄድ አውቀው ሊታለሉ የሚፈልጉ ፈረንጆችን ያታልልበት እንደሆነ እንጂ በሀገሪቱ ያለውን የፖለቲካ ቀውስ በፍጹም ሊፈታ እንደማይችል የታወቀ ነው። የፖለቲካ ኃይሎች በነፃነት መንቀሳቀስና እንወክለዋለን ከሚሉት ሕዝብ ጋር በነፃነት መምከር ሳይችሉ ትርጉም ያለው ወደ ዘላቂ ሰላም የሚወስድ ድርድር ማድረግ ከቶውኑም አይችሉም። ሽጉጥ በግንባር ደግኖ “ከነብስህ ወይንም ከገንዘብህ” ብሎ ምርጫ ለሚሰጥህ ማጅራት መቺ ሕይወትን ለማትረፍ “ገንዘቤን ውሰድ” ቢባል በማጅራት መቺውና በሰባው መካከል “የሰጥቶ መቀበል ድርድር ተደረገ” እንደማይባል ሁሉ በግንባራቸው ላይ ሽጉጥ ደግኖ፤ ወይንም በእስር ቤት ከከተተ በኋላ የሚደረግ ድርድር በምንም አይነት በነፃነትና በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ድርድር ተደርጎ አይወሰድም፤ ተቀባይነትም የለውም። ስለዚህ ይህ አዋጅ በተግባር ላይ እስካለ ድረስ የሀገር ውስጥ ሰላማዊ ተቃዋሚዎችን በማስፈራራት እየሰበሰቡ ወያኔን ብቻ አሸናፊ የሚያደርግ የድርድር ሙከራ ከእስረኞች ጋር የሚደረግ ድርድር ስለሆነ ምንም ተቀባይነት የለውም። የሕዝባዊ ትግሉም በእንዲህ አይነት የማደናገሪያ ሂደት ከጀመረው የነፃነት ትግል ላንዲት ጋት እንኳን እንደማይዘናጋ እንዲታወቅ ያስፈልጋል።
ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ!!!!
በዚህ የመጨረሻ የፍልሚያ ወቅት ጥቂቶቻችን ልናልፍ እንችላለን። ለነፃነታችን ስንል ሕይወታችንን ብንሰጥ ፈጣሪያችን በአምሳሉ ሲፈጥረን የሰጠንን የሰውነት ማንነት እውን ለማድረግ በምናደርገው ትግል ነውና የምናልፈው፤ የፈጣሪያችንን ፈቃድ ለማስፈጸም የገበርነው ሕይወታችን ነውና በደስታ የምንጠጣው ጽዋችን ነው። ይልቅስ ፈጣሪያችን ለምንግዜውም ይቅር የማይለን ከሌላው እንሰሳ ለይቶ የሰጠንን ይህን በነፃነት የታጀበ የሰው ልጅነት፤ እንደ እንሰሳ ለሚበላና ለሚጠጣ ቁሳዊ ጥቅም ሸጠን፤ ሰው መሆንን በእንሰሳዊ የባርነት ሕይወት ቀይረን እኛ ባርነትን ተቀብለን ከራሳችን አልፎ ባርነትን ለልጆቻችን ያስተላለፍን እንደሆነ ነው። የዛሬ ትውልድ ኢትዮጵያውያን የባርነትን ኑሮ ከኛ እንዳያልፍና ወደ ልጆቻችን እንዳይጋባ ማስቆም ታሪክ የጣለብንና በእርግጠኛነት የምንፈጽመው ተግባራችን እንደሆነ ከቶውንም አልጠራጠርም።

ጥቅምት 7 ቀን 2009 ዓ.ም. 
እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ
አንድነት ኃይል ነው !!!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ !!!

No comments:

Post a Comment