በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዴ ኃይቅ በዓመታዊው የእሬቻ በዓል ላይ ባለፈው ዕሁድ ትርምስ ከተቀሰቀሰ በኋላ የብዙ ሰው ሕይወት መጥፋቱን ተከትሎ በበርካታ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች አለመረጋጋቱ እየተባባሰ መምጣቱን ያስገነዘቡት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቃል አቀባይ ሩፔርት ኮርቪይ ተቃዋሚዎች ከሁከት አድራጎቶች እንዲቆጠቡና ሁከትን እንዲያወግዙ ጠየቁ።
የፀጥታ ኃይሎችም ቢሆኑ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎችንና ደረጃዎችን ማክበር እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
በእሬቻ በዓል ላይ ከተቀሰቀሰው ተቃውሞ በኋላ ከፀጥታ ኃይሎች ሲሸሹ ገደልና በየጉድጓዱ፤ አለዚያም ኃይቁ ውስጥ እየገቡ ብዙ ሰዎች መሞታቸውን ያመለከቱት የከፍተኛ ኮሚሽነሩ ቃል አቀባይ ሩፔርት ኮርቪይ የሁከቱ ሁኔታ እየተባባሰ የመጣው በከፊልም የመንግሥት ባለሥልጣናት በበዓሉ ላይ ስለተከሰቱት ሁኔታዎች በሚሰጧቸው ማብራሪያዎች ላይ ሰዉ እምነት በማጣቱ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም በተፈጠረው ሁኔታ የሞቱት ሰዎችን ቁጥርም ሆነ በወቅቱ የፀጥታ ሃይሎች ያሣዩትን ምግባር በተመለከተ እጅግ በጣም በተለያያ ፅንፍ የሚሰጡት መግለጫዎች ለተቃውሞው መባባስ ምክንያት ሳይሆኑ እንዳልቀሩ ተንትነዋል፡፡
የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቃል አቀባይ አያይዘውም በእሬቻ በዓል ላይ የተከሰተው ምን እንደሆነ በትክክል ለማወቅ ነፃ ምርመራ እንዲካሄድ አሳስበዋል።
በዕሁዱም ብቻ ሳይሆን ካለፈው ኅዳር እንስቶ በተካሄዱት ተቃውሞች ዙሪያ የተፈጠሩት በርካታ የሁከት ሁኔታዎች ተጠያቂነት የት እንዳለ መረጋገጥ እንዳለበት አሳስስበዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በአዲስ አበባ እና በሌሎችም የሀገሪቱ አካባቢዎች የሞባይል መገናኛ አገልግሎቶችን ከማቋረጥ ይልቅ እየተባባሰ ላለው ጥረት መፍትኄ የሚሆን ተጨባጭ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል፡፡
በተለይም ነፃ ታዛቢዎች ወደ አማራና ኦሮምያ ክልሎች ገብተው ሁሉንም ወገኖች በማነጋጋር ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ እንዲያጣሩ መንግሥቱ እንዲፈቅድ አሳስበዋል።
የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ኢትዮጵያ በሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ግዴታዎቿ መሠረት ወደተጠቀሱት ክልሎች ለመግባት ፈቃድ እንድስትሰጥ ኮሚሽኑ ባለፈው ነኀሴ መጠየቁን አስታውሰው አሁንም በድጋሚ እንማፀናለን ብለዋል።
በሁለቱም ክልሎች በርካታ ሰዎች እየታሠሩ ስለመሆኑ የሚደርሱን ሪፖርቶች አሳስበውናል ያሉት ቃል አቀባዩ ሩፔርት ኮርቪይ መንግሥቱ ሃሣባቸውን የመግለፅ መብታቸውን በመጠቀማቸው ምክንያት ያሠራቸውን እንዲፈታ ጠይቀው “ተቃውሞና ትችትን ማፈን ውጥረትን ከማባባስ የተለየ ውጤት የለውም” ብለዋል።
No comments:
Post a Comment