ጥቅምት ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአርበኞች ግንቦት7 ሊ/መንበር ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ህወሃት መራሹ መንግስት ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተመለከተ ዛሬ በሰጡት መግለጫ አዋጁ “ ሰው ሆኖ መኖርን የናፈቀውና ካሁን በኋላ ያለነፃነት በፍጹም አልኖርም ብሎ ፍርሀትን በሚገርም ጀግንነት አሸንፎ ውድ ሕይወቱን እየከፈለና እየታገለ ያለውን፤ ከሞላ ጎደል መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ እንደገና በፍርሀት ቆፈን ውስጥ መልሶ በመክተት ከቀድሞውም በባሰ ባርነት ውስጥ ዘፍቆ ለመግዛት” ታልሞ የወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
“የኢትዮጵያ ሕዝብ ካሁን በኋላ ባርነትን የሚሸከምበት ምንም ጫንቃ የለውም። በዚህ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ሕዝብ በፍጹም በፍጹም ተመልሶ የባርነት ሕይወት ውስጥ ሊኖር አይፈቅድም። ስለዚህ ከዚህ በኋላ የፍትህና የነፃነት ኃይሎች ዋና ተግባር ያላቸውን አቅም ሁሉ አስተባብረውና ነፃነት የራበውንና የጠማውን ሕዝባቸውን ከጎናቸው አሰልፈው፤ ጊዜውና ሁኔታው የሚፈቅደውን ተለዋዋጭና ተለማጭ የትግል ስልት እየተጠቀሙ ይህ አዋጅ በፍጹም ተግባራዊ እንዳይሆንና እንዳይሳካ ማድረግ” ይኖርባቸዋል ያሉት ፕ/ር ብርሃኑ፣ ይህ አዋጅ ተሳካ ማለት የኢትዮጵያ ህዝብ ላልተወሰነ ጊዜ በባርነት መቀመቅ ውስጥ እንዲኖር መፍረድ ነው ብለዋል።
ስለዚህም ይላሉ ፕሮፌሰሩ፣ ይህን አዋጅ አከሸፍነው ማለት የወያኔ ስርዓት አከተመለከት ማለት በመሆኑ፣ የመጨረሻውን የሞት ሽረት ትግል እናድርግ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል። “ባርነትን በጉልበት ሊጭንብን ጦር ሰብቆ የመጣውን እኩይ ኃይል፤ ምርጫችን ሆኖ ሳይሆን በላያችን ላይ የተጫነ ግዴታ ስለሆነ ከእንግዲህ ገድሎ መሞት እንጂ “በሰላምተኝነት” መሞት የሌለ በመሆኑ፣ ነፃነት የጠማው ኢትዮጵያዊ ሁሉ የነጻነት ሃይሎችን እንዲደግፍ እና እንዲቀላቀል ጠይቀዋል። ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጥሪ ያስተላለፉት ፕ/ር ብርሃኑ “የዛሬ ትውልድ ኢትዮጵያውያን የባርነትን ኑሮ ከኛ እንዳያልፍና ወደ ልጆቻችን እንዳይጋባ ማስቆም ታሪክ የጣለብንና በእርግጠኛነት የምንፈጽመው ተግባራችን” ይሆናል ብለዋል።
No comments:
Post a Comment