በ1928 ዓም በአዲስ አበባ የካ በሚባለው አካባቢ የተወለዱት ኢንጂነር ሃይሉ ሻውል ባደረባቸው ህመም በህክምና ሲረዱ ቆይተው ሃሙስ መስከረም 26 ቀን 2009 ዓም በ80 አመታቸው ከዚህ አለም በሞት መለየታቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል። የመአድ መስራች፣ ቀጥሎም የመኢአድ በኋላም የቅንጅት ሊቀመንበር የነበሩት ኢንጂነር ሃይሉ ሻውል ህይወታቸው ያለፈው ህክምና ሲከታተሉ ከነበሩበት የባንኮክ ታይላንድ ሆስፒታል መሆኑ ታውቋል።
የሲቪል ምህንድስና ሙያተኛ የነበሩት ኢንጂነር ሃይሉ ሻውል በተለያዩ አለም አቀፍ ድርጅቶች በቅጥርና በማማከር አገልግሎት መስጠታቸው ተከትሎ ባካበቱት ሙያ አገራቸውን ለመጥቀም ባደረባቸው ፍላጎት በተለያዩ መስሪያ ቤቶች በበላይ ሃላፊነት አገልግለዋል። እነዚህም ውስጥ የአባይ ሸለቆ ጥናት ፕሮጄክት ሃላፊ፣ የኢትዮጵያ ስኳር ፋብሪካዎች ዋና ስራ አስኪያጅ፣ የኢትዮጵያ አውራ ጎዳና (በአሁኑ አጠራር የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን) ዋና ስራ አስኪያጅ በመሆን አገራቸው ኢትዮጵያን አገልግለዋል።
ኢንጂነር ሃይሉ ሻውል የአውራ ጎዳና ዋና ስራ አስኪያጅ በነበሩ ሰዓት ወራሪው የሱማሊያ (ዚያድባሬ) ጦር ኢትዮጵያን በወረረ ሰዓት የድሬዳዋ አውሮፕላን ጣቢያን ቀን ከሌት በክትትል በማሰራት የኢትዮጵያን አየር ሃይል የበላይነቱን እንዲይዝና ጦርነቱ በኢትዮጵያ ድል አድራጊነት እንዲጠናቀቅ የላቀ የዜግነት ድርሻቸውን ተወጥተዋል።
ኢንጂነር ሃይሉ ሻውል በሙያቸው ባስመዘገቡት ውጤት መሰረት የመንግስት እርሻዎች ሚኒስትር በመሆን በከፍተኛ ሃላፊነት ማገልገላቸው የህይወት ታሪካቸው ያመለክታል። በመንግስት የእርሻ ሚኒስትርነትም ለሁለት አመት ተኩል ቆይታ አድርገዋል።
ኢንጂነር ሃይሉ ሻውል ፖለቲካ ተሳትፏቸውን በተመለከተ መአህድን ከመመስረት ጀምሮ “የመአህድ የውጭ ግንኙነት ዘርፍ ሃላፊ” በመሆን የድርጅቱ ፖሊሲ የማስፈጸም፣ ደጋፊና አባላትን የማፍራት ስራ ሰርተዋል። በማስከተልም የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)ን በመመስረት በሊቀመንበርነት አገልግለዋል። መኢአድ የከፈለውን መስዋዕትነትና ትግል በግንባር ቀደምትነት መርተዋል።
ኢንጂነር ሃይሉ ሻውል በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ጉልህ ድርሻ ባለው የምርጫ 97 እንቅስቃሴ ወቅት የተቃዋሚ ፓርቲ የሆኑት መኢአድ፣ ኢዴፓ፣ ኢዴሊና ቀስተደመና በጋራ “ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ (ቅንጅት)” በመመስረት በሊቀመንበርነት ተመርጠው የምርጫ እንቅስቃሴውን በበላይነት መርተዋል።
ከምርጫው በኋላ የህወሃት አገዛዝ በፈጠረው የማጭበርበርና የንጹሃን ህይወት ግድያ አቅጣጫ ለማሳየት ኢንጂነር ሃይሉ ሻውል ከትግል አጋሮቻቸው ወደ እስር ቤት የተወረወሩ ሲሆን፣ ለሁለት አመታት ያህልም በእስር በኢት የስቃይና መከራ ቆይታ አድርገዋል።
በተለያዩ ጊዜያቶች በጨለማ ቤት የመታሰር እጣ ፋንታ ደርሶባቸዋል።
ኢንጂነር ሃይሉ ሻውል ከፖለቲካ አመራርነት ተሳትፎ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስን በተለይም “የኢትዮጵያ ነጽዳ ጋዜጠኞች ማህበር(ኢነጋማ)” በመደገፍ ዙሪያ በአርአያነት የሚጠቀስ ስራ መስራታቸውን የማህበሩ አመራሮች በየጊዜው የሚያስታውሱት ነው።
ኢንጂነር ሃይሉ ሻውል ባለትዳርና የስድስት ልጆች አባት ነበር።
መላው የኢሳት ቤተሰብ ለኢንጂነር ሃይሉ ቤተሰቦች ወዳጆቻቸው መጽናናትን ይመኛል።
No comments:
Post a Comment