Friday, June 17, 2016

ዳግመኛ የመንግሥት ዋይታ በተቃዋሚዎች ላይ (ጣሰው አሰፋ)

ጁን 11 2016 በፍራንክፈርት ከተማ ላርበኞች ግነቦት7  የድጋፍ ማሰባሰቢያ (Fundraising) ፕሮግራም ላይ ተገኝቼ ስለነበር አንዳንድ ገጠመኞቼን በቦታው ላልነበሩ ለማሰማት የሚለው የዚህ ማስታወሻ መነሻዬ ነው። ዳሩ ግን፤  በሱ ላይ ትረካዬን ከመቀጠሌ በፊት፤ ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ፤ አንድ ከ 11 ዓመት በፊት የሆነና በ11.06. 2016 ከሆነው  ሁኔታ ጋር ተመሳሳይነት የነበረው ድርጊትን ስላስታወስኩ እሱን ላስቀድም፤


ኖቬምበር 2005  ዓ.ም.  አንደኛ/ ኮማንደር መስከረም አታላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሊቀ-መንበር
ሁለተኛ/ አቶ ቱሃት ፖል ቻይ የኢትዮጵያ አንድነት አርበኞች ግንባር ሊቀመንበር፤ ወደጀርመን ሃገር መጥተው ስለኢ ትየጵያ ጊዜያዊ ሁኔታ፤ ስለየድርጅቶቻቸውም አካሄድና እንዲሁም ሊደረግላቸው ስለሚፈልጉት ድጋፍ  ከኢትዮጵያውያን ጋር ውይይት እንዲያደርጉ ፐሮገራም ይዘጋጅላቸዋል፤ እነዚህን ሁለት ሰዎች ወደጀርመን አገር ጋብዘው ያስመጧቸው አቶ ከሳየ መርሻ የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር የውጭ አካል የአመራር አባል ከሌሎች ተባባሪዎቻቸው ጋር በመሆን ነበር።

ጉባዔው የተዘጋጀው ለኖቬምበር 18 . 2005 ሲሆን። ቦታው ከፍራንከፈረት ወጣ ያለች ሩሰልስሃይም የምትባል ትንሽ ከተማ ነች። ዕለቱ ቅዳሜ ነው፤ አዘጋጆች አዳራሹን ለመክፈት ወደ ስፍራው ይደርሳሉ፤ ስፍራው በፖሊስ ተወሯል። ምነው ሲባል፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ስብሰባ አድራጊዎቹ ጦርነት አውጀውብኝ ለዚያ ጦርነት ማራመጃ ገንዘብ ሊሰበስቡ የተዘጋጁ ናቸውና ስብሰባው እንዳይደረግ ይታገድልኝ ብሎ ስላመለከተ፤ ስብሰባው አይካሄድም ይላል ፖሊስ ነፍሴ፤

ልብ በሉ፤ ቀኑ የበዓል ቀን ነው አቤት የሚባልበት ቦታ የለም፤ መስሪያ ቤት ሁሉ ዝግ ነው። በመሰረቱ ስብሰባው እንዳይደረግ ሲወሰን ለአዘጋጅዎቹ በቅድሚያ ማስታወቅ ሲገባ ፖሊስ ያለምንም ማስጠንቀቂያ ብዙ የተደከመበትን ዝግጅት ሳይደረግ ቢቀር ለሚያደርሰው ኪሳራና ሌላም ጉዳት ማን ተጠያቂ እንደሚሆን ለማወቅ የሚቻል አልነበረም። ለተባለው ውንጀላም ይህን አሳማኝና ተጨባጭ መረጃ ባለመኖሩ፤ አራት ሰዓት የፈጀ ክርክረና ውጣ ውረድ ከተደረገ በዃላ አቶ ካሳዬ መረሻና ሌሎችም ባደረጉት ጥበብ የተሞላበት ደርድር  ፖሊስ በስብሰባው ላይ ተገኝቶ ውይይቱንና ሂደቱን ተከታትሎ መረጃውን ሊያሰባስብ እንደሚችል  ስምምነት ላይ ተደረሶ ከአራት ሰዓት መዘግየት በዃላ ስብሰባው እንዲጀመር ተደረገ። ፖሊስም ለተወሰኑ ደቂቃዎች ቁጭ ብሎ በአስተርጓሚ ከተከታተለ በሁዋላ ለቀረበው ውንጀላ ማዳበሪያ የሚሆን መረጃ የሚገኝ መስሎ ስላልታየው ጥሎን ወጣ፤ ስብሰባው ተካሄደ። የወያኔ መንግስት እንዳሰበውም ሳይሆን ቀረ።

እንደ ዕውነቱ ከሆነ፤ ጉባዔው በጥሩ ሁኔታ መካሄዱ ብቻ ሳይሆን፤ በተለይ አቶ ቱሃት ፖል ባደረጉት ሰፊ ንግግር ሲያጠቃልሉ፤ ያሉትን ብጠቅሰው ጥሩ መታሰቢያ ይሆነናል፤ “… ብሶት ተናጋሪዎች በመሆን ብቻ ተፈርጀን ታሪካዊ ሐገራችንና ሕዝባችንን በድቅድቅ የባርነት ጨለማና አዘቅጥ ውስጥ እንደምንከተው ተገንዝበን፤ ለወያኔ ዕድሜ ማጠር ከተፈለገ፤ ጠላትን ከህዝብ ነጥለን ለመምታት እንድንችል፤ በብሄረሰብ፤ በባሕል፤ በቋንቋ፤ በሃይማኖት፤ በጾታና በክልል የፈጠሩብንን ስነ-ልቦናዊ ችግሮች እርግፍ አድርገን በመተው፤ ብሔርተኝነትንና ትምክህተኝነትን ገድለን በመቅበር ወያኔ ሃገራችንና ህዝባችንን ለማጥፋት ቆርጦ የተነሳ የባዕዳን ምንደኛ መሆኑን ተገንዝበን፤ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በኢትዮጵያዊነቱ በመተያየት ላለፉት 15 ዓመታት ወያኔ ለነሰነሰው መርዝ ሰለባ ሳንሆን፤ እጅ ለእጅ ተያይዝን የወያኔን ግብዓተ መሬት በሁለንተናዊ መለኩ በተቀነባበረ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ትግል በማፋጠን፤ በሱ ከርሰ-መቃብር ላይ አንድነቷና ሉአላዊነቷ የተከበረ፤ የግለሰቦች መብትና ነጻነት የተረጋገጠባት፤ የሁሉም ብሔር/ብሔረሰቦች የጋራ ቤት የሆንች ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለተተኪው ትውልድ እናስረክበ!” ነበር ያሉትና፤ እንዳጋጣሚ ዛሬ ከ11 ዓመት በሁዋላም ይህንኑ እያልን እንደምንገኝ አስቡት።

በመጨረሻም ከተሰብሳቢው የገንዘብ ዕርዳታ ተሰብስቦ ለአቶ ቱሃት የተሰጠ ሲሆን፤ ውይይቱ ለወደፊቱም   መነቃቃትን የፈጠረ፤ ንቅናቄዎቹንም በቀጣይ ለመደገፍ የቀሰቀሰ አንደነበረና፤ ከዚያም በሁዋላ በጀርመን አገር ቀጣይ የሆነ የድጋፍ ማሰባሰቢያ የሚሆን ፕሮጄክት ተነድፎ መንቀሳቀስ የሚቻልበትን ዘዴ ለመጀመር የሚያስችል ዘዴ ተቀይሶ ነበር። ዳሩ ግን አቶ ቱሃትም ከጀርመን  ከተመለሱ በሁዋላ ብዙም ሳይቆዩ ዱካቸው ይጠፋል፤ ኮማንደሩም እዚሁ ጀርመን አገር ቀርተው በችረቻሮ ንግድ ይተዳደራሉ የሚል ወሬ አለ። ስለዚያ ጉባዔ ሁኔታ ለማስታወስ ያህል ይህንን  አህል ካልኩ  በሁዋላ ወደ 11.06.2016 የፍራንክፈርቱ የአርበኞች ግንቦት7 ገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ልመልሳችሁ፤

ይሄኛውም ስብሰባ ከ11 ዓመት በፊት እንደሆነው ለሁለተኛ ጊዜ የወያኔ መንግሥት ተቃውሞ ገጥሞታል። የተቃውሞው መንገድ ግን ከቀደመው የተለየ ነው። እንደሚመሰለኝ በቀደመው ሙከራ የተፈለገው ውጤት ባለመደረሱ አልተሞከረም፤ ወይም ጥያቄው በባለስልጣናቱ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቶ፤ – ስለምክንያቱ መረጃ የለኝም –  ወይም ያ እርምጃ እንደጥፋት ተቆጥሮ እሱን መድገም አላስፈለገም። ጥፋት ስላለመድገም ጉዳይ ከተነሳ፤  መለስ በ2002 ዓ.ም. ምርጫ ጊዜ በ1997ቱ ምርጫ ሰለተፈጸመ ስህተት ሲናገር እንዲህ ብሎ ነበር ” ኢሕአዴገ? ዋና ልምዱ ጥፋቱን አይደግምም። በ97 ዓ.ም. ምርጫ የተፈጸመው ስህትት እንዳይደገም አስፈላጊው ጥንቃቄ ተደረጓል” ብሎ ነበር። ፕሮፌሰር መስፍን ወያኔ “ገርበብ አድርጎ የከፈተውን በርግደን ገባን” እንዳሉት፤ መለስ ሲቀናጣ “እንከን የለሽ” እያለ ያሞካሸውንና ውጤቱ መርዝ እንደበላች ውሻ አቅለብልቦ ከሰውነት ወደ አውሬነት የለወጠውን ምርጫ ነበር እንደጥፋት ቆጥሮ አይደገምም ያለው። በርግጥም ታዲያ እንዳለውም ከዚያ በዃላ አልተደገመም። የሰውዬውን ሃቀኝነትም መጠራጠር አይቻልም።

በ11.06.2016ቱ ተቃውሞ በሰላማዊ ሰልፍ እንዲሆን ነበር የተደረገው። ወደ 15 የሚሆኑ ሰዎች ግንቦት7  የሻቢያ ተላላኪ ነው ከሚለው ያረጀውና ያፈጀው፤ እስከ ግንቦት7 የናት ጡት ነካሽ ነው እስከሚለው አዲስ መፈክር የተጠቃለሉ “ጥሩ ጥሩ” ቅሌት ያልበዛባቸው “የጨዋ” መፈክሮች ሲያሰሙ ውለዋል። ተሰላፊዎቹ አርበኞች ግንቦት7 የሚለውን ስም የሰሙ አይመስለኝም፤ ግንቦት7 ሲሉ ነበር የዋሉት፤ ግንቦት ሰባት ቴሬሪስት ነውና የጀርመን መንግስት እንዲከለክለው የሚልም ጥያቄ ነበር። ተሰላፊዎቹ በደንብ ማጥናት የነበረባቸውን ያሰጠኗቸው አልመሰለኝም። ምክንያቱም ኦባማም ግነቦት7ን ቴሬሪስት በልልን ተብሎ በወያኔ ተጠይቆ አይሆንም መባሉን አላወቁም።

ከዚህ በተረፈ ስለዚህ ሰላማዊ ሰልፍ እንድተርክ ካደረጉኝ ምክንያቶች፤  እውጭ በሰላማዊ ሰልፉ ዙሪያ የተደረጉ የሃሳበ ልውውጦችና በአዳራሹ ውስጥ ስለዴሞንሰትሬሽኑ የተሰጡ አስተያየቶች/ትችቶች ነበሩ። ውጭ በሰልፉ አካባቢ በሰልፍ አድራጊዎቹና ከድጋፍ ማሰባሰቢያው ፐሮግራም ታዳሚዎች መካከል አንዳንድ ግለሰቦች መሃከል  በተደረገ  እንካ ስላንቲያ አንድ ያስደነቀኝ ነገር ነበር። አንዱ ያዳራሸ ፐሮግራም ታዳሚ  ተናድዶ እየጮኸ ያዙኝ ልቀቁኝ ይላል፤ ይህን ያየ ሌላ ያዳራሹ ፕሮግራም ተሳታፊ  ምን ሆነሃል? ምን ያስጮህሃል? ይለዋል “አንዴ! አንተ ደርግ ነህ አለኝ እኮ!” ሲለው፤ ታዲያ ይሄ ምን ያናድዳል? ምርቃት እኮ ነው። ታስታውሳለህ? በደርግ ጊዜ እኮ አንድ ነበርን። አሁን እኮ ተበጣጥሰን እኛና እነሱ እያልን ነው ሲል በጣም አስደነቀኝ። ከዚህ ሌላ ደግሞ፤ በአዳራሹ ውስጥ ስለሰልፉ ከተሰጡ አስተያየቶች/ትችቶች ከማስታውሳቸው፤-

ከአዘጋጂዎቹ መካከል አንዱ ” መንግሥት የተቃዋሚዎች ስብሰባን ተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ አደረገ ሲባል በጣም ያሰጋል፤ የጤና አይመስለኝም፤ ሲል ሌላው አከታትሎ ዱሮ እኮ እነሱ እውስጥ ሆነው እኛ ነበርን እውጭ ሆነን የምንጮኸው ይህ የሚና ልውውጥ ትልቅ ድል ነው ብለን እንወስደዋለን ይላል። ብርሃኑ ነጋም “እኔ ኖረዌይ ከተደረገልኝ ሰፊ አቀባበል የበለጠ  በአውሮፓ ሌላ ቦታ ይገጥመኛል ብዬ አላስብኩም ነበር፤ ፍራንክፈርት ግን ከዚያም አልፎ  ወያኔም ጭምር ተሰልፎ ተቀበለኝ” ያለው የሰልፉ በጎ ገጽታ ነበር። ያም ሆነ ይህ መንግሥት በተቃዋሚዎች ላይ ሰላማዊ ሰልፍ ከወጣ መጽሃፉ “መንግስተሰማያት ቀርባለችና ንስሃ ግቡ” እንደሚለው ዓይነት መሆኑ ይሆን? ማን ያውቃል? ስለሰለፉ አበቃሁ።

አንዲት ሃሳብ ላክልና ሃሳቤን ልቋጭ፤ ባሁኑ ጊዜ በዲያስፖራው አካባቢ የማጤነው አንድ ነገር ስላለ ምናልባት ይህንን ግንዛቤዬን ለአንባብያን ላካፍል ብያለሁ፤ ይኸውም የሰዎች በፖለቲካ ድርጅቶች የስብሰባ ጥሪ ላይ በስፋት የመገኘትንና ያለመገኘትን በተመለከተ ነው። ባለፉት አምስት ዓመታት ለኢሳት ድጋፍ ተብለው በጀርመን አገር በተደረጉት ስብሰባዎች የሚገኘውን የህዝብ ብዛት በስፍራው በመገኘት ተከታትያለሁ። በጣም የሚያስደስት ነው። አንዳንዴ ወደሺ ሰው የሚያስተናግድ አዳራሽ ተይዞ በቦታ እጥረት ምክንያት የሚመለሱ ሰዎች እንዳሉ አይቻለሁ። ይህ ሚዲያን በሚመለከት ነው። በፖለቲካ ድርጅት በኩል ደግሞ፤ አርበኞች ግንቦት7 የሚባለው ስብስብ ከተፈጠረ ወዲህ ድርጅቱ በየቦታው በሚያደርጋቸው ስብሰባዎች ላይ የሚገኘውን የተሳታፊ ብዛት ስመለከት በጣም ጉድ የሚባል ነው።

ታዲያም በዲያስፖራ የሚንቀሳቀሱ ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ያሉትን ያህል፤ የሚያሰሙት ተደጋጋሚ እሮሮ “ስብሰባ ጠርተን ሰው አልመጣልንም፤” የሚል ነው። እንደኔ ሮሮ ብቻ እያሰሙ ከመኖር ለመላቀቅ እንደመፍትሄ ሊረዳ ይችላል የምለው፤ ከላይ እንደጠቀስኩት  እነዚህ ብዙ ህዝብ የሚያሰባስቡ ድርጅቶችን በመመርመር እኔ የሌለኝ ሌላው ያለው ምንድነው? እኔ ለምን ሕዝብን መሳብ አልቻልኩም? የህዝብን ጆሮ ለምን አላገኘሁም? የሚለውን ጥያቄ በማንሳት እራስን መጠየቅ። ይህን የምልበትም ዋና ምክንያት ድርጅቶች ሁሉ ለሕዝብ ጥቅም የቆምን ነን ብለው የሚንቀሳቀሱ እስከሆነ ድረስ አንዱ ከሌላው ሊማር የሚችለው ነገር ካለና ለመማር ቢሞክር፤ በምንም መመዘኛ ወደ “ሲኦል” የሚያወርድ መንገድ እንደማይሆን እርግጠኛ ነኝ።

ሰፊ ሕዝብ በተሰበሰበበት ቦታ እየተገኙ ሁኔታዎችን በማጥናት ሕዝብ ምን እንደሚፈልግ ለመረዳት ሞመከር፤ ከዚህ ግንዛቤ በመነሳትም፤ “እንደኔ የጠራ አቋም፤ መርህና ፕሮግራም ያለው የለም በማለት ብቻ እራስን አንቱ ከማለት ወጣ ብሎ፤ ህዝብ ምን እንዲደረግለት እንደሚፈልግ፤ የልቡ ትርታ ወዴት እንደሚመታ ማዳመጥና ከዚያ ተነስቶ አቅጣጫንና ሰትራቴጂን አቃንቶ መሄድ። የዚህ ዓይነቱ አካሄድ ደግሞ ልብ ብለን ካየነው፤ ተባበሩ፤ ተቀራረቡ፤ ተባብራችሁ ስሩ ለሚለውም ጩኸት ምላሽ ለመስጠት አመቺ አጋጣሚ ሊሆን የማይችልበት ምክንያት አይኖርም። ይህም ማለት ዞሮ ዞሮ ሁሉም ፊቱን ወደ አንድ የሕዝብ ፍላጎት አቅጣጫ  ካዞረ፤ ይህ ወደ አንድ አቅጣጫ የሚመለከት ሃይልም በመጨረሻ  የትብብርንና የአንደነትን መንገድ ከመከተል ሌላ አማራጭ ሊኖረው እንደማይችል ግልጽ ነው። ለጥንቃቄ ያህል፤ አርበኞች ግነቦት7 የትጥቅ አመጽ ጭምር የሚያከሂድ በመሆኑ፤ ከስሙ ጋር ንክኪ ያለው መልዕክት የትጥቅ ትግልን ለማይቃወሙ ብቻ ይሁን።

ጣሰው አሰፋ
ጀርመን

tassat@t-online.de

No comments:

Post a Comment