ኢሳት ያነጋገራቸው በአገር ውስጥ የሚገኙ ሰዎች መንግስት በሌሎች አገሮች እንደሚደረገው ሁሉ ለሟቾች ኢትዮጵያውያንም የክብር አቀባበል ሊያደርግላቸው ይገባል ይላሉ። የሞተ ሰው የለም በማለት መካድ ህዝብን ለማሞኘት መሞከረው ነው ሲሉ ያክላሉ።
አልሸባብ የተባለው የሶማሊያ ታጣቂ ቡድን በአፍሪካ የሰላም አስከባሪ ቡድን በደረሰበት ተደጋጋሚ ጥቃት ከዋና ከዋና የሶማሊያ ግዛቶች ለቆ ቢወጣም፣ ተከታታይ የደፈጣ ጥቃቶችንና የቦንብ ፍንዳታዎችን ማድረጉን አለቆመም። በነዚህም ጥቃቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ የሰላም አስከባሪው ጦር አባላት ተገድለዋል።
ትናንት ሰኔ 2፣ 2008 ዓም ማእከላዊ ሶማሊያ በሚገኘው የኢትዮጵያ ጦር ላይ ታጣቂ ሃይሉ በፈጸመው ጥቃት 60 ኢትዮጵያውያን መገደላቸውን ሲያስታውቅ፣ የአፍሪካ ህብረት፣ የሶማሊያ መንግስት እና የኢህአዴግ መንግስት በበኩላቸው እርስ በርስ የሚጋጭ መግለጫ ሰጥተዋል። የአፍሪካ የሰላም አስከባሪው ባወጣው መግለጫ የአልሸባብ ጥቃት መክሸፉንና 110 አባላቱ መገደላቸውን ሲገልጽ፣ የሶማሊያ መንግስት ቃል አቀባይ እና የኢህአዴግ መንግስት የኮሚኒኬሽን ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው በአልሸባብ በኩል 245 ወታደሮች መገደላቸውን ፣ በኢትዮጵያ በኩል ግን የሞተ ወታደር እንደሌለ ገልጸዋል። በኢትዮጵያ በኩል የተሰጠው መግለጫ ተአማኒነቱ ጥርጣሬ ላይ ወድቋል። ከፍተኛ የቦንብ ጥቃት በተፈጸመበት እና የተኩስ ልውውጥ በተደረገበት የጦር ካምፕ “አንድም ወታደር የሞተ የለም” ብሎ በመንግስት በኩል መግለጫ መስጠቱ ለብዙ ተችዎች አልተዋጠላቸውም። አንደኛው ወገን 245 ታጣቂዎችን እስኪገድል ድረስ ሌላው ወገን፣ ያውም ድንገተኛ ጥቃት ለመፈጸም የመጣ ሃይል፣ አቶ ጌታቸው እረዳ እንደተናገሩት ደግሞ ከዚህ በፊት ሲያደርግ ከነበረው ጥቃት በተለዬ በሰውና በከባድ መሳሪያ ሃይል ተደራጅቶ በመምጣት በፈጸመው ጥቃት፣ አንድም የኢትዮጵያ ወታደር ሳይገድል ተደምስሷል ብሎ መግለጫ መስጠት ከውትድርና ሙያ አንጻር ብቻ ሳይሆን ምንም ወታደራዊ እውቀት የሌለው ሰው እንኳ ሊቀበለው የማይችል መግለጫ መሆኑን አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።
የኢህአዴግ መንግስት በሰላም አስከባሪ ስም ወደ ሶማሊያ የሚልካቸው ወታደሮች በአልሸባብ ታጣቂዎች ሲገደሉ ቁጥራቸውን ይፋ የማድረግ ልማድ የለውም። የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት በሶማሊያ ምን ያክል ኢትዮጵያውያን እንደተገደሉ ሲጠየቁ “ የሟች ወታደሮችን አሃዝ ይፋ የማድረግ ግዴታ የለብኝም” ብለው ከተናገሩ ጀምሮ፣ በአንድ የድርጅት አባላት ብቻ የተሞላው ፓርላማ በሶማሊያ ስለሚገደሉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ለስራ አስፈጻሚው አካል ጥያቄ አቅርቦ አያውቅም። የኢትዮጵያ ህዝብ ስለሚገደሉት ልጆቹ ከመንግስት በኩል ትክክለኛ መረጃ የማግኘት መብት ቢኖረውም ፣ ይህ መረጃን የማግኘት መብቱ እስከዛሬ ተከብሮለት እንደማያውቅ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ። የሟቾቹን ቁጥር ይፋ ማድረጉ የኢትዮጵያን ጦር ሞራል የሚገድለውና የአልሸባብን ሞራል ደግሞ ከፍ እንደሚያደርገው ቢታወቅም፣ በተቃራኒው ግን ህዝቡ “በሶማሊያ የሚደረገው ጦርነት አዋጪ ነው ወይስ አይደለም፣ ሌላ መፍትሄስ ይኖር ይሆን?” የሚሉትን ጥያቄዎች በማንሳት ለመወያየትና መፍትሄ ለመፈለግ ያስችለዋል የሚሉ አስተያየቶችም ቀርበዋል።
የኢህአዴግ መንግስት የሟቾቹን ቁጥር መደበቁ ለችግሩ መፍትሄ እንዳይገኝለት ማድረጉ ብቻ ሳይሆን ፣ ለሟች ወታደሮች አንድም ቀን የክብር አቀባበል አለማድረጉ የአገሪቱ መሪዎች “ለሚያሰማሩዋቸው ወታደሮች እንኳን ክብር የላቸውም” የሚሉ አስተያየቶች እንዲሰጡ አድርጓል።
አልሸባብ ከአንድ አመት በፊት በብሩንዲ ፣ በዩጋንዳና በኬንያ የሰላም አስከባሪ ሃይሎች ላይ ድንገተኛ ጥቃት ሲፈጽም፣ አገራቱ ለሟች ወታደሮቻቸው የክብር አቀባባል እና የሀዘን ስነስርዓት አድርገዋል። የእነዚህን አገራት ድርጊት የተመለከቱ የኢትዮጵያ ወታደሮች “ ከእኛ ወገን የሚሞቱተስ ለምን ተመሳሳይ አቀባባል አይደረግላቸውም? በቁማችንም ሞተንም ተገቢው ክብር ለእኛና ለቤተሰቦቻችን አይሰጠም ” የሚል ጥያቄ በማንሳታቸው ፣ ከአካባቢው እንዲርቁ የተደረጉ ወታደሮች መኖራቸው ኢሳት ቀደም ብሎ መዘገቡ ይታወቃል።
የኢህአዴግ መንግስት “ በአልሸባብ የተገደለብኝ ወታደር የለም” በማለት ማስተባበሉን ትቶ፣ ሌሎች በሰላም አስከባሪነት በሶማሊያ የተሰማሩት የብሩንዲ፣ ዩጋንዳ እና ኬንያ መንግስታት እንዳደረጉት ሁሉ ፣ለሟች የኢትዮጵያ ወታደሮች ተገቢውን ክብር በመስጠት አቀባባል ሊያደርግላቸው እንደሚገባ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ። ይህን ማድረግ መቻል እና አለመቻሉ በሚቀጥሉት ቀናት ውስጥ የሚታይ ይሆናል።
No comments:
Post a Comment