በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ በፌደራል አቃቤ ህግ የሽብር ክስ የተመሰረተባቸው የኦፌኮ ም/ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ 22 ተከሳሾች ግንቦት 26/2008 ዓ.ም ላቀረቡት የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ አቃቤ ህግ መልስ ሰጥቷል፡፡
ዛሬ ሰኔ 20/2008 ዓ.ም የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት የአቃቤ ህግ የመቃወሚያ መልስን በጽሁፍ ተቀብሏል፡፡ አቃቤ ህግ መልሱን በሁለት ከፍሎ ያቀረበ ሲሆን፣ አንደኛው ከ1-4ኛ ተከሳሾች እንዲሁም ሁለተኛው ከ5-22ኛ ተከሳሾች ያዘጋጀው መሆኑ ተመልክቷል፡፡ የአቃቤ ህግ መልስ በሁለት የተከፈለ ይሁን እንጂ በይዘት ተመሳሳይ መሆኑን ካቀረበው የጽሁፍ መልስ ለመገንዘብ ይቻላል፡፡
ሁሉም ተከሳሾች የፍ/ቤቱን የሥረ ነገርና የከባቢ ዳኝነት ስልጣንን በተመለከተ ጉዳያቸውን ማየት የሚገባው ፌደራል ፍ/ቤት ሳይሆን የኦሮሚያ ክልል ፍ/ቤት መሆን አለበት በሚል ላቀረቡት መቃወሚያ አቃቤ ህግ የጸረ ሽብር አዋጁን አንቀጽ 31 በመጥቀስ የሽብርተኝነት ወንጀል የዳኝነት ስልጣን የፌደራል ጠ/ፍ/ቤት እና የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ስለመሆኑ የተመለከተ ስለሆነ ተከሳሾች በኦሮሚያ ክልል ፍ/ቤት እንዳኝ የሚለው መቃወሚያ ውድቅ እንዲደረግለት አመልክቷል፡፡
ተከሳሾች የተከሰሱበት ድርጊት በህገ ወጥነቱ በህግ ያለተደነገገና በህግ የማያስጠይቅ ነው በሚል ከህጋዊነት መርህ (principle of legality) ጋር በተያያዘ ላነሱት መቃወሚያ፣ አቃቤ ህግ ‹‹ወንጀሉ በግልጽ በህግ የተቀመጠ…በመንግስትና በህዝብ ንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰ…ስርዓቱን በኃይል እናስወግዳለን በማለት ማስተር ፕላኑን ሽፋን በማድረግ…›› ህገ ወጥ ድርጊት በመፈጸማቸው ክስ እንደቀረበባቸውና ይህም የወንጀል ህጉን መርህ የተከተለ ስለሆነ መቃወሚያቸው ውድቅ ይደረግልኝ ሲል ጠይቋል፡፡
ሌላው ተከሳሾች የቀረበባቸው ክስ የእኩልነትን መርህ እንደሚጥስ ጠቅሰው መቃወሚያ ማቅረባቸው የሚታወስ ሲሆን፣ አቃቤ ህግ ለዚህ መቃወሚያቸው ተቃውሞው አግባብነት እንደሌለው በመጥቀስ ‹‹የአቃቤ ህግ ተቋም ህገ መንግስቱን የማስከበር ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ ማስረጃን መሰረት በማድረግ ተገቢውን ክስ›› ማቅረቡን አመልክቷል፡፡ ስለሆነም የቀረበው መቃወሚያ ‹‹የህግና የማስረጃ›› ድጋፍ የሌለው በመሆኑ ውድቅ ይደረግልኝ ብሏል፡፡
አቃቤ ህግ የምስክሮቹን ዝርዝር እንዲጠቀስ በተከሳሾች የቀረበው መቃወሚያም ተገቢነት የሌለው ነው ሲል መልስ ሰጥቷል፡፡ በአጠቃላይ አቃቤ ህግ በፌደራል ረዳት ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ወ/አገኝ በኩል ተጽፎ በቀረበው መልሱ በተከሳሾች የቀረቡት ሁሉም መቃወሚያዎች ወድቅ እንዲደረጉለት አመልክቷል፡፡
የተከሳሾች አቤቱታ
በአቶ ጉርሜሳ አያኖ የክስ መዝገብ የተከሰሱት የኦፌኮ አመራሮችና አባላት በተደጋጋሚ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተፈጸመባቸው እንደሚገኝ ሲያሳውቁ ቆይተዋል፡፡ ዛሬም በተለይ የኦፌኮ አመራሮች አቶ በቀለ ገርባ፣ ጉርሜሳ አያኖ፣ ደጀኔ ጣፋና አዲሱ ቡላላ በቂሊንጦ እስር ቤት እየደረሰባቸው ስላለው የመብት ጥሰት ለፍርድ ቤቱ አቤት ብለዋል፡፡
አቶ ደጀኔ ጣፋ ሌሎችንም ተከሳሾች በመወከል ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት ቂሊንጦ እስር ቤት አስተዳደር በተከሳሾችና በቤተሰቦቻቸው ላይ በደል እየፈጸመባቸው ይገኛል፡፡ ‹‹በእስር ቤት መገለል እየደረሰብን ነው፡፡ ንጽህና በሌለውና ፍሳሽ በሚያስገባ ጨለማ ቤት ውስጥ ነው የታሰርነው፡፡ በዚህ ምክንያት ለጤና ችግር እየተጋለጥን ነው፡፡ ዓይናችንን እየታመምን ነው፡፡ እዚህ ለምንናገረው ስንመለስ የእስር ቤቱ አስተዳደር በቀል ይፈጽምብናል፡፡
‹‹እኛ ይህ ፍ/ቤት ጫና አለበት ብለን እናምናለን፤ ነጻ አይደለም፡፡ እኛ የሀገሪቱን ፖለቲካ እንረዳለን፡፡ ቤተሰቦቻችንን የምናየው እኮ ለ3 እና 5 ደቂቃዎች ብቻ ነው፡፡ ይህ መገለል ነው፡፡ አሁን 30 ደቂቃ ትጠየቃላችሁ ብለውናል፡፡ እንደፈለጉ ነው የሚያደርጉት፡፡ እኛ ለቤተሰቦቻችንም እንሰጋለን፡፡ በእውነት ይህ ፍ/ቤት ጫና የሌለበት ከሆነ ይህን ችግራችንን ይፍታልን›› ሲል አቶ ደጀኔ የእስረኞችን አቤቱታ በቃል አሰምቷል፡፡ ተከሳሾች በእስር ቤት የሚደርስባቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተመለከተ ከቃል በተጨማሪ በጽሁፍም አቤቱታቸውን ለችሎቱ ቀደም ብለው ማስገባታቸው ተጠቅሷል፡፡
አቶ ደጀኔ በተጨማሪ ቤተሰቦቻቸው ችሎት እንዲታደሙላቸው ከአሁን በፊትም ማመልከታቸውን በማስታወስ አሁንም ችሎት መታደም አለመቻላቸውን አንስተዋል፡፡ ‹‹እኛ ምን እንዳደረግንና ምን እንደምንባል እያንዳንዷን ነገር ቤተሰቦቻችን ችሎት ገብተው እንዲያውቁልን እንፈልጋለን፡፡ ይህ ለምን አይደረግልንም? ለምሳሌ የ85 አመት አያቴ 300 ኪሎ ሜትር አቋርጠው የእኔን ችሎት ለመስማት መጥተው ነበር፡፡ ግን ይኸው ችሎት አልገቡም›› በማለት ቤተሰቦቻቸው ችሎት እንዲታደሙ አመልክተዋል፡፡ በዛሬው ችሎት ከጋዜጠኞች በስተቀር ‹ቦታ የለም› በሚል የተከሳሽ ቤተሰቦች ችሎት ሳይታደሙ ቀርተዋል፡፡
ፍ/ቤቱ ችሎቱን በተመለከተ ለቀረበው አቤቱታ፣ ችሎቱ ዝግ አለመሆኑንና ግልጽ ችሎት መሆኑን በመጥቀስ፣ ዛሬ ተከሳሾች ስለበዙ ቦታ መጣበቡንና በቀጣይ ለማስተካከል እንደሚሞከር መልስ ሰጥቷል፡፡
በሌላ በኩል የተከሳሽ ጠበቆች ቂሊንጦ እስር ቤት ደንበኞቻቸውን አነጋግረው ሲወጡ ማስታወሻዎቻቸውንና ወረቀቶችን እየተነጠቁ መሆኑን ለፍ/ቤቱ ገልጸው አስፈላጊው ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው አመልክተዋል፡፡
ፍ/ቤቱ የቀረቡለትን አቤቱታዎች ካዳመጠ በኋላ ሁለት ተለዋጭ ቀጠሮዎችን ሰጥቷል፡፡ በዚህም ሰኔ 27/2008 ዓ.ም በተከሳሾች በኩል በጽሁፍና በቃል የቀረቡ አቤቱታዎች ላይ የቂሊንጦ እስር ቤት አስተዳደር መልስ እንዲሰጥ የተቀጠረ ሲሆን፣ በመቃወሚያ ላይ ብይን ለማሰማት ደግሞ ለሐምሌ 25/2008 ዓ.ም ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡ እስር ቤቱ ምላሽ እንዲሰጥበት በተቀጠረበት ዕለት ሁሉም ተከሳሾች ችሎት እንዲቀርቡ እንዲደረግ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡
No comments:
Post a Comment