Tuesday, June 7, 2016

በእነ ብርሃኑ ተክለያሬድ የክስ መዝገብ የተከሰሱት ተከሳሾች መከላከል አትችሉም ተባሉ ግንቦት ፴(ሠላሳ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና

- የኢትዮ-ኤርትራ ድንበርን አቋርጠው ኤርትራ የሚገኘውን የአርበኞች ግንቦት 7 ወታደራዊ ክንፍ ሊቀላቀሉ ከአዲስ አበባ ተነስተው ሲጓዙ ማይካድራ የሚባል የድንበር ከተማ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠቅሶ የፌደራል አቃቤ ህግ የሽብር ክስ የመሰረተባቸው  ብርሃኑ ተ/ያሬድ፣ እየሩሳሌም ተስፋው፣ ፍቅረማርያም አስማማውና ደሴ ካህሳይ  ፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 14ኛ ወንጀል  የካቲት 4 ቀን 2008 ዓ.ም በዋለው ችሎት አቃቤ ሕግ ተከሳሾቹ መከላከያ እንዲያቀርቡ ወስኖ የነበረ ቢሆንም፣ ውሳኔውን በዛሬው ችሎት ሽሮታል።

ውሳኔውን ተከትሎ ተከሳሾቹ ከ200 በላይ የሰውና የሰነድ ማስረጃ ይዘው ቢያቀርቡም
ፍርድ ቤቱ ከግንቦት 30 እስከ ሰኔ 8 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ ምስክሮቻቸውን እንዲያሰሙ ያሳለፈውን ውሳኔ በመሻር የቀጠሯቸው ቀን ሳይደርስ ባለፈው ሳምንት ፍርድ ቤት ቀርበው ጭብጥ እንዲያሲዙ ተጠይቀዋል። ተከሳሾቹም የምስክርነት ጭብጥ ምስክሮች መሃላ ሳይፈፅሙ መያዝ እንደሌለበት በመቃወም ለፍርድ አሳውቀው ውሳኔውን ለመስማት ለዛሬ ተቀጥረው ነበር። ፍርድ ቤቱም ከአራት ወራት በላይ የተመላለሱበትን ጉዳይ በመሻር ከሕግ አግባብ ውጪ መከላከያ ምስክር ማሰማት እንደማይችሉ በመግለጽ ለመጨረሻውን የፍርድ ብያኔ ለመስጠት ለሃምሌ 13 ቀን 2008 ዓ.ም. እንዲቀርቡ ወስኗል። አንደኛው ተከሳሽ ፍቅረማርያም አስማማው ለፍርድ ቤቱ ለማቅረብ አዘጋጅቶች በነበረው ሰነድ ላይ ለምን በረሃ ለመውረድ እንደወሰነ እንዲሁም በእስር ቤት ውስጥ የደረሰበትን ግፍ ዘርዝሮ አቅርቧል።
“የሰማያዊ ፓርቲ አባል በመሆን ሰላማዊ ትግሉን ከተቀላቀልኩ ጀምሮ ጎንደርና ድሬዳዋን ጨምሮ ለቀናትም ቢሆን ከአስር ጊዜ በላይ ታስሬያለሁ፡፡የሚገርመው ነገር በአንዱም እንኳን ጥፋተኛ ተብየ ተቀጥቼ አላውቅም፤ ምክንያቱም ስርዓቱ ጉልበተኛ ስለሆነ ነው እንጂ እታሰር የነበረው ጥፋት አጥፍቼ አልነበረም፡፡ በነዚህ በታሰርኩባቸው ጊዜያት በግፍ መታሰሬ ሳያንስ ስድብና ዛቻ እንዲሁም ድብደባ ይደርስብኝ ነበር፡፡ከሁሉም በላይ ግን ‹‹ወንድ ከሆንክ በረሃ አትገባም እንዴ!›› እያሉ በማፌዝ የሚዝቱብኝ ይገርመኝ ነበር፡፡እኔ በሰላማዊ መንገድ የምታገለውን ‹እዚህ ከተማ ተቀምጠህ ስርዓት መለወጥ ያምርሃል? ይህ ስርዓት የተገነባው በደም እንጂ በከተማ ጫጫታና በምርጫ እንዳይመስልህ! ስለዚህ የምትችል ከሆነ በረሃ ግባ፡፡ ያኔ እኛ መልስ መስጠት እንችልበታለን!›› የሚል ማስፈራሪያ ያደርስብኝ ነበር፡፡ ታዲያ ዛሬ ምርጫየን የመሳሪያ ትግል አድርጌ በረሃ ስገባ ለምንድነው የምታሰረውና የምጠየቀው? በነገራችን ላይ ይህን ወደበረሃ ውጣ ጥሪ ከሚያስሩን ደህንነቶችና ፖሊሶች በተጨማሪ ሟቹ ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በተደጋጋሚ ይጠቀሙት ነበር፡፡ የአሁኑ ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝም በጥቅምት 2008 ዓ.ም ከዛሚ ኤፍ.ኤም ሬድዮና ከኢ.ቢ.ሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ ‹እዚህ ሆኖ ከሚያስቸግር ከቻለ መሳሪያ ያንሳ› የሚል ጥሪ በሰላማዊ ትግል ለተማረሩና ተስፋ ለቆረጡ ወጣቶች አስተላልፈዋል፡፡” ብሎአል ፍቅረማርያም።
“አንድ ሀገር ላይ ለዜጎቹ ግፈኛ አምባገነን ስርዓት ስልጣን ሲይዝ ህዝብን ከጥቃት የሚታደግ፣ የስርዓቱን ግፍ ለመመከት የሚመጥን ትግል ያስፈልጋል፡፡ ለዚያም ነው ግንቦት 7ን ምርጫየ ያደረኩት፡፡በመጨረሻም መናገር የምፈልገው እኔን ወደዚህ ትግል የመለመለኝ ስርዓቱ የሚያደርስብኝ ግፍና በደል እንጂ ማንም ሰው እንዳልሆነ ነው፡፡“ ያለው ፍቅረማርያም፣ መንግስት በአገሪቱ ውስጥ እየፈጸመ ያለውን ግፍ በዝርዝር አቅርቧል። ሙሉ ጽሁፉን በኢሳት የፌስ ቡክ አካውንት ማንበብ እንደምትችሉ ለመግለጽ እንወዳለን። ወጣት እየሩሳሌም ተስፋው፣ ብርሃኑ ተክለያሬድና ፍቅረማርያም አስማማው ከእስር ቤት ሆነው ለሚጽፉዋቸው ጽሁፎች በርካታ ወጣቶች አድናቆታቸውን በፌስ ቡክ ላይ ሲሰጡዋቸው ቆይቷል።

No comments:

Post a Comment