Friday, June 17, 2016

የአዕምሮ ሚዛን የመጠበቅ ስትራቴጂ ፡ ዶ/ር ታደሰ ብሩ


በተፋፋመ ቅራኔ ውስጥ የገባ ሰው የአዕምሮ ሚዛኑን ሊያጣ ይችላል። ቀድመው ያልታዩ እንቅፋቶች፣ ጥርጣሬዎች፣ ከወዳጆች የሚቀርቡ ትችቶች እና መሰል ነገሮች ተደራርበው ፍልሚያ ው1ስጥ ያለን ሰው እዕምሮ ሊረብሹ ይችላሉ። በዚህም ምክንያት ተፋላሚ ሰው በጥርጣሬና ንዴት ውስጥ ሆኖ ውሳኔዎችን የሚሰጥበት አደጋ አለ። ሆኖም ግን ይህ ሰው በአሸናፊነት እንዲወጣ የአዕምሮውን ጉልበት በሚገባ መጠቀም ይኖርበታል።

ማንኛውም ዓይነት ጦርነት በቅድሚያ የሚደረገው በጭንቅላት ውስጥ ነው። ፍልሚያ ውስጥ ስትሆን የአዕምሮ ሚዛንን በተመለከተ እንደ ግብ ልትይዛቸው የሚገቡ ሁለት ነገሮች አሉ: (1) የአንተ በተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ መገኘት፣ እና (2) የጠላቶችህ መረበሽ። ያንተ መረጋጋት ሁኔታዎችን የመቆጣጠር ችሎታህንና በሌሎች ላይ ተጽዕኖ የማድረግ እድልህን ከፍ ያደርገዋል። “ከአንድ ጄኔራል አዛዥ የሚፈለግ ባህርይ በመልካምም ሆነ በመጥፎ ዜና የማይፈጥዝ ወይም የማይረበሽ የተረጋጋ አዕምሮ ያለው ሰው ሆኖ መገኘት ነው” ይለናል ናፓሊዮን ቦናፓርት።
ብዙ አጣዳፊ ጉዳዮች በበዙ መጠን በዛፎች ተከልሎ ደኑን ማጣት ሊመጣ ይችላል። ስለዚህም ሙሉውን ጦርነት ማለትም ትልቁን ስዕል ከማየት ከሚያግዱህ ነገሮች ራስህን አንፃ። ወደፍልሚያ ስትገባ ዝግጁና የተረጋጋህ ሁን፤ እንዲህ ስትሆን ችግሮችን አስቀድመህ ማየትና መዘጋጀት ትችላለህ፤ በሚገባ የተዘጋጀ አዕምሮ ባዶ አይሆንም። በዝግጅት ወቅት ጥንቃቄ ያስፈልጋል፤ አንዴ ፍልሚያ ተጀምሮ ትንንቅ ውስጥ ከተገባ አዕምሮን ከስጋት ማጽዳት ይገባል፤ እየተዋጋህ ስለማፈግፈግ አታስብ። በማጥቃትህ ተደሰት፤ የአጥቂት ስሜት ይዞህ ይጓዝ። በፍልሚያ ወቅት ብዙ ሰዎች የተለያዩ “ምክሮችን” መስጠት ይሻሉ፤ የተለያዩ ጥያቄዎችን ይጠይቃሉ። በምክር ብዛት መሪዎች ትኩረት ሊስቱ ይችላሉ። ጓዶችህ ጥርጣሪዎችን ሲያጭሩብህ፤ በስጋት በተሞሉ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ሲያጨናንቁህ የምትሰማ መስለህ ናቅ አርገህ ተዋቸው፤ አንተ ቀድመሃቸዋልና ስጋት አይግባህ። ያንተ መረጋጋት እነሱንም ያረጋጋቸዋል። ሰዎች እንደ ቡድሀ መነኩሴ ከሁከት ራስህን አጥተህ በመለኮታዊ ኃይል የምትታገዝ ይመስላቸው፤ የአንተን ባህሪ መረዳት መቸገራቸው ላንተ ጥሩ ነው።
እኛ የሰው ልጆች ራሳችንን ምክንያታዊ እንደሆንን፤ ከእንስሳት የሚለየንም ማሰብና መመራመራችን እንደሆነ እንገምታለን፤ ይህ ግን ግማሽ ሀቅ ነው። ከእንስሳት የሚለየን መሳቅ፣ ማልቀስ፣ መወደድ፣ መጥላት፣ መፍራትና መናደድን የመሰሉ ስሜቶችን የምገልጽ በመሆናችን ጭምርም ነው። ሰዎች አስተዋይ ብቻ ሳይሆን ስሜታዊ ፍጡርም ነን፤ ቀላል የማይባሉ ተግባሮቻችን የሚወሰኑት በወቅቱ በነበረን ስሜት ነው። በተለይ ምቹ ባልሆነ ሁኔታ ውስጥ ስንገኝ ምክንያታዊነት ይማሽሽና ስሜቶች ቦታውን ይተኩታል። በተለይ ጥቃት በደረሰብን ጊዜ እርምጃዎቻችን የሚወስኑት ከምክንያታዊነት ይልቅ ቁጭት፣ ንዴት፣ ሀዘን እና መሰል ስሜቶች ናቸው። እነዚህ ስሜቶች የማስተዋል አቅማችንን ይቀንሱታል። ጥሩ የጦር መሪ ለመሆን የተራቀቀ የጦር እውቀት ባለቤት መሆን አይበቃል፤ ከዚያ የበለጠ አስፈላጊው ነገር ስሜቶችን መቆጣጠር መቻል ነው።
ስሜቶታችንን ለመቆጣጠር ጥብቅ የአስተሳሰብ ዲስፕሊን ማዳበር ይጠይቃል። የአስተሳሰብ ዲሲፕሊንን ከመፃህፍት መማር አይቻልም። የአስተሳሰብ ዲስፕሊን ከልምምድና ከሕይወት ተሞክሮ ነው የምናዳብረው ነው። የአስተሳሰብ ዲሲፕሊን ራስን የመግዛት ክህሎት እምብርት ነው።
ራስህን ለቅራኔ አጋልጥ
ፍርሀትን የማስወገጃ አንዱ መንገድ የምትፈራውን ነገር መጋፈጥ ነው፤ ፍርሀትህን እየተደበቅህና እየሸሸህ ከመኖር ፊት ለፊት ተጋፈጠው። ፍርሀት የአዕምሮ መረጋጋትን ከሚቀሙን አፍራሽ ስሜቶች ቀዳሚው ነው፤ ምን ሊገጥመን እንደሚችል አለማወቅ ለበርካታ አስፈሪ የአዕምሮ ምስሎች መከሰት ምክንያት ይሆናል። ራስን ለሚያስፈራው ቅራኔ በማጋለጥ አዕምሮዓችን ውጥረቱን እንዲለማመደው ማድረግ አንዱ መፍትሄ ነው። አንድ አስፈሪ ሁኔታ በድል መወጣት በራስ የመተማመን ስሜትን በከፍተኛ መጠን ያሳድጋል። ብዙ ቅራኔዎች በተወጣን መጠን በጦርነት የተፈተነ አዕምሮ ይኖረናል።
ክልብህ መጥፋት የሌለበት ሌላም ዓቢይ ጉዳይ አለ። ስትጀግን ኩራቱና የመንፈስ ርካታው የአንተ ብቻ አይደለም። አባል የሆንክበት ድርጅት፣ መላውን ቤተሰብና ወዳጆችህን፣ ከዚያም አልፎ አባል የሆንክበት ማኅበረሰብን ባንተ ጀግንነት ይኮራሉ፤ ይመካሉ። በአንፃሩም፣ በፍርሀት ምክንያት ሚዛናዊ መሆን ቢያቅትህ የምታዋርደው የገዛ ራስህን፣ ስምህን፣ ዝናህን ብቻ አይደለም። ባንተ መዋረድ የውርደት ስሜት የሚሰማው ብዙ ነው። የትንሽም ይሁን ትልቅ ድርጅት መሪ ከሆንክ ደግሞ ያለብህ ኃላፊነት የላቀ ነው። በአንተ ጀግንነት ተከታዮችህ ይኮራሉ። የእነሱ ደህንነት በአንተ ውሳኔና ብርታት ይወሰናል። የአንተ አዕምሮ ሚዛን የመጠበቅ ጥቅምና ጉዳት በአንተ ላይ ብቻ ተወስኖ የሚቀር አይደለም።
በራስህ ተማመን
በሌሎች ሰዎች ወይን ድርጅቶች ላይ ጥገኛ መሆንን የመሰለ መጥፎ ስሜት የሚፈጥር ነገር የለም። ጥገኝነት ለተለያዩ አሉታዊ ስሜቶች ያጋልጣል። ክህደት፣ ተስፋ መቁረጥ፣ መከፋት ... የጥገኝነት ውጤቶች ናቸው። ጥገኝነትን ለመከላከል በራስ መተማመንን ማዳበር ይገባል።
ስለራሳችን ያለንን ግምት ከፍ በማድረግ በራሳችን ላይ ያለንን መተማመን ማዳበር መልመድ ይገባል። ይሁን እንጂ በራስ መተማመን ማለት ሁሉን አውቃለሁ ማለት አይደለም፤ ሁሉን እኔ ካልሰራሁትና ካልተቆጣጠርኩት ማለትም አይደለም። በራስ መተማመን ማለት ለገዛ ራስም ለሌሎችም ተገቢውን ዋጋ መስጠት ማለት ነው። በሌሎች ሰዎች የተሻለ ሊሰሩ የሚችሉ ሥራዎችን ለሌሎች መስጠት እና በአንተ መሰራት ያለባቸውን ሥራዎች መለየት በራስ መተማመን ነው። በራስህ የመተማመንህ መሰረቶች ትህትና እና የሙያ ብቃት ይሁኑ። ትህትና እና የሙያ ብቃት ያንተ መለያ ባህሪያት ይሁኑ።
በብቃት ያልተደገፈ በራስ መተማመን ትዕቢት ነው። ትዕቢት አንተ ዘንድ ቦታ ሊኖረው አይገባም። የሙያ ብቃቱ ሳይኖራቸው በትዕቢት ከተወጠሩ ሰዎች ጋር መሥራትህ ግድ ከሆነ ግን አትፋለማቸው። ከእነሱ ጋር መፋለም ከመላላጥ ያለፈ ትርፍ የለውም።ይልቁንም ልክ እንደ ሕፃናት ቁጠራቸው፤ ስሜትህ በእነሱ ምክንያት አይቆጣ። በውስጥህ እየሳቅክባቸው ቸል ብለሃቸው ሥራህን ከእነሱ ሸሽገህ ሥራ።
በቀላሉ ሊተገበሩ በሚችሉ ተግባራት ላይ በማትኮር መረበሽን አስወግድ
ሁኔታዎች አስፈሪ ሲሆኑብን አዕምሮዓችን ማለቂያ የሌላቸው አስጨናቂ ምስሎችን ይፈጥርብናል። ይህን ለመቆጣጠር ሀሳብን መቆጣጠር ያስፈልጋል፤ ሀሳብን መቆጣር ደግሞ ቀላል ነገር አይደለም። ሀሳብን ለማረጋጋት ቀላሉ መንገዱ በቀላሉ ሊተገበሩ በሚችሉ እና በምናውቃቸው ተግባራት ላይ ራሳችንን መጥመድ ነው። አዕምሮህን በሥራ ስትጠምድ ወደ ተፈጥሮዓዊ ባህርይ ትመለሳለህ። በሥራ የተጠመደ አዕምሮ ለመቃዠት ጊዜ አይኖረውም። የአዕምሮ ሚዛንህን ከጠበቅህ ትላልቆቹን ችግሮችን ለመጋፈጥ ትችላለህ። አዕምሮን በሥራ መጥመድ ልማድ እስኪሆንህ ድረስ ችግር በገጠመህ ጊዜ ሁሉ ልትለማመደው ይገባል።
የፈጣን ውሳኔ ቀልብ (intuition) አዳብር
“የአዕምሮ መረጋጋት” ሲባል በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሆኖ በአስፈላጊ ጉዳዮች ላይ ማትኮርን የሚመለከት ብቻ ሳይሆን ተገቢ ውሳኔዎችን በፍጥነት መስጠትንም ይጠይቃል። ውሳኔዎችን ማዘግየት በጦርነት ላይ ላለ ሰው የሚመከር አይደለም። አንዳንድ ውሳኔዎች ወዲያውኑ መሰጠት አለባቸው። እነዚህ ውሳኔዎች ታስቦባቸው የሚደረጉ ሳይሆን ከመቅስፈት በስሜት የሚሰጡ ናቸው። እንዲህ ዓይነቱ ቀልብ (intuition) ማዳበር ተገቢ ነው። የሰዎችን ፊት፤ ቦታዎችን፤ መሣሪያዎችን ስታይ ቀልብህ የሚነግርህ ነገር ፈጣን ርምጃ መውሰድ ከሆነ አድርገው። ጠላቶችህ ማን፣ ምን፣ እንዴት እንደመታቸው ሳያውቁ የምታነጥፋቸው በእንዲህ ዓይነት ፈጣን ውሳኔዎች ነው።
የተረጋጋ አዕምሮ ማዳበር ለችግር ጊዜ ብቻ የሚያስፈልግ ነገር አድርገን መውሰድ የለብንም። የተረጋጋ አዕምሮ ለዘወትር ሕይወታችን አስፈላጊ ነው። በራስ መተማመን፣ ድፍረት እና ራስን መቻል በጦርነት ጊዜ የሚያስፈልጉትን ያህል በሰላም ጊዜም ያስፈልጋሉ።
ማሳረጊያ
ሁሌ ይሳካል ማለት አይደለም፤ የተረጋጋ አዕምሮ ባለቤት ለመሆን ጥረት እያደረግንም ቢሆን ልንረበሽ፣ ልንናደድ ከዚያም አልፎ አቅላችንን ልንስት እንችላለን። እንዲህ ዓይነት ነገር ሲያጋጥም ወደዚህ ሁኔታ እንዴት እንደገባን ማጥናትና ለወደፊቱ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ እንዳይከሰት ምን ማድረግ እንዳለብን ለማጥኛነት እናውለው። “ፈጽሞ ተናድጄ አላውቅም” የሚል ቢኖር እውነቱን አይደለም፤ ከሆነ ደግሞ አደጋ ነው፤ አንድ ቀን ድንገት ቢናደድ ምን እንደሚሆን አይታወቅምና።
በዓለም የታወቁ የጦር ጄኔራሎች ከንዴትና ብስጭት አልፎ የአዕምሮ መታወክ ውስጥ የገቡባቸው ጊዜዓት ነበሩ፤ ቁም ነገሩ ቶሎ ራሳቸውን ማረጋጋት መቻላቸው ነው። ስለሆነም “ፈጽሞ መናደድ የለብኝም” ማለት ሳይሆን “በቶሎ ራሴን መቆጣጠር መቻል አለብኝ” ነው ማለት ያለብን።
ወዳጄ ሆይ፤ ለሁለት ነገሮች አልም - (1) ራስህን ማረጋጋት፤ እና (2) ጠላቶችህን ማበሳጨት፣ ማብገንና ማሳበድ። ጠላትህን ተነኳኩሰህ የአዕምሮውን ሚዛን አናጋ፤ የአበደው ጭንቅላቱ የአንተን ሥራ ይሰራልሃል።
.....................
ሮበርት ግሪን ከፃፈው “33 ቱ የጦርነት ስትራቴጂዎች” (The 33 Strategies of War) በሚለው መጽሀፉ ላይ በፃፈው ላይ ተመስርቶ የተፃፈ

No comments:

Post a Comment