Saturday, October 1, 2016

“የመለስ ልቃቂት” ሆድ እቃ ሲገለጥ” [ሚካኤል ደርቤ (ቦስተን ማሳቹሴት)]

መንደርደሪያ    
%e1%8b%a8%e1%88%98%e1%88%88%e1%88%b5-%e1%88%8d%e1%89%83%e1%89%82%e1%89%b5-satenaw-news
ደረቅ ፖለቲካዊ መረጃዎች የተዘጋጀበት መጽሀፍ እንዲነበብ%e1%8b%a8%e1%88%98%e1%88%88%e1%88%b5-%e1%88%8d%e1%89%83%e1%89%82%e1%89%b5-satenaw-news ከተፈለገ በአቀራረቡና በአፃፃፍ ስልቱ የሚያጓጓ ሊሆን ይገባል። በተለይም ስለ ዘረኛ ኋላቀርና ቆሞ ቀር የሆነውን የወያኔ ፖለቲካ መጽሐፍ ጽፎ አንባቢ መሳብ በጣም አስቸጋሪ ነው። ሩቅ ሳንሄድ  የእንግሊዝ የወያኔ መፈንጫ የሆነው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ውስጥ ተከማችቶ የአይጥ መናኸሪያ የሆነውና በአስወጋጅ ኮሚቴ የተቃጠለው የውሸት አለቃ የሆነው በረከት ስምኦን የበሬ ወለደ ፕሮፖጋንዳ መጽሃፍ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። የውሸት አለቃው መጽሃፉን በውድ ዋጋ ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ ቢያሳትምም፣ በሸራተን ሆቴል ውስኪና ሻምፓኝ አስከፍቶ ቢያስመርቅም፣ በታዋቂ ሆድ- አደር አርቲስቶችን ምዕራፍ እያስነቀሰ ቢያስነብብም፤ በማዕዛ ብሩ ሸገር ሬዲዮ በግድ እንዲተረክ ሙከራ ቢያደርግም መነበብ አልቻለም ከዚህ በተጨማሪ አንባቢዎች መጽሃፉን የፃፈው ሰው የደበቀው ነገር ሊኖር ይችላል፤ አሊያም ሃሰትን በእውነት ተለውሶ የተከተበ መሆን ጥርጣሬ ካሳደረ የመነበብ እድሉ ዝቅተኛ ነው። እርግጥ “ማን ያውራ የነበረ፣ ማን ያርዳ የቀበረ” የሚባል የተለመደ ሀገራዊ ብሂል ቢኖርም የወያኔን የሴራ ፖለቲካ ለማንበብ ከዚያም በላይ ትዕግስት ይጠይቃል። ወያኔ በጠላትነት መጥቶ እንደ ንብ መንጋ ኢትዮጵያን አፓርታይድ በሚመስል አሰራር ተቆጣጥሮ ያደረሰው የግፍ ግፍ የሂሳብ ስሌት ሳይሰሩ የሚያቀርቡ ሰዎች ለማውራትም ሆነ ለማርዳት የመታመን እድላቸው ጠባብ አይደለም። የሚቀርቡት መጽሀፎች በመረጃ የተጠናከሩ፤ ግራ ቀኝ  አመለካከቶችን ማገናዘብ ከቻሉ፤ በሀቅ ላይ የተመሰረቱ ትናንትናዎች ይዘው የሚነሱ ከሆነ መነበብ የሚችሉበት እድል ሰፊ ይሆናል።

ስለሆነም በአንድ በኩል ተጨባጭ መረጃዎችንና እውነታዎችን ሳይዛቡ የሚቀርቡበት፤ በሌላ በኩል ከሙያም ከፖለቲካ ልምድም በመንሳት የግል ምልከታን ሳያቅማሙና ሳይተሻሹ ለማቅረብ ከፍተኛ ድፍረት ይጠይቃል። ለምሳሌ ወያኔ ከልቡ ማውጣት ያልቻለው ገብሩ አስራት ጠቃሚ መረጃዎችን የያዘ ዳጎስ ያለ መጽሃፍ ቢያበረክትም በርካታ ሚስጥሮችን ሊሸሽግ በመሞከሩ “ከነገረን የደበቀን ይበልጣል” መባሉ መነሻው ይሄ ነው። በተለይም ኤፈርትን የመሳሰሉ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ አጥንት የጋጡ የዝርፊያ ማዕከላት “በኢትዮጵያ ያሳደሩት ኢኮኖሚያዊ ተጽእኖ እዚህ ግባ አይባልም” ማለት እንኳን የገፈቱ ቀማሽ ለሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ለገብሩ የመንፈስ ልጆችም አያሳምንም። ከገብሩ አስራት ጋር “መድረክ” የሚል ድርጅት የመሰረቱን ፕሮፌሰር መረራንም ሆነ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በገብሩ አገላለጥ ከማዘን አልፈው መናደዳቸው አይቀርም።

“የመለስ ልቃቂት” የተባለው የኤርሚያስ ለገሰ መጽሀፍ በቅድሚያ ለመመርመር የሞከርኩት ከዚህ አንጻር ነበር። ይህንን ጽሁፍ ለመሞነጫጨር ያነሳሳኝ የመጀመሪያ ምክንያት ይሄ ነው። ያለማጋነን ከገመትኩት በላይ በበርካታ መረጃና ማስረጃዎች የታጨቀው ይህ መጽሀፍ የህዉሃት በዝርፊያ የተመሰረቱና የፋፉ ኢኮኖሚያዊ ሃይሎች ላይ መብረቃዊ ምት ያሳረፈ ነው። ፀሃፊው ኤፈርት-መር ካፒታሊዝም እያለ በተደጋጋሚ ቢገልጠውም ለእኔ ግን በዝርፊያ የገነባው ካፒታሊዝም (Crony Capitalisim) ሆኖ አግንቼዋለሁ። በሌላ በኩል ፀሃፊው የዝርፊያ ማዕከሉን በግማሽ መንገድ እንዳለ አስልቶ “ልቃቂት” ደረጃ ደርሷል ቢልም በዚህ መልኩ ለጥቂት ጊዜያቶች ከቀጠለ የአገሪቱ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ህይወት በአያሌው የሚናጋ ይሆናል። ጊዜ ከተሰጠው የኢትዮጵያ ህዝብ ስርአቱን ለመገርሰስ ከፍተኛ መስዋዕትነት የሚያስከፍል ይሆናል። ከልቃቂት ያለፈው የዝርፊያው ካፒታሊዝም (ክሮኒክ ካፒታሊዝም) በጠምንጃና በሰደፍ የፖለቲካ ስልጣንን ማቆየትንና በህዝብ ላይ ሸክሙ የሚከብድበት ሁኔታ ይፈጠራል። ከመጽሀፉ መገንዘብ የቻልኩት ነገር ቢኖር የወያኔ አገዛዝ በዝርፊያ ቁምጣን የያዘው ቢሆንም በቃን የሚል አይደለም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያ ህዝብ ባደረሰባቸው አደገኛ ምት እንደተጎዱ መውሰድ ቢቻልም የቆሰለ አውሬ ሆነው የሚቀትሉበት ሁኔታ እድሉ ዝግ አይደለም። አደብ እንዲገዙ ካልተደረገ አልጠግብ ባይነታቸው በበለጠ ቁጭትና በቀል ተጠናክሮ የሚቀጥልበት ሁኔታ ይፈጠራል።
የአገሪቱን ሀብት የተቆጣጠሩት የህዉሃት የብርቅ ልጆች በአንድ በኩል በሃብት ጋራ ላይ ሰማየ ሰማያት እየረገጡ የሚሄዱበት፤ በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የሃዘን ቤትነቷ የሚቀጥል ይሆናል። ይህ እንደ አሳ ከጭንቅላቱ የገማ ስርአት ያለምንም ከልካይ የአገሪቷን አንጡራ ሃብት የሚቆጣጠርበት ሁኔታ ይፈጠራል። ፀሃፊው በመጽሐፉ እንደገለጸው ሁኔታዎች በፍጥነት ካልተቀየሩ ነገ ከነገወዲያ “የኢትዮጵያ አየር መንገድ”፣ “የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ”፣ “የኢትዮጵያ ቴሌኮሚዩኒኬሽን” የሚባሉ ተቋማት በባለቤትነትና በስም ተቀይረው የምናይበት ጊዜ ሩቅ አይደለም። ዛሬ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከሰጠው ብድር 40% ያህሉን ወያኔ ኤፈርትን ለመሰሉ ዘራፊ ኩባንያዎች እንዲሰጥ ካስገደደ፤ ከአመታት በኋላ እንደ አንፀባራቂው የመቶ ፐርሰንት ምርጫ ውጤት የብድር መጠኑም ተመሳሳይ ይሆናል።
ለምሳሌ ያህል “የመለስ ልቃቂት” ገጽ 139 ላይ “ልማት ባንክ የማነው? የትግራይ አይደለምን?” በሚል ርዕስ ስር እንዳመለከተው “በዘመነ መለስ ዜናዊ” የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከሰጠው 8.5 ቢሊዮን ብር ብድር ውስጥ 5ቢሊዮን ያህል (59%) የወሰዱት የትግራይ ክልላዊ መንግስትና የዘረፋ ካፒታሊዝም እየገነባ ያለው ኤፈርት ነው። ልማት ባንኩ ዳይመንድ ጁባይል ኢዩቤልዩውን ባከበረ አመት ብቻ  ለማበደር በእቅድ ከያዘው 2.78 ቢሊዮን ብር ውስጥ 1.7 ቢሊዮን ብር (63%) የዘራፊው ቡድን ንብረት ለሆነው መሶቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ ማስፋፊያ ፕሮጀክት አስቀድሞ የተያዘና የተፈቀደ ነው። ከሁሉም የሚያሳዝነው አበዳሪም ተበዳሪም የሆነው ኤፈርት በራሱ የሰጣቸው ብቻ ሳይሆን እንደ ጆፌ አሞራ ከየቦታው የለቃቀማቸውን የኤፈርት ብድሮች የተበላሹና የማይሰበሰቡ በማለት ከአካውንቱ እንዲወጣ አድርጓል። “የመለስ ልቃቂት” የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ምዕራፎች አየር መንገዱ፣ ጉምሩክ ባለስልጣን፣ ቴሌ ኮሙዩኒኬሽን፣ መንገዶች ባለስልጣን፣ ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ፣ ንግድ ባንክ፣ የፍትህ ሚኒስቴር፣ ደህንነት ቢሮ፣ መከላከያ፣ ኢምግሬሽን ቢሮ፣ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤትና ኤምባሲዎች፣ የሚዲያ ትርቋማት (ኢቲቪ፣ ፋና፣ ዋልታ)…. ወዘተ በምግባር የማናቸው የሚለውን ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ ነው።

“የመለስ ልቃቂት ጭብጦች”                                                                                                                                                                       
ye-meles-lekakit-standing-book
እስከገባኝ ድረስ “የመለስ ልቃቂት” መፅሃፍ ውስጣዊ ይዘት ስመረምር ለጊዜው ሦስት ያህል ቁልፍ ጉዳዮችን ተመልክቻለሁ። እነዚህ ቁምነገሮች በተጠናጥል የቆሙ ሳይሆን አንደኛው ለቀጣዩ መሰረት ሆኖ የሚያገለግል ነው። ለዚህም ሃፍረተቢስነታቸውም ያስመሰከሩ በቂ ምክንያቶች ቀርበዋል። ወያኔዎች ከራስ በላይ ንፋስ እንደሚባለው ብሂል “ወደ ውስጥ ተመልካች” (Inward Looking) በመሆናቸው ስለደህንነት መዋቅራቸው፣ ስለ ኢኮኖሚ ሞኖፖሊያቸውና የፖለቲካ የበላይነት ለማረጋገጥ የሚሰሩት የተቀናጀ ስራ ጠቅላላውን የፖለቲካ ሃይል አሰላለፍና ጉዞ እንድንመለከት ያስችለናል። ለማንኛውም “የመለስ ልቃቂት” ዋና ዋና ጭብጦች የሚከተሉት ይመስሉኛል።

ጭብጥ አንድ፦ የመጽሃፉ መንደርደሪያና ፍሬ ሃሳብ በምዕራፍ አምስት “የማስታወሻ አስኳል” በሚል ርዕስ እናገኘዋለን። የማስታወሻው አስኳል ባለቤት ሟቹ መለስ ዜናዊ ሲሆን ኤርሚያስ “ስድስቱ የመለስ አስተምህሮዎች” በማለት ከፋፍሎ ለብቻ አቅርቦታል። እነዚህ አስተምህሮዎች መለስ ዜናዊ ድንክዬ ልጆቹንና የቤት ውስጥ ባለሟሎቹን ለማደቆን ያዘጋጀው ሰነድ ላይ እንደሚገኝ ያስገነዝባል። “የመለስ ልቃቂት” ገጽ 165- 166 ስድስቱ አስተምህሮቶችን ጭማቂ እንደሚከተለው ይገልጻል፦

አስተምህሮ አንድ፦“ትእምት የህዉሀት ንብረት ያልሆነ በትጥቅ ትግሉ ወቅት በተሠባሠበ ገንዘብና ንብረት በህግ የተቋቋመ ግብረ-ሠናይ ድርጅት ነው”
አስተምህሮ ሁለት፦“ትእምት የተቋቋመበት ተልዕኮ በመንግስትም ሆነ በባለሀብቶች ሊሸፈን የማይችል ቀዳዳ ለመድፈን  ነው።”
አስተምህሮ ሶስት፦  “ትእምት አመራር ስርአት በግልፅነት መርህ ላይ የተመሠረተ ነው።”
አስተምህሮ አራት፦ “ትእምት ከመንግስት ያገኘው ወይም የወሰደው ቅንጣት ሳንቲም የለም። ወደፊትም አይኖርም።”
አስተምህሮ አምስት፦ “ትእምት ኢኮኖሚውን ሊቆጣጠር፣ ባለሀብቶችን ሊያፍን ነው የተቋቋመው በማለት የሚናፈሠው  አሉባልታ መሠረ-ቢስ ነው”
አስተምህሮ ስድስት፦ “ትእምት በክልሎች መካከል የተመጣጠነ እድገት መኖር አለበት ብለን ያስቀመጥነውን መርህ  አይጻረረም”
ኤርሚያስ በመጽሀፉ አስኳል ላይ የመለስን አስተምህሮ ለምን በስድስት ገድቦ ለማቅረብ እንደፈለገ ግልፅ አይደለም። የማስታወሻውን አስኳል ነጥብ በነጥብ ለተመለከተ ሰው ተጨማሪ የመለስ የቅጥፈት አስተምህሮቶችን መመልከት ይቻላል። ለምሳሌ ያህል “በመለስ ልቃቂት” ገጽ 182 ላይ እንደተገለጸው መለስ ዜናዊ “ኩባንያዎቹ የወያኔን ፖለቲካዊ ስራዎች ለማከናወን ገንዘብ አይሰጡም” የሚል የጠራራ ፀሃይ ውሸት ጽፏል። ድንክዬዎቹና ባለሟሎቹ “የደንቆሮዎች ውይይት” በመሰለ የሃሳብ ውዥንብር ውስጥ ካልዳከሩ በስተቀር ህዉሃትና በተለያየ ጊዜ ጠፍጥፎ የፈጠራቸው ድርጅቶች በዘረፋ የተደራጁት ኩባንያዎች ቀጥተኛ ተጠቃሚዎች ናቸው። ከዚህ አንፃር የዝርፊያ ኩባንያዎቹ ያደረጉትና እያደረጉት ያለው አስተዋጽኦ በለሆሳስ የሚታለፍ አይደለም። ፓርቲዎቹ ለሚሰሩት ስራ፣ ለአባሎቻቸው የሚከፍሉት መደለያ ገንዘብ ህዝቡን ለማፈን ለሚዘረጉት መዋቅር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የገንዘብ ምንጫቸው እነዚህ ኩባንያዎች ናቸው።
ያም ሆነ ይህ “የመለስ ልቃቂት” ከመጀመሪያው ምዕራፍ እስከ መጨረሻው  ገጽ ድረስ የሟቹ መለስ ዜናዊ ኑዛዜ ቃላት (“አስተምህሮ”) በቅጥፈት የተሞሉና ውሸት መሆናቸውን በመረጃ አስደግፎ ያቀርባል። በዝርዝር እንዳየሁት ከሆነ ይህ “አሳ ጎርጓሪ” የሆነ መጽሃፍ ከኢኮኖሚ ሂሳብ ባሻገር የወቅቱን የህዉሃት የፖለቲካ የበላይነት የተረጋገጠበት ነው።
ጭብጥ ሁለት፦ “የመለስ ልቃቂት” የወያኔ ሦስቱ የዘረፋ የኢኮኖሚ ሃይሎች የሆኑትን ኤፈርት፣ ትልማ(ትግራይ ልማት ማህበር) እና ማረት (ማህበረ ረድኤት ትግራይ) አስቀድሞ በታቀደና የአፓርታይድ መርሆ በሆነ መንገድ የኢትዮጵያን አንጡራ ሃብት የማግበስበስ ስራ በቅንጅትና በመደጋገፍ እንደሚፈጽሙት ያስረዳናል። በጠምንጃ የተደገፈው የወያኔ ስልጣነ መንግስት ለሦስቱ የፖለቲካል- ኢኮኖሚ ሃይሎች የተለያየ ተልዕኮ በመስጠት የኢትዮጵያንም ሆነ ከውጭ የሚመጡ እርዳታዎችን በመቀራመት ወደ ትግራይ እንዴት እያሻገረ መሆኑን መረዳት ይቻላል። የኤፈርት፣ ትልማና ማረት ጓዳ ጎድጓዳ ሲመረመር በአገሪቷ ላይ ያደረሱትና እያደረሱ ያሉት የጥፋት መጠን ምን ያህል ከፍተኛ እንደሆነ በቀላሉ መገመት ይቻላል። ርግጥም በኢትዮጵያ የሰፈነውን ኢ-ፍትሃዊነትና የተዛባ ተጠቃሚነት ለመዳሰስ የሦስቱን የፖለቲካል- ኢኮኖሚ ሃይሎች አመሰራረት፣ አደረጃጀት፣ ራዕይ፣ ተልዕኮና ተጨባጭ ተግባራት አብጠርጥሮ ማወቅ የወያኔ መሪዎች የኢኮኖሚ ራዕይ “የትግራዋይ” መሆኑን ይደርስበታል። ያለምንም ማጋነን “የመለስ ልቃቂት” ኢትዮጵያን አፓርታይድ በሚመስል መልኩ የያዙት የወያኔ መሪዎች ለሩብ ክፍለዘመን ቆዳቸውን እየቀያየሩ የሚያሳዩትን ድራማ በመረጃ አስደግፎ ያቀረበ በሳል መጽሃፍ ነው።
በተለያዩ መጽሃፍትና መጣጥፎች እንደተገለጠው የወያኔ የኢኮኖሚ አውታር ስለሆነው “ኤፈርት” ብዙ ተብሏል። ኤርሚያስ በዚህ መጽሃፍ ላይ በርካታ መረጃዎችን በመጨመር ያጠናከረው ሲሆን በአገሪቷ ህግ መሰረት የተቋቋመ መሆኑና አለመሆኑን ጥያቄ አስነስቶበታል። የፖለቲካ ፓርቲዎችና አመራሮቻቸው ላይ መነጋገር መጀመር እንዳለባቸው አስገንዝቧል። እኔም የጸሃፊውን ሃሳብ እጋራለው። ከወያኔ በኋላ የሚገነባው አዲስ ስርአት በእነዚህ የዝርፊያ ተቋማት ላይ አስቀድሞ አቋም መውሰድ እንደሚገባው አምናለሁ። የተዘረፈው የኢትዮጵያ ህዝብ ሀብት ለባለቤቱ የሚመለስበት ሁኔታ መፈጠር ይኖርበታል። በስሙ የሚነግድበት የትግራይ ህዝብም ኤፈርት፣ ትልማም ሆነ ማረት ህገ-ወጥና ኢፍትሃዊ በሆነ መንገድ የተቋቋሙና የኢትዮጵያን ህዝብ አጥንት በመጋጥ የፋፉ መሆኑን ተገንዝቦ ድርጅቶቹ ላይ ለሚወሰዱት እርምጃዎች ትብብር ማድረግ ይጠበቅበታል።
ጭብጥ ሦስት፦ “የመለስ ልቃቂት” የወያኔ ሦስቱ የዝርፊያ ድርጅቶች የትግራይ የህዝብን በልዩ ሁኔታ ተጠቃሚ አድርገዋል የሚል ድምዳሜ ላይ መድረሱን በተለያዩ ቦታዎች አሳይቷል፡፤ ይህንን ድምዳሜ በመጽሃፉ ሆድ እቃ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በጀርባ ሽፋኑም ላይ አጽንኦት ሰጥቶ አስፍሯል። ከብዙ በጥቂቱ እንዲህ ይላል፣
“ትግራይ አልተጠቀመችም የሚለው የፖለቲካ መንገድ በየትኛውም መከራከሪያ እያረጀና እያፈጀ ሄዷል። ተጠቃሚነት መለካት ያለበት በየደረጃው ነው። …. ሁሉም የትግራይ ተወላጅ ሚሊኒየር ሊሆን አይችልም። ሁሉም የትግራይ ተወላጅ የመንግስት ተቀጣሪ ሊሆን አይችልም። ሁሉም የትግራይ ተወላጅ ዩንቨርስቲና ኮሌጅ ሊገባ አይችልም።…. ትግራይ ተጠቅማለች ሲባል ሁሉም የትግራይ ወጣትና ሴት የፋብሪካ ሰራተኛ ኩባንያዎች በሆኑት አዲግራት መድሃኒት ፋብሪካ፣ አልመዳ ጨርቃጨቅ፣ በትራንስ፣ በህይወት ሜካናይዜሽን፣ መሶቦ ሲምንቶ፣ ኢዛና…. ወዘተ የመሳሰሉት ዘመናዊ ፋብሪካዎች ተቀጥረው የሚሰሩት የትግራይ ተወላጆች ናቸው” ይላል።
“የመለስ ልቃቂት” የወያኔ መሰረት የትግራይ ስለሆነች የትግራይ ህዝብ በየደረጃው እንዲጠቀም አድርጓል ትለናለች። ወያኔ ከምንም በላይ የሚፈራውና የመኖር ህልውናውን የሚያናጋው የትግራይ ህዝብ ስለሆነ ህዝቡ ቢፈልግም/ባይፈልግም የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቱን ማረጋገጡ የማይቀር እንደሆነ ያስገነዝበናል። ትግሬዎች ለወያኔ አገዛዝ ባላቸው ቅርበትና ርቀት ልክ ተጠቃሚነታቸው እንደሚረጋገጥላቸው ኤርሚያስ እማኞችን እያቀረበ ያሳየናል።  በዚህ ማስረጃ ውስጥ ገዥዎቻችን ምን አይነት ሰዎችና ምን አይነት ባህሪ እንዳላቸው እንመለከታለን። ወያኔዎች ከኢትዮጵያ ጥቁር አፈር ስለመፈጠራቸው ሳንወድ በግድ ጥያቄ እንድናነሳ ያደርገናል።
በአጠቃላይ መልኩ ብዙ እንደተላለፉት የሚያስታውቀው “የመለስ ልቃቂት” መጽሃፍ ወያኔ የፖለቲካ ሞኖፖሊውን እያስፋፋ የሄደውን ያህል የኢኮኖሚ ሞኖፖሊውን በአስተማማኝ መሰረት ላይ እየገነቡ ነው። ለፖለቲካው ፍፁም የበላይነትና መደላድል ወሳኝ የሚሆነው ኢኮኖሚውን መቆጣጠር እንደሆነ የሚገለጥበት አባባል ትክክል መሆኑን ያረጋገጠበት ነው። አዋጁን በጆሮ ካልተባለ በስተቀር ወያኔ የገነባው የዝርፊያ ካፒታሊዝም በራሱ መናገር ጀምሯል። የንቅዘቱ ደረጃ ከወያኔ የፕሮፖጋንዳ ማሽን ከሚነዛበት ቅጥፈት በላይ ተሻግሯል። ሦስቱ የወያኔ የዝርፊያ ማዕከላት ሁሉንም እየጠቀለሉ ነባር ሀገራዊ ከበርቴዎችን ከጨዋታ ውጭ እየወጡና ከትግራይ ውጭ አዳዲሶች እንዳይወለዱ እየተደረገ ነው። ከዚህ ሁኔታ ተነስተን አገራችን ኢትዮጵያ ያለችበት የወቅቱ ሁኔታና የወደፊት እጣ ፋንታ እጅግ አሳሳቢ ሆኗል። በአድሎና መገለል ምክንያት ጨጓራው የተላጠውና ቆሽቱ ድብን ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድ ባልታወቀ ጊዜ ፈንድቶ የወጣ እለት ውጤቱ ምን እንደሚሆን ለመገመት ነብይ መሆን አይጠይቅም።  “የመለስ ልቃቂት” የታመቀውን የህዝብ ብሶት በንዴት ገንፍሎ ሊያወጣው እንደሚችል ሙሉ እምነት አለኝ። ከዚህ አንጻር ኤርሚያስ መጽሓፉን መታሰቢያ ያደረገለት አንጋፋው ሙሉጌታ ሉሌ በጦቢያ መጽሔት ላይ “ስም ያልወጣለት ወንጀል” በሚል ርዕስ ያቀረበው መጣጥፍ ይታወሰኛል። አንጋፋው ብዕረኛ እንደገለጠው ከሆነ አንድ በአገዛዝ ውስጥ ያለ ህዝብ ደም የሚያስተፋ ንዴትና ቁጣ ካልተሰማው መሰረታዊ ለውጥ አይመጣም ይለናል።
“መናደድ ትልቅ ነገር ነው። መናደድ ብንችል ደግሞ አንዱ የዚች አገር ማዳኛ የትግል መቅድም ይሆናል። ግን ለመናደድ ለመብሸቅና ከተቻለም እህህህ ብሎ ደም መትፋት መቻል አለብን!! በማለት ብዕረኛው ይገልፃል።
“የመለስ ልቃቂት” መናደድ የማይፈልገውን ከውስጡ ፈንቅሎ በተዋረደ ስሜት የሚናደድበት ሁኔታ ይፈጥራል። ወጣቱ አዲስ የቁጭት ስሜት ፈጥሮ ወደ ተግባር የሚገባበት “የማታገያ ሰነድ” እንዳገኘ እቆጥራለሁ።
መልካም ንባብ!!
- See more at: http://www.satenaw.com/amharic/archives/22220#sthash.1BA3QPvB.LK7AJlse.dpuf

No comments:

Post a Comment