መነበብ ያለበት--በኤርሚያስ ለገሰ
" የጥፋት ልጆችን እንዴት እንታገል"
ብዙ ሰዎች የወይዘሪት ሚሚ ስብሀቱ ስብእና ፊቱ ላይ እየተደቀነ ሴትየዋን እና በዙሪያዋ የተሰባሰቡ ትናንሽ ሰዎች የሚያቀርቡትን ፕሮግራም የመስማት ፍላጐት ያጣል። ርግጥም የእነ ሚሚ ፕሮግራም በቅዱስ መጵሀፋ " የአመጳ ሰው እርሱም የጥፋት ልጅ" እንደሚለው የሚፀነሰው በአደንዛዥ እጵ እና በስካር መንፈስ መሆኑ ይታወቃል። በዚህም ምክንያት አብዛሀው በንቀት ፣ በመፀየፍ እና አቃሎ በመመልከት ቢያልፈው የሚያስገርም አይደለም። እውነትም እነዚህ የመንፈስ ድሀዎችን ማዳመጥ ጊዜ እንደማጥፋት ቢቆጥረው እና ትእግስት ቢያጣ ትክክል አይደለህም አይባልም።
ነገር ግን እንደ አንድ ስርአቱ ውስጥ እንደነበረ እና የአገዛዙ የኮሙዩኒኬሽን መልእክቶች እንዴት ተቀርፀው፣ እንዴት እንደሚተላለፋ ለሚያውቅ ሰው ጉዳዩን ከብዙ ኢትዬጲያውያን በተለየ እመለከተዋለሁ። በአጭሩ እነ ሚሚ የሚናገሩት በሙሉ ሳይቀነስ ሳይጨመር የኮሙዩኒኬሽን እና ደህንነት ጵ/ቤት ሀላፊዎች አዘጋጅተው የሚሰጧቸውን ብቻ ነው። የመልእክቱ ማእከላዊ አላማ ደግሞ ህውሀት እና መሪዎቹን የበላይነት፣ የገዥነት እና ከህግ በላይ መሆንን ማሳየት ነው። ከዚህ በተጨማሪም ለሌሎች ብሔረሰቦች ያላቸውን ንቀትና ጥላቻ ባገኙት አጋጣሚ ማሳየት ነው። እዛው ሳለ በቀጣይ ሊወሰዱ የሚችሉ ጥቃቶችን እና ሰለባዎችን የሚያመላክቱበት ነው። የእነ ሚሚ ንግግር አይን ያወጣ ክህደት እና የልብ ውፋሬ የሚታይበት በዚህ ምክንያት ነው።
እናም በፓለቲካ ውስጥ ተሳትፎ ያላችሁ ሰዎች እነዚህ የመንፈስ ድሆች እና የቤት ውስጥ ባሪያዎች ተክለ ሰውነት ወደ ጐን ትተው ከአንደበታቸው የሚወጣውን መስማት የሚከፋ አይደለም። " እኛ ከመልእክቱ እንጂ፣ ከተናጋሪው ምን አለን" የሚለው አባባል እዚህ ላይ የሚሰራ ይመስለኛል። ለማንኛው ለዛሬ ሶስት ነገሮች ላይ ላተኩር፣
1• የአሜሪካን ድምጵ (VOA) ኦሮምኛ እና አማርኛ ፕሮግራም፣
እነ ሚሚ በዛሬው ዝግጅታቸው የአሜሪካ ድምጵን (VOA) ከሽብርተኞች ጋር ግንኙነት ፈጥሯል፣ መረጃ የሚያስተላልፈው ከእነሱ እየተቀበለ ነው የሚል ክስ አቅርበዋል። ይሄ ምን ማለት ነው?…ለምን ይሔ ክስ አሁን መጣ? …የሚሉትን ጥያቄዎች ማንሳት ተገቢ ይመስለኛል። እውነት ለመናገር የአሜሪካን ድምጵ የአማርኛ እና ኦሮምኛ ፕሮግራም ባለፋት ሁለት ወራት ባስተላለፋቸው ፕሮግራሞች የህዝብን በደል እና ገፍ ለማሳየት የሔደበት እርቀት ምስጋና የሚቸረው ነው። በኦሮሚያ፣ በቅማንት፣ ወልቃይት ኢትዬ ሱዳን እና ድንበር ፣ ረሀብ ዙሪያ፣… የተቃዋሚ አመራሮችን ፣ የአገዛዙን ባለቤቶች ፣ የአገሬ ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ ልሂቃን …ወዘተ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ይበል የሚያስብል ነው። በተለይ የኦሮምኛ ፕሮግራም አዘጋጅ እህታችን ጋጠ ወጡ ሰውዬ ሳይወድ በግድ "የተፋውን ክርፋት መልሶ እንዲውጥ!" በማድረግሽ አድናቆቴ ይድረስሽ።
እናም አሁን የሚነሳው ትልቁ ጥያቄ ቪኦኤ በዚህ መልኩ እንዲቀጥል እድል ይሰጠዋል ወይ?… ከጀርባ በሚጐነጐን ሴራ እና ጫና ተጠልፎ ይወድቅ ይሆን ወይ? የሚለው ይሆናል። …ምላሹን በቀጣይ ቀን እና ወራት በሚያቀርበው ዝግጅት ድምፀት የምንመለከተው ቢሆንም የኢትዬጲያ ህዝብ ከጐኑ ሊቆም ይገባል።
2• ኦህዴድን በተመለከተ
የደህንነት እና ኮሙዩኒኬሽን መስሪያቤቱ በእነ ሚሚ ውስጥ አድሮ እንዲነገርለት የፈለገው ሌላ ቁምነገር ኦህዴድን በተመለከተ ነው። ይኸውም " አሁን በኦሮሚያ የተፈጠረው ችግር ኦህዴድ ሊፈታው የሚችል አይደለም" የሚል ነው። ይህ አባባል ሀሰት አይደለም። በኦሮሚያ የተፈጠረው ችግር በእነ አባዱላ እና ሙክታር አቅም የሚፈታ አይደለም። እንደውም የእነሱ መሳተፍ ችግሩን የበለጠ ያሰፋዋል እንጂ መፍትሔ አያመጣም።
ሁላችንም እንደምናውቀው የኦሮሞ ህዝብ እያካሔደ ያለው ትግል ማእከላዊ አላማ ከፓለቲካ፣ ከኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ እና መንፈሳዊ እስር ለመላቀቅ የሚደረግ ነው። ስለዚህ ራሱን ከጭቆና እና ርግጫ ማላቀቅ ያልቻለ ፍጡር የመፍትሔው አካል ሊሆን አይችልም። የእነ አባዱላን ተሳትፎ በዚህ ተራ ውስጥ አሰልፎ መመልከት ያስፈልጋል። እነሱ የለውጡ አደናቃፊ እንጂ የለውጥ ሐዋርያዎች የሚሆንበት እድል ከዜሮ በታች ነው። ባይሆን ቀኑ እስኪመጣ ድረስ ከሀገር ቤት ከሚሸሸው 26 ቢሊዬን ዶላር ድርሻቸው ስንት እንደሚሆን አሳዳሪያቸውን እንዲጠይቁ ይፈቀድላቸው።
እዚህ ላይ " በኦሮሚያ የተፈጠረው ችግር በኦህዴድ አቅም የሚፈታ አይደለም" በሚለው አባባል ላይ የለውጥ ሀይሉ እና ህውሀት (ደህንነቱም፣ ኮሙዩኒኬሽኑም እነሱ ስለሆኑ ነው) የምንስማማ ቢሆንም በትርጉም ደረጃ የምንለያይ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። የለውጥ ሀይሉ " በኢትዬጲያዊ ስነ ምግባር " ታንጶ የሚናገር በመሆኑ የእነ አባዱላን የሰው ልጅነት ጥያቄ ውስጥ አናስገባም። እነ ሙክታር ከድር ማንነታቸውን በተለያዩ ምክንያቶች አሳልፈው የሰጡ የቤት ውስጥ አገልጋይ ፣ ግን ደግሞ የሰው ልጆች ናቸው። ከዚህ በተቃራኒ ለህውሀቶች በተለይም የመከራ ጊዜ ሲመጣ እነ ሙክታር እና መዋቅራቸው ሰዎች አይደሉም። ይህን ደግሞ እኛ የምንለው ሳይሆን በስጋ ሞቶ በመንፈስ የሚኖርላቸው አቶ መለስ በተደጋጋሚ የገለፀው ነው።
( በነገራችን ላይ በዚህ የእነ ሚሚ ስብሀቱ የጠረጴዛ ውይይት ላይ አቶ መለስ ለስድስት ያህል ጊዜ ስሙ ተጠርቶአል። በጠረጴዛው ላይ የተቀመጡት ሶስቱም ሰዎች በተናጠል ሁለት ሁለት ጊዜ በመጥራት ውዳሴ አቅርበዋል። እነሱ ላነሷቸው ቁልፍ ችግሮች መፍትሔው የሙት መንፈሱ መሆኑን አስረግጠው ተናግረዋል። ርግጥም ሚሚ እንዳለችው አቶ መለስ " ከናዳ ለማምለጥ እንደ ኤሊ ሳይሆን እንደ አቦሸማኔ እንሩጥ!" እያለ ዘወትር ይናገር ነበር። ከተናገረው በተቃራኒ ሮጠ መሰለኝ…?? …
ሌላም ነጥብ አለ። አቶ መለስ ስድስት ጊዜ እንደ ፍቱን መዳኒት ሲጠቀስ ላለፋት ስድስት አመታት በምክትል እና ዋና ጠቅላይ ሚኒስትርነት የተሾመው አቶ ሐይለማርያም አንድ ጊዜም አልተነሳም። በጥቅስ ውስጥ ገብቶ የሚነገርለት አባባልም አልተገኘለትም። ለነገሩ እኛም ፈልገን ማግኘት ስላቃተን የሰሞኑን የኦቦ ሌንጮ ለታ ለጠቅላይ ሚኒስትር ሐይለማርያም የተጳፈ ደብዳቤ ለመምዘዝ ተገደናል። ኦቦ ሌንጮ በደብዳቤያቸው ላይ <<ጀነራል ሳሞራን እና ጌታቸው አሰፋን በአስቸኳይ አባር!>>" የሚለውን ቧልት ጵፈው ዘና አድርገውናል።)
ወደቀደመው ስንመለስ በአቶ መለስ መንፈስ የሚመራው የህውሀት መስሪያቤት ኦህዴድን እንደ ሰው አይቆጥርም። ኦህዴድ ለአቶ መለስ " የዝንብ ጥርቅም" ነው። መረጃ ካስፈለገ " የአብዬታዊ ዲሞክራሲ የአመራር ጥበብ" የሚለው የምጡቁ ፣ ባለራእዩ፣ በክፈለ ዘመን አንዴ የሚፈጠሩት ታጋይ መለስ መጵሀፍ ኦህዴድን በተመለከተ ምን እንዳሰፈረ እንመልከት፣
" ስልጣን የያዝን እንደመሆናችን ወደ እኛ የተጠጋ የተለያዩ ጥቅሞችን ማግኘቱ የማይቀር ነው። ማር ባለበት አስቀድሞ የሚያርፈው ዝንብ ነው። ስልጣን ባለበት አስቀድሞ የሚያንዣብበው ከስልጣኑ ተጠቃሚ መሆን የሚፈልገው ነው። …በደቡብ እና ኦሮሚያ አባላት በብዛት እንመለምላለን። ዝንቦች ሆነው ይገኛሉ። እናራግፋቸዋለን። እንደገና እንሞላለን። ዝንብ ሆነው እናራግፋለን" በማለት ይገልጳል።
3• ጠባብ/ ትምክህት/ አክራሪነት
የህውሀቱ መስሪያቤት በእነ ሚሚ ውስጥ አድሮ እንዲተላለፍለት የፈለገው ሌላኛው መልእክት አሁን እየተካሔደ ያለውን ህዝባዊ እንቢተኝነት ስርአቱ እንደ ማስፈራሪያ የሚጠቀምባቸው " ጠባብ፣ ትምክህት፣ አክራሪ" በሚሉ ቃላት መቀባት ነው። እዚህ ላይ መናገር የማይፈልጉት በአቶ መለስ ስጋ እና መንፈስ የምትመራው " አዲሲቷ ኢትዬጲያ" ላለፋት 25 አመታት በስልጣን ላይ ቆይቶ ባለበት ሁኔታ የተባለው ችግር ቢኖር እንኳን ምንጩ ማነው? ሀላፊነቱን መውሰድ ያለበት ማን ነው? የሚለውን ይሆናል።
የመብት፣ የፍትህ መታፈን፣ ምዝበራ በተንሰራፋበት ሁኔታ (የተባሉት አመለካከቶች በተዛባ ትርጉማቸው ተቀብለንም ቢሆን) ለምን አይኖሩም? …አንዱ አካባቢ ከማሳቹሴት ኢንስትትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ(MIT) ጋር የሚመጣጠን መቀሌ ኢንስትትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ (MIT) ሲገነባ እያየ ሌላው ቅሬታ ቢቋጥር ለምን ይገርመናል?…አንድን ብሔረሰብ አግንኖ እና የገዥነት አስተሳሰብ እንዲኖረው አድርጐ እንዲሳል ማድረግ በሌላው ላይ የሚፈጥረው ስሜት ምን እንደሆነ ማወቅ እንዴት ይቸግራል?… ለአንዱ "የወርቅነት" ማእረግ ተሰጥቶት፣ ከወርቁ ጥምዝ ውስጥ ተፈልቅቆ የወጣው "የእንቁነት" ደረጃ አግኝቶ ሌላው መኖሪያው እስርቤት ሲሆን እንዴት ቂም አይቋጥርም?…ዋናው ስልጣን ተሰብስቦ በአንድ አካባቢ ተከማችቶ እየተመለከተ ፣እንዴት የእኔ አካባቢ ሰው በቁልፍ ስልጣን ቦታ የለም ብሎ ቢቆጭ ለምን ጠባብነት እንለዋለን?… " አዲሲቱ ኢትዬጲያ" ለስርአቱ ባለቤቶች የገነት ምድር የሆነችበት ( ለንግድ እና መዝናኛ በዱባይ ፣ አሜሪካ እና አውሮፓ ቤት የሚኖራት)፣… ለሌላው ደግሞ ገበሬ፣ ባህታዊ እና ቄስ ጭምር በረሀ አቋርጠው የሚሰደዱባት በሆነበት እንዴት ቁርሾ አይያዝም?… 70% የሚሆነውን መሬት ለራሱ እና ለባእዳን ገጰ በረከት ሰጥቶ ሲያበቃ፣ መሬቱን የተነጠቀው ተኩሶ እየገደለ " መሬቴን ልቀቁ!" ቢል ለምን ይገርመናል?…አገዛዙ መሰረቴ አይደለም ከሚለው አካባቢ ማእድን፣ ቡና ፣ ሰሊጥ፣ ጫት እና የመሳሰሉትን እየነጠቀ ኤክስፓርቲ አድርጐ ሲያበቃ፣ በሌላ በኩል ባለቤቱን የበይ ተመልካች ሲያደርግ ለምን ነፍጥ አያነሳም? …ለምን " አይናችሁ ላፈር!" አይልም!!
በመሆኑም በአሁን ሰአት በኦሮሞ ተወላጅ የሆኑ ኢትዬጲያውያን የተነሳው እምቢተኝነት የሞራል መሰረት እና ልእልና ያለው ነው። ህዝባዊ ንቅናቄው የጥቂቶች ንቀት፣ ጥላቻ ፣ ብዝበዛ እና በመንግስት ውስጥ ሌላ መንግስት መፈጠር የለበትም የሚል ትግል ነው። ተወደደም ተጠላ የተቀጣጠለው አመጵ የኦሮሞ ህዝብ እና መላው ኢትዬጲያ የተነጠቀውን ነጳነት የማስመለስ ነው።
በዚህ ህዝባዊ ጐርፍ ውስጥ ግልጵ ያልሆኑ ነገሮች፣ ጥርጣሬ የሚፈጥሩ አጋጣሚዎች አይፈጠሩም ወይ?… ድብን አድርገው ይፈጠራሉ። ትግሉን ለመቀልበስ እና ሌላ አቅጣጫ እንዲይዝ የሚፈልጉ ሰርጐ ገቦችና ሌሎች ጥቂት ሰዎች አይኖሩም ወይ? …ያለምንም ጥርጥር ይኖራሉ። ዘረኝነትን የሚዋጉ " ዘረኞች!" አይኖሩም ወይ?…አሁንም ያለምንም ጥርጥር ይኖራሉ።
ታዲያ እነዚህ ኢምንት ችግሮች ፋፍተው ለውጡ ላይ ጥላሸት እንዳይቀቡ መፍትሔው ምንድነው?
ትላንት አመሻሽ ላይ የአሜሪካ ጥቁሮች የነጳነት ቀንዲል የሆነውን የማርቲን ሉተር ኪንግ ፣ የጓደኞቹን እና የህዝቡን ትግል የሚያሳይ አንድ መጵሀፍ ሳነብ ነበር። የጥቁሮች " ፀረ -ዘረኝነት" ትግል አጋጥሞት ከነበረው መለስተኛ ፈተና አንዱ " ዘረኝነትን የሚዋጉ ዘረኞች" እያቆጠቆጡ መሄድ ነበር። እነዚህ "ዘረኝነትን የሚዋጉ ዘረኞች " ነጭ ባዩ ቁጥር ደማቸው የሚፈላና ለመተናኮል የሚፈልጉ ነበሩ። ሁሉንም ነጭ በአንድ ቅርጫት ከተው የሚመለከቱ ነበሩ። ከዛም አልፈው ጥቁርነት ከነጭ ይበልጣል፣ ጥቁር የውበት መገለጫ ነው ( ዲንፕል፣ የመመረቂያ ጋዋን፣ የቀሳውስት ልብስ፣ ሙሉ ልብስ…ወዘተ) የሚሉም ነበሩ። በተለይ ድል በተቃረበ ቁጥር እንደዚህ አይነት አመለካከቶች እዚህም፣ እዚያም መደመጡ የማይቀር ነው። የድል አጥቢያ አርበኞች በመድረኩ ላይ ለመቆየት ህብረተሰቡን ሊያቃቅሩ የሚችሉ አባባሎችን መዘው ማውጣታቸው አይቀርም። እነዚህ ደግሞ በአብዛኛው ተማርን የሚሉ የድሉን ጭስ ከሌላው ቀድመው ማሽተት የሚችሉ ናቸው።
ስለዚህ የመጀመሪያው መፍትሔ እንደዚህ አይነት የነጳነት ትግሉን የሚያደበዝዙ ጥቂት ሐይሎች እንደሚኖሩ አምኖ መቀበል ያስፈልጋል። ወደ አደባባይ እያወጡም በግልጵ በመነጋገር እያረቁ መሄድ እና መተማመን መፍጠር ያስፈልጋል። ጥርጣሬዎች ባሉበት ሁኔታ ትግሉን ይጐዳል፣ መከፋፈል ይፈጥራል በሚል "የሆድ ይፍጀው" መፍትሔ የትም አያደርስም። የዛሬ ገዥዎቻችን የትግላቸው እንቅስቃሴ አስር አመት ሲሞላው ቁጭ ብለው ገምግመዋል። በግምገማቸው ትግራይ ሪፐብሊክ ብቻ አይበቃንም፣ ኢትዬጲያን መግዛት እንችላለን ብለው አቋማቸውን ለውጠዋል። ከፈለጉት አላማ ጋር አይሔድም የሚሉትን አራግፈዋል። ኢትዬጲያን ለመግዛት በእኛ የሚታዘዝ የሌላ ብሔረሰብ ፓርቲ እናቋቁም በማለት ጠፍጥፈው ፈጥረዋል። ይህን በማድረጋቸው የድል ባለቤት ሆኑ እንጂ ጠፍተው አልቀሩም።