Tuesday, February 9, 2016

የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በሳምንት ሁለቴ ፍ/ቤት ይቀርባሉ *አቶ የሺዋስ አሰፋ ለ7 ወራት በቤተሰቦቹ እንዳይጠየቅ መደረጉን ገልጹዋል *ዳንኤል ሺበሽ ጨለማ ቤት መታሰሩን ተናግሯል በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር


በፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ከተከሰሱበት የሽብር ክስ ነጻ የተባሉትና አቃቤ ህግ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ የጠየቀባቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች በሳምንት ጊዜ ውስጥ ሁለት ቀጠሮዎች ተሰጥቷቸዋል፡፡ 
ዛሬ የካቲት 01/2008 ዓ.ም ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ከማረሚያ ቤት የቀረቡት አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ አቶ አብርሃ ደስታ፣ አቶ ዳንኤል ሺበሽ እና መምህር አብርሃም ሰለሞን በይግባኙ ክርክር ላይ ዛሬም ብይን ሳይሰጣቸው ለየካቲት 7/2008 ዓ.ም ተቀጥረዋል፡፡ አቃቤ ህግ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት አራቱ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ማለትም፣ አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ አቶ አብርሃ ደስታ፣ አቶ ዳንኤል ሺበሽን በሚመለከት ከብሄራዊ ደህንነትና መረጃ ማዕከል ተገኘ የተባለው ማስረጃ ‹ኦርጂናሉ›ን ያቀርባል ተብሎ ይጠበቅ ነበር፡፡
ሆኖም አቃቤ ህግ ማስረጃውን ለማቅረብ ተጨማሪ አንድ ሳምንት እንዲሰጠው በጽሁፍ ጠይቋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ማስረጃው እንዲቀርብለት ትዕዛዝ የሰጠው ከሦስት ሳምንታት በፊት ቢሆንም አቃቤ ህግ ግን ማስረጃውን ከብሄራዊ ደህንነት ለማግኘት ደብዳቤ የጻፈው ጥር 30/2008 ዓ.ም መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ 
አቃቤ ህግ የብሄራዊ የመረጃና ደህንነት ማዕከል ‹‹የግለሰቦቹን የመልዕክት ልውውጥ በሚያሳይ መልኩ ተስተካክሎ እንዲቀርብ …. በስራ ጫናና መደራረብ ምክንያት በተጠየቀው ቀን ማድረስ ስለማይቻል…›› የሚል መልስ እንደተሰጠው ጠቅሶ ተለዋጭ ቀጠሮውን ጠይቋል፡፡ 
ተከሳሾች በበኩላቸው የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ‹‹…የመልዕክት ልውውጥ በሚያሳይ መልኩ ተስተካክሎ እንዲቀርብ…›› ሳይሆን ቀጥታ ኦርጅናሉ እንዲቀርብ መሆኑን በማስታወስ ፍርድ ቤቱ ይህን እንዲገነዘብላቸው ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም የተከሳሾችን ማስታወሻ ተቀብሎ እስከ የካቲት 7/2008 ዓ.ም እንዲቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ስለሆነም ይግባኝ መልስ ሰጭዎች በዚህ ቀን ውሳኔ ይሰጣቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በሌላ በኩል በቃሊቲ ማረሚያ ቤት የሚገኙት አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ አቶ አብርሃ ደስታና አቶ ዳንኤል ሺበሽ በማረሚያ ቤቱ አስተዳደር በደል እየተፈጸመብን ነው ሲሉ አቤቱታቸውን አሰምተዋል፡፡ አቶ ዳንኤል ሺበሽ ጨለማ ቤት መታሰሩንና ቤተሰቦቹን ማግኘት እንደተከለከለ እንዲሁም ከውጭ የሚገባ ምግብ እንዳይደርሰው እንደተደረገ ገልጹዋል፡፡ አቶ የሽዋስ አሰፋ በበኩሉ ለሰባት ወራት በቤተሰቦቹ እንዳይጠየቅ እንደተከለከለ ተናግሯል፡፡ አብርሃ ደስታም ተመሳሳይ የመብት ጥሰት እየተፈጸመበት መሆኑን ገልጹዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ የሶስቱን ተከሳሾች አቤቱታ የመዘገበ ሲሆን የቃሊቲ ማረሚያ ቤት አስተዳደር ለየካቲት 3/2008 ዓ.ም ቀርቦ መልስ እንዲሰጥ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

No comments:

Post a Comment