ሰሞኑን ዶ/ር ብርሃኑ እንድ ግራምጣ የሚሰነጣጠቅ ሁሉም የየራሱን ጫፍ ነክሶ የሚያልመዘምዘው ንግግር በታዳሚያቸው ጆሮዎች ማዕዛው እንደሚናፈቀው የሃገሬ ጠጅ አንቆርቁረውታል ለስለስ ሸከር፤ ጣፈጥ መረር የሚል ቅኝት ግን ነበረው። የወደደውም ያልወደደውም ፈቅዶም ይሁን ተገዶ ብቻ ከሁሉም አቅጣጫ ታዳሚም አድማጭም ነበራቸው። በፈቃዱ የታደመው በጋለ ናፍቆት ሲጠባበቅ ሌላው ደግሞ ምን ሊል ነው በሚል የግዳጅ ቅምጫ ሬት ሬት እያለውና እየጎመዘዘው ማወራረዱ አልቀረም ሁሉም ግን እንደ አመጣጡ ታድሟል። አቤት ያንተ ያለህ! ስንቶቹ ደም ስሮች ተበጣጥሰዋል? ስንቶቹስ ዘና ለቀቅ ብለው ይሆን? እሱን አንድዬ ይመርምረው በእርሱ ስራ ማን ይገባል?። ንግግሩ ግን ከሁሉም አቅጣጫ ቸል የሚባል አልነበረም ይልቁንስ የሚጠበቅና ቀልብን የሚገዛ ለመሆኑ የግልብጥ ለመናገር መንገድ የለም።
የዶ/ሩን ንግግር በአንክሮ አድምጫለሁ። “ያገሬ ሰው ሆይ ስማኝ” የሚል ቃና ያለው ጥሪያቸው እኔን እንደ አድማጭ አዕምሮዬን በፍጥነት መጭ በል ብሎ ያሰገረው አንድ ወቅት ዊኒስተን ቸርችል /House of commons, London, 13 may 1940/ ወደ አደረጉት ንግግር ነበር። ሁለቱም የመልዕክታቸው ይዘት የሃገር አድን ነጋሪት ጉሸማ አለበት ንግግሮቹ የጭንቅ ወቅት ጣሮች ናቸውና። እናም ነገሩ ግጥምጥም አለብኝና ሁለቱንም የጭንቅ ቀን ሰዎች ለንፅፅር ይሆኑኝ ዘንድ በጽሑፌ አትሮን ጎን ለጎን አቆምኳቸው። “ጀግናን ጊዜ ይወልደዋል” አይደል የሚባለው? አንዳንድ ጊዜ ሃገር በምጥ ውስጥ ስትሆን ህዝብ ወለሌ ሲል ድንገት ቡልቅ የሚሉ እንደ ፈረሰኛ ውኃ ደራሽ ፊታውራሪዎች በትውልድ መካከል ሲቆሙ ማየት የተለመደ ነው።
መጽሓፈ ምሳሌ እንዲህ ይላል “ጻድቃን ሲነግሱ ከተማ ትደሰታለች ኃጥኣን ሲነግሱ ህዝብ ያለቅሳል።” ህዝብ ሲያለቅስ ኑሮ ይኮመጥጣል፤ ጢሶች ከየጎጆው ይታጎላሉ፤ እንስሳትና አዕዋፋት ይሸበራሉ፤ አየሩ ሃዘን ያቁታል፤ ነፋሳት ትንቢትንና ምልኪን ያዝላሉ፤ ደመናት በቀለማትና በምስል ይዥጎረጎራሉ። ፍጥረት መፍትሄ ፍለጋን ያንጋጥጣል። ሃገር ኧረ የሰው ያለህ፤ ህዝብ የጀግና ያለህ በሚል የህብር ሙሾ ሰቆቃዎ አዳም -ወሄዋንን ይቀኛሉ። አይቀሬው ዕውነት ግን የሃገር ምጥና የህዝብ ጩኽት አብነትን በመውለድ ይገላገላሉ። ጀግናን ያፈልቃሉ!።
ቸርችል የተናገሩበት ወቅት እንግሊዝ ትላንት የነበረ ገናናነቷን አፈር ላይ የሚደባልቅ፤ ሰር ; ሎርድ የተሰኘን ማንነትን የሚንድ የሚንንቀጠቀጡለትን ክብራቸውን የሚፈረካክስ ጊዜ ነበር። መላዋ እንግሊዝም የጀግና ያለህ፤ የወንድ ያለህ እያለች የምትዋልልበት ወቅት ነበር። ጊዜው ለእንግሊዞች የጨለማው ድንዳኔ የበረታበት፤ ነገ ምን ዓይነት እንግሊዝ እንደምትኖራቸው እርግጠኛ ያልሆኑበት የግራ መጋባት ዘመን ነበር። እናም ቸርቸል እንዲህ አሉ “Hitler knows that he will have to break us in this island or lose war”. በንግግራቸው ውስጥ ማዕበል እንዳለ እናስተውላለን።
አዎ እኛም የጭንቅ ወቅት ላይ ነን የገጠመን ፈተናና የተገዳደሩን የዲያብሎስ ሰራዊቶች እንዲህ ቀላል የሚባሉ ዓይነት አይደሉም። ጠልቀን ካልቆፈርን የቸከሉብን የጥላ-ወጊ ሟርትም የሚያላውሰን አልሆነም። የኛው ብርሃኑ እንዳሉት “ትንሽ ቢገፉት ይወድቃል” የሚባል ዓይነት አይደለም። እናም ሃገር የጀግና ያለህ፤ ህዝብ የወንድ ያለህ እያሉ ያሉበት የጭንቅ ወቅት መሆናችንን ልብ ልንል ይገባል። ብርሃኑ ከቸርችል ጋር በሚሞካሽ ንግግራቸው ይህንን የጋራ ጭንቅ ሲገልጡት “ የጊዜው አንገብጋቢ ጥያቄ ነገ የምንምኛት፤ ኢትዮጵያ የምትሰኝ ሃገር ትኖረናለች ወይስ አትኖረንም? የሚል ነው” አዎ የህዝብ ጭንቀት ይህ ነው። ከብርሃኑም ውስጥ ከደማቸው ነጥቦ የወጣ የምጥ ንግግር ነው።
ቸርችል ሃገራቸው የገጠማትን የመኖር ወይም ያለመኖር የህልውና ጥያቄ እሳቸው ብቻቸውን እንደማይፈቱት የመላውን እንግሊዛውያን የጋራ ርብርብ እንደሚጠይቅ አበክረው ሲገልጡም “ምናልባትም ለታላቁ የውድቀታችን ግስጋሴ የሚመጥን ንግግር አላደረግሁም ይሆናል ስለዚሀም ሁላችሁን ይቅርታ እጠይቃለሁ ነገር ግን ይህን ወቅት ልብ ብለን ካስተዋልን አንድችን ላንዳችን አቃቂር የምናወጣበት፤ በግልምጫ የምንገፋፋበት ሳይሆን እጅ ለጅ ተያይዘን አባቶቻቸን በአደራ ላስርከቡን ትልቅ ሃገር ከውርደት ለማዳን በትውልዳችን ፊት ለተጋረጠው ፈተና መልስ የምንሰጥበት ወቅት ላይ እንገኛለን። እናም የወትሮ ወዳጆቼም ሆናችሁ አዳዲስ ጓደኞቼ፤ በፖለቲካችን ሰጣ ገባ የተጎዳችሁ ያዘናችሁ የሃገሬ ልጆች ሁላችሁም ሃገራችንን ከጭንቅ ለማውጣት በአንድ ላይ ተነሱ” ሲሉ ጥሪ አቀረቡ።
የእኛው ዶ/ር ብርሃኑም የሲቪክ ማህበራትን፤ ልዩ ልዩ ብሄረሰቦችንና ምሁራንን በጥልቅና በዕውነተኝነት ስሜት የዕንያያዝን ጥሪ አቅርበዋል። ሲቀጥሉም “ምናልባትም በአርበኞች ግንቦት ሰባት የማትደሰቱ ብትኖሩ እንኳን ወደ የፈለጋችሁት የትግል አቅጣጫ ተሰማሩና ተያይዘን ሃገራችንን ከገባችበት አሮንቃ እናውጣት። ዳር ወጥተንና እጃችንን አጣምረን የምንቆምበት ጊዜ አይደለም።” የሚል የህሊናን ሚዛን ሲጢጥ የሚያሰኝ እርሳቸውም እንደቸርችል ጥሪ አቅርበዋል።
ቸርችል ሲቀጥሉም “ለዚህች ሃገር የምከፍለው ምንም ነገር ባይኖረኝ እንኳን ልከፍለው የምችለው ግን ደም፤ ብርቱ ድካምና ልፋት፤ እንባ እና ላብ አለኝ ይህንን ለማቅረብ ደግሞ ተዘጋጅቻለሁ።” ሰውየው በዚህ ንግግራቸው እንግሊዛውያንን ምክኒያተ-ቢስ አደረጓቸው ገንዘብ ባይኖርህ ደም አለህ፤ ዕውቀት ባይኖርህ ላብ አለህ በማለት።ዶ/ር ብርሃኑም “ደም ለመክፈል እንዲሁም ነጭ ሱፋችንን አውልቀን ለላብና ለጭቃ የሚመጥኑ ቀላል ልብሶችን ለመልበስ እንዘጋጅ ብለዋል።” እርሳቸውም ግንባር ቀደም በመሆን ከወርዱበት የኤርትራ በርሃም ምንም ነገር ሊነጥላቸው እንደማይችል ዕቅጩን ነግረውናል።
ልክ እንደ ቸርቸል ሁሉ ታሪካዊ አድርገን ልንወስደው በሚገባ በዚሁ በዶ/ር ብርሃኑ ንግግር ውስጥ የሁላችንንም ትኩረት የሚሻ ሌላኛውን ነጥብ አስቀጠሉ አልሞ ስለመደቆስ!፤ ጠልቆ ስለማሰብ!። ነጮቹ (Critical thinking) ስለሚሉት ዶ/ሩ ደጋግመው ነው የተናገሩት። ይህ ደግሞ ለእኛ እጅግ አስፈላጊ እና አንገብጋቢ ጉዳይ ለመሆኑ ሁለት ሶስት ጊዜ ማሰብ የማይጠይቀን ግን ደግሞ ስለሌለን ስለዚህ ድንቅ ንጥረ -ነገር ትኩረት መስጠት እንዳለብን ከጠለቀው መረዳታቸው አካፍለውናል በተጨማሪም ከስሜት የጸዳን እንድንሆንና ከዚያ ይልቅ የምስጢረ – ሃሳብ ፈልፋዮችና የተመስጥዖ ሰዎች (Critical thinkers ) መሆን እንዳለብን ደግመው ደጋግመው ነግረውናል። ስለ ተመስጦአዊ- እሳቤ አበው በእራፊ ስንኝ ሲሸበልሏት እንዲህ አሉ።
ወትሮ ነበር እንጅ አልሞ መደቆስ፤
አሁን ምን ያደርጋል ወጭት ጥዶ ማልቀስ።
ከድርጊት በፊት ጠልቆ ማሰብን የምትጠይቅ ስንኝ ናት!።
ሃገር በስሜት አትገነባም፤ በሆታና በጩኽትም ከጥልቁ በክፋት ሰልጥነው የመጡትን ሰው መሰል ጭራቆችን ማባረር አይቻልም። ለተጠበበ መሰሪነት የሚመጥን ስራ ሰርተን መገኘት ይጠበቅብናል። ይህን ስል የሃሳብ ልቀት እንጅ የክፋት ጥልቀት አያስፈልገንም ጉዞአችን እነርሱን ተከቶና መስሎ ለመቀጠል አይደለምና!። የሄዱበትን መንገድ መከተል አያሻንም ምንጩ ሴዖል ነው ያ ደግሞ የሰውን ልጅ ለማሰቃየት የተፈጠረ የጥፋት ባህር ነውና አይጠቅመንም። በሌላኛው ጫፍ ላይ ሆኖ ግን የረቀቁ ሃሳቦችን፤ የፈረጠሙ ጡንቻዎችን የመገንባቱ ሂደት በትኩረት ሊሰራበት የሚገባ ዓቢይ ጉዳይ ነው።
ተመስጦአዊ -እሳቤ (Critical Thinking) በተመረጡ ሃሳቦቻችንና እቅዶቻችን ውስጥ ያሉ የስነ-አመክንዬ ህብለ ተያያዥነት እንድናስተውል ይረዳናል። በግምጋሜያቸን ጊዜ የነጠሩ ክርክሮችን ብልት እንድንለይ፤ ምኑን ከየትኛው ጋር ገጣጥመን እንደምንገነባው እና ዕቅዶቻችን በተክታታይነት መፍሰስ እንዳይችሉ ያደረጋቸውን ዘጊ ቆሻሻዎች ለማስዎገድም በዚህ ምክኒያትም የሚከሰቱ ተደጋጋሚ ስህተቶችን ለይቶ ለማወቅ አቅም ይሰጠናል።
አዎ ይህንን የሚወልዱ በተመሰጥዖ የሚያስቡ (Critical Thinkers) ለትግላችን ዳር መድረስ በጅጉ ያስፈልጉናል። ሩቁን የሚያቀርቡ፤ ደካማውን የሚያበረቱ፤ ጠማማውን የሚያቀኑና ተራራውን ሜዳ ሊያደርግ የሚችል የነጠረ ሃሳብ ያላቸው ሃገር ገንቢ፤ የማህረሰብ አናጺዎችን በመብራት የመፈለጉ ጊዜ አሁን ነው። እርግጥ ነው እነዚህን ሰዎች መድረክ ላይ ተፍ ተፍ ሲሉ አናገኛቸው ይሆናል፤ በሰልፉ ፊተኛው ረድፍ ላናያቸው እንችላለን እንደዚህ ዓይነት ሰዎች የአደባባይ ስዎችም ላይሆኑ ይችላሉ ጭዋታቸው ከሂሳባቸው ጋር ነው። በንጉስ ዳዊት ዘመን ስሙ አኪጦፌል የተባለ ሰው ነበር መጽሓፍ ስለዚህ ሰው ሲናገር “ምክሩ እንደ እግዚአብሄር ምክር ነበረች” ይለዋል እነዚህ ሰዎች ዋና ትርፋቸው ከኋላ ሆነው የተመረጡና የደቀቁ ሃሳቦችን የመምራት ክህሎት ላላቸው ማቅረብ ነው። ሁላችንም በሁሉ ነገር ላይ እኩል ዕውቀት የለንም ወይም ሁሉን አናውቅም። የአርበኞች ግንቦት ሰባት ወገኖቼ ከወንድማችን ብርሃኑ ዕምነት ጋር ተጣምረው ከጥሪው ባሻገር ብዙ ርቀትን ተጉዘው እነዚህን ዓይነት ሰዎች የመፈላለጉን ጉዳይ ትግሉ ከሚጠይቃችው ግብዓቶች እንደ አንዱ በመውሰድ ሊተጉ ይገባል ብዬ አምናለሁ።
ለእኔ ጋሽ መስፍን (ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም) በዘመናቸን ልናያቸው ከሚገቡን የተመስጥዖ-እሳቤ ባለቤቶች አንዱ ነው ብዬ አምናለሁ። ችግሩ እንደርሱ ዓይነት ሰዎች ያጠለቁት መነጽርና አብዛኞቻችን ያጠለቅናችው ለየቅል መሆናቸው ነው። ጋሽ መስፍን በዘመኑ ” አረ ሃገር ገደል ገባች” ሲል “አብደሃል” ፤ “የለም የለም” ሲላቸው “ጨለምተኛ” እያሉት ሃገር በህሊና ዕውራን እየተመራች ገደል አፋፍ፟ ላይ ስትደርስ ፤ ሰው እያለ እንደሌለ ሃገር በእኛ ዘመን ነገር አለሟ ሲያከትም ማየት እንደርሱ ዓይነት ሰዎችን እንዴት አያበሳጭ?። አሁንም እንዲህ ዓይነት ሰዎችን የቱንም ያክል ርቀት ተጉዘን ልናቀርባቸው ይገባል።
ሰዎች ወደ ተመስጦ – እሳቤ ልክ ሲደርሱ ያጠለቁት መነጽር ነገሮችን ከግል ጥቅማቸው አንጻር እንዲመለከቱ አይፈቅድላቸውም። የተመስጦ – እሳቤ ባለቤት ለመሆንም የግድ በታላላቅ የትምህርት ተቋማት ማለፍ ብቻም አይደለም ሰው ሆኖ መገኘት እንጅ!። እርግጥ ልሂቅ ማን ነው ? የሚለውም ገና የሚያከራክረን የቤት ስራችን ነው። በአንድ ከፍተኛ ተቋም ውስጥ አልፎ ከሆዱ በቀር ሌላ ነገርን አሻግሮ ማየት ካልቻለ ለኔ እንዲህ ዓይነት ሰው የሰለጠነ እንስሣ ነው። ለእንዲህ ዓይነት ሰው ባህል፤ ቋንቋ ፤ ማንነት ማለት ምንም ማለት አይደሉም። ሆዱ ካልጎደለ በቀር ምንም ነገር ቢገላበጥ ግድ አይሰጠውም። ነገን ማየት አይሆንለትም ከእንስሣ አቅም በላይ የሆነን ነገር ማሰብ ያቅተዋል እናም እንደ አህያዋ ” እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል”ን ነጠላ ዜማ እያዜመ ኖረ ሞተ ይሆናል የእርሱ ነገር።
ጽሁፌን ሳጠቃልል ለአርበኞች ግንቦት ሰባትም ሆነ ለእኛ ያለኝን ሃሳብ እንደ ዜጋ በመሰንዘር ነው። ለድርጀቱ መሪዎች የምለው የድርጅቱ ጥንካሬ የሚለካው በየደረጃው ያሉ መዋቅሮቹ በተገቢው መሰረት ላይ ሲመሰረቱ ብቻ ነው እናም በየጊዜው ሳይደክሙና ሳይታከቱ መዋቅሮቹን መፈተሽ፤ ዕውቀት ነዳጅ ነውና ወደ ሚፈለገው ድል ለመድረስም ሆነ ከድል በኋላ ለሚኖረው አስቸጋሪ ስራ አባላቱ በስነ-ምግባር የታነጹ እንዲሆኑ አስፈላጊውን ትምህርት አቅሙ ባላቸው ሰዎች እንዲሰጡ ማድረግ ጋንገስተሮችን እንዳንፈለፍል ፤ ምክርና ሃሳብ ከየትም አቅጣጫ ይምጣ ያለመናቅ ማስተናገድን መልመድ። ለእኛ አድማጮች እንግሊዞች ቸርችልን እንዳገኙ እኛ ደግሞ ብርሃኑን እንደተቀበልን ይታየኛል። የመሪ ያለህ ብለን እንደጮህን ከስጦታችን ጋር መፍሰሰ ደገሞ የእኛን አስተዋይነት ይጠይቃል። ጩኽታቸው ወደ ጸባዖት ደርሶ ሙሴን የተቀበሉ እስራኤላውያን በሙሴ ላይ ደንጋይ ሊወረውሩ እንደተነሱ የማይሆን ነገርን በመወረወር የመከራ ጊዜአችንን አናስረዝም። እንግሊዞች ቸርችልን ለጊዜው የሚያስፈልግ ትክክለኛው ሰው እንደተቀበሉት እኛም የእኛውን ብርሃኑን እንዲህ ብለን እንቀበለው። ሰልፍ የጀግና ነው ድል ግን የግዚአብሄር ነው። በቸር ስንብቱልኝ።
No comments:
Post a Comment