Wednesday, February 10, 2016

የኢትዮጵያ መንግስት ሃሳብን በነጻነት በሚገልፁት ዜጎች ላይ የሚወስደው የአፈና ተግባር እንዳሳሰባት አሜሪካ ገለጸች። ኢሳት (የካቲት 2 ፥ 2008)


የኢትዮጵያ መንግስት ሃሳብን በነጻነት ለመግለጽ በሚደረጉ ጥረቶች ላይ እየወሰደ ያለው አፈናና እስራት አሳስቧት እንደሚገኝ አሜሪካ በድጋሚ ገለጠች።
ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር በተገናኘ በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰው ተቃውሞም ከፕላኑ ያለፉ ብዙ ጉዳዮችን ያነገበ መሆኑንም የአሜሪካ ውጭ ጉዳት ሚኒስቴር ማክሰኞ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጠው መግለጫ አመልክቷል።
በተያዘው ሳምንት ሰኞ በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኢትዮጵያውያን ዘንድ የተካሄደውን ሰላማዊ ሰልፍ አስመልክቶ ጥያቄ የቀረበላቸውን የአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጆን ክርቢ ሃገራቸው በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ልዩ ትኩረት በመስጠት እየተከታተለች እንደሆነ ገልጸዋል።
ይሁንና፣ መንግስት ሃሳብን በነጻነት ለመግለጽ በሚደረጉ ጥረቶች ላይ ቀጥሎ የሚገኘው አፈና አሜሪካንን በጽኑ አሳስቧት እንደሚገኝ ቃል አቀባዩ አስታውቀዋል።
እየተወሰደ ያለው የመንግስት እርምጃም ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ከህዝብ ጋር በመወያየት እልባት ለመስጠት በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዲያሳድር ጆን ከርቢ ተናግረዋል።
ቃል አቀባዩ መንግስት አፈናውንና እስራቱን መቀጠሉ ቢያረጋግጡም በዚሁ ዘመቻ ምን ያህል ሰው ለእስር እንደተዳረገና ጉዳት እንደደረሰበት ዝርዝር መረጃን ከመስጠት ተቆጥበዋል። 
አሜሪካ ለዚሁ የኦሮሚያ ክልል ተቃውሞ ልዩ ትኩረትን ሰጥታለች ያሉት ቃል አቀባዩ ከአንድ ሳምንት በፊትም የአፍሪካ ህብረት ልዩ ጉባዔን ለመሳተፍ ወደኢትዮጵያ ተጉዘው የነበሩ ከፍተኛ የሃገሪቱ ባለስልጣናት በጉዳዩ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ተወካዮች ጋር መወያየታቸውን አውስተዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት እየወሰደ ካለው እርምጃ ተቆጥቦ በሃገሪቱ ሃሳብን በነጻነት የመግለፅና የመደራጀት እንዲሁም የመናገርንና የመጻፍን መብት እንዲያከብር የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሳስቧል።
በዚሁ የኦሮሚያ ክልል ተቃውሞ ተደጋጋሚ መግለጫን ስታወጣ የቆየችን አሜሪካ ተቃውሞው ከማስተር ፕላኑ ያልፉ ብዙ ጉዳዮችን ያዘለ እንደሆነም ለመጀመሪያ ጊዘ ይፋ አድርጋለች።
ይሁንና፣ የሃገሪቱ ባለስልጣናት ጉዳዮቹን በዝርዝር ከመግለጽ የተቆጠቡ ሲሆን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማትና ግለሰቦች እንዲሁም በርካታ ነዋሪዎች ከመልካም አስተዳደር ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች ተቃውሞውን እንዲባባስ እንዳደረጉት ሲገልፁ መቆየታቸው ይታወሳል።

No comments:

Post a Comment