Friday, February 19, 2016

ከሕይወት እምሻው .....................................................................# ከሰማኒያ አመታት በፊት ኢትዮጵያዊያን ዘማቾች አይተው የማያውቁትን የአውሮፕላን ድብደባ የገለፁበት ግጥም እንዲህ ይላል፡፡


ከሕይወት እምሻው
.....................................................................#
ከሰማኒያ አመታት በፊት ኢትዮጵያዊያን ዘማቾች አይተው የማያውቁትን የአውሮፕላን ድብደባ የገለፁበት ግጥም እንዲህ ይላል፡፡
.
‹‹በትግራይ ቢመጣ መቼ ይገባ ነበር፣
በጎንደር ቢመጣ መቼ ይገባ ነበር፣
በሸዋ ቢመጣ መቼ ይገባ ነበር፣
በጎጃም ቢመጣ መቼ ይገባ ነበር፣
በሰማይ ላይ መጣ በማናውቀው አገር….››
.
ጣልያኖች በማናውቀው ሀገር በሰማይ መጡብን፡፡
የአድዋን ሽንፈት ለመበቀል ጣልያኖች በአውሮፕላን እና በታንክ የመርዝ ጢስ ሰንቀው፣ ለቂም በቀል ድግስ መጡብን፡፡
.
.
ታንክ ሲያዩ ‹‹አሳማዋ መጣች›› የሚሉት ኢትዮጵያውያን፣
ቦምብን ለማጥፋት በእሳት አቀጣጥለው እንደ ማገዶ ይቆሰቁሱ የነበሩ ኢትዮጵያውያን፣
አውሮፕላንን እንደ ንብ ስለምትጮህ በሴት የሰየሙት ኢትዮጵያዊያን፣ ‹‹በሀገሬን አልቀማም›› ወኔ ብቻ
አመጣጡን ላላወቁት ጠላት በሕይወት
ከመምበርከክ ሞተው መውደቅን መረጡ፡፡
.
.
ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ እንዳሉት፤ በእርግጥም የኢትዮጵያውያን እና የጣልያኖችን የጦር አቋም የትዬለሌ ልዩነት ላየ የሚገርመው ነገር የኢትዮጵያውያን መሸነፍ
ሳይሆን ያን ያህል መዋጋታቸው ነው ፡፡ ግን ተዋጉ፡፡
.
.
ኢትዮጵያዊያን በማይገለፅ ጀግንነት ተዋጉ፡፡ ከዚያም አልፎ ለአምስት አመታት ሀገራቸውን በከፊል ቢነጠቁም ጠላት ሰላም አጥቶ፣ ሳይደላው እንዲቀመጥ ብዙ መስዋእትነት ከፍለዋል፡፡
.
.
አምስቱን አመት እፎይ ሳይል እና ሲቅበዘበዝ በየከተማውና በየካምፑ ተወሰኖ እንዲቀር ሺዎች ቆስለዋል፡፡
ሺዎች ደምተዋል፡፡
ሺዎች ሞተዋል፡፡
.
ከነጋ ጠባው ጦርነት ሌላ፤ በ1929 ዓ.ም. የሙሶሎኒን ቀኝ እጅ ግራዚያኒን ለመግደል የተደረገው ድፍርት ባስቆጣው የፋሺስት መንግስት የእብድውሻ ፍርድ የተነሳ የካቲት 12፣ 13 እና 14 …በሶሰት ቀናት ብቻ ሰላሳ ሺህ
ኢትዮጵያዊያን ተረሽነዋል፡፡ ተሰቅለዋል፡፡
.
.
አቤት ባይ በሌለበት በጎጇቸው ሳሉ በእሳት ተለብልበዋል፡፡ በግፍ ተገድለዋል፡፡
በሶስት ቀናት ብቻ ሰላሳ ሺህ ኢትዮጵያውያን ያለርህራሄ ለሞት ተሰጥተዋል፡፡
.
.
ቢሆንም…
የእነሱ አንገት ለገመድ በመሰጠቱ የእኛ አንገት ቀና ብሏል፣
.
በእነሱ በእሳት መለብለብ የእኛ የነፃነት ችቦ በርቷል፣
በእነሱ በግፍ መገደል እኛ በነፃነት ኖረናል እና …
የየካቲት 12፣
የየካቲት 13 እና
የየካቲት 14 ሰማዕታትን መቼም መቼም አንረሳቸውም!

No comments:

Post a Comment