Friday, February 26, 2016

ጭፍጨፋውን ለማስቆም ሆ ብሎ መነሳት ብቸኛው መፍትሄ ነው ! ============================


የዛሬ 79 አመት ባህር አቋርጦ ድንበር ተሻግሮ የመጣው የጣሊያን ፋሽስት ሠራዊት በአዲስ አበባ ነዋሪ ወገኖቻችን ላይ ከፈጸመው ዘግናኝ የጭፍጨፋ እርምጃ የማይተናነስ እልቂት፣ ዛሬም በኦሮሞ ወገናችን ላይ በአገር በቀል የህወሃት አልሞ ተኳሽ የአጋዚ ጦር ሠራዊት እየተፈጸመ ይገኛል ::
የካቲት 12 ቀን 1929፣ በሮዶልፎ ግራዚያኒ ትዕዛዝ የአዲስ አበባን ነዋሪ ሕዝብ በደም ጎርፍ ባጥለቀለቀው ዘግናኝ ጭፍጨፋ ህጻናት፣ ጎልማሶች ፣ ሽማግሌዎች፣ አሮጊቶች፤ ነፍሰጡሮች፣ ለጋ ወጣቶች፣ በአጭሩ ኢትዮጵያዊ የሆኑ ሁሉ ዘራቸው ፣ ሃይማኖታቸውና ጾታቸው ሳይለይ በጅምላ በመታረዳቸው፣ ደማቸው በስድስት ኪሎ አደባባይ እንደ ወራጅ ወንዝ መፍሰሱን፣ ታሪክ ጊዜ በማያደበዝዘው ብዕሩ መዝግቦት ይገኛል። የግራዚያኒ ጦር በወገኖቻችን ላይ ያንን አሰቃቂ እልቂት የፈጸመው ለነጻነታቸው ቀናይ የሆኑት ሞገስ አስግዶምና አብረሃ ደቦጭን የመሳሰሉ ጀግኖች ኢትዮጵያኖች፣ የጣሊያንን ቅኝ አገዛዝ በመቃወም በጠላት ላይ የፈጸሙትን ጥቃት ለመበቀልና በጠመንጃ ሃይል የአገሪቱን ህዝቦች በባርነት ቀንበር ሥር አውሎ ሃብትና ንብረት ለመዝረፍ በማለም ነበር። 
ከጊዜ ወደ ጊዜ ግልጽ እየሆነ የመጣው በፋሽስት ጣሊያንና ለጠባብ የቡድንና የግል ጥቅም የመንግሥትን ሥልጣን የሙጥኝ ባለው ህወሃት መካከል ያለው ልዩነት አንዱ ባዕድ ወራሪ ሌላኛው አገር በቀል ከመሆን ያለፈ አይደለም:: ጣሊያን የኢትዮጵያን ማዕከላዊ ሥልጣን የፈለገው ለአገሩ ኢንዱስትሪ የሚሆን ጥሬ የተፈጥሮ ሃብት ፍለጋ ሲሆን፣ ህወሃት ደግሞ የአገሪቱን ለም መሬት በርካሽ ዋጋ ለባዕድ በመቸብቸብ ጭምር ባለሥልጣናቱና የጥቅም ተጋሪዎቹ ሃብት እንዲያካብቱ ከማድረግ የዘለለ ራዕይ ኖሮት እንዳልሆነ በበርካታ ተግባሮቹ አስመስክሯል ::

ወያኔ አጋዚ የሚባል ልዩ ጦር አሰልጥኖና አስታጥቆ ከህዝብ የሚነሳን ተቃውሞና እሮሮ ለመጨፍለቅ የሚወሰደው ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ፣ መነሻው ለዘረፋ መሣሪያ አድርጎ የሚጠቀምበትን በትረ ስልጣን ለመከላከል እንደሆነ በተደጋጋሚ ገልጿል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኦሮሚያ አካባቢ የተጀመረውን ህዝባዊ ተቃውሞ በሃይል ለመጨፍለቅ የህወሃት ልዩ ቅልብ ጦር በህዝባችን ላይ እየወሰደ ያለው ጭፍጨፋ የፋሺስት ግራዚያን ጦር አዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ህዝብ ላይ የዛሬ 79 አመት ከፈጸመው የሚለየው በሟቹች ቁጥር እና በገዳዮቹ ማንነት ብቻ ነው:: የአጋዚን ጦር አሰልጥኖና አስታጥቆ በገዛ ወገኑ ላይ ፣ እንደባዕድ ሠራዊት፣ ጭካኔ የተሞላበት ጭፍጨፋ እንዲፈጽም ያሰማራው ህወሃትም ሆነ ከአለቆቹ የተሰጠውን ትዕዛዝ በፍጹም ታማኝነት ተቀብሎ በገዛ ወገኖቹ ላይ ታሪክ ይቅር የማይል ወንጀል በመፈጸም ላይ የሚገኘው ይህ ሠራዊት፣ ላለፉት 25 አመታት ያልአግባብ ያፈሰሰው ደምና የቀጠፈው ወገኖቻችን ህይወት ቁጥር ለመቁጠር እያዳገተ መጥቷል።

በተለያዩ ጊዜዎች በኦጋዴን፤ በጋምቤላ፤ በቤኔሻንጉል፤ በአፋር፤ በአማራና ደቡብ አካባቢዎች ከደረሰው የግድያ ፍጅት በተጨማሪ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኦሮሚያ አካባቢ የተነሳውን ህዝባዊ ተቃውሞ ለመደፍጠጥ የአጋዚ ጦር ከአለቆቹ በተሰጠው ትዕዛዝ የጨፈጨፋቸው ዜጎች ቁጥር ከ300 በላይ ደርሷል:: ቁጥሩ ከዚህ በእጥፍ የሚበልጥ ቁስለኛና ከ8 ሺህ በላይ እስረኞችም እንዳሉ ገለልተኛ የሆኑ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እየተናገሩ ነው። በአልሞ ተኳሾች ህይወታቸው ከተቀጠፉት መሃል ዕድሜያቸው ገና 8ና 9 አመት የልበለጣቸው ታዳጊዎች ፤ አሮጊቶችና እርጉዝ ሴቶች ይገኛሉ:: ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በአምቦ ከተማ በደረሰው ጥቃት የ9 አመት ታዳጊ ህጻንን ግንባር አነጣጥሮ የመታው የአጋዚ ጦር፣ ወንድሟን ከወደቀበት ለማንሳት ጎንበስ ያለቺውን እህቱን በሌላ ጥይት በመምታት ቤተሰቦቿንና የከተማውን ህዝብ የመረረ ሃዘን ውስጥ ጥሏል፤ ተመሳሳይ ግድያ በአሰላ ከተማ ውስጥ በምትኖር የ8 ዓመት ታዳጊ ላይም ተደግሟል::
በሴቶችና በህጻናት ላይ ጥይት የሚያስተኩስ የአውሬነት ባህሪ ከየትኛው ባህላችን የመጣ ነው? ይህንን አሰቃቂ ድርጊት የተመለከተ ወይም የሰማ ሰው እንዴት አድርጎ ነው ሠራዊቱንና አዛዦቹን ከአብራኩ የተገኘ የአገሩ ዜጋ አድርጎ ማሰብ የሚችለው ? የዚህ አይነት አሰቃ ድርጊት ዛሬ የጀመረ ሳይሆን በድህረ ምርጫ 97 በአዲስ አበባና በሌሎችም የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥም ተፈጽሟል። በመለስ ዜናዊ ትዕዛዝ በወቅቱ ከተማዋን ወሮ የነበረው የአጋዚ ጦር ያገኘውን ሁሉ በጥይትና በቆመጥ ሲያዋክብ፣ ሠይድ የተባለ የ10 አመት ልጅ የጨርቅ ኳሱን ከመሬት አንስቶ ለመሮጥ ሲንደረደር አናቱን በጥይት ተመቶ እስከወዲያኛው አሸልቦአል:: በስተርጅናቸው ይጦሩኛል ብለው መርካቶ ውስጥ ሽንኩርት በመቸረቸር ሁለት ልጆቻቸውን ተቸግረው ያሳደጉ የእነ ፍቃዱ እናት በአጋዚ ጥይት ሁለቱንም በአንድ ጀንበር ተነጥቀዋል:: ምንም ጥፋት እንዳላጠፋ እየመሰከሩ ባላቸውን ከእስር ለመታደግ የሞከሩ የልጆች እናት ወ/ሮ እቴነሽ ሴት ልጆቻቸው ፊት በጥይት ተገድለው ቤተሰብ የተገደሉበትን ጥይት ዋጋ ከፍሎ አስከሬን አንዲወስድ ተደርጓል:: የ14 አመቱ ነብዩ አለማየሁም ባንክ ልትዘርፍ ነበር ተብሎ በግፍ ተገድሏል። ያ እሮሮ ያ ጩኸት ወያኔ ሥልጣን ላይ እስካለ ብቻ ሳይሆን እስከ ወዲያኛውም ከህሊናችን አይጠፋም:: ታሪክ ራሱን ይደግማል እንዲሉ የድህረ ምርጫ 97 አይነቱ ጭፍጨፋ አሁንም የኦሮሚያ ከተሞችንንና መንደሮችን እያዳረሰ ነው። "እናቴን ለምን ገደላችሁብኝ" ያለ ወጣት ደምቢዶሎ ውስጥ በጠራራ ጸሃይ ህዝብ ፊት ተረሽኗል፤ ምንም አይነት መሣሪያ ያልታጠቁ እናትና ልጅ በአንድ ቀን በአንድ ጀንበር በግፈኞች ጥይት ለህልፈት በቅተዋል፤ በደኖ ውስጥ ፍሮምሳ አብዲ የተባለ የ10 አመት ታዳጊና ወላጅ እናቱም እንዲሁ። ምስራቅ ሃራርጌ ውስጥ ደረታቸው ላይ በተተኮሰ ጥይት ህይወታቸውን ያጡት የ60 አመቷ አዛውንት አዴ ጁሃራ ሙሳንና የሌሎች ሰለባዎችን ፎቶግራፍ በማህበራዊ ድህረ ገጽ የተመለከትን ሁሉ ልባችን በሃዘን ተወግቶአል ፤ በቁጭትም በግኗል:: በመቻራ፤ በነገሌ፤ በነቀምት፤ በኮፈሌ፤ በመንዲ፤ በሆሮ ጉዱሩ፡ በቦቆጂ ፤ በአሰላ ፤ በሮቤ ፤በጎባ፤ በመቱ ወዘተ በየቀኑ እየፈሰሰ ባለው ደም ምክንያት ተመሳሳይ ለቅሶ ተመሳሳይ ዋይታ የአገራችንን ምድር እያናወጠ ነው። ይህ አረሜኔያዊ ጭፍጨፋ የዕለት ተዕለት በሆነበት ሰሞን ባለፈው ሰኞ ለአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ የኦሮሚኛ ፕሮግራም ቃለመጠይቅ የሰጠው ጌታቸው ረዳ፡ በገዛ ወገኑ ላይ እንዲህ አይነት ዘግናኝ እርምጃ እየወሰደ ያለውን የአጋዚ ጦር "በመልካም ሥነምግባር የታነጸና ህዝባዊ ወገናዊነቱን ያረጋገጠ" በማለት ሲያሞካሸው ተሰምቷል :: ከሶስት አራት ቀን ቆይታ ቦኋላ ደግሞ ሃይለማሪያም ደሳለኝ በኦሮሚያ ያለው እንቅስቃሴ "የመንግሥትን ሥልጣን በሃይል ለመንጠቅ የሚደረግ እንቅስቃሴ ስለሆነ የማያዳግም እርምጃ ይወሰዳል" ሲል በቴለቪዢን መስኮት ብቅ ብሎ ዝቷል:: ታዳጊ ህጻናትንና እርጉዝ ሴቶችን ግንባር አልሞ የሚመታ ሃይል ከማሰማራትና ህዝብ ከማስጨፍጨፍ የበለጠ ምን አይነት የማይዳግም እርምጃ ለመውሰድ ህወሃት እንደተዘጋጀ ሃይለማሪያም ደሳለኝ እራሱ የሚያውቅ አይመስለንም። ህዝባዊ ተቃውሞ በሚካሄድባቸው ቦታዎች ታንክና መትሬየስ እየተተራመሰ እየተመለከትን የማያዳግም እርምጃ የሚሉን እንደ ባህሪ አባታቸው ፋሽስት ጣሊያን የመርዝ ጭስ ከአየር የሚለቅ አይሮፕላን ለማሰማራት ፈልገው ይሆን ? ወቅቱ ፈቀደም አልፈቀደ ወያኔ ሥልጣኑን ለመከላከል ይጠቅማል ብሎ እስካመነ ድረስ የማይወስደው የጭካኔ እርምጃ ይኖራል ብሎ ማሰብ ቢያዳግትም፣ እንደ ሁለተኛው የአለም ጦርነት የመርዝ ጭስ በመጠቀም ሥልጣን ላይ ተደላድሎ መቀመጥ እንደማይቻል የመረዳት አቅም ያለው ወያኔ ውስጥ አለ ብሎ መዘናጋት አያስፈልግም። 
በህዝብና በአገር ሃብት ጠንካራ ሠራዊት ገንብቶ ህዝብ እየገደለ፤ እያፈናቀለና እያሰደደ እስከወዲያኛው ሥልጣን መቆጣጠር የቻለ መንግሥት በታሪክ አይታወቅም። የወያኔም መንግስት የመጀመሪያው ሊሆን አይችልም:: የግራዚያኒ ቁራጭ የዛሬው ጥቁር ፋሽስት ወያኔ እራሱን የተለየ ጠንካራ አድርጎ የሚቆጥረው የአለም አምባገነኖችን ታሪክ ብቻ ሳይሆን የአገራችንን የቀደምቶቹን አወዳደቅ ታሪክ እንኳ መለስ ብሎ ለመመልከት ባለመቻሉ ነው።

በጠመንጃ ሃይል በአንድ ወቅት በአንድ ቦታ የሚነሳውን ወይም የተነሳውን ተቃውሞ ማዳከም ወይም መቆጣጠር ይቻል ይሆናል። አፍኖና ነጻነት ገፎ ሥልጣን ላይ ተደላድሎ ለረጅም ጊዜ መኖር ግን በፍጹም እንደማይቻል ወያኔ እራሱ ካካሄደው የጸረ ደርግ ትግል መማር ነበረበት:: ባለመማሩም የራሱን የወደፊት ዕጣ ከቀድሞው የዩጎዝላቪያ ፕሬዝደንት ስሎባዳን ሚሎሶቪችና የአይቬርኮስቱ ሎሬንት ባግቦ ተርታ እያሰለፈ ነው:: ሁለቱም በየአገራቸው ባደራጁትና በሚመሩት ሠራዊት ተማምነው በአገርና በህዝብ ላይ ለፈጸሙት ወንጀል በመጨረሻቸው አፍንጫቸውን ተሰንገው አለም አቀፍ ፍርድ ቤት ተወረውረዋል:: የአገር መከላኪያ ጦር ዋና አላማና ተግባር የአገርን አንድነትና ሉአላዊነት ከባዕድ ወረራ መከላከል ነው። ወያኔ እየገዛት ባለችው አገራችን ግን እየሆነ ያለው በሠላም አስከባሪነት ሥም ለወያኔ መሪዎችና የጦር ጀነራሎች በውጪ ምንዛሪ ገቢ የሚያስገኝ ድንበር ዘለል ግዳጅ ተግባር ላይ መሠማራት ወይም የገዛ ወገንን መግደልና ማሠር ሆኗል:: ይህ አካሄድ በአስቸኳይ መቆም አለበት:: የወያኔን የሥልጣን ዕድሜ ለማራዘም ሲባል የሚሰጠውን ትዕዛዝ ተቀብሎ ህዝብ መጨፍጨፍ፤ ማቁሰልና ማሰር የፍርድ ቀን ሲመጣ "ታዝዤ ነው" በሚል ከተጠያቂነት ነጻ የማያደርግ ወንጀል መሆኑን ሁሉም ሊያውቅ ይገባል:: አሁን በኦሮሚያ ውስጥ እየተካሄደ ባለው ተቃውሞ ህዝብ በመፍጀት ለወያኔ ግዳይ ጥሎ የመሸለም አባዜ የተጠናወታቸው አዛዦች ካሉ ቆም ብለው ማሰብና ከድርጊታቸው መታቀብ ያለባቸውም ከታሪክና ከህግ ፍርድ እራሳቸውን ለማዳን ነው።
አርበኞች ግንቦት 7 በኦሮሚያ ህዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለውን ጭፍጨፋ ለማስቆም ሁላችንም ሆ ብለን መነሳት፤ አምርረን በመታገል ይህን እጅግ ጨካኝ ዘረኛ ስርአት በማስወገድ ወንጀለኞቹን ለህግ ማቅረብ መቻል ይኖርብናል ብሎ ያምናል:: አባቶቻችን በፋሽስት ጣሊያን ጦር የተሰነዘረብንን ወረራና ጥቃት ለማክሸፍ ሆ ብለው በህብረት እንደዘመቱት ሁሉ፣ ይህ የኛ ትውልድም አገራችንንና ህዝባችንን ለከፋ መከራ የዳረገውን የወያኔ አገዛዝ ከላያችን አሽቀንጥሮ ለመጣል በህብረት መነሳትና መዝመት ያለብን ግዜው አሁን ነው።
በወያኔ ከፋፍለህ ግዛው ፖሊሲ ምክንያት በፍርሃትና በጥርጣሬ መተያየታችን የአገዛዙን ጡንቻ አፈርጥሞታል። አንዱ ሲጠቃ ሌላው ዝም ማለቱን ከቀጠለ ሁላችንም በየተራ ተደቁሰን በባርነት ቀንበር ሥር ስንማቅቅ እንኖራለን። ይህ እንዳይሆን የፈለገ ሁሉ ዛሬውኑ በኦሮሚያ እየተቀጣጠለ ያለውን የነጻነት ትግል ይቀላቀል። ከአሁን ጀምሮ አንዱ ሲደማ የሌላው ከዳር ሆኖ ተመልካችነት ማብቃት ይኖርበታል። አርበኞች ግንቦት 7 የወያኔን ጭፍጨፋ ለማስቆምና አገራችን ውስጥ ሠላም ፍትህና እኩልነት እንዲሰፍን የሚያካሂደውን ትግል ከጫፍ እስከ ጫፍ ያለው ኢትዮጵያውያን ሁሉ እንዲቀላቀሉት የትግል ጥሪውን በድጋሚ አጠናክሮ ያቀርባል።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !!

No comments:

Post a Comment