ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ህዝቡ ትግሉን እንዲቀላቀል ጥሪ አቀረቡ
የአርበኞች ግንቦት7 ሊቀመንበር ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ በዲሲ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ባደረጉት ንግግር፣ ወያኔን መጣል የሚቻለው በምኞት ሳይሆን ጠንክሮ በመታገል ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ያለው ግጭት ከመንግስት ሽፍትነት ጋር የተያያዘ መሆኑንና የገለጹት ፕ/ር ብርሃኑ፣ የመሬት ቅርምቱ የዚህ ሽፍትነት ዋና ማሳያ ነው ይላሉ። ዝርፊያው በአንድ በኩል፣ የልማት መንግስት በሌላ በኩል የፈጠሩዋቸው በርካታ ችግሮች መሆናቸውን ገልጸው፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረቱ የዚህ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብ እንዳለፈው 50 አመት እንደዚህ ቅጣ ያጣ መንግስት ያዬ አይመስለኝም ነበር ያሉት ፕ/ር ብርሃኑ፣ 20 ሚሊዮን ህዝብ ተርቦ በሚገኝበት ወቅት የመንግስት ባለስልጣናቱ ድርቁን ተቆጣጥረነዋል ማለታቸው ግብዝነታቸውን ያሳያል ብለዋል።
ለከፋፍለህ ግዛው በሚል በሰፊውና በተወሰነም ደረጃ በስኬት እየተጠቀሙበት የማንነት ፖለቲካ መልሶ ራሳቸውን የሚነክስበት ደረጃ ደርሷል ያሉት ፕሮፌሰሩ፣ በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ የብሄር ጥያቄያቸውን በምሳሌነት አንስተዋል። ከማንነት ፖለቲካ ጋር ተያይዞ የተነገረው ተስፋ እና ስርዓቱ ሊያመጣ የቻለው ሊጣጣም አለመቻሉን የገለጹት ፕ/ር ብርሃኑ፣ አሁን እየተነሳ ያለው ጥያቄ ያላሰቡትና ያልጠበቁት ነው ብለዋል። የማንነት ጥያቄ ራስን የማስተዳደር ጥያቄ በመሆኑ በመሰረተ ሃሳቡ የዲሞክራሲ ጥያቄ ነው ያሉት ፕ/ር ብርሃኑ፣ ወያኔ ይህን ጥያቄ ለመመለስ በፍጸም አይችልም ይላሉ።
ለወያኔ ስልጣን ማለት ለመዝረፍ የሚያመች መሳሪያ መሆኑን በመግልጽ፣ ለመዝረፍ ደግሞ ፍጹም የፖለቲካ ስልጣን የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ ለማንም ስልጣን ለማካፈል ዝግጁ አለመሆናቸውን ተናግረዋል። ስልጣን የማያካፍሉት ለመዝረፍ ስለማያመቻቸው በመሆኑ፣ ጥገናዊ ለውጥ እናምጣ ብለው ለተነሱት ፖለቲከኞች የማይመቸ መሆናቸውም ገልጸዋል።
በኦሮምያ እየተካሄደ ያለው ተቃውሞ ስሜታዊ እንደሚያደርግ የገለጹት ብርሃኑ፣ በኦሮምያ በእርጉዝ እናቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸመውን ግፍ ለማውገዝና ለመናደድ ኢትዮጵያዊ መሆን የለባችሁም ያሉት ፕ/ር ብርሃኑ፣ የመጀመሪያው መልሳችን ማንም ያድርገው ማውገዝ አለብን ብለዋል።
በወገኖቻችን ላይ መሆኑ የሚጥልብን እዳ አለ ያሉት ፕ/ር ብርሃኑ ፣ በወገናችን ላይ ይህ ግፍ ሲፈጸም ከንፈር ከመምጠጥ በላይ ማድረግ ያለብንን ነገር ማድረግ አለብን ብለዋል።
የችግሩ ዋና መንስኤ የመሬት ዝርፊያ መሆኑንም ተናግረው፣ ዝርፊያው በተለያዩ አካባቢዎች እየተፈጸመ መሆኑን የኦሮምያን ልዩ የሚያደርገው ኦሮሞዎች ለመታገል መወሰናቸው ነው ብለዋል። ወጣቶቹ ፣ ተማሪዎቹ፣ ኦሮጌቶች ይህን አታደርጉም ብለው ታገሉ፣ እኛ ይህን ማንደግፈው ለምንድነው? ቅናት ነው ሲሉም ተሰብሳቢውን ጠይቀዋል። ያነሱት የመሬት ጥያቄና ለመታገል መወሰናቸው በራሱ ይህን ትግል እንድንደግፈው እንጅ እንድንቃወም አያደርገንም ሲሉም አክለዋል።
ከመሬት ቅርምትና ዝረፊያ ጋር በተያያዘ መሆኑን ካዬን ጥያቄው የኢትዮጵያውያን መሆኑን መቀበል አለብን ያሉት ፕሮፌሰሩ፣ የራሳቸውን የግል አቋም ያሉትንም አቅርበዋል። "ከዘላቂ የመረጋጋትና እውነተኛ ዲሞክራሲን ከመፍጠር አኳያ የማንነት ፖለቲካ አይጠቅመንም ብቻ ሳይሆን በዜግነት እኩልነት ላይ የተመሰረተ ስርዓት ብቻ ነው የፖለቲካ መረጋጋትን የሚሰጠን ብዬ አምናለሁ" ሲሉ ተናግረዋል። በማንነት ፖለቲካ ላይ ተመስርቶ የተረጋጋ አገር መፍጠር አይቻልም ብዬ አምናለሁ ያለት ፕሮፌሰሩ፣ ከዚህ ፖለቲካ የምንሻገርበትን መንገድ መፈለግ አለብን ብለዋል። የማንነት ጥያቄ እንዴት መጣ የሚለውን ማወቅ እንደሚያስፈልግ ፣ የምንሰጠው መፍትሄም ካለው ችግር ጋር የሚመጥን መሆን አለበት ያሉት. የአርበኞች ግንቦት7 ሊቀመንበር፣ ችግሩ የህዝብን መብት ጠብቆ የሚያስተዳድር ስርዓት መፍጠር ባለመቻላችን የመጣ መሆኑን አክለዋል።
ፕ/ር ብርሃኑ አርበኞች ግንቦት7 ትግሉን ኢትዮጵያ ውስጥ እያካሄደ መሆኑን በመግልጽ፣ ህዝቡ ትግሉን እንዲቀላቀል ጥሪ አቅርበዋል።
No comments:
Post a Comment