የቀድሞ የኢትዮጵያ ጦር ሃይሎች አመሰራረቱ በምድር ጦር ፤ በአየር ሃይልና በባህር ሃይል ፤ ፖሊስ ሰራዊት , የሚሊሺያና ብሄራዊ ዉትድርናን እንዲሁም አባት ጦርን በመያዝ ተዋቅሮ ለኢትዮጵያ ዳር ድንበርና ሉዑላዊነት መከበር ትልቅ አስተዋፅኦ ሲያደርግ የነበረ፤ ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍልና ህዝብ የወጣ ነዉ። ይህ ጦር ለኢትዮጵያ የአየርና የባህር ብሎም የምድር ድንበርን ለማስከበር በብሄር ወይም በዘር ፤ በፆታ ፤ በሃይማኖት ልዩነት ላይ ተመርኩዞ የተመሰረተ ሳይሆን ይልቁንም በወታደራዊ አወቃቀር መሰረት በሃይሎች ፤ ክፍለ ጦር ፤ ብርጌድ ፤ሻለቃ ፤ ሻምበል ፤ የመቶና ጓድ በመሆን የተደራጀ ጠንካራና ግዙፍ ኃይል ነበር። የዛሬ 25 ዓመት ይህ ጦር በራሱ አዛዦች ትዕዛዝ መሳሪያዉን አሰቀምጦ ወደየመጣበት እንዲሄድ ታዞ መሳሪያዉን ካስቀመጠ በኋላ በሻቢያና ወያኔ አማካኝነት የደረሰበትን አሰቃቂ ወንጀል ዛሬ ባንዘረዝረዉም አሁን በህይወት ያሉ የእያንዳንዱ የሰራዊቱ አባላት ታሪክ ቢነገር ማለቂያ የለዉም። የቀድሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት ለ17 ዓመታት ከሶማሊያና ከገንጣይ አስገንጣይ ወንበዴ ጋር ያለምንም እረፍት ሲታገል ኖሮ በወቅቱ ለደርግ ባለስልጣናት ባለዉ ቅሬታ ብቻ ይህ ጦር ከአብራኩ እንዳልወጣ ሁሉ ከኢትዮጵያ ህዝብ የተሰጠዉ ዉልታ ግን በመወደስ ፈንታ መጠላትን ፤ የደርግ ጦር በማለት በማዋከብ ለከፍተኛ እልቂትና ስደት መዳረግን ፤ ቁስለኛና አቅመደካማዉን መንገድ ዳር በመጣል ለልመናና ለቋሚ በሽታ ማጋለጥና አልፎ ተርፎም በምርኮ ላይ ያሉትን በአሁኑ ሰዓት በኤርትራ በረሃ የሲኦል ኑሮ የሚኖሩትን ወንድሞቻችንን ማንም ዞር ብሎ ያያቸዉ የለም ። በቅርቡ በአሜሪካ ያሉትን የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለነዚሁ ምርኮኞችና በየጎዳናዉ ለወደቁትና ብተሰባችዉ ለተበተነዉ የቀድሞ ሰራዊት ተጠይቀዉ በንቀትና በለበጣ አመላለስ በመገረም << እንዴ ! ምርኮኛ አለእንዴ ? በመንግስታችን ዘንድ እኛ አናዉቅም ። ቢኖሩም የኤርትራን መንግስት አንጠይቅም ፤ ሌለዉ ደግሞ የምን ለማኝና መንግድ ላይ የተጣለ የጀግኖች ዓምባ ታወራላችሁ ! ዛሬ በኢትዮጵያ ዉስጥ አሉ ከሚባሉት ሚሊየኔር በብዛት የቀድሞ ሰራዊት አባላት ናቸዉ >> በማለት መልሰዋል ።ታድያ እኛ የቀድሞ ሰራዊት አባላት ከያለንበት ወጥተን በአንድ ድምፅ መናገር መቻል የለብንም ? በአንድ ላይ ሆነን ኮሾሮ ፈጭተን በልተን ቁስሎቻችንን እርስበርስ አክመን የተሰዉትን ጀግኖች አባሎቻችን አንድ ላይ አዝነን ቀብረን ያሳለፍነዉን እናስተዉስ። አንድነታችን የጥንካሬያችን ልዩ ምልክት እንደነበረ ሁሉ ዛሬም ከተቀመጥንበት እንነሳና አንድነታችንን እናምጣ ። ምንም ያህል ግዜዉ ቢርቅም ያካበትነዉ ከፍተኛ በህብረት የመስራት ልምዳችንን በማስታወስ በተለያየ ምክንያት ሁለት የጦር ኃይል ማህበር ፤ ሁለት የባህር ሃይል ማህበር፤ የአየር ኃይል ማህበር በየቦታዉ በተለያየ ስም የተዋቀረዉን በአንድነት አሰባስበን ወደ አንድ ጠንካራ ኃይል ለማምጣት እንስራ ። በተለይም በተለያዩ ከተሞች ያሉና በከፍተኛ ማዕረግ ላይ የነበሩ የቁርጥ ቀን ደራሽ የነበሩ ጀግኖች መሪዎቻችን ምንም ነገር እንደማይመለከታቸዉ ከመቀመጥ ይልቅ ዛሬ ቢይፋ ወጡና ስትመሩት ለነበረዉ ጦር አለን ብትሉ ለመሰባሰባችን አንዱ ቁልፍ አካል ስለምትሆኑ አስቡበት። ይህንን ዓላማ ለማሳካት በቅርቡ ግዚያዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ለመመስረት ዝግጅት ላይ ያለን ሲሆን ሁላችሁንም ለዚህ ዓላማ መሳካት የበኩላችንን ድርሻ እንወጣ እያልን በማክበር እንጠይቃለን።
የእትዮጵያ አንድነት ለዘላለም ይኑር !
No comments:
Post a Comment