Friday, February 19, 2016

(የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ ሬድዮ) ‪#‎ህወሓት‬ በሚቆጣጠረው አየር ኃይል ውስጥ ከፍተኛ አለመረጋጋትና ውጥረት ሰፍኗል፡፡ የሰባት ዓመት ኮንትራታቸውን የጨረሱ ቁጥር ስፍር የሌላቸው አብራሪዎች፣ ቴክኒሻኖች እና የስታፍ ሰራተኞች የስንብት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ የልምምድ በረራዎች በድሬ ደዋ እንዳይደረጉ ጥብቅ መመሪያ ወርዷል፡፡ ====================================================


ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ በለስ ቀንቶት በ1983 ዓ.ም አገሪቱን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥሩ ስር ካዋለ በኋላ በሁለት መንግስታት የተገነባውን፣ ገናና ስምና ዝና ያተረፈውን እና ጠንካራ ተክለ ቁመና የነበረውን የኢትዮጵያ አየር ኃይል በበቀል መንፈስ ተነሳስቶ ሙሉ በሙሉ አፈራርሶ ኦና አስቀርቶታል፡፡ የራሱን የደደቢት ድኩማኖች በውስጡ በመሰግሰግ እንደ አዲስ ሊያዋቅረው ሞክሮ ውጤቱ ፍሬቢስ ሲሆንበት ያለምንም የአገልግሎት ዋጋ ክፍያ በመጥረጊያ ጠራርጎ አውጥቶ የጣላቸውን የቀድሞው ጦር አባላትን በ1990 ዓ.ም ለመመለስና አዳዲስ ወጣቶችን ከዩኒቨርሲቲዎች ለመመልመል ሞክሯል፡፡
ሆኖም ግን በአየር ኃይሉ ውስጥ ስር በሰደደው ዘረኝነት፣ ኢ-ፍትሀዊ አስተዳደር፣ ከዘመኑ ጋር አብሮ የማይሄድ ኋላቀር የአሰለጣጠንና የትምህርት ስርዓት እንዲሁም በተጨማሪ አገዛዙ በህዝቡ ላይ በሚያደርሰው የማያቋርጥ ግፍና በደል ምክንያት በርካታ አብራሪዎች፣ ቴክኒሻኖችና የስታፍ ሰራተኞች ተዋጊ ሄሊኮፕተርና ጀት ጭምር በመያዝ ከአገር በመውጣት በበረሃ እየተደረገ የሚገኘውን የትጥቅ ትግል በመቀላቀል ላይ ይገኛሉ፡፡
አሁን ደግሞ በኦሮምያ ህዝባዊ አመፅ ከተቀሰቀሰ ወዲህ በአየር ኃይል በተለያዩ አየር ምድቦች ውስጥ ከፍተኛ አለመረጋጋት ተከስቷል፡፡ የኦሮምያ ተወላጅ የሆኑ አባላት ከፍተኛ ክትትል እየተደረገባቸው እንደሚገኝም ታውቋል፡፡ ስለዚህም በየቀኑ ከሚጠፉት ባሻገር የሰባት ዓመት ኮንትራት ጊዜያቸውን በመጨረሳቸው የስንብት ጥያቄ የሚያነሱ አብራሪዎች፣ ቴክኒሻኖችና የስታፍ ሰራተኞች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን በእጅጉ እየናረ መጥቷል፡፡ በተለይም ደግሞ በ1994፣ 95፣ 96 እና 97 ዓ.ም የተቀጠሩ አብዛኞቹ ቴክኒሻኖች ሰላማዊ ስንብት የማይደረግላቸው ከሆነ ሌሎቹ እንደሚያደርጉት ከመጥፋት የሚያግዳቸው ምንም ነገር እንደሌለ መናገራቸው ተሰምቷል፡፡
አገዛዙ በአየር ኃይል ውስጥ ተፈጥሮ የቆየውንና አሁን ደግሞ አየተባባሰ የመጣውን የአባላት መጥፋትና የስንብት ጥያቄ ማቅረብ ለማስታገስ የተለያዩ ማባበያዎችን ቢያደርግም ችግሩ ሊፈታ አልቻለም፡፡
በመሆኑም ድሬ ደዋ በሚገኘው ምስራቅ አየር ምድብ ምንም አይነት የበረራ ልምምድ እንዳይደረግ ጥብቅ መመሪያ ተላልፏል፡፡ የበረራ ልምምዱ ወደ ደብረ ዘይት ተዛውሯል፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ድሬ ደዋ ለጎረቤት አገሮች ቅርብ በመሆኑ እና ለመክዳት አመችነት ስላለው ነው ተብሏል፡፡

No comments:

Post a Comment