በተለያየ የስልጣን ደረጃ እና በደህንነት ስራ ላይ ተመደባችሁ በማገልገል ላይ ለምትገኙ የቤተ ጉራጌ ተወላጆች፦
ህወሃት ስልጣን ከተቆጣጠረ ጀምሮ በህዝባችን ላይ እያወረደው ያለው የጥላቻ ዱላ እስከዛሬም እንደቀጠለ እንዳለ ከእናንተ የተሸሸገ አይደለም።
1/ ህወሃት ስልጣኔ ዘለቄታ ሊኖረው የሚችለው የኢኮኖሚና የፖለቲካ የበላይነቱ በፍፁም የበላይነት ስቆጣጠር ነው ብሎ በአላማ የተነሳ ድርጅት ነው። ይህ እምነቱ በራሱ ችግር አይደለም። ችግር የሆነው ከባዶ ተነስቶ ፤ በታታሪነት ሀብት ያፈራውን የጉራጌ ተወላጅን በሃገሪቱ ሆን ተብሎ በተዘረጋው ለወያኔ አባላትን ለታማኝ አገልጋዮቹ ፍፁም በሆነ መልኩ በሚያዳላው አስራር መገፍተራቸው ነው። ይህ ሳያንስ ሳያንስ በተለይ ምርጫ ዘጠና ሰባትን ተከትሎ በተለይም ባብዛኛው የማህበረሰቡ ተወላጆች በንግድ ስራ ተሰማርተው በሚገኙበት አዲስ አበባ በመመሪያና ጉዳዩን የሚያስፈፅም ሰው መድቦ ህዋሃት ለዘመናት ያፈሩትን ሃብት ካላቸው ሃብትና ከስራ ቦታቸው ጋር የማይመጣጠን፤ ለዚያው አጠገባቸው ካለውና ተመሳሳይ ስራ ከሚሰራ ነጋዴ ጋር ምንም የማይመጣጠን ክፍያ በታክስ ስም እየተጠየ ቁልቁል እንዲያድጉ ተገደዋል። በዚህም ሳያበቃ ላባቸውን አንጠፍጥፈው የሰሩት ቤት በጠራራ ፀሃይ እየተነጠቁ በኢንቨስትመንት ስም ለህወሃት አባላትና ለታማኝ አገልጋዮቹ ተሰጠ። ይህ በደል ደግሞ በአአዲስ አበባ የተወሰነ አይደለም የናዝሬት አዳራሽ ጉራጌዎቹን ለማባረር ከአምስት አመት በፊት እንዳፈረሱትና አሁን በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ ይታወቃል። ጉራጌው ማህበረሰብ በየተሰማራበት ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ለማጋጨት ህወሃት ባዛጋጃቸው ሰዎች አማካይነት የሚደርስበት ችግር የሚታወቅ ነው።
2/ የጉራጌ ማህበረሰብ ከየትኛውም ኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር ተስማምቶ የመኖር ችግር የለበትም። ሆኖም ግን ጉራጌ ደቡብ ክልል ውስጥ መካተቱ የህገ መንግስቱን ድንጋጌ ያልተከተለ ነው። ህገ መንግስቱ ክልል የሚወሰነው የነዋሪዎቹ ቋንቋ ባህልና ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥን መሰረት ባደረገ መልኩ ነው ይላል። ጉራጌ ግን ደቡብ ውስጥ መካተቱ ከነዚህ መስፈርቶች ውስጥ የትኛውንም አሟልቶ ሳይሆን ሆን ተብሎ ጉራጌን እንደ ኢኮኖሚው ሁሉ ከልማትና ከፖለቲካው ለማግለል በህወሃት የተሸረበ ሴራ ነው። ለረጅም ጊዜ የልማት ጥያቄ ሲነሳ ሌሎቹ በልማት ወደኋላ የቀሩ የክልሉ ዞኖች ስላሉ ቅድሚያ ፍትሃዊ እንዲሆን ለነሱ ይሰጥ በሚል ሸፍጥ ጉራጌ ክልል ለልማት እንዴት ባዳ ሆኖ እንደኖረ ቢያንስ በፖለቲካው የቆያችሁና ለፖለቲካብ ቅርብ የነበራችሁ ታውቃላችሁ።
በቅርብ ጊዜ የተሰራው የወልቂጤ ዩንቨርስቲና አስፓልት መንገዶችም ቢሆን በተቃውሞ ጎራ የነበርነው ስናስተጋባውና ህዝብ ስንቀሰቅስበት እንዲሁም የኢህአዴግ ካዲሬ የነበሩትንም እንዲጠይቁ ስንወተውታቸው ከነበሩ የልማት ጥያቄዎች በዋነኝነት ይጠቀሱ የነበሩትና ካዲሬዎቹም ህዝቡ እንደዚህ በአንድ ልብ ኢህዴግን ያልመረጠው በእናንተ ድካም ነው በሚል ይመጣባቸው ለነበረው ጫና እንደመከላከያ ይጠቀሙበት ስለነበር የተሰጠ የይስሙላ ምላሽ እንደሆነ ግልፅ የሚያደርገው ከ1997 ዓ ም የእምድብር የመሰናዶ ትምህርት ቤት በክልሉ ውሳኔ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤት እንዲሆን ከተደረገና አንድ መኪናም በክልሉ መንግስት ተሰጥቶት ስራ ከጀመረ በኋል በፌደራል መንግስት(ህወሃት) ትእዛዝ ቴክኒክና ሙያው እዲንዲታጠፍና መኪናውም እንዲወሰድ መደረጉ ይታወቃል። ይሁን እንጂ ጉራጌ አካባቢ አንድ እንኳ በመንግስት የተሰራ ሆስፒታል የሌለበትና ዛሬም ልማትን በቴሌቪዥን መስኮት ብቻ የሚያውቅ አካባቢ ነው።
3/ ከህገ መንግስቱ ውጪ በሆነ መልኩ በተከለለበት ክልል ውስጥ ለኮታ ያህል ከሚሰጠው የካቢኔነት ቦታ ውጪ ይሄ ነው የሚባል የውሳኔ ሰጪነት ሚና ኖሮት አያውቅም። በህወሃት የሚዘወረው የክልሉ ኘሬዝዳንት ቦታ በ25 ዓመት ጊዜ ውስጥ ለጉራጌው እንኳንስ የሚያዝ የሚታሰብም አይደለም። ጉራጌ ለይስሙላ በሚሰጥና እውነተኛ ስልጣን በትሩ ግን የህወሃት በሆነበት የፌደራል መንግስትም ውስጥ ቦታ የለውም። ባለፉት አመታት እዳየነው ለይስሙላ ይሰጠው የነበረው ቦታ የከተማና ልማት ሚኒስቴርነት ነበር። ይህ የሚኒስቴር መስሪያ ቤት ደግሞ ስሙ ነው እንጂ ሙሉ ለሙሉ ማለት ይቻላል በአዲስ አበባ የተወሰነ ነው። እሱም ቢሆን አበቅርብ ጊዜ አቶ መኩሪያ ሃይሌ ከቦታው መነሳታቸው ይታወቃል። መቼ ከሌሎች ሚኒስቴሮች ያነሰ ችሎታም አፈፃፀምም እንደሌላቸው እናንተ የበለጠ ታውቃላችሁ። ሆኖም ህወሃት ለይስሙላ ሰጥቶ ራሱ በሚዘውረው ስልጣን እንኳ ጉራጌን ማየት እንደማይፈልግ ለማድረግ ይመስላል።
4/ በዘር የከፋፈለው ስርአት ከሁሉም ኢትዮጵያዊ በበለጠ መላው ኢትዮጵያ ቤቴ ነው ብሎ በሁሉም የሃገሪቱ ክፍል ተበታትኖ የሚኖረውን የጉራጌ ተወላጅ በገዛ ሃገሩ ባዳነት እንዲሰማውና ለሞትና ለእንግልትም እንዲዳረግ መደረጉ ከማንም የተሰወረ አይደለም።
5/ ይህ ሁሉ ምንም ባላጠፋው የቅጣት መኣት በህወሃትና በቃኛቸው ሰዎች የወረደበት የጉራጌ ማህበረሰብ ወያኔ ራሱ በፈቀደለት ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ምርጫ ኢህአዴግን ባለመምረጡ በህወሃት ፍፁም ንቀትና ትዕቢት በተሞላ መልኩ "ጥገኛ" ተብሎ ተሰደበ።
ታዲያ የጉራጌው ማህበረሰብ በጥላቻ ይህ ሁሉ የመከራ ገፈት እየተጋተ ባለበት በዚህ ወቅት እናንተም ህዝቡ ለመብቱ በሰላማዊ መንገድ እንዲታገል ውስጥ ለውስጥ መስራትና ይህ ጫንቃችን ላይ ተንጠልጥሎ ደማችንን እየመጠጠ ያለውን ስርዓት ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ጋር ለማስወገድ በሚደረገው ትግል የበኩላችሁን አስተዋፅኦ ማበርከት ይጠበቅባችኋል፤ የሞራል ግዴታም አለባችሁ።
ይህ ሳይሆን ቀርቶ ይባስ ብሎም ህወሃት ጉራጌን ከሌላው ለማጋጨትና በጉራጌ ክልል የሌለው ድጋፍ ያለው ለማስመሰል የተመረጡ ሰዎችን በማታለልና በማስፈራራት ሰላማዊ ሰልፍ ለማስወጣት በአንዳንድ አካባቢዎች እንቅስቃሴ መጀመራችሁን ደርሰንበታል ። ይህ የጀመችሁትን እንቅስቃሴ የማታቆሙ ከሆነ ነገ የማትወጡበት አዘቅት ውስጥ ራሳችሁን እየጣላችሁ እንዳለ እንድታውቁና ሰልፉም ወደ ወያኔ ተቃውሞ እንደሚቀየርና ሰፊውም ህዝብ እንደሚቀላቀል ከወዲሁ እናስታውቃለን።
መላው ህዝብ ደግሞ ከዚህ በፊት በ1997 ዓ ም እንዳደረገው ሁሉ አንዳንድ የተሳሳቱትንና ባለማወቅ ለህወሃት በታማኝነት የሚያገለግሉትን መክሮ በመመለስ ከወገኖቹ ጎን እንዲሰለፍ እንዲያደርግ። በባህላችን መሰረት እሺ ብሎ የአባቶች ምክር የሚሰማውን የሚመርቅ እንቢ የሚለውን ደግሞ የሚያወግዝ መሆኑን እንዲያሳውቅ በአክብሮት እንጠይቃለን።
በመጨረሻም ህዝባችን ሳይጎዳ የሚታገልባቸው ዘዴዎችን እንደ አስፈላጊነቱ እየቀያየርን በየጊዜው የምናቀርብ ስለሆነ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ተከታትሎ ተግባራዊ እንዲያደርግ እንጠይቃለን።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!! የቤተ-ጉራጌ ህዝባዊ እምቢተኝነት አስተባባሪ ኮሚቴ
No comments:
Post a Comment