አባይ ሚዲያ
ራሱን ህዝባዊ ወይኔ ሃርነት ትግራይ በማለት በሚጠራው የጸረ-ኢትዮጵያ መሰሪዎች አምባገነናዊ አገዛዝ ላለፉት ሃያ አምስት አመታት የዘለቀ ስቃይ እና ጥቃት ኢላማዎች የነበሩት የኢትዮጵያ አንድነትና ኢትዮያዊነት ብቻ ሳይሆኑ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችም በተናጠል እና በየተራ ግፍ እና ስቃይ ሲቀበሉ ቆይተዋል አሁንም በከፋ መልኩ ስቃዩ ቀጥሏል።
ጸረ ኢትዮጵያዊው ሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ በተደራጀ መልኩ የጥፋት ሰይፉን በዋናነት የመዘዘበት ኢትዮጵያዊነት ደግሞ አንዳንዶች እንደሚያምኑት የብሄር ብሄረስቦች ማለትም የኦሮሞው፣የአማራው የትግሬውየሶማሌው የሲዳማው፣የጉራጌው ፣ የአፋሩ፣የከምባታው እንዲሁም የሌሎች ብሄረሰቦች ድምር ማንነት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊነት ከብሄሮች ድምር (The sum of its parts) በላይ ነው። ኢትዮጵያዊነት ለዘመናት የተገነባ ማንነት ነው። የየትኛውም ብሄር ወይም ነገድ ባህልና ቋንቋ ብቻውን ኢትዮጵያዊነትን አይገልጸውም፣ አይበቃውም፣ አይተረጉመውም።
ኢትዮጵያዊነት ሚሊዮኖች በጋራ የምንጋራው ውስጣዊ ማነትታችን ነው። ስነ-ልቦናዊም ህሊናዊ ባህሪያት ያሉት ልንገልጸው ከምንችለው በላይ ረቂቅ ነው ፡፡ ለዘመናት የተገነባውና ሚሊዮንኖች በጋራ የሚጋሩት ይህ ማነንታችን መሰረታችን ከሆነው ብሄር ማንነት በላይ ሁለመናችንን የሚገዛን መንፈስ ነው።ድሃ ብንሆንም በጨቋኝ ስርዓቶች ወስጥ ብናልፍም የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎችን አሳፍሮ በደም የተከበረው፣በማህበራዊ ትስስር የተገመደው ኢትዮጵያዊ ማንነታችን ያረካናል፣ ያጠግበናል።
ከሁለት ብሄር እና ከዚያ በላይ ቤተሰብ የተገኙ ሚሊዮኖች ኢትዮጵያዊነትን በብሄር አጥር እንደማናቆመው ህያው ማሳያዎች ናቸው። በአዲስ አበባ፡ በአዳማ ፣በደሴ፡ በሃረር፣ በድሬዳዋ፣ በጎንደር፣ በባህር ዳር፡ ጅማ፣ አዋሳ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ዋና ዋና ከተሞች ተወልደው ያደጉ ሚሊዮን ከተሜዎች (Cosmopolitans) በመሆናቸው ራሳቸውን ከተወለዱበት ብሄር/ዘውግ ማነንት ጋር የሚያቆራኙበት ሁኔታ ባለመኖሩም፣ ማንነታቸው ኢትዮጵያዊነት ነው።
ዘውግ ሳይለይ ከሁሉም ማህበረስቦች መሰረታቸው የሆነ እንዲሁም ከእያንዳንዱ የዘውግ ማህበረስብ የተወለዱ/ወይንም መሰረታቸው የሆኑ ሚልዮኖች በቀዳሚነት የማንነታቸው መገለጫ ያደርጉት ኢትዮጵያዊነት በሂደት በህልቆ መሳፍርት ውስብስብ የረጅም ዘመናት ታሪካችንን የሚመግቡ ብዙ የታሪክ ጅረቶች የተገነባ ነው። ኢትዮጵያዊነት ረጅም የዘመናት ጉዞ ውጤት ነው። ውድቅት፣ ማንሰራራት፣ መነሳት፣ መስፋትና መጥበብ በተፈራረቁባት ጥንታዊት የሆንችው ኢትዮጵያ ምድር ደቡብ የነበረው ማህበረስብ ወደ ሰሜን ሲፈልስ፡ የሰሜኑ ህዝብ ወደ ድቡብ ሂዶ ሲሰፍር ፡ ምስራቅ የነበረው ወደ ምእራብ ፣ ከመሃል ወደ ደቡብ ፣ከደቡብ ወድ ምስራቅ፣ ከሰሜን ወደ መሃል ወዘተ፡ ለስራ፣ ለግጦሽ፣ ለግብርና፣ ለንግድ ልውውጥ፣ የቋንቋና የባህል መወራረሶች፡ በመዋለድ፡ በመዛመድ፡ በግጭትም ሆነ በሰላም ማህበረስቦችን ያገናኘ፣ ያስተሳስረ ፡ በረጅም ዘመናት ግንኙነቶች ውርርሶች የተገመደ ፣ የተገነባም ሀገራዊና ብሄራዊ ማንነት ነው ኢትጵያዊነት ።
ኢትዮጵያዊነት ዛሬ በምትገኘው ኢትዮጵያ ድንበር ውስጥ የሚገኙ ልዩ ልዩ ማህበርሰቦች ሀገራዊ መጠሪያ ብቻ ሳይሆን በብዙ ሚልዮኖች የሚቆጠሩ የኢትዮጳያ ልጆች የህልውናቸው፣ የማንነታቸው መገለጻጫ ነው። ኢትዮጵያዊነት በልዩ ልዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ሚልዮኖችን ያስተሳሰረ ማንነት ነው።
ኢትዮጵያዊነት በጸረ-ኢትዮጵያዊ የትግራይ ነጻ አውጭ አገዛዝና በተባባሪዎቹ በተቃጣበት የሰነልቦና የታሪክ ክህደት፣ የታሪክ ብረዛ፣ የባህልና የሞራል ሽርሸራ፣ ጦርነት ብዙ ቢደማም፣ ብዙ ቢቆስልም ማንም ምድራዊ ሀይል ሊበጣጥሰው ያልቻለ ውስብስብ እና ረቂቀ ሆኖ ቀጥሏል። አሁንም ለህልውናው እየተጋደለ ሲሆን፣ኝ በአንጻሩ የኢትዮጵያዊነት ጠላቶቹ እየተዳከሙ የመጡበት ውቅት ላይ እንገኛለን።
የዚህ ትውልድ አባቶች፣ አያቶች ፣ቅድም አያቶች የሰሩዋቸው ታሪኮች በረጂም ዘመናት ሂደት የተገነባው የኢትዮጵያዊ ማንነት ግንባታ አካል ብቻ ሳይሆኑ እነዚህ አያት ፣ ቅድማያቶቻችን ደማቸውን አፍሰሰው ፣አጥንታቸውን ከስክሰው፣ ህይወታቸውን ገብረው ኢትዮጵያዊነትን አለምልመውታል። በአለም ታሪክ በብቸኝነት የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎችን ተቋቁማ፣ ሀገራዊ ነጻነትዋን ጠብቃ የኖረች ኢትዮጵያ የምትባለውን ወብ አገር አውርሰውን አልፈዋል። የአውሮፓ ወራሪ ጣልያኖች ላይ በኢትዮጵያውያን መስዋእትነት የተገኘው ታላቁ የአድዋ ድል የዚህ ትውልድ ቅድመ አያቶች መስዋአትነት ስለከፈሉ፣ ህይወት ሰለገበሩለት ነበር። በባርነትና በቅኝ ተጘዥነት ሲማቅቁ ለነበሩ በአለም ዙሪያ ለሚገኙ የጥቁርና የአፍሪካ ህዝቦች ትልቅ የሞራልና የስነልቦና መነቃቃትን የፈጠረው አንጸባራቂው የአድዋ ድል የአማራ፡ የኦሮሞ፡ የወላይታ ፡የትግሬ፡ የጉራጌ የከንባታና ሌሎች የጦር ኣበጋዞችና ከእነዚህ ማህበረስቦች የሄዱ ሰራዊቶች ለኢትዮጵያ አንድነትና ነጻነት ኢትዮጵያዊነትን በመገንባት የጋራ መስዋትንነት የተከፈለበት የድል ታሪክ እንጂ የአንድ ብቸኛ ዘውግ ወይንም ብሄር ብቻ የተገኘ ድል አይደለም። በኣድዋ ከዘመቱት የኢትዮጵያ የሰራዊት ኣባላት መካከል የዚህ ጸሃፊ በኣባቱ በኩል ቅደመ ኣያቱ የሆኑትንና ከትውልድ ቀዬቸው ከጌጃ ፡ ሸዋ ተነስተው ከራስ መኮንን ጉዲሳ ሰራዊት ጋር በመዝመት ሀረርጌ የሰፈሩትን የሸዋ ኦሮሞ ኣቶ ጃቶ ወለገራን ይጨምራል።
በሁለተኛውና 5 አመታት የቆየው የጣልያን ፋሽቶች የወራራ ዘመን በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ከአራቱም ማዕዘን ያሳዩት የአርበኝነት ተጋድሎ፡ አኩሪ ጀግንነት ኣና መስዋእትነት ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ነጻነትና አንድነት የተደረገ፣ ለኢትዮጵያዊነት የተከፈለ ዋጋ ነበር። ራስ አበበ አረጋይ በቸሬ በሸዋ ፣ኮ/ል አብዲሳ አጋ በጣልያን በረሃዎች፡ እንዲሁም ከወጣቱ ኣርበኛ ደጃዝማች አብቹ አስከ ደጃዝማች በላይ ዘለቀ በጎጃም ፣ ከራስ አሞራው ውብነህ በጎንደር አስከ ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ፡ ከልጅ ሀይለማርያም ማሞ አስከ ሻለቃ በቀለ ወያ ፣ከጀ/ል ጃጋማ ኬሎ በሸዋ አስከ ኡመር ሰመተር የኢትዮጵያ አርበኞች የጀግነት ታሪክ ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ነጻነት በኢትዮጳዊት የጋራ ብሄራዊ ማንነት ስር የሚገኝ ታሪክ እንጂ የአንድ ዘውግ ወይንም የአንድ ነገድ ቋንቋ ተናጋሪዎች ብቻ ሊሆን አይችልም።
እነዚህ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አርበኞ ያፈሰሱት ደም፡ የከስከሱት አጥንት ፡ የገበሩት ኣይተኬ የህይወት መስዋእትነት የጋራች የሆነውን ኢትዮጵያውነትን ለማለምለም ግዙፍ አሰተዋጾ አድርጓል። በኣምስቱ ኣመት የፋሽስት የጣሊያን ወረራ ዘመን መስዋእትነት ከከፈሉትና ከኣርበኝነት ትግሉ በሁዋላ በህይወት ከተረፉት ኣርበኞች መካከል የዚህ ጸሃፊ በእናቱ እናት በኩል የወንድ ቅድመ ኣያቱ ባላምበራስ እሻግሬ ተሰማ በፋሽስቶች ጋር በተደርግው የኣርበኝነት ተጋድሎ የተሰዉ ፡ ባላንበራስ ደምሴ ተሰማ ታላቅ ወንድማችው እንደዚሁ የተስው፡ እናም በህይወት የተረፉትን ፊታውራሪ ተገኔ ተሰማ፡ ቀኛዛች ጥላሁን ተስማን ፡ “አጥሬ ተሰማ የባህር አዞ ጠላቱን ገዳይ ኣናዞ ኣናዞ” ተብሎ የተገጠመላቸውን ሻምበል ኣጥሬ ተሰማን ፡ የኣርበኝነት ገድላቸ የተጻፈላቸውንና ከመሰረታቸው ከሰሜን ሸዋ ኣማራ የሆኑትን ስባቱን ወንድማማች የባሌና የሀረር ኣርበኞች ይጨምራል።
ከሰባት ወራት በፊት ጀግናው የጎንደር ህዝብ በጎንደር ከተማ ላይ ባቀጣጠለው ታላቅ ህዝባዊ የእቢተኝነት ተቃውሞ ሰልፍ የወያኔው መንጋ ለ25 ኣመታት የኦሮሞና የአማራን ነገዶች ለመነጣጠል ያንሰራፋውን የከፋፍለህ ግዛ ሴራ የበጣጠሰ ብቻ ሳይሆን፣ በአማራው ህዝብ ዘንድ የሚገኘውን ከአንድ ብሄር በላይ የሆነውን፤ ከሌሎቹ ብሄሮች ጋር የሚጋራውን ኢትዮጵያዊነት ያረጋገጠ ጭምር ነው፣ የወያኔ ስርአት በዘርጋው ክልላዊነት ለሃያ አምስት አመታት ሲሰብክ የኖረውን ብሄርተኝነትንም ሰብሮ የወጣ፣ መቋቋም የሚችል (Resilient) ክስተት ሆኖም አይተናል።
ላለፉት 25 አመታት የተሰበከውን የኢትዮጰያን የመቶ አመት ታሪክ ተረትነትም አጋልጧል። የአክሱም ሀውልት ለወላይታው ምኑም አይደለም በማለት ለብዙ ዘመናት የተገነባውን ኢትዮጵያዊነትን በማሳነስ፡ በማንኳሰስ ዓመታት ያስቆጠሩት የትግራይ ነጻ አውጪ ነን ባዮች ዛሬ የኢትዮጵያዊነት፣ ሀገራዊ ማንነት ካባ በማጥለቅ እንደለመዱት ህዝብን ለማጭበርበር እየሞከሩ ይገኛሉ።
እነዚሁ በጭካኔ የተካኑ መሰሪ ወያኔዎች ላለፉት 25 አመታት እንዳደርጉት ሁሉ አሁንም ኢትዮጵያና ህዝቦችዋ፣ ዜጎቹዋን ከዳር እስከዳር በጭካኔያዊ አርምጃዎቻቸው የማጥቃትና የማድማት ተግባራቸው ተጠናክሮ እንደቀጠለ ሁላችንም በየእለቱ የሚያመንና የሚያንገበግበን እውነታ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያውያንን በጅምላ እየፈጁ፣ ከዚያው 40 ዓመት ካረጁበት የዘር ከረጢታቸውም ሳይወጡ የኢትዮጵያዊነት ሰባኪ ሆነው ብቅ ብለዋል። ።
በቅርቡም ኢትዮጵያዊነትንና ኢትዮጵያውያንን ቤት አልባዎች በሚል ከጥበትና የከድንቁርና ብቻ በሚመንጭ ድፍረት የተናገሩም ሰምተናል፡፡ ኢትዮጵያዊነት ሁሉ ቤቱ ነው፡ የኢትዮጵያዊነት ቤት ከሀረር እስከ ጎንደር ፡ ከእንድብር እስከ ኢሉባቡር፣ ከጂማ እስከ መተማ ፣ ከወሎ እስከ ያቤሎ፡ ከወላቃይት አስከ ወልቂጤ ከኦሮሞ የቅደመ ኣያቴ ትውልድ ቦታ ከጌጃ፡ ሸዋ እስከ ጅጅጋ፡ ሀረር፡ ኣማራ ቅድሜ ኣያቶቼ መሰረታቸው ከሆነው ከቡልጋ ፡ ሸዋ እስከ ባሌ ጎባ የኢትዮያውያና የኢትዮጵያዊነት ቤቱ ነው። ይህን መብት የሚነቀንቅ ምድራዊ ሃይል አይኖርም። አራቱም የሀገሪቱ ማእዘናት የኢትዮጵያዊነት ቤቶች ናቸው።
በዚህ ረጅም ዘመና ሂደት እንደማንኛውም ሌሎች ሀገሮች ታሪክ ታሪካችን ብዙ በጎ ጎኖች የነበሩት ቢሆንም አሉታዊ ጎኖችም ነበሩት ፣ ታሪካችን አልጋ በአልጋ አልነበረም፡፡ በእነዚህ አሉታዊ የታሪካችን ጎኖች ሳቢያ ኢትዮጵያዊነት ሁሉም የቋንቋና የባህል ማህበረሰቦች በእኩልነት የኔም ነው የሚሉት፣ ባለቤትነት፣ ባለድርሻነት የሚሰማቸው የእድገት ደረጃ አልደረሰም ለማለት ይቻላል። ምክነያቱም አድጎ ለምልሞ አላለቀም ፣ ሂደት ነው። ሁሉም አገሮች የተጓዙበት ሂደት የተለየ አይደም። ከእንግሊዝ ኣስከ ቻይና ከሩስያ እስከ ህንድ ገና ኣላለቁም። የሁለት መቶ ኣመት ታሪክ ያላት ዲሞክራሲያዊ ሰረት ከባርሪያ ኣሳዳሪ ኢኮኖሚ ጋር ተጣምሮ፣ የጡቁሮች፡ የሴቶችና ከኣንግሎ ሳክስን ውጭ የነበሩ ማህበረሰኖች ሲብደሉ የነበሩባት ሃያልዋ አሜሪካም ፡ የጎደሉ መብቶች፡ ነጻነችን በህገ መንግስታዊ አርምጃዎችና በህዝብ ትግል እያስተካከልች መጥታለች። ሂደቱዋን ግን ኣልጨረስችም።
ከላይ እንደተጠቀሱትና እንዳልተጠቀሱትን የኣለም ሀገሮችና ህዝቦች የኛም ሂደት ወደ ሚቀጥለው እድገቱ የሚሸጋገረው ወያኔዎች እንደሞከሩት ኣሁንም በሁልም ጎራ የሚገኙ ጽንፈጮች እንደሚሞክሩት ያለፈውን በማፍረስ ወይንም በብሄር ማንነቶች ብቻ እንዲተካ፣ እንዲሳሳ በማድረግ ሳይሆን ሁሉን አቃፊ ሁሉንም የቁዋንቋና ባህል ማህበረሰቦች እኩልት፡ የሚረጋገጥበት፣ አሳታፊ የሆነ ዲሞክራስያዊ የፓለቲካ ስርአት እውን ማደረግ ስንችል ነው። በቀላል ቋንቋ ኢትዮጵያ የሁሉም የጋራ እናት እንጂ እንጀራ እናት ያለመሆንዋን የሚያረጋግጡ ሁኔታዎች መፍጠር ሲቻል ነው።
እስካሁን ይህን ማድረግ አልቻልንም,። በጥቁሩ ዓለም ብቸኛው ሀገራዊ ነጻነት የነበራትን ሃገር ለህዝቧ፣ ለማህበርስቦቿ እኩልነት፣ ነጻነት የሰፈነባት ሀገር ማድረግ ይገባናል።በዚህም ነው ኢትዮጵያዊነትን ወደ ሚቀጥለው የእድገት ደረጃ ማሸጋገር የሚቻለው።
ኢትዮጵያዊነት ወደ ሚቅጥለው የእድገት ደረጃ ሊሸጋገር የሚችል ሁሉን አሰባሳቢ፣ ሁሉን አቃፊና አሳታፊ ዲሞክራሲ የፖለቲካ ስርአት በትግላችን መመስረት ሲቻል ብቻ ነው። ይህን ማድረግ ካልተቻለ እስከአሁን የነበው የጋራ ብሄራዊ ማንነት — ኢትዮጳያዊነት– እንዲሁም የኢትዮጵያ ሀገራዊ አንድነትም አደጋ ላይ ሊወድቁ ይችላሉ ። በዚህ ትውልድ ኢትዮጵያዊያን ፊት የተደቀነው ትልቁ ፈተናም የጋራ ቤታችን የሆነችው ኢትዮጵያን የተጋረጠባት አደጋ ነው፡፡ዛሬ ላይ የምንገኝ የዚህ ትውልድ ኢትዮጵያውያንም እረፍት የነሳን ፣ እንቅልፍ ያሳጣን ይህ በኢትዮጵያ ሀገራዊ አንድነትና በኢትዮጵያዊነት ላይ የተቃጣው አደጋ ነው::
ስለዚህ ነው የጋራ ትግላችን ዋና ተልእኮ ይህን አደጋ መመከትንና መቀልበስ ይሆናል።የሀገር አደጋውን ልንቋቋም የምንችለው፣ ለኢትዮጵያ ሀገራዊ አንድነት፣ ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ማንነት ልምላሜና መጠናከር ዋስትና የሚሆነው ‘ ለሁሉም እኩል የሆነች፣ ሁሉም ዘውጎች፡ ሁልም ማህበረሰቦች የእኔም ናት የሚልዋት፤ መገለል፣ መገፋት፣ መረገጥ ያከተሙባት፤ ህዝቧ የስልጣን ባለቤት፣ ዜጎቿ ነጻ የሆኑባት፣ ባይተዋር ያልሆኑባት፣ ባለቤት የሚሆኑባት፣ የበይ ተመልካች ያልሆኑባት፣ ፍትሃዊ የስልጣንና የሀብት ክፍፍል የሰፈነባት፣ ሁሉም ተጠቃሚ ሁሉም የአገሪቱን ጸጋዎች፣ እሴቶች ባለድርሻ የሚሆኑባት፣ ሁሉም ማህበረስቦች/ በጠቅሉም የኢትዮጵያ ህዝብ የስልጣን ባለቤትነቱ የተረጋገገጠበት ሀገረ መንግስት (state) ስንመሰርት እና ይህ የሚገለጽበት ህገ-መንግስታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርአት እውን ማድረግ ስንችል ብቻ ነው። ይህን ሁኔታ በመፍጠር ብቻ ነው አገራችንን ከጥፋት ማዳን የሚቻለው።
የኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ነገዶች የቋንቋና የባህል ማህበርስቦች ሙሉ ክብርና እኩልነት የሚጎናጸፉባት ፣ ሀገራዊ ማነንታቸው ለዘመናት ሁለንተናዊ ግንኙነች የገነቡት ትስስርና ውርርስ እንዲጠናከር በባለቤትነት፣ በዜግነት መብቶቻቸው ሀገራዊ የጋራ ብሄርተኝነት – ኢትዮጵያዊንትን የሚያዳብሩባት፡ በእኩልነት የሁሉም የሆነች ኢትዮጵያ – የአማራው የኦሮሞው ፣ ጉራጌው፣ የከምባታው፣ የአፋሩ፣ የሶማሌው፣የኣንዋኩ ወዘተ የሆነች ኢትዮጵያ – የሰው ልጅ በዘውግ ማንነቱ ብቻ ሳይሆን በቀዳሚነት ሰው በሰውነቱ ፡ በስብእናው በተፈጥሮና በፈጣሪ የተሰጡት ሁለንተናዊ ነጻነቶችና መብቶች ከፍተኛ ክብርና ሞገስ የሚጎናጸፍባት ኢትዮጵያ ፡ የሰው ልጅ፡ የማናቸውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ መብት፡ ነጻነትና ክብር የነገሰባት፣ እንክባብካቤ የሚደረግባት፡የሚነገሱባት፡ የሚንስራፉባት ኢትዮጵያን እውን ስናደርግ ነው።
ኢትዮጵያዊነት የጋራ ብሄራዊ ማንነት የሚጠናከረውና የሚያብበው የተገፉ፡ በታሪክ ሂደት ተገቢ የስልጣን ውክልና ያልተጎናጸፉ ማህበረሰቦች በእኩልነት በፖለትካ ስርአቱ በፍትሀዊ የስልጣንና የሀብት ክፍፍል ባለድርሻ የሚሆኑበት ስርዓት ሲዘረጋ ነው፣በዲሞክራሲያዊ ህገ-መንግስታዊ ስራአት የተረጋገጡ መብቶች ሲሟሉ ብቻ ነው። ያኔ ሁሉም የኔም ነው የሚለው ከቨርዥን 1.0 ወደ ቨርዥን 2.0 ( የኮምፑተር ሶፍት ዋር አናሎጂ ለመጠቀም) የተሸጋገረ የሁሉም የጋራ ማንነት የሆነ ኢትዮጵያዊነት ያብባል። የሚያድጉ የሚዳብሩ እርምጃዎችንና ግንባታዎች በማድረግ የኢትዮጵያ ጸጋና ውበት የሆኑትን ልዩ ልዪ ባህሎችና ቋንቋዎች የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሀበቶች ጭምር መሆናቸውን ማረጋገጥ ይገባል። ይህ ሁሉ ዕውን የሚሆነው የ በዙሃን (pluralism in all its manifestations) ህብረ ቀለምን በአንድነት(unity with diversity) ማሰተናገድና ማቻቻል የሚችል ዲሞክራሲያዊ የፖለካ ስራአት ስንመሰርት ነው። ይህን የፖለቲካ መሰረት ስንጥል ነው በሙሉ ትኩረትና በሙሉ ጉልበት አገራችን ኢኮኖሚያዊ አድገትና የቴክኖሎጂ ምጥቀት ተጠቃሚ እንድትንሆን፡ እንዲሁም ሁለንተናዊ ልማትና የተፈጥሮ ሀብታችን እንክብካቤ ላይ በማተኮር ከድህነትና ጠኔ ነጻ የወጣ ጤናማ ኩሩ ህዝብ ለመሆን የምንችለው ።
ከማንም የአለም ሕዝቦች በላይ የኢትዮጵያ ህዝብና በውስጡ የሚገኙ ማህበርሰቦች ጥንታውያን ናቸው። ጥንታዊ ግሪካዊያን የታሪክ ጸሀፊዎች ኣንዱ የሆነው ሄሮዶተስ የታወቀውና ጥንታዊ ኢትዮጵያውያንን ኣስመልክቶ የሚጠቀሰው “the blameless Ethiopians where the Gods love to feast with” ኣማልክት ከኢትዮጵያውን ጋር ድግስ መብላት ይወዳሉ ብሎ ነበር የጻፈው። ነብዪ መሐመድ- ለአደጋ ተጋለጡ የእስልም ተከታዮችን ፍትህ ወደ ማያጉዋድለው ወደ ኢትዮጵያ ንጉስ ሂዱ በለው ነበር የላኩዋቸው። ሌሎች በታሪክ የተመዘገቡና ኢትዮጵያን የሚያሳዩት በጥንት ዘመን ብዙ ብጎ ምግባሮችና ጻጋዎች ማማ የነበረች ምድርም እንደነበረች ይገልጻሉ። አሁንም ኢትዮጵያዊያን የዚያን የሩቅ ዘመን ከፍተኛ ስብዕናና የፍትህ እሴቶች የሚበልጡ የፍትህ፡ እኩልነት፡ የሰው ልጆች ነጻነት የነገሰባት ዘመናዊ ሀገር መገንባት የማንችልበት ምክንያት የለም።ለዘመናት የኖረውን ከኣለም ሀገሮች ብቸኛው ሀገራዊ ነጻነት የነበረን ህዝቦች የማህበርስቦች እኩልነት፣ የዚጎች ነጻነት የሰፈነባት ሀገር እንድትሆን ማሸጋገር ፡ስንችል ነው ኢትዮጵያዊነት ወደ ሚቀጥለው የእድገት ደረጃ የሚሸጋገረው። ሀገራዊ የነጻነት የዘመናዊ ታሪካችን በዜጎች ነጻነትና ፍትህ መመንዘር፡ ለሁሉም ማህበሰቦች እኩልነትን ማሟላት ስንችል ነው።
ስለዚህ ትግላችን ይህን የጋራ ቤታችን የሆነችዋን ኢትዮጵያ አገራችንን የማዳን ትግል ነው፡፡ ትግላችን ኢትዮጵያዊነትና የኢትዮጵያዊት ቤት የሆነችውን ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ማዳን ነው። ለኢትዩጵያዊነትና ለሁሉም ኢትዮጵያውያን መታገል የንቅናቄያችን መብትም በውዴታ የገባንበትም ግዴታ ነው። ከወያኔ ፋሽስታዊ የጨካኞች ስርአት ጋር የመረረ የከረረ ሁለገብ/ሁለንተናዊ ትግል ማድረግ ያለብንም ይህን የተሻለ የህዝብና የዜጎች መብቶችና ነጻነቶች የሚረጋገጡባት የፓለቲካ ስርአት እውን ለማድርግ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሀገራዊ አንድነትና ኢትዮጵያዊነት ህልውና አደጋ ውስጥ በመሆናቸውም ጭምር ነው።
ይህንን ኢትዮጵያን የማዳን ሀገር አድን ታላቅ ራዕይና ተልዕኮ ቃል ኪዳን የሚመጥን ቃልን ወደ ተግባር ፡ ዲስኩርን ወደ ተግባር የሚተረጉም እንቅስቃሴዎችን ከከፍተኛ አመራሮቹና በሺ የሚቆጠሩ አባላቱ እያደረገ ይገኛል። አመራሮቹ ታጋዮቹ ሆነው ሲገኙ፣ መስዋዕትነት ሲከፍሉ ሲያታግሉና ሲታገሉ ቆይተዋል።የአርበኞች ግንቦት 7 ሀገራዊ ራዕይና ተልዕኮ ለትልቅ ሀገር ለመቶ ሚሊዮን ህዝባችንን የሚመጥነውን ዲሞክራሲዊ ስራአት እውን ማድረግ ነው። ንቅናቄችን ብዙ መስዋትነት እየከፈለም ነው። ወድፊትም ይከፍላል። ኢትዮጵያዊነትና ኢትዮጵያን ለማዳን ለህዝብ ነጻነትና ለሁሉም ዜግጎች መሰረታዊ መብቶች ለሁልም ዘውጎችና ማህበረሰቦች እኩልነት መታገል ብሎም ምስዋዕትነት መክፈል አጅግ የምንኮራበት እንጂ የምናፍረብት፣ ግንባራችንንም የምናጥፍበት በፍጹም አይሆንም።
አርበኞች ግንቦት 7 ውስት የሚገኙ አባላት የተሰባሰቡት በኢትዮጵያዊነት ነጻነትና ፍትህ የጠማቸው ስለሆኑ እንጂ ዘር እየተቋጠሩ አይደለም። ንቅናቄያችን የልዩ ልዩ ዘውጎችና ብሄሮች ተወላጅ የሆኑ አባላት ቢኖሩትም ራዕይው ሀገራዊ፣ ኢትዮጵያዊ ነው። የጋራቸው የሚያስተሳስራቸው ያሰባሰባቸው ለዘመናት የተገነባው ከሁሉም ብሄሮች ማንነት በላይ የሆነው ኢትዮጵያዊነታቸው ነው። የንቅናቄው አርማ የኢትዮጵያ አንድነት ነው። ኢትዮጵያዊነት ነው። ግባችን ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ስርአት ነው። ስለዚህም ነው አርበኛች ግንቦት 7 የወደፊትዋ ኢትዮጵያ በዜግነት እኩልነትና ነጻነት ላይ የተመሰረተ ሀቀኛ የዲሞክራሲያዊ ስርአት ለኢትዮጵያ አንድነትና በአገራችን ለሚገኙ ዘርፈ ብዙ ውስብስብ ችግሮች ብቸኛ አገር አድን የፓለቲካ መፍትሄ ነው ብሎ በጽኑ የሚያምነው የሚያቀነቅነው። መስዋእትነት በመክፈል ላይ የሚገኘው።
ጥሪያችን ኢትዮጵዊነትና ኢትዮጵያ ሀገራችንን በትግችን ለማዳን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ቆርጦ ለተግባራዊ ትግልና ኣስተዋጻኦ እንዲነሳ ነው!!
ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ለዘላለም ይኖራሉ!! ፡በትግላችን መስዋእትነት አንድነቱዋ የተጠብቀ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እውን እናደርጋለን!!
ኑው ዮርክ፡ ፊብሩዋሪ 17፡ 2017
No comments:
Post a Comment