በዘርይሁን ሹመቴ
አገዛዙ የአማራና የኦሮሞ ብሄር ተወላጆች የሆኑየመከላከያ ሰራዊት አባላትን በሶስት መካከለኛ የጭነትት ተሽከርካሪ ወደ ሸዋ ሮቢት እስር ቤት ማስገባቱን ምንጮች ገለጹ።
በትላንትናው እለት አመሻሹን ወደ እስር ቤቱ ከተወረወሩት ከእነዚህ አባላት ውስጥ ነባርና አዳዲስ ምልምሎች እንደሚገኙበት የውስጥ መረጃዎች ያመለክታሉ።
እንደ ምንጮች ዘገባ መሰረት እነዚህ አባላት እጣ ፋንታቸው ወደ ሸዋ ሮቢት እንዲሆን ያደረገው ምክንያት ከአገዛዙ ጋር የአቋም ልዩነቶችን በማንጸባረቃቸው እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።
በሶስት መካከለኛ የጭነት ተሽከርካሪ ተጭነው ወደ እስር ቤቱ የታጎሩት እነዚህ አባላት ከየክፍለ ጦሩ የተለቀሙ መሆናቸውም መረጃዎች ጠቁመዋል።
እነዚህን ወታደሮች ለሸዋ ሮቢት እስር ቤት የዳረጋቸው በተለያዩ የስብሰባ መድረኮች ላይ አገዛዙን በመቃወም በግልጽ ትችታቸውን በመግለጻቸው እንደሆነ በቅርበት ሁኔታውን ሲከታተሉ የነበሩ ምንጮች አጋልጠዋል።
ወደ እስር ቤት የተላኩት እነዚህ የመከላከያ ሰራዊት አካላት የወያኔ አገዛዝ በህዝቡ ላይ የከፈተውን ጦርነት በመቃወም ህዝቡ ላይ በሚወሰዱ ግዳጆች ላይ እንደማይሳተፉ ሲገልጹ የነበሩ መሆናቸውንም በደህንነት ምክንያት ማንነታቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የውስጥ ምንጮች ገልጸዋል።
ለእስር የተዳረጉት የመከላከያ አባላት መካከል የቆሰሉና የተደበደቡ እንዳሉ እማኞች አሳውቀዋል። ምን አልባት ወደ ሸዋ ሮቢት ከመላካቸው በፊት ሰፍረው በነበሩበት የጦር አካባቢዎች ታስረው ሲሰቃዩ እንደነበረም ተገምቷል።
የመከላከያ አባላቱ ሸዋ ሮቢት እስር ቤት በተለያዩ የጨለማ የማሰሪያ ክፍሎች ውስጥ እንዲታሰሩ መደረጋቸውን ትንሳኤ ሬዲዮ ምንጮቼ አረጋግጠውልኛል በማለት የእስረኞቹን ወቅታዊ ሁኔታ ዘግቧል።
በህውሃት የበላይነት የሚመራውን የመከላከያ ሰራዊትን በመክዳት በቁጥር ብዙ የሆኑ የመከላከያ አባላት እና የፌደራል ፖሊሶች ወደ ትጥቅ ትግሉ እየተቀላቀሉ እንደሆነ አገዛዙ ወቀሳውን በተደጋጋሚ ሲያሰማ እንደነበረ የሚታወስ ነው።
No comments:
Post a Comment